የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በምዕራፍ አንድ አንቀፅ 5 ከንዑስ አንቀፅ1እስከ3 ባስቀመጠው ድንጋጌ፤ ማናቸውም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እኩል እንደሆኑ፤ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንደሆነ እንዲሁም ክልሎች የራሳቸውን የሥራ ቋንቋ መወሰን እንደሚችሉ ያስቀምጣል። ሆኖም በአንዳንድ ወገኖች ህገ መንግሥቱ በሚደነግገውም ይሁን ከዚያ በተለየ መንገድ ቋንቋን መሰረት ያደረጉ ፅንፍ የወጡ ሃሳቦች በተለያዩ መድረኮች ሲያነሱ ይደመጣል። ለመሆኑ የቋንቋ እና የስነ ልሳን ምሁራን ይህን ጉዳይ እንዴት ይመለከቱታል?
ዶክተር ዮሐንስ አድገህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ባህሎች አካዳሚ የስነ ልሳን ተመራማሪ ናቸው። እንደ እርሳቸው እይታ በማህበረሰቡ እና በተለያየ አደረጃጀት ያሉ ቡድኖች በቋንቋ ላይ ያላቸው አመለካከት እጅግ የተለጠጠ ነው። የደርግ ስርዓት መውደቅ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን ቋንቋ የመንከባከብና የማሳደግ እድል እንዲያገኙ አድርጓል። ይህ መልካም መሆኑን ቢያምኑም ቋንቋ ከስነ ልሳናዊ ተግባሩ ባለፈ የማንነት መግለጫ እና ማህበራዊ ተግባሩ ጎልቶ እንዲወጣ መሰበኩ ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ።
«ቋንቋ ሁለት ዋና ዋና ተግባራት አሉት። የመጀመሪያው ስነልሳናዊ ሲሆን ከምንም ነገር ሳይያያዝ የአንድን ተናጋሪ ሃሳብ፣ ስሜት፣ ፍላጎት ፍልስፍና እንዲሁም ማንነት በቀጥታ ለሌሎቹ መልዕክቱን ያስተላልፋል ማለት ነው» የሚሉት ዶክተር ዮሐንስ፣በዚህ ትርጓሜው ቋንቋ ከብሄር፣ ከፖለቲካ፣ ከጎሳ፣ ከሃይማኖት፣ ከመልክዓምድር፣ ከፆታ፣ ከባህል፣ ከእድሜ፣ ከማህበራዊ ሁኔታ እንዲሁም ከትምህርት ደረጃ ጋር የማይያያዝ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ሁለተኛ ተግባሩ ደግሞ ማህበራዊ ሲሆን በውስጡም ብዙ ዘርፎችን የሚይዝ ነው። «ከአነጋገር ይፈረዳል፤ ከአያያዝ ይቀደዳል» እንዲሉ፤ አንድ ሰው በሚናገርበት ጊዜ ሌሎቹ ማንነቶቹ በቋንቋው ውስጥ ይንፀባረቃሉ በማለት ቋንቋ የተናጋሪውን ማንነት መግለጫ መሆኑን ያስረዳሉ። ተመራማሪው ከላይ የጠቀሱትን የቋንቋ ትርጓሜ መነሻ አድርገው የወቅቱን ሁኔታ በመቃኘት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው አመለካከት «የቋንቋን ማህበራዊ» ፋይዳውን ብቻ አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
«ቋንቋ ብቻውን የማንነት መግለጫ አይደለም። ባህል፣ ፆታ፣ እድሜ፣ መልክዓምድርን ጨምሮ በርካታ የማንነት መገለጫዎች አሉት» የሚሉት ተመራማሪው፤ ይሁን እንጂ ከስነ ልሳናዊ አገልግሎቱ በላይ፤ ማህበራዊ ፋይዳውን አጉልቶ በማንሳት የማንነት መገለጫነቱ ተለጥጦ እና ዋጋ ተሰጥቶት መታየቱ ትክክል አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ከማቀራረብ ይልቅ የማራራቅ፤ ከመቻቻል ይልቅ የማቀያየም አቅሙ ከፍተኛ ይሆናል ይላሉ።
ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ባህሎች አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር እና የዘርፉ ተመራማሪ ናቸው፡፡ እርሳቸውም ማንኛውም ቋንቋ ምሉዕ መሆኑን ይናገራሉ። በስነ ልሳን ፍልስፍና አንዱ ቋንቋ ካንዱ ያንሳል ተብሎ ሊነገር የሚችልበት ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለ ይናገራሉ። ጠቀሜታው ላይ ሲመጡ ግን አንዳንዱ ወንዝ ተሻጋሪ፤ አንዳንዱ ደግሞ ባለበት ተወስኖ የሚቆይ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ። ወንዝ ተሻግሮ በሌሎች ማህበረሰቦችና በብዙሀን የሚነገረው ቋንቋ ደግሞ የጋራ አስተሳሰብን እና ግንኙነትን የመፍጠር አቅሙ ከፍተኛ እንደሆነ ይገልፃሉ።
«ቋንቋ በጥንቃቄ ከተጠቀምንበት የእውቀት ማሸጋገሪያ ነው። የማንነት መገለጫም ነው። በተፈጥሮ የሚገኝ ስጦታ ነው» የሚሉት ተመራማሪው፤ ሆኖም ቋንቋ የሚያቀራርብ፣ ልምድ እና እውቀትን የሚያስተሳስር የመግባቢያ መሳሪያ መሆኑን ማህበረሰቡ ካልተረዳ «የኔ ቋንቋ ካልሆነ በሌላው አልግባባም» የሚል አመለካከት ካዳበረ ተጎጂ የሚሆነው እራሱ መሆኑን ያብራራሉ።
«የአንድን ብሄር ቋንቋ ማሳደግ እና በራሱ ቋንቋ ጋር እንዳይደርስ እና እንዳይገለገልበት ማለት አይደለም» የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ፤ ቋንቋን መሰረት በማድረግ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ከሚያደርጉ የጋራ ጉዳዮች በላይ ልዩነት እና የግል እሴት ላይ በጉልህ ተሰርቷል፡፡ ይሄ ደግሞ መራራቅ እየፈጠረ መሆኑን ነው የተገነዘቡት።
ተመራማሪዎቹ አሁን አሁን ቋንቋን መሰረት አድርገው የሚፈጠሩ ልዩነቶችን ጥልቀት እና ስፋት ከዳሰሱ በኋላ መፍትሄ የሚሉትን ምክረ ሃሳብ አስቀምጠዋል፡፡ የስነ ልሳን ተመራማሪው ዶክተር ዮሐንስ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታየ ያለውን የአመለካከት እና የፖለቲካ ልዩነት ለማጥበብ እና የጋራ እሴቶችን ለማጉላት በርካታ ሥራዎች መሰራት እንዳለበት ያምናሉ፡፡
የራስን ቋንቋ ከማበልፀግ ጎን ለጎን ከብሄር ብሄረሰቦች ጋር ለሚኖረው የእርስ በእርስ መስተጋብር እንዲሁም አንድነትን ለማስቀጠል የሚያስተሳስር ቋንቋ ሊኖር ይገባል። አማርኛ ቋንቋ የፌዴራሉ መንግስት የሥራ ቋንቋ ከመሆኑ አኳያ በተግባርም ጭምር ታግዞ የብሄር ብሄረሰቦችን አንድነት እንዲያጠናክር ሊሰራበት ይገባ የሚል ምክረ ሀሳባቸውን ያስቀምጣሉ። ሁሉም «የኔ ቋንቋ ይሄ ነው ሌላው አይመለከተኝም» የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ማራመዱም ተገቢ አለመሆኑን እና ይህን መሰል አመለካከት ዘመኑን የማይመጥን መሆኑን በምክንያት ያስቀምጣሉ።
«አማርኛ ቋንቋን ለመግባቢያነት መጠቀም አማራ አያደርግም፤ ማንነትንም አይሸረሽርም» የሚሉት ዶክተር ዮሐንስ፤ እያንዳንዱ ብሄረሰብ የራሱን ቋንቋ ከማዳበር በተጨማሪ ከወንድም እህቶቹ፤ ከብሄር ብሄረሰቦች ጋር ሊያስተሳስረው የሚችል ቋንቋ ቢማር ወይም ቢያውቅ ክፋት የለውም ይላሉ።
የጋራ ቋንቋ ለመፍጠር እና ያለውንም ደረጃ ከፍ ለማድረግ በሁሉም ክልሎች የቋንቋ ማበልፀጊያ ማእከል ከፍቶ ማህበረሰቡ ማህበራዊ ተግባቦቱ እንዲሰፋ ማስተማር ተገቢ ነው። በዚህ የተነሳ ዜጎች ክልላዊ፣ አገራዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሚናቸውን ማስፋት እንደሚችሉም ያምናሉ።
በዘርፉ ላይ የረጅም ጊዜ ልምድ እና የምርምር ሥራ ያከናወኑት ዶክተር ሙሉጌታ ከዶክተር ዮሐንስ ጋር የተቀራረበ መፍትሄ ይጠቁማሉ፡፡ እርሳቸው የብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋ በተለይም አንድ የጋራ መግባቢያ ቋንቋን ማወቅ እድላችንን ያሰፋል። «አገር ለመምራት እና ለማሳደግ የጋራ የሆነ ቋንቋ የመኖሩን ጠቀሜታ ልንረዳ ይገባል። በዚህ መንገድ የሚያለያዩ ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ በማድረግ አንድ የሚያደርጉ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል» ብለው ያምናሉ።
«የራስን ሰጥቶ የሌላውን መቀበል መልመድ ይኖርብናል» የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ፤ በታሪክ አጋጣሚ ተፈጥረው በጋራ ሊያግባቡ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል የሚል ምክረ ሀሳብ በማስቀመጥ አስተያየታቸውን ይቋጫሉ።
የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት እና የቅርብ ጊዜ የምርምር ፅሁፎች በኢትዮጵያ ከ80 ቋንቋዎች በላይ ቢኖሩም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ወደ ፅሁፍ ያደጉት 52 ብቻ መሆናቸውን ያሳያሉ። የአገሪቷ ባህል፣ እውቀት እና ታሪክ በስፋት የተዳሰሰበትና የዳበረ የፅሁፍ መረጃ ያለው የግእዝ ቋንቋ እንደሆነም ከነዚህ መረጃዎች መረዳት ይቻላል። በቀጣይነት አማርኛ ቋንቋ ይቀመጣል፡፡ ኦሮምኛ እና ትግርኛ ቋንቋዎች የስነ ፅሁፍ ደረጃቸውን እያሳደጉ ከመጡት ቋንቋዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከስነ ልሳን ተመራማሪዎቹ አስተያየት እና ምክረ ሀሳብ መረዳት የሚቻለው የቋንቋ ጉዳይ በቶሎ ለውይይት ቀርቦ መፍትሄ የማይበጅለት ከሆነ በርካታ መዘዞች ይዞ መምጣቱ አይቀሬ ነው። የቆጡን ሲያወርዱ የብብትን ላለመጣል ሲባል ስነ ልሳናዊ ፋይዳዎቹን ባለመዘንጋት አገራዊ በሆኑ የጋራ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል። ካልሆነ ግን በብሄር ብሄረሰቦች መካከል የእኔ ይበልጥ የእኔ ይበልጥ የሚለው አስተሳሰብ ይሰፋል። ይህን ተከትሎም መራራቅ፣ መቃቃር እንዲሁም ግጭቶችን የመፍጠር አቅሙም ከፍተኛ ይሆናል። ከሁሉም በላይ ግን አብሮ የመኖር እሴትን ይሸረሽራል።
ዳግም ከበደ