ተወልዶ ያደገው በሳውዲ አረቢያ ነው። የትውልድ ሀረጉ ከኢትዮጵያ አርሲ ዞን ይመዘዛል። የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ገጽታ፣ የአየር ንብረትና የህዝቦቿን አኗኗር ከወላጆቹ አንደበት እንደተረት እየሰማ አድጓል። ኢትዮጵያን ሳያያት እየናፈቃት በሰው ሀገር ለበርካታ ዓመታት ኖሯል። ወላጆቹ በሳኡዲ አረቢያ ከሃምሳ ዓመት በላይ ኖረዋል። ከወላጆቹ ጋር መጥቶ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ አይቷት ከተመለሰ በኋላ ደግሞ ቀልቡ እዚሁ ቀርቷል።
ውስጡ ይሳሳላታል፤ ሀገሩ ቤቱ ፤ ሀገሩ ክብሩ ፤ ሀገሩ ተስፋው እደሆነች በሚገባ ተረድቷል። የአረብ ሀገራት ሚዲያዎች ታላቁን የህዳሴ ግድብ አስመልክተው የሀገሩን ጥቅም የሚነካ ዘመቻ ሲከፍቱ ዝም ብሎ ሊሰማቸው አልፈለገም። ይልቁንም በሚገባቸው ቋንቋ ግድቡ ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ፤ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት በማይጎዳ መልኩ ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ተጠቃሚ የመሆን መብት እንዳላት እውነትን ይዞ ሲያስረዳና ሲሞግት ከርሟል። በተለያዩ ጊዜያት ዛቻ ፣ ስድብና ማስፈራሪያ ቢደርሱትም ከያዘው አቋም ፍንክች ሳይል በተለያዩ መድረኮች ለእናት ሀገሩ ጥብቅና እየቆመላት ዛሬ ለተገኘው ድል የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል – መሀመድ አልአሩሲ።
ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ አስመልክቶ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በደስታ ፈንጥዘዋል። የመሃመድ አልአሩሲ ደግሞ ከዚህም በላይ ነው። ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት በስኬት ማጠናቀቅ ምን አይነት ትርጉም እንዳለውና ምን አይነት ደስታ እንደፈጠረበት ጠይቀነው እንደሚከተለው ነግሮናል።
‹‹ከትናንት ማታ ጀምሮ የህዳሴው ግድ የውሃ ሙሌት መጠነናቀቁን የሚያሳዩ ምስሎች በሶሻል ሚዲያው ሲዘዋወሩ እያየሁ ነበር። እውነቴን ነው የምለው የተሰማኝ ደስታ ወደር አልነበረውም። አልጀዚራና ሌሎች የውጭ ሚዲያዎችም ወደ እኔ እየደወሉ ሊያረጋግጡ ይሞክሩ ነበር። ይህ ዓለም በትኩረት የሚከታተለው ትልቅ ጉዳይ ስለሆነ መንግስት ይፋዊ መግለጫ የሚሰጥበት ነው ስላቸው ነበር። መንግስት ውሃ መያዝ መጀመሩን በይፋ እንዳሳወቀ ሁሉ መሙላቱንም እንደዚያው ያሳውቃልና አትቸኩል ትሰሙታላችሁ ብያቸዋለሁ። ›› ይላል መሀመድ አልአሩሲ።
‹‹አንዳንዶች እየደወሉ የሚያናግሩኝ በቁጭት ነበር። ኢትዮጵያ እንዴት ግብጽና ሱዳን ሳይስማሙ ግድቡን ልትሞላ ቻለች? ይሉኛል። እኔ እስከማውቀው ድረስ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት በስምምነቱ መሰረት የተከናወነ ነው። ኢትዮጵያም በስምምነቱ መሰረት እንደምትሞላ ቀድማ አሳውቃለች። ብዙዎች ኢትዮጵያ ባለባት የውስጥ ችግር ምክንያት ትፈርሳለች የሚል ሀሳብ ስለነበራቸው ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት በሰላም ማጠናቀቋ ያስገረማቸው ይመስለኛል። ከንግግራቸው የተረዳሁት ይህንን ነው፤ ፈጥኖ መሙላቱም ግራ ያጋባቸው ይመስላል ይላል መሀመድ አለአሩሲ።
‹‹ ኢትዮጵያ ድሮም ቢሆን የትብብር መንፈስ ካለ ውሃው ለሶስቱም ሀገራት በቂ እንደሆነ ስትናገር ነበር፤ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት እንዲህ በአጭር ጊዜ መጠናቀቁ ውሃውን በአግባቡ ከተጠቀምንበት በቂ መሆኑን የሚያሳይ ነው። እንግዲህ የታችኞቹ ሀገራት ከሚያነሱት መከራከሪያ አንዱ የውሃ አሞላሉ በረዥም ጊዜ እንዲሆን የመፈለግ ነው። አሁን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል ውሃ መያዝ እንደሚቻል ሲመለከቱ ግድቡ ቀስ እያለ መሞላት አለበት የሚለውን ሰበብ እንዲተው ትምህርት ያገኙ ይመስለኛል።
የኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎቱ ልማት እንጂ ግብጽና ሱዳንን መጉዳት እንዳልሆነ በተገኙት መድረኮች ሁሉ ሲያስረዳ ነበር። ውሃው አገልግሎት ሰጥቶ ይሂድ የሚለውን የኢትዮጵያን አቋም መደገፍ ቢችሉ ኖሮ ይህን ያህል መነጋገር አያስፈልግም ነበር። የቀድሞው የሱዳን ውሃ ሚኒስትር የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ትልቅ ጥቅም እንዳለው በተለያየ ጊዜ ሲናገር ሰምቻለሁ። ዛሬም ሁለተኛው የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን አስመልክቶ አልጀዚራ ቴሌቪዢን ባደረገልን ግብዣ እኔና ይህ ሰው ቀርበን ነበር።
ይህንኑ ሀሳብ ሲያወራ ነበር። ይህ ሰው በዘርፉ እውቀት ያለው ሰው ነው። ሱዳኖች የዚህን ሰው ምክር ሊቀበሉ ይገባ ነበር። ከሰሞኑ እንኳን ሱዳን በጎርፍ ስትጠቃ አይተናል። የህዳሴው ግድብ ውሃ መያዝ መጀመሩ ጠቀማት እንጂ እንደበፊቱ የከፋ የጎርፍ አደጋ ይደርስባት ነበር።
አሁን ዓለም ስለ ኢትዮጵያ ትክለኝነት የሚረዳበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስለኛል። የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ሙሌቱን ለማደናቀፍ ገና የንግግር ቀጠሮ ይዘው እያለ ግድቡ በተያዘለት እቅድ መሰረት መሞላቱና በታችኛዎቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ምንም አይነት ችግር አለመፍጠሩ ሲታይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነው።
የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ከተባበሩት መንግስታት ሴኩሪቲ ካውንስል እጅ ወጥቶ በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ በመደረጉ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና ነበር ፤ ዛሬ ሁለተኛውን ሙሌት ማጠናቀቋ ደግሞ በአንድ ወር ውስጥ ሁለት ድል እንድታገኝ አድርጓታል። እውነት አሸንፏል እላለሁ።
በተለያዩ መድረኮች እውነትን ይዤ በመሟገቴ ሰዎች በማያውቁት ነገር ስሜታዊ እየሆኑ ጸያፍ ስድቦችን ሰድበውኛል። እኔ ከኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦቼ ስርዓትን ተምሬ ያደግኩ በመሆኑ ለእነሱ አጻፋ ከመስጠት ይልቅ የተነሳሁበትን ሀሳብ በጥሞና ለማስረዳት እሞክር ነበር። ዛሬ አውነት አሸነፈ የምለው ለዚህ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብና የሌላው አረብ ሀገራት ህዝቦች ይለያያሉ። እኔ እራሴ ስለኢትዮጵያ የበለጠ የተረዳውት እዚህ ከመጣሁ በኋላ ነው። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ገና መኖር ያልጀመረ ነው። እንጨት እያነደደ ምግቡን የሚያበስልና ለዘመናት የመብራት አገልግሎት አይቶ የማያውቅ ነው።
ስለዚህ ለዚህ ህዝብ የሃይል አቅርቦት ከምንም በላይ ያስፈልገዋል። መንግስት ህዝቡን ከችግር ለማውጣትና ኢትዮጵያን ለማሳደግ እንዲህ አይነት ጥረት ሲያደርግ ጎረቤት አገራት ማገዝ ይኖርባቸዋል ብዬ አስባለሁ። ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በአንድ ቀጠና የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ናቸው ። እርስ በእርሳቸው በመረዳዳት ህዝባቸው የተሻለ ኑሮ እንዲኖር ማድረግ ይኖርባቸዋል። የኢትዮጵያ እድገት ለሱዳንና ለግብጽ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው መታሰብ አለበት።
የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ የኢኮኖሚ አቅም እጅ ለእጅ ተያይዞ የህዳሴውን ግድብ ዳር እያደረሰው ነው። ከገጠር እስከ ከተማ ያለው ምስኪን ህዝብ የዚህን ግድብ መጠናቀቅ በጉጉት ይጠብቀዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ህልሙ ካለበት ችግር መላቀቅ ነው። ለዚህም ነው የህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት በደስታ የሚያስፈነጥዘው።
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በአረብኛ ሚዲያዎች ላይ የኢትዮጵያን አቋም የማሳውቀው እኔ ብቻ አይደለሁም። አሁን በዝተናል። ቁጭት ያደረባቸውና አረብኛ ቋንቋ የሚችሉ በርካታ የሀገሬ ሰዎች በተለያዩ ሚዲያዎች እና በሶሻል ሚዲያዎች እውነቱን ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ ጥረዋል። አማርኛ የሚናገሩትም ቋንቋውን ለሚችሉ ሰዎች መልእክት አድርሰዋል። ይህ ጥረታችን ተጽእኖ የፈጠረ ይመስለኛል።
ቢያንስ ግብጽ አባይ ከራሷ ግዛት እንደሚመነጭ አስመስላ የምታስወራውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እያፈራረስን ዓለም ትክክለኛውን ምስል እንዲያይ አድርገናል። ፈጣሪ ረድቶን ውጤታማ ሆነናል። በሃይማኖት፣ በቋንቋ በአስተሳሰብ ብንለያይም ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን ነች። ስለዚህ ምንግዜም በሀገር ጉዳይ በጋራ መቆም ይኖርብናል። ሀገራችንን መስራት ፤ ሀገራችንን ማሳመር ይኖርብናል።
እኔ አሁን ለኢትዮጵያ ህዝብ የማስተላልፈው መልዕክት አንድነታችንን እንድናጠናክር ነው። አንድ ከሆንን ማንኛውንም ችግር በድል መወጣት እንችላለን። ሀገራችን በተፈጥሮ ሃብቷ የታደለች ነች። ከየትኛውም ሀገር የተሻለች እንጂ ያነሰ ሃብት የላትም። መተማመን፣ መከባበር፣ በጋራ መቆመ ፣ የውጭ ሃይሎች ጣልቃ እንዳይገቡብን እድል አለመስጠት ከቻልን የማደግ ተስፋ ያለን ህዝቦች ነን።
ሌሎች ሀገራት ስለኛ ሀገር ጉዳያቸው አይደለም እንደውም እርስ በእርስ አባልተውን ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ ነው የሚፈልጉት። ይህን የውጭ ሃይሎች ሴራ በመቀልበስ ምስኪኑ ህዝባችን የተሻለ ኑሮ የሚኖርበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይኖርብናል›› ይላል መሃመድ ።
መሃመድ አልአሩሲ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን የሚገልጹ ምስሎችን በማህበራዊ ሚዲያ ሲመለከት ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶት እንደነበር ይገልጻል። ከደስታው ብዛት የውሃና መስኖና ኢነርጂ ምኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ጋር ለመደወል አስቦ እንደነበር ይናገራል። በተለይም ከውጭ የተለያዩ ሚዲያዎች እየደወሉለት ግድቡን በጉልበታችሁ ሞላችሁት አይደል? ሲሉት የድል አድራጊነት ስሜት እንደተሰማው ይገልጻል።
መሀመድ ከቅርብ ዓመት ወዲህ ጓዙን ከሳውዲ አረቢያ ነቅሎ ወደ ሀገሩ በመግባት በህዳሴው ጉዳይ ዙሪያ ከተለያዩ የአረብ ሚዲያዎች ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጠ ከርሟል። አሁን ባገኘው ድል እጅግ በጣም ደስተኛ እንደሆነ የሚናገረው መሃመድ በቀጣይም ስለህዳሴው ግድብ ዝርዝር ማብራሪዎችን በመስጠት የተቀናቃኞቻችንን አፍ ለማዘጋት ጠንክሮ እንደሚሰራ ይገልጻል። ህዳሴው ግድብ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ስራ መስጠት እስኪጀምር ድረስ እንቅፋት በመፍጠር ሊያደናቅፉት የሚሞክሩ ሃይሎችን ሁሉ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2013