ዳንኤል ዘነበ
የኮሮና ቫይረሰ ሥርጭቱን በቀጠለ ቁጥር አዳዲስ ዝርያዎች እየፈጠረ እየሄደ ይገኛል። የዓለምን የኮሮና ወረርሽኝ ሁኔታ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” አድርገውታል የተባሉ የተለያዩ የቫይረሱ ዝርያ ዓይነቶች እየተገኙ ይገኛሉ። አዲስ የሚፈጠሩት ቫይረስ ዝርያዎች ቁጥር ሥፍር የላቸውም። ከእነዚህ መሀከል ግን በአሳሳቢነት ደረጃ የሚመደቡ አሉ። አለም አቀፉ የጤና ደርጅት የነዚህን አሳሳቢ ቫይረስ ዝርያ ቁጥር ወደ አሥር ከፍ አድርጎታል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አልፋ፣ ቤታ፣ ጋማ እና ዴልታ በሚል የሚጠሩ የኮሮና ዝርያዎች የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ዴልታ የተባለው አዲስ መጤው ቫይረስ በአሳሳቢነት ደረጃ ይመደባል።
በሕንድ መጀመሪያ የተገኘ ዴልታ የተሰኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ መምጣቱ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። ሦስተኛው የኮቪድ19 ወረርሽኝ ጅማሮ እየታየ እንደሆነ ያመላከተው ድርጅቱ፤ ላለፉት ተከታታይ አራት ሣምንታትም ዓለም ላይ የዴልታ ዝርያ ኮቪድ19 ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን አስታውቋል። በዚህም መሠረት አዲሱ የዴልታ ቫይረስ ዝርያም አሁን ላይ በ111 ሀገራት በአስጊ ደረጃ እየተዛመተ ይገኛል። በአዲሱ ዴልታ ኮቪድ19 ቫይረስም ዓለም ላይ ከአራት ሚሊየን በላይ ሰዎች ለሕልፈት ተዳርገዋል። ቫይረሱ በሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ኢንዶኔዥያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል።
ይህ ዓይነቱ የኮሮና ዝርያ በአሳሳቢነት ደረጃ እጅጉን የበረታ መሆኑን ተከትሎ ከወዲሁ ትልቅ ሥጋትን የደቀነ ሆኗል። በስፋት በመሠራጨት ላይ ያለው ይህ ቫይረስ፤ በኢንግላንድ ባለው የኮሮና ሥርጭት ዘጠና ከመቶ በዚህ ቫይረስ ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ለዚህ ነው እንግሊዝ ሙሉ በሙሉ ከመክፈት ዘግየት እንድትል የተገደደችው።
በአሜሪካ ደግሞ ከዚህ ቀደም ሰባት በመቶ የነበረው የዚህ የዴልታ ቫይረስ ሥርጭት ወደ ሀያ ከመቶ አድጓል። ይህ አሃዝ እየጨመረ እንደሚሄድና ይህ ዴልታ ቫይረስ እንደ ኢንግላንድ ሁሉ ሥርጭቱን ሊቆጣጠረው ይችላል ተብሎ ይገመታል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት መሰራጨት ዴልታ የተሰኘው ዝርያ ወደ ኢትዮጵያ መግባት አለመግባቱ አልተረጋገጠም።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ዴልታ የተባለው ሦስተኛው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአፍሪካና በሌሎች ዓለማት መከሰቱን ተከትሎ ፤ በኢትዮጵያም የመከሰት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ነው። በሀገራችን አልፋ እና ቤታ የተሰኙ የቫይረሱ ዝርያዎች መኖራቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ የዴልታ ዝርያ ስለመኖሩ ለማረጋገጥ ምርመራ ተጀምሯል። የምርመራ አቅምን ለማጠናከር ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በጋራ እየተሰራ ይገኛል። ወደ ሀገራችን ቫይረሱ መግባት አለመግባቱን ለማረጋገጥ በሂደት ላይ ብንሆንም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዴልታ ቫይረስ ወደ አሳሳቢነት ደረጃ ከተሸጋገረ ውሎ አድሯል።
በከፍተኛ ደረጃ ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ እንደሚችል በማስመስከሩ እንደሆነ ይታመናል። ከዚህ በተጨማሪም፣ የበሽታና የመግደል ችሎታውም ጨምሯል። ሌላው ችግር ወይም አሳሳቢነት ደግሞ ይህ አዲስ ቫይረስ በአሁኑ ወቅት በመሰጠት ላይ ያሉ ክትባቶችን ማሸነፍ ወይም ማምለጥ ይችል ይሆን የሚለው ነው። ለዚህ ምላሽ ጥናቶች ተደርገው የቀረቡ ውጤት አሉ።
በዚህ ቫይረስ ላይ ጥናት የተደረገው በፋይዘርና በአስትራ ዜኔካ ክትባቶች ላይ ነው። አገር ቤት የሚሰጠው የአስትራ ዜኒካው ክትባት ነው። ሁለቱም ክትባቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሰጡ በኋላ በተደረገው ጥናት እነዚህ ክትባቶቸ በዴልታ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ወደ በሽታ እንዳይቀየር የማድረግ ችሎታቸው 33 ከመቶ ነበር (33%)። እንደሚታወቀው በቂ መከላከያ ለማግኘት እነዚህ ክትባቶች ሁለት ጊዜ ነው የሚሰጡት።
ሁለተኛው ክትባት ከተሰጠ በኋላ በዴልታ ቫይረስ ምክንያት የበሽታ ሥሜትን የማስጣል ችሎታቸው በፋይዘሩ ክትባት በኩል ወደ 88 በመቶ 88% ሲያድግ በአስትራ ዜኔካው ክትባት በኩል ደግሞ ከመቶ 60% ከፍ ብሏል። ነገር ግን በዴልታ ቫይረስ አማካኝነት ሰዎች ወደ ሆስፒታል እንዳይገቡ የመከላከል ችሎታ ሲታይ ክትባቶቹ የሚያረጋጋ ውጤት አሳይተዋል። ሰለዚህ ከሁለት ክትባቶች በኋላ የፋይዘር ክትባት 96% ሰዎች በሕመም ምክንያት ሆስፒታል የሚያስገባ ደረጃ እንዳይደርሱ የሚያደርግ ሲሆን፤ የአስትራ ዜኒካው ደግሞ በ92 በመቶ የማስጣል ወይም የመከላከል ችሎታ እንዳለው ተገልጿል። ይህ መረጃ ከኢንግላንደ በኩል የሕዝብ ጤና ካደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ የተገኘ ነው።
በአጠቃላይ ከዚህ ውጤት መረዳት እንደሚቻለው ክትባት ለወሰዱ ሰዎች ትልቅ እፎይታ የሚፈጥር መሆኑን ነው። ስለዚህ እኛም ከወዲሁ ቫይረሱ ከሚያደርሰው ጉዳት ለመጠበቅ ህብረተሰቡ ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። ህብረተሰቡ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳትና የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ በመተግበር የቫይረሱን ሥርጭት መገደብ ይኖርበታል።
በተጨማሪም ክትባቶች በሽታን ከመከለከልና ሊያደርሰው ከሚችለው ጉዳት አንጻር ተመሳሳይ የመከላከል አቅም ያላቸው በመሆኑ ህብረተሰቡ ሊከተብ ይገባዋል። በመጨረሻም በአሁኑ ወቅት አሳሳቢው የቫይረሱ ዝርያ ዴልታ ቢሆንም፣ ነገ የሚመጣው ወይም የሚፈጠረው አዲስ የቫይረስ ዝርያ ባህሪ እየከፋ እንጂ እየለዘበ አይሄድም። ስለዚህ አዲስ የቫይረስ ዝርያ የሚፈጠረው ደግሞ ሥርጭቱ በቀጠለ መጠን መሆኑን በመገንዘብ፣ ሁሉም የዚህ ቫይረስ ሥርጭት ለመግታት መጣር አለበት።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም