
አስናቀ ፀጋዬ
አዳሚ ቱሉ፡- የምስራቅ ሸዋ ዞን በአዳሚ ቱሉ ኮምቦልቻ ወረዳ ቀደም ሲል በኢንቨስትመንት ስም ታጥሮ የቆየ መሬትን አስለቅቆ የአካባቢው አርሶ አደሮችን በክላስተር በማደራጀት በሜካናይዜሽን የተደገፈ የስንዴ እርሻ ተጀመረ፡፡
የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር አቶ አባቡ ዋቆ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ፣መንግሥት አርሶ አደሩ በሙሉ በክላስተር ተደራጅቶና በመካናይዜሽን ምርትና ምርታማነትን እንዲጨምር አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በዚሁ መሠረትም ዞኑ በአዳሚ ቱሉ ኮምቦልቻ ወረዳ ቀደም ሲል በኢንቨስትመንት ስም ታጥሮ የነበረ ስድስት መቶ ሄክታር መሬት በሰላሳ ዘጠኝ ክላስተር ለተደራጁ አንድ መቶ ሃያ ሁለት አርሶ አደሮች በማስተላለፍ በመካናይዜሽን በተደገፈ መልኩ ስንዴ መዘራት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ ምርታቸውን አምርተው ለፋብሪካዎች ሲያቀርቡ በተዘዋዋሪ ከአንድ መቶ አርባ አምስት በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩና አስካሁን በዞኑ ከ 7 ሺ 940 ሄክታር መሬት በላይ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በፊት ሞዴል አርሶ አደሮች በአንድ ሄክታር ማሳ ከስልሳ እስከ ሰማኒያ ኩንታል ያመርቱ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አባቡ ፣ ሞዴል ያልሆኑ አነስተኛ አርሶ አደሮች ከተመሳሳይ ማሳ ከአስራ ሁለት እስከ ሃያ ኩንታል እንደሚያመርቱ አስታውቀዋል።
በአዳሚ ቱሉ ወረዳ በዚሁ በየክላስተር ተደራጅተው ስንዴ መዝራት የጀመሩ አርሶ አደሮችም ከአንድ ሄክታር ማሳ እስከ ሰማንያ ኩንታል ምርት ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ በክላስተር ተደራጅተው ሲያመርቱ የገበያ ትስስር ችግራቸውን ከመቅረፍ በዘለለ ምርትና ምርታማነታቸውን እንደሚያሳድጉ የጠቆሙት አቶ አባቡ፤በመሬቱ ላይ ለአንድ ዓመት ካመረቱበት በኋላ ለሌሎች አስረከበው እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡
መሬቶች ምርት ሳይሰጡ ፆማቸውን እንዳያድሩ በሚለው መርህ በዞኑ 7 ሺ 940 ሄክታር በላይ የማይመረትባቸው ማሳዎች በየዓመቱ ለልማት እንዲውሉ መደረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡
የክላስተር እርሻው ምርትና ምርታማነት ከመጨመር በላይ ሳይታረሱ ጾም የሚያድሩ መሬቶች በማረስ የአካባቢውን ብሎም የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንደሚረዳ አመልክተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አርሶ አደሩ የልምድ ልውውጥ በማድረግ ያገኘውን እውቀትና ክህሎት ለሌላ አርሶ አደር የማስተማር እድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል። እርሻ በማሽነሪ መካሄዱ ምርት በሁለት እጥፍ ዕንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም