
አዲስ አበባ፡- መንግሥት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ በቀጣይ ሰላም ማስፈንና የህዝብ ለህዝብ መቀራረብ መፍጠር እንደሚጠበቅበት የአዕምሮ ህክምና ባለሙያ እና የሀገር ሽማግሌ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አስታወቁ፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤በምርጫው የህዝብን ይሁንታ ያገኘው ብልጽግና የአገር ውስጥ ሰላም ማስፈንና የህዝብ ለህዝብ ቅርርብ መፍጠር ጥልቅ የቤት ስራው ነው፡፡
የውስጥ ሰላምና የህዝብ ለህዝብ መቀራረብ አንድነትን በማጠናከር የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ሴራ ለማክሸፍ እንደሚረዳ ያመለከቱት ፕሮፌሰር መስፍን፣ የመረጡትንም ያልመረጡትንም እኩል በማገልገል ፍትሐዊ አሠራር ማስፈን ፓርቲው እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡
‹‹ህዝብ መንግሥትን ሲመርጥ ሰላም እንዲያሰፍንለት፣ ልማት እንዲያመጣለት ኃላፊነት ነው የሰጠው›› ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ብልጽግና ልማት ለማምጣት የሚያደርገው ጥረት ህዝብን አሳታፊ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ህዝብ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከሰቱትን ያውቃል፤ መንግሥትን አምኖ የመረጠው እነዚያ ችግሮች እንዲቀረፉና ልማት እንዲመጣለት ስለሚፈልግ ነው፡፡ ብልጽግና ይሄን ለማስተካከል በሁሉም ዘርፍ እስከታች ያለውን መዋቅሩን መፈተሽና ማስተካከል ይገባዋል፡፡
ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገሪቱን ለመምራት መንግሥት መመስረት የሚያስችል ድምጽ ያገኘው ብልጽግና በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በገባው ቃል መሰረት ይመራኛል ብሎ አምኖ ለመረጠው ህዝብ ሰላምን ሊያሰፍንለት ይገባል ብለዋል፡፡
በምርጫው ዕለት የነበረውን ረጅም ሰልፍና የሰዎች የመምረጥ ፍላጎት ከፍተኛ ነበር ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ይህ የህዝብ የመምረጥ ፍላጎት የሚያሳየው ህዝቡ ሰላም የሚያሰፍንለትን መንግሥት ለመምረጥ መፈለጉን እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ገለጻ፤ ብልጽግና ማሸነፍ ሳይሆን የህዝብን ይሁኝታ ነው ያገኘው፡፡ ለሚቀጥለው አምስት ዓመታት የህዝብን ፍላጎትና ጥያቄ የሚመልስበት ኃላፊነት ነው የተሸከመው፡፡ አገሪቱ ካሳለፈቻቸው ክስተቶች አንፃር ብዙ ተግዳሮቶችን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ ቅድሚያ መስጠት ያለበትም ለሰላም ነው ብለዋል፡፡
‹‹ጥይት የማይተኮስባት ኢትዮጵያን ነው ማየት የምንፈልገው›› ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ሁሉንም ነገር በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ በመነጋገር መፍታት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ህዝቡ በሰላም ውሎ ለመግባት እና ለመስራት ብልጽግና ላይ እምነቱን ጥሏል ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ይህንም ማድረግ ካልቻለ የሰላም አለመኖር ከአገሪቱ ድህነት ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ ክስረት ሊመጣ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም