
አዲስ አበባ፡- የኢድ -አል አድሐ አረፋ በዓል ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ ዱዓ በማድረግ እና በአንድነት ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ኢድሪስ አስታወቁ ፡፡ የህዳሴውን ግድብ ተባብረን እንደጀመርነው ተባብረን ልናጠናቅቀው ይገባል፤ ይህን ለማድረግ እስከመጨረሻው ድረስ አንድነትን ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል::
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ኢድሪስ የኢድ -አል አድሐ አረፋን በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንዳስታወቁት፤ የአረፋ በዓል በሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በዓል ነው።
የሙስሊሙ ህብረተሰብ በዓሉን ሲያከብር የዕምነቱን ስርዓት ተከትሎ የተቸገሩትን በመርዳት፣ ዱዓ በማድረግ እና በአንድነት ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል ፡፡
6ኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም በመጠናቀቁ መደሰታቸውን የተናገሩት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ፤ በምርጫው ላሸነፉ አካላትም የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሰላም የአገር መሰረት መሆኑን አውቀን ሰላማችንን መጠበቅ ይገባናል፡፡ አሁን በሕዝብ ዘንድ የተመረጡትም በቀጣይ ሁሉንም ሰው በእኩል በማየት ማስተዳደርና በብሔርና በብሔረሰብ መከፋፈልን ማውገዝ አለባቸው ብለዋል፡፡ መሪዎች ሲሳሳቱ ተማሪዎች ማረም፣ ጥሩ ሲሰሩም ማበረታታት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡
የአገር ሰላም ለመጠበቅ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተገቢውን ድርሻ እንዲወጡ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ስም ጥሪ አቀርባለሁ ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ፤ የህዳሴውን ግድብ ተባብረን እንደጀመርነው ተባብረን ልናጠናቅቀው ይገባል፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ እስከመጨረሻው ድረስ አንድነትን ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ጦርነት፣ አመጽ፣ መቃረንና መወጋገዝ ለየትኛውም ዕምነት እንደማይጠቅምም አመልክተዋል፡፡
የሚቃወም ሰው ለአገር፣ ለሰላምና ለአንድነት ደንታ የሌለው መጥፎ ነው፡፡ ከዚህ መጥፎ አመለካከት በመውጣት ወደ ሰላምና አንድነት መሄድ ያስፈልጋል፡፡ አላህ ለሁሉም ሀብትና ስልጣን አይሰጥም፤ ሰው በመግደልና በመዝረፍ አገርን በማውደም ስልጣን አይገኝም ብለዋል፡፡
በመነጋገርና በመመካከር ወደ ሰላም መመለስ አስፈላጊ ነው፣ መንግስትም ወደ ሰላም እንመለስ የሚለውን ሀሳብ ሊገፋበት ይገባል፤ ሁሉም ተቀብሎ ወደ አንድነት በመምጣት አገርን ከማፍረስ ልንቆጠብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2013