
አስመረት ብስራት
አዲስ አበባ፡- የጅማ እፅዋት አፀድ ለዘንደሮው አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚውል ከመቶ ሰማኒያ ሺ በላይ ችግኞች እያሰራጨ መሆኑን አስታወቀ። ችግኝ የማፍላት ሥራ ከጀመረ አንስቶ እስከአሁን ከአንድ ሚሊየን በላይ ሀገር በቀል ችግኞች እንዲተከሉ ማድረጉን አመለከቱ።
የእፅዋት አፀዱ ዳይሬክተር አቶ ደሬሳ አቤቱ በተለይ ከአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፣ የእፅዋት አፀዱ በተለይም በመጥፋት ላይ በሚገኙ ዝርያዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው።
ተቋሙ በጅማና በጅማ ዙሪያ ለሚገኙ ሦስት ዞኖች የሚውል ችግኝ በስፋት አፍልቶ ማዘጋጀቱን የገለጹት አቶ ደሬሳ ፣ ዘንድሮም ለአረንገዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚውል ከ20 በላይ የሀገር በቀል እፅዋት ዝርያ ያላቸው ችግኞችን በማፍላትና በማሰራጨት ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
ከሁለት ሺ ዘጠኝ ዓመተ ምህረት ጀምሮ ችግኝ እያፈላ በነፃ ማከፋፈል የጀመረ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ በተለይም ሊጠፉ ለተቃረቡ ዝርያዎች ቅድሚያ በመስጠት ከመቶ ሰማኒያ ሺ በላይ ችግኞች ጥያቄ ላቀረቡ አካላት አፍልቶ በማሰራጨት ላይ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የጅማ እፅዋት አፀድ በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ስር ከሚገኙ ሁለት ትልልቅ እፅዋት አፀዶች አንዱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደሬሳ፣ የሚያፈላቸው ችግኞች አካባቢውን የተላመዱና ስርዓተ ምህዳሩ እንዲያገግም የሚያደርጉ ቀደምት ዝርያዎች ናቸው ብለዋል።
የችግኝ ተከላው በጣም እየተጎዱ ያሉ ስነምህዳሮች እንዲያገግም የሚያደርገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ደሬሳ፣ ችግኝ የሚሰጠው ፍላጎታቸውን በደብዳቤ ላቀረቡ ፣ የት አካባቢ በምን ያህል ሄክታር ላይ እንደሚተከሉ እና ለመንከባከብ ኃላፊነት ለሚወስዱ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደሆነ አስታውቀዋል።
የችግኝ ማፍላቱ ሄደት ሀገር በቀል ችግኞች፤ በመጥፋት ላይ ያሉ ዘርያዎች፤ እና ጠቀሜታቸው ላቅ ያለ የዛፍ ዓይነቶችን በመለየት የሚሠራ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ደሬሳ ፣ለምሳሌ ዋንዛ የተባለ እንጨት ጠቀሜታው የላቀ በመሆኑ ለሱ ቅድሚያ ተሰጥቶት በብዛት ይሰራጫል። ለቡና ጥላ የሚሆኑ ዛፎችም ለገበሬው ይከፋፈላሉ ብለዋል።
“አረንጓዴ እናልብስ” ሲባል ዝም ብሎ የተገኘውን ሁሉ መትከል ሳይሆን ከስነ መህዳሩ ጋር የተስማማ ሀገር በቀል ችግኞችን ምርጫ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል። በየዓመቱ ችግኝ ከመትከል ባለፈ ጠቀሜታውን በመረዳት በመንከባከብ እድገቱ እንዲፋጠን ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም