ትምህርት ሚኒስቴር ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም ከኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር በመተባበር በአገር አቀፍ ደረጃ ለ9ኛ ጊዜ “አገርኛ ቋንቋዎች ለልማት፤ለሰላም ግንባታ እና ለአብሮነታችን” በሚል መሪ ቃል በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በአሰላ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት እያተከበረ ይገኛል፡፡
በዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ መሃመድ አህመዲን ለተሳታፊዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት በአፍ መፍቻ ቋንቋ መጠቀም አስፈላጊነትን በህብረተሰቡ ዘንድ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግና በአፍ መፍቻ ቋንቋ መጠቀም ያለውን ፋይዳ ለማስገንዘብ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመጠቀምና የማልማት ህገ መንግስታዊ መብታቸው መሆኑን አመላክተዋል ፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በ53 ቋንቋዎች ትምህርት እየተሰጠ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 27ቱ 10ኛ ክፍል የብሄራዊ ፈተና እንደሚሰጥባቸው ፤38 ቋንቋዎች ከ1ኛ-4ኛ ክፍል በማስተማሪያነት፤ 29ኙ ከ1ኛ-8ኛ በማስተማሪያነት፤ 19 ቋንቋዎች በመምህራን ትምህርት ኮሌጅ ትምህርት የሚሰጥባቸው 9 ቋንቋዎች በዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ እና በሁለተኛ ዲግሪ በትምህርት ዓይነትነት በመማሪያና በማስተማሪያነት እያገለገሉ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ሁሉም የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች የበለጠ መልማት እንዲችሉ በዚህ በዓል ላይ በሚቀርቡ ጥናታዊ ፅሁፎችና በሚደረጉ ውይይቶች ችግሮችንና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በመጠቆም ተሳታፊዎች ሙያዊ ሃላፊነታቸውንም እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ከሁለቱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ባለሙያዎችና አመራሮች፤የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤የክልል ትምህርት ቢሮ ተወካዮችና አባ ገዳዎች እና መምህራን የተገኙ ሲሆን የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎችም ቀርበዋል።
ምንጭ ትምህርት ሚኒስቴር