
በአካባቢው የሚታዩት አብዛኞቹ ያረጁ የቀበሌ ቤቶች ናቸው። ቤቶቹ የአገልግሎት ዘመናቸው ያለፈባቸውና ለበርካታ ዓመታት እድሳት ናፍቋቸው የቆዩ ስለመሆናቸው ገጽታቸው ይመሰክራል – የፒያሳ አካባቢ ሰራተኛ ሰፈር መኖሪያ መንደሮች። ከመኖሪያ ቤቶቹ ጋር አብረው ያረጁ ነዋሪዎች ደግሞ ያለዕድሜያቸው ተጎሳቁለዋል። ኑሮ በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሁልጊዜ ክረምት በመጣ ቁጥር ከደጅ አይሻል የሆነው ቤታቸው ጣሪያው ዝናብ፤ ግድግዳው ደግሞ ብርዱን እያስገባ ሌላ ጭንቀት ሆኖባቸዋል። ዘንድሮን እንዴት እናልፍ ይሆን የሚለው ሀሳብም የአእምሮ ስራ ሆኖባቸው በአንድ በኩል በላስቲክ ሌላውን በወረቀትና ካርቶን መጠጋገኑን ተያይዘውታል።
‹‹የተነቃነቀ ጥርስ መውለቁ አይቀርም›› እንዲሉ የዘመመው ደሳሳ ጎጆ ከዛሬ ነገ በእነርሱና በልጆቻቸው ላይ እንዳይወድቅ ለሌት ተቀን መስጋታቸው አልቀረም። ነገር ግን ስጋታቸውን በውስጣቸው ሸሽገው ላይ ታች በማለት ጎርሰው ለማደር መሯሯጣቸውን አላቆሙም። ሌላ አማራጭ የላቸውም እና። በጎስቋላ መኖሪያ ቤት ጎስቋላ ኑሮን ለመኖር የኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ዋናው ምክንያታቸው በመሆኑ ሽንቁርቁሩን የቤት ጣሪያ ለመድፈን አልሞከሩም። እጅግ ዝቅተኛ በሆነው የጉልት ንግድ፣ በሰው ቤት ስራና ልብስ ማጠብ፣ እንጀራ በመጋገር፣ አሻሮ በመቁላት እና በሌሎችም ጊዜያዊ ስራዎች የሚተዳደሩ ናቸው።
አድካሚና ውጣ ውረድ የበዛባቸውን ሥራዎች ሰርተው የሚያገኙት ገቢ ከዕለት ጉርስ በዘለለ የኑሮ ቀዳዳዎችን ለመሙላት አይችልምና መኖሪያ ቤታቸው የአገልግሎት ዘመኑን ጨርሶ ቢያፈስም ሆነ ቢወድቅ የግድ ነው። ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል ሆነና እነዚህ አቅመ ደካማ ነዋሪዎች የዕድሜያቸውን አጋማሽ የሚሆን ጊዜ በደሳሳው ጎጆ ለማሳለፍ ተገደዋል።
እጅግ ፈታኝና አሰቃቂ በሆነ መኖሪያ ውስጥ የስጋትና የሰቀቀን ኑሮ ከሚገፉት መካካል ወይዘሮ አጸደ ጅንገታ አንዷ ናቸው። ወይዘሮ አጸደ ዘጠኝ ቤተሰቦች ያላቸው ቢሆንም መኖሪያቸው ግን እንኳንስ ለዘጠኝና ለሶስት ሰዎችም በቂ አይደለም። ከቤቱ መጠን መጥበብ ባለፈ የቤቱ ሁኔታ ፈታኝና የሰው ልጅ ሊኖርበት የማይችልና የህዝብ መጸዳጃ ቤት አጠገብ ነው።
በቤቱ የነበረው ሽታ ለመኖር አይደለም ለደቂቃዎች መቆም የማያስችል እንደነበር የሚያነሱት ወይዘሮ አጸደ፤ ዛሬ ላይ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ በላያቸው ላይ ሊወድቅ በደረሰ ቤት ውስጥ መኖር ከጀመሩ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ ይላሉ። ታዲያ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ዕድሜያቸውን የኖሩበት ይህ ቤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመና እየተጎሳቆለ መጥቶ ዛሬ በላያቸው ላይ ሊወድቅና ዝናብ በመጣ ቁጥር ሳፋና ባልዲ ደቅነው በስጋት ቢቀመጡም ከዛሬ 47 ዓመት በፊት ግን ቤቱ በጥሩ ቁመና ላይ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ይሁንና 47 ዓመታት የኖሩበት የወይዘሮ አጸደን ቤት ጨምሮ በአካባቢው ያሉ አብዛኛው ቤቶች ከዕድሜያቸው የተነሳ ለነዋሪዎች ፈታኝ ሕይወትን እንዲገፉና የስጋት ምንጭ መሆን ከጀመሩ ዓመታትን ያስቆጠሩ ናቸው። ወይዘሮ አጸደም መኖሪያ ቤታቸው ምንም እንኳን ለመኖሪያ ምቹ ያልሆነና የሚረብሽ ሽታ ቢኖረውም ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ኑሯቸው የሚተርፍ ነገር የለምና በችግር ውስጥ ሊኖሩ የግድ ሆነ። እርሳቸውን ጨምሮ ለዘጠኝ ቤተሰብ የዕለት ጉርስ ለማጉረስ ይታትራሉ፤ ይወጣሉ፣ ይወርዳሉ እንጂ ሞልቶላቸውና አቅም አግኝተው ቤት አልቀየሩም።
በሰዎች ቤት በመዘዋወር ልብስ በማጠብ፣ እንጀራ በመጋገር፣ ጠላ በመሸጥ እና የተለያየ የቤት ውስጥ ስራ በመስራት በሚያገኙት ገቢ ልጆቻቸውን ያሳድጋሉ። ልጆችን ይዞ በሚያፈስና ከነገ ዛሬ ወደቀ በማለት ስጋት ሆኖ መኖር እጅግ ፈታኝ እንደሆነ ያነሱት ወይዘሮዋ፤ የሚኖሩበት የህዝብ ሽንት ቤት በሆነ ቦታ ላይ በመሆኑ በተለየ ሁኔታ ኑሯቸውን የከፋ አድርጎታል። ለመጸዳጃው ቅርብ በመሆናቸው ሽታው በእጅጉ ይረብሻቸዋል። በክረምት ወቅት ደግሞ ጣራው የሚያፈስ በመሆኑ ዝናብ ሲዘንብ ሳፋ፣ ባልዲና ምጣድ በየቦታው ደቅነው ያድራሉ።
በእንደዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ሂደት ውስጥ እያለፉ ዘጠኝ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት ወይዘሮዋ፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ወንድ ልጃቸው ወላጅ እናቱን ሊያግዝ አረብ ሀገር ሄዶ አልተሳካለትም። በሄደ በስምንት ወሩ በለበሰው ልብስ በነጠላ ጫማ ተመልሷል። ታዲያ አግዛለው ብሎ ሳይሳካለት የቀረው ወጣትም በብስጭት ውሎ አዳሩ ጎዳና ሆነ። እናትም አይዞህ ብለው ልጃቸውን ከጎዳና አንስተው በጉያቸው ያስገቡ መሆናቸውን ወይዘሮ አጸደ እንባቸውን እያፈሰሱ ነው የተናገሩት ።
እንደ ወይዘሮ አጸደ ሁሉ ወይዘሮ ኢክራም አብዶም እንዲሁ ለመኖሪያ እጅግ ፈታኝ በሆነ ቤት ውስጥ ትኖራለች። ኢክራም የሶስት ልጆች እናት ስትሆን የልጆቿ አባት በሕይወት የለም። ስለዚህ ልጇቿን እንደ እናትም እንደ አባትም ሆና ለማሳደግ ተገደደች። በመሆኑ ከቤቱ ጎን ጉልት በመቸርቸር ላይ ስትሆን በዚሁ ቤት ውስጥ ለ17 ዓመታት ኖራለች።
ቤቷ ጣራው ከማፍሰሱ በተጨማሪ ከጀርባ ያለው ግድግዳ ሊወድቅ አዘንብሎ እንደነበር ትናገራለች። ታዲያ የሚያፈሰውን ጣራ የቤቱን እቃ ደቅና ብትከላከለውም ያዘነበለው ግድግዳ ግን እረፍት ነስቷት ከራርሟል። መቼ ልጆቼ ላይ ወደቀ በማለትም በርካታ የሰቀቀን ለሊቶችን አሳልፋለች። ‹‹በተለይም የክረምት ወቅት ሲመጣ ጭንቀቴ ይጨምራል እንዳላሰራው አቅም የለኝ›› የምትለው ኢክራም፤ ሌትም ቀንም ሳፋ እየደቀነች የዝናቡን ፍሳሽ ትከላከላለች። ያም ሆኖ ግን አልፎ አልፎ በሚዘንበው ጠንከር ያለ ዝናብ ቤቱ ካሁን አሁን ወደቀ በማለት በስጋት ከርማለች።
ወይዘሮ አጸደ እና ወይዘሮ ኢክራምን ጨምሮ በአካባቢው 20 የሚደርሱ ዜጎችን ካሉበት የስጋት መኖሪያ ሊያወጣ ከዛም ባለፈ እራሳቸውን የሚችሉበትን የሥራ ዕድል መፍጠርን ያለመ ራዕይ ሰንቆ ብቅ ያለው ታዲያ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለየ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ የጀመረ መሆኑን የሚኒስቴሩ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ ታመነ ያስረዳሉ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ በተያዘው ክረምት የበጎ ተግባር መርሃ ግብሩ በአራዳ ክፍለ ከተማ በተለይም ሰራተኛ ሰፈር ያሉ ለመኖሪያ ምቹ ያልሆኑ ቤቶችን ባዋቀረው ኮሚቴ ለይቶ ለማደስ የበጎ ሥራውን ከሰሞኑ ጀምሯል። የቤት ማደስ መርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች በዘፈቀደ ያልተመረጡና ኮሚቴ ተቋቁሞ በጥንቃቄ የተለዩ በመሆኑ የከፋ ችግር ያለባቸውን ነዋሪዎች መለየት ችሏል። በመሆኑም 20 በከፋ የመኖሪያ ቤት ውስጥ ያሉትን አቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት የማደስ ሥራውን ጀምሯል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሌሎች ተቋማት እያከናወኑ ካሉት የበጎ ተግባር መርሃ ግብር ለየት የሚያደርገው አንድ ሁለት ብሎ በተናጠል መኖሪያ ቤቶችን ከማደስ ባለፈ የንግድ አገልግሎት የሚሰጡ ለገቢ ምንጭነት የሚያገለግሉ ቤቶችንም አብሮ ለመስራት አስቧል። ቤቶቹ የሚሰሩት አንድ ፎቅ ወደላይ ሲሆን ከላይ ያለው ቤት ለመኖሪያቸው ይሆናል። ከስር ያለው ደግሞ ቤት የታደሰላቸውና መኖሪያቸውን ፎቅ ላይ ያደረጉ አቅመ ደካማ የሆኑ ነዋሪዎች የሚችሉበትና ከጠባቂነት ወጥተው እራሳቸውን የሚያሻሽሉበት የተለያዩ የንግድ ዘርፎች ይከወኑበታል።
በመሆኑም አቅመ ደካማ የሆኑና ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላቸው እንዲሁም ከዚህ ቀደም ይተዳደሩበት የነበረውን ስራ በተመቻቻ መንገድ እንዲሰሩ ይደረጋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች፣ የእንጀራ መጋገሪያና ሌሎችንም በባለሙያዎች አስጠንቶ የነዋሪዎችን ህይወት በዘላቂነት መቀየርና ከጠባቂነት መላቀቅ የሚስችላቸውን የሥራ ዘርፍ የሚያቀርብ ይሆናል። የቤቱ አሰራርም ለየት ያለ ሲሆን ከተሰራ ላይቀር ከፍ ያለና የማያዳግም ሥራ መስራት እንዳለበት ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ካለባቸው የመንግስት ሀላፊነት ባለፈ ሰውኛ ባህሪያቸው አስገድዷቸው ነዋሪዎቹን ድርብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችለውን የበጎ ተግባር መርሃ ግብር ሲጀምሩ፤ ታች ወርደው ቤቶቹ ከመፍረሳቸው አስቀድሞ ምን ይመስሉ ነበር በማለት ነዋሪች ምን ያህል ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ለመረዳት በነዋሪዎቹ ቤት ውስጥ ገብተው ከተመለከቱና የችግሩን ጥልቀትና አስከፊነት ከተረዱ በኋላ ቤቶቹን በማፍረስ የበጎ ሥራውን በይፋ አስጀምረዋል።
የሚታደሰው ቤት በአንድ ግቢ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ካጠገቡ የግል ቤቶችም ስለነበሩ አብረው እንዲታደሱና እነሱም የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። ቤቶቹ ውስጥ ሲገባ እጅግ የሚያሳዝን ታሪኮች አሉ። ተጠባብቀው ባሉት ትንንሽ የመኖሪያ ክፍሎች ውስጥ በጣም በትንሹ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ቤተሰቦች ይኖራሉ። የነዋሪዎቹ አመጣጥ ደግሞ የልማት ተነሺ ሆነው የመጡ እና እዛው ተወልደው ያደጉ ነዋሪዎችም አሉ።
ታዲያ እነዚህ ዜጎች ምቹ ባልሆነና ከፍተኛ ስጋት ያለበት መኖሪያ ውስጥ የነበሩ ሲሆን በተለይም እሳት አደጋ ቢነሳ ነዋሪዎቹ የሚወጡበት ለማምለጫ የሚሆን የማርያም መንገድ እንኳን አልነበራቸውም። እንዲህ አይነት ቤቶችን ማደስና ሙሉ ለሙሉ አፍርሶ መስራት ለነዋሪዎች ከሚሰጠው እፎይታ ባለፈ የከተማዋን ገጽታ የሚገነባ መሆኑን ዳይሬክተሯ አስረድተዋል። ይህን ማህበራዊ ሀላፊነት በመወጣት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የመቀየርና የማሻሻል ሥራ እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
መስሪያ ቤቱ አሁን ላይ በአራዳ ክፍለ ከተማ በሰራተኛ ሰፈር ከጀመረው የቤት እድሳት በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች ማለትም እሪ በከንቱ አካባቢ በተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ሥራን እየሰራ ይገኛል። የበጎ ተግባር ሥራው ቀጣይነት የሚኖረውና ክረምትን ብቻ ጠብቆ የማይሰራ መሆኑንም ዳይሬክተሯ አመላክተው የአንድና የሁለት አካባቢ ቤቶችን አድሰን በከተማዋ ያለውን ምቹ ያልሆነ መኖሪያ ቤት ችግር መፍታት የማይቻል በመሆኑ አቅም በፈቀደው ልክ ሥራው ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል።
ቤቶችን ከማደስ በተጨማሪም አቅመ ደካማ ዜጎች ከተረጂነትና ከጠባቂነት የሚወጡበትንም ዕድል የማመቻቸት ሥራ በተጓዳኝ በመስራት የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚደረግ ይሆናል። ሥራው የተጀመረው የሰራተኛ ሰፈር የቤት እድሳትም ግንባታው በሁለት ወራት ውስጥ ተጠናቅቆ ለነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል።
መንግስታዊ ሀላፊነትን ከመወጣት ባለፈ በአይነቱ ልዩ የሆነውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአቅመ ደካማ ዜጎች እያበረከተ ያለው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያደረገላቸውን በጎ ተግባር አንስተው የደስታ እንባቸውን እያፈሰሱ ሲቃ በተናነቀው ድምጽ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ወይዘሮ አጸደ እና ወይዘሮ ኢክራም የሰሙትን ሳይሆን በአይናቸው ያዩትንም ማመን አቅቷቸዋል።
‹‹በውስጤ ብዙ ቁስል አለ። ቢሆንም አሁን ፈጣሪ ምድር ላይ ወርዶ እንደተመለከተኝ እቆጥራለሁ። ለዚህም እጅግ በጣም ደስታኛ ነኝ ፤በጣም አመሰግናለሁ። ጥሩ ላሰበና መልካም ሥራ ለሰራ ሁሉ ፈጣሪ በእጥፍ ድርብ ይክፈለው›› በማለት ወይዘሮ አጸደ ሲመርቁ፤ ሶስት ልጇቿን ያለ አባት የምታሳድገው ወይዘሮ ኢክራምም እንዲሁ ላቅ ያለ ምስጋናዋን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ለአካባቢው ወጣት አቅርባ ድጋፉ ለሌሎችም ቢደርስ መልካም ነው በማለት ሀሳቧን ቋጭታለች።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2013