ስራን ‹‹ሀ›› ብሎ የጀመረው ገና በልጅነቱ ነው። በለጋ እድሜው ከሊስትሮ እስከ ፅዳት፣ ከፅዳት እስከ ሸንኮራ ንግድ፣ ከሸንኮራ ንግድ እስከ ሱቅ በደረቴ፣ ከሱቅ በደረቴ እስከ ጋራዥ ቤት ድረስ የተለያዩ ስራዎችን ሠርቷል። በአነስተኛና ጥቃቅን ከሌሎች ወጣቶች ጋር ተደራጅቶም የብረትና የእንጨት ሥራዎችን ሞክሯል።
በመጨረሻ ልቡ ወደ ማስታወቂያ ስራ አዘምብሎ ከአንድ ጓደኛው ጋር በመሆን የጀመረው ስራ ዛሬ ፍሬ አፍርቶ የራሱን የማስታወቂያ ድርጅት እንዲከፍትና ከራሱ አልፎ ለሌሎችም የስራ እድል እንዲፈጥር አስችሎታል። በከተማዋ አሉ ከተባሉ አስር የማስታወቂያ ድርጅቶች ባለቤቶች ውስጥ አንዱ ለመሆንም በቅቷል- የአዱሊያን ማስታወቂያና ፕሮሞሽን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ቦርሶማ።
አቶ ሀብታሙ ውልደቱ አስመራ ቢሆንም እድገቱ ግን አዲስ አበባ ሳር ቤት አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም በብሩህ ተስፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ በሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። በ1996 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተግባረእድ ትምህርት ቤትም በጄኔራል ሜካኒክስ በአስር ሲደመር ሶስት ዲፕሎማ አግኝቷል። ከዛ በኋላም በግራፊክ ዲዛይን፣ በቋንቋና በጥገና አጫጭር ኮርሶችን ወስዷል።
ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እየተማረ በለጋ እድሜው ከስራ ጋር የተዋወቀው ሸንኮራ እያዞረ በመሸጥ ነው። ቀጥሎ ደግሞ ወደ ሊስትሮ ስራ አመራ። ከሊስትሮ ስራ ደግሞ ወደ ፅዳትና ሱቅ በደረቴ ዞረ። ይህም አላዋጣ ሲለው ጋራዥ ቤት ተቀጥሮ ለመስራት ፊቱን አዞረ። በመቀጠልም የባት ላሜራና የቶርኖ ሞዲፍክ ስራዎች ገባ። ይህም ስላላረካው ወደ በርና መስኮት እንዲሁም ዲሽ ሞዲፊክ ስራን ተቀላቀለ።
በ1995 ዓ.ም የብረት በርና መስኮት እንዲሁም የሳተላይት ዲሽ ሞዲፊክ ስራዎችን ከአንድ ጓደኛው ጋር በመሆን መስራት ጀመረ። ይህንኑ ስራ ከጓደኛው ጋር እየሰራ እንደገና በ1997 ዓ.ም በአነስተኛና ጥቃቅን ከሁለት ወጣቶች ጋር በመደራጀት አራት በአምስት ሜትር የምትሆን የቆርቆሮ ቤት ሰሩ። በቆርቆሮ ቤቷ ውስጥም ከብረታብረት እስከ እንጨት ስራ፣ ከእንጨት እስከ ፑል ማጫወት፣ ከፑል ማጫወት እስከ ፀጉር ስራ ድረስ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ከወጣቶቹ ጋር አብሮ ሲንቀሳቀስ ቆየ።
ይሁንና ስራው ምንም አይነት ውጤት ሊያመጣ ባለመቻሉ በ2004 ዓ.ም ከአንድ ጓደኛው ጋር በመሆንና ሌላ የዲዛይን ሞያ ያለው ሰው በመቅጠር ቀደም ሲል በነበረችው የቆርቆሮ ቤት ውስጥ በአነስተኛ ካፒታል የማስታወቂያ ስራ ጀመረ። በሂደትም የማስታወቂያ ስራው ውጤት እያመጣ ሄደ። ሆኖም ግን ስራውን ከጓደኞቹ ጋር በመግባባት ወደፊት ማስቀጠል አልተቻለም። በዚህም ምክንያት በ2006 ዓ.ም ከሁለቱ ጓደኞቹ ጋር በስምምነት ተለያይቶ እነርሱ ድርሻቸውን ወስደው የራሳቸውን ሥራ ሲጀምሩ እርሱም የማስታወቂያ ሥራውን ለብቻው አስቀጠለ።
አቶ ሀብታሙ የማስታወቂያ ስራውን ለብቻው ከያዘ በኋላ ትልልቅ የማስታወቂያ ስራዎችን መስራት ጀመረ። በማስታወቂያው ዘርፍ ያሉ ትልልቅ ተሞክሮዎችን ከባህር ማዶ በማምጣት ስራ ላይ ማዋል ቀጠለ። ወደ ዱባይ በመሄድም በማስታወቂያው ዘርፍ ያለውን ልምድና ተሞክሮ ቀሰመ። ወደ ቻይና፣ ህንድ፣ ቱርክ፣ ጣልያን፣ ፈረንሳይና ጀርመን ጭምር በመሄድ በዘርፉ ያሉ ተመሳሳይ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ይዞ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። እነዚህኑ የአለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት የተለያዩ ማስታወቂያዎችን መስራት ቻለ።
በመቀጠልም አዱሊያን ማስታወቂያና ፕሮሞሽን ድርጅት በህገወጥ ስደት ዙሪያ የሚያውጠነጥኑና ትምህርት ሰጪ የማስታወቂያ ስራዎችን በመስራት የድርሻውን ተወጣ። በተለይ ደግሞ ከሴቶችና ህፃናት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በኢሚግሬሽን በር ላይ ኤቨንቶችን በማዘጋጀት በህገ ወጥ ስደት ዙሪያ በርካታ አስተማሪና ግንዛቤ የሚያስጨብጡ መልእክቶችን በተለያዩ ማስታወቂያዎች ማስተላለፍ ችሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ ከመንግስታዊ ተቋማትና ታዋቂ ሰዎች ጋር በመሆን የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ በከተማዋ ትላልቅ ኤቨንቶችን አዘጋጅቷል፤ ስልጠናዎችም እንዲሰጡ አድርጓል። የተለያዩ አስተማሪና አዝናኝ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ሰርቷል።
በአሁኑ ጊዜ አዱሊያን ማስታወቂያና ፕሮሞሽን ድርጅት በጥሩ መስመር ላይ የሚገኝ ሲሆን ሀያ ሁለት ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ፈጥሯል። እንደየስራው ሁኔታ ደግሞ እስከ አርባ ለሚሆኑ ዜጎች በጊዜያዊነት የስራ እድል ይፈጥራል። ከስድስት በላይ የሚሆኑ የባነር፣ ስቲከርና የሌሎችም ማሽኖችም ያሉት ሲሆን አጠቃላይ አመታዊ ሽያጩም 19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ደርሷል። ይህም ድርጅቱ ምን ያህል ሰዎችን አንቀሳቅሶ በርካታ ስራዎችን እንደሚያከናውን ያሳያል።
ሳር ቤት አካባቢ በተከራየው 575 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ላይት ቦክሶችን፣ ቢል ቦርዶችን፣ ባነሮችን፣ ስቲከሮችን፣ የቲሸርትና የኮፍያ ላይ ህትመቶችን፣ ዎል ብራንዲንጎችን፣ የህንፃ ዲኮሮችን፣ ሞደፊኮችንና አጠቃላይ የማስታወቂያ ሥራዎችን ያከናውናል። ከተማዋ ውስጥ ካሉ ከትላልቅና አንጋፋ ከሚባሉ ድርጅቶች ጋር ድርጅቱ መስራቱ ደግሞ ለነዚህ ስራዎች ጥሩ ማሳያ ይሆናል። ለአብነትም ድርጅቱ ከተለያዩ ባንኮች፣ ድርጅቶች፣ ከሪል እስቴቶችና ከሌሎችም ጋር ይሰራል። በልዩ ልዩ ዘርፎች ማስታወቂያ የማምረት አቅሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ከሚሰራቸው የማስታወቂያ ሥራዎች ጎን ለጎንም ድርጅቱ ወጣቶች ከሱስ ተላቀው ስራ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል። አቅመ ደካማ እናቶችን በመርዳትም ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
በቀጣይም ድርጅቱ በዚህ የማስታወቂያ ስራ ዘርፍ ላይ ለበርካታ ዜጎች በተለይ ለወጣቶች የስራ እድል የመፍጠር ሀሳብ አለው። በቀጣዮቹ አምስት አመታት ውስጥ እስከ 250 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ለመፍጠርም አቅዷል። በጊዜያዊነት ደግሞ እስከ 500 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ አስቀምጧል። የመስሪያ ቦታ በማመቻቸት ከውጪ ሀገር ማሽኖችን በማስገባትና የህትመት ማስታወቂያዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጪ ምንዛሬን የማዳን ውጥንም ይዟል። መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል የህትመት ማቴሪያሎችን በሀገር ውስጥ የማምረት ሃሳብም አለው።
ድርጅቱ የማስታወቂያው ዘርፍ እንደ አገልግሎት ሳይሆን እንደ አንድ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲታይ በኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የመስሪያ ሼድ ኖሮ የተለያዩ ማስታወቂያዎች የሚያመርትበት እድል በመንግስት በኩል ሊመቻች ይገባል የሚል አስተያየት አለው። ለማስታወቂያ ዘርፉ አስፈላጊ የሆኑ ማሽኖች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡና የተለያዩ ብድሮች እንዲመቻቹ በመንግስት በኩል ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባም ይናገራል።
ማህበራዊ ሃላፊነትን ከመወጣት አኳያም ድርጅቱ ቀደም ሲል ለአቅመ ደካማ እናቶች ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላል። ወጣቶች ከሱስ እንዲላቀቁ እና ወደ ስራ እንዲገቡ፣ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እና ወደ መልካም ህይወት እንዲመለሱ በመምከር፣ ከራሱ ተመክሮ ተነስቶ በማስተማርና በማሰልጠን የመደገፍ እቅድ ይዟል። በማስታወቂያው ዘርፍ የተለያዩ ሞያዊ ስልጠናዎች የመስጠት ሃሳብም አለው። ከመንግስት ጋር በተጠናከረ መልኩ አብሮ የመጓዝ፤ በማስታወቂያው ዘርፍ በተቋቋመው ማህበር በኩል የተለያዩ ስራዎችን ለመስራትም ሰፊ እቅዶች እንዳሉት ይናገራል።
‹‹የማስታወቂያው ዘርፍ ገና ብዙ ያልተሰራበትና ገና መስፋት የሚችል ነው›› የሚለው አቶ ሀብታሙ እያደገ ከመጣው ቴክኖሎጂ እኩል ዘርፉ ማደግ እንዳለበትና በዚህ ረገድ ደግሞ መንግስት ከቦታ ጀምሮ ብድር እስከማመቻቸት ድረስ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ያመለከታል።
ዘርፉ ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው ቢሆንም በአሁኑ ግዜ በዚሁ ዘርፍ በተቋቋመው ማህበር አማካኝነት ከመንግስት ጋር በትብብር የመስራት ሁኔታ ስለተመቻቸ በቀጣይ ይበልጥ ትኩረት ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ይጠቁማል።
ካለው የስራ አጥነት ቁጥር ከፍተኛነት አንፃር የማስታወቂያውን ዘርፍ ጨምሮ ሌሎች የስራ አጥ ጫናውን ሊቀንሱ የሚችሉ ዘርፎችን መንግስት መደገፍና ማበረታታት እንደሚገባም ይጠቅሳል።
በማስታወቂያ ስራ አስር አመታትን የቆየው አቶ ሀብታሙ እስካሁን ባለው ሂደት ውጤታማ መሆኑን ይናገራል። በተለይ ደግሞ በሀገሪቱ የህግ ማነቆዎችና ቢሮክራሲዎች እንዳሉ ሆነው እስከ ስልሳ ለሚሆኑ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠሩና በርካታ የማስታወቂያ ስራዎችን መስራቱ የውጤታማነቱ ማሳያ መሆኑንም ይጠቁማል።
እጅግ ፉክክርና እሽቅድድም በበዛበት የማስታወቂያ ስራ ዘርፍ ድርጅቱ ከሌሎች አቻ የማስታወቂያ ድርጅቶች ቀዳሚ ሆኖ ለመገኘትም በርካታ የሰው ሃይል በማሳተፍ ስራዎችን እንደሚያከናውን አቶ ሀብታሙ ይገልፃል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ስራ ሲቀበል በርካታ የሰው ሃይል በማሳተፍ ስራውን ለማስረከብ ከተሰጠው ግዜ አስቀድሞ በማስረከብ ያተረፈውን ግዜ ሌላ ስራ ለመስራት እንደሚጠቀምበት ያብራራል። በይበልጥ ደግሞ ለአብዛኛዎቹ ስራዎቹ የራሱን ማሽኖች መጠቀሙ ስራውን በአጭር ግዜ አጠናቆ ለማስረከብ እንዳስቻለውም ይገልፃል።
‹‹እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የቻልኩት ተስፋ ባለመቁረጥና የተለያዩ ስራዎችን በመሞከር ነው›› የሚለው አቶ ሀብታሙ፤ ልክ እንደእርሱ ሁሉ ሌሎች ወጣቶችም በዚህ የማስታወቂያ ዘርፍ ገብተው መስራት ከፈለጉ በቅድሚያ ተስፋ ሳይቆርጡና ስራዎችን ሳያማርጡ በትጋት መስራት እንዳለባቸው ይመክራል። ስራውን ለመስራት ምክርና ሞያዊ ድጋፍ ፈልገው ወደ እርሱ ድርጅት ቢመጡም በሩ ክፍት መሆኑንም ይጠቁማል። የማስታወቂያው ዘርፍ ገና ብዙ ያልተሰራበት ከመሆኑ አኳያም ገብተው ቢሰሩበት ውጤታም የመሆን እድል እንዳላቸውም መልእክቱን ያስተላልፋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2013