አመልካቹ ..
ሰውዬው በማለዳው ከፖሊስ ጣቢያ ተገኝተዋል። ተፈጽሟል ያሉትን የወንጀል ድርጊት በአግባቡ አስረድተው ቃላቸውን እየሰጡ ነው ። የዕለቱ ተረኛ ፖሊስ ተበዳይ የሚሉትን እያዳመጠ ሀሳባቸውን ያሰፍራል።በንብረታቸው ላይ የስርቆት ወንጀል ተፈጽሞ ጉዳት ደርሷል። እልህና ብሽቀት የሚታይባቸው ሰው ሁኔታውን በወጉ ለማስረዳት እየሞከሩ ነው።
ግለሰቡ ከአንድ ቀን በፊት ወደቤታቸው ለመግባት መኪናቸውን ከሰፈራቸው አቅራቢያ አቆሙ፤ እንዲህ ማድረግ አዲሳቸው አይደለም። ለዓመታት መኪናቸውን በስፍራው እያቆሙ ከቤታቸው አድረዋል።
አካባቢው መንገድ ዳር ስለሆነና በቂ ጥበቃ ስላለው ለአንድም ቀን አስበው አያውቁም። ዛሬ ማለዳ ግን አንድ ሰው በእጅ ስልካቸው ደውሎ መኪናቸው መንገድ ዘግታ መቆሟን ነገራቸው።
ሰውዬው ሲሮጡ ከስፍራው ደረሱ። መኪናዋ ማታ ባቆሟት ስፍራ የለችም።ደነገጡ። ደጋግመው ዙሪያገባውን ቃኙ፤ አላገኙዋትም። ፈጽሞ አለመኑም ። እየተንጠራሩ ፣ እያሻቀቡ አሻግረው ተመለከቱ። መኪናዋ የለችም።ጥቂት ራሳቸውን አረጋጉና የአካባቢውን ጥበቃዎች ጠየቁ። ‹‹ መኪናዬስ፣መኪናዬስ፣›› እያሉ ጮሁ።
ጥበቃዎቹ ሰውዬው በሚሉት ተደናገጡ።የእሳቸው መኪና ትናንት ምሽት ከስፍራዋ እንደቆመች አይተዋል። ከሌሎች መኪኖች ጋር ሲጠብቁ ማደራቸውን ያውቃሉ። መልስ ከመስጠታቸው በፊት ተዟዙረው ፈለጓት። የለችም። በአካባቢው ድንጋጤ ሰፈነ።
ጥበቃዎቹ በማህበር ተደራጅተው የሚሰሩ ናቸው።ብዙ መኪኖችን ተረክበው ሲጠብቁ ያድራሉ። አንዳንዴ የመኪና ዕቃ ሊሰርቅባቸው ይችላል። አሁን ግን መኪና ከነነፍሱ ተሰርቆባቸው በኃላፊነት እየተጠየቁ ነው። ለፍቶ አዳሪዎቹ ድንጋጤ ዋጣቸው ፤ግራ እንደገባቸው ባለመኪናውን አስተዋሉ።ሰውዬው በእጅ ስልካቸው እያወሩ ነው ።
ሰውዬው መኪናቸውን ከተለመደው ስፍራ አጥተዋታል። ከደቂቃዎች በፊት ወደተደወለላቸው ስልክ ደወሉ። የመኪናቸውን አድርሻም ጠየቁ። መኪናቸው ላንቻ አካባቢ ከአንድ የብረት ምሰሶ ጋር ተጋጭታ ስለመቆሟ ተነገራቸው።
ሰውዬው ከተባለውን ስፍራ ሲሮጡ ደረሱ።አካባቢው የጥቂት ሰዎች ግርግር ይታይበታል።ቆም ብለው አስተዋሉ፤ ብዙዎች በአንዲት መኪና ዙሪያ ቆመው ያወጋሉ።አብዛኞቹ ሾፌሩ ምሽቱን ሲጠጣ አድሮ መንገድ እንደሳተ ይገምታሉ። አንዳንዶች የመኪናውን ፍሬን መበጠስ እየገመቱ የሾፌሩን ችሎታ ያደንቃሉ። ሌሎች የመኪና አደጋን አስከፊነት እያወሩ ያልፋሉ።
ሰውዬው ወደመኪናዋ ጠጋ ብለው የሆነውን አስተዋሉ።በትክክል የራሳቸው ንብረት ናት ። ከፊት ለፊቷ ያለው የፊት መስታወት ረግፏል።ዞር ብለው የኋላ አካሏን ዳሰሱ ።ከጀርባው ያለው መስታወት እንዳልሆነ ሆኗል።የመኪናው ባለቤት በንብረታቸው መገኘት እፎይ አሉ።መኪናቸው ዳግም ጥቅም የመስጠት ቁመና የላትም።
ሰውዬው ንብረታቸውን በመዝረፍ ጉዳት ያደረሱትን ግለሰቦች በህግ ለመፋረድ ህግ መጠቀም እንዳለባቸው አውቀዋል።ጥቂት ተረጋግተው በአካባቢው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ አመሩ።በመኪናቸው ላይ የሆነውንና በአይናቸው ያረጋገጡትን እውነት ተናግረው ክስ መሰረቱ።
ፖሊሱ ከእሳቸው ያገኘውን በቂ የሚባል ማስረጃ ካሰፈረ በኋላ አድራሻቸውን መዝግቦ በክብር ሸኛቸው።ሰውዬው ቢሮውን ለቀው ሲወጡ በፖሊሱ አቀባበልና ባገኙት ተስፋ በፊታቸው ፈገግታ ታየ ። በድጋሚ ከልብ አመስግነው በሰላምታ ተሰናበቱት።
ከአንድ ቀን በፊት …
የቦሌ ጎዳና ድምቀት ምሽቱን ብሶበታል።ከግዙፍ ህንጻዎች የሚወጣው ደማቅ ብርሀን የአካባቢው ውበት ነው።መንገዱ እንደሌሎች ሰፈሮች አይደለም። በጊዜ ጭር አይልም።ከላይ ታች የሚከንፉ መኪኖችና በእግራቸው የሚጓዙ መንገደኞች ምሽቱን ቀን እንዳስመሰሉት ነው። አንዳንዴ ቀንና ማታን መለየት ይቸግራል።
የነሐሴ ወር እየተጋመሰ ነው። በዝናብ የዋለው ቀን ምሽቱን እንዳኮረፈ ዘልቋል። በብርሀን ታጅቦ የሚያስገመግመው ነጎድጓድ ልብ ያሸብራል። ደጋጋሚው ብልጭታ በዝናብ እየተመላለሰ ምሽቱን አክብዶታል።
በዚህ ሰዓት ብዙዎች ከቤታቸው አልያም ከአልጋቸው አርፈዋል።የቦሌ መንገድ ታዳሚዎች ይህ ያሳሰባቸው አይመስልም። ቦሌ እንደደመቀች አምሽታለች እንደሌሎች ሰፈሮች የመብራት መጥፋትና የጨለማ ስጋት የለባትም።
አሁን ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ተኩል ሆኗል ። ምሽቱ እንደጅማሬው አልዘለቀም። የዝናቡ ማየል ብዙዎችን በጊዜ በር አዘግቷል ።አንዳንዶች ካመሹበት መዝናኛ ወደቤት እየገቡ ነው።ሌሎች ከቆዩበት መመለስ ይዘዋል።
አንዲት መኪና ከመስቀል አደባባይ ወደ ደምበል የሚወስደውን አቅጣጫ ይዛ እየመጣች ነው ።የቀኝ መታጠፊያው ላይ ስትደርስ ፍጥነቷን ቀንሳ ወደ ግራ ዞረች ።ጥቂት አለፍ እንዳለች ጥቂት መኪኖች ከሚታዩበት ባዶ ስፍራ ቆማ ሞተሯን አጠፋች።
ሾፌሩ ከውስጥ ወጥተው የበሮቹን መዘጋት አረጋገጡ ።ወዲያውም የቤታቸውን አቅጣጫ ይዘው መራመድ ጀመሩ። ቦታው የመኪናዋ የሁልጊዜ መቆሚያ ነው ። አዳሯን በዘቦች ስትጠበቅ፣ስትቃኝ ታድራለች።
በረከት አየለ ትውልድና ዕድገቱ ደብረሊባኖስ ገዳም አካባቢ ነው። በትምህርቱ እምብዛም አልገፋም። የወላጅ አባቱ ድንገቴ ሞት የቤተሰቡን ጫና እንዲረከብ ግድ ቢለው አማራጮችን ፈለገ።
ትምህርቱን አቋርጦ ሥራ ለማግኘት ሮጠ። የእሱን እገዛ የሚሹ ቤተሰቦች ውሎ ሲገባ እጁን ያያሉ። በረከት በቀላሉ ሥራ አላገኘም። ቆይቶ ግን ከአካባቢው የማያርቅ እንጀራ መጣለት ። በደብረሊባኖስ ገዳም መኪና ላይ በረዳትነት ተቀጠረ።
በረከት አሁን ውሎ ሲገባ አይሳቀቅም። ከእጁ የሚገኝ የዕለት ገንዘብ የእናቱንና የእህት ወንድሞቹን ጥያቄ ይመልሳል። ለወራት የራሱንና የቤተሰቦቹን አቅም ሲደጉም ቆየ።ሥራው ከበርካቶች አስተዋውቆ አማራጮችን አመላከተው።
በሥራው ጥቂት እንደዘለቀ ጤናው ተቃወሰ።ጠዋት ለሥራ ሲወጣ ቀስፎ የሚይዘው ህመም ሰላም ነሳው። ቤተሰቦቹ ጠበል ወስደው አቆዩት። ከጊዚያት በኋላ ራሱን አበርትቶ ወደሥራው ተመለሰ።እንደቀድሞው ከመኪናው እየዋለ ገንዘብ ማግኘት ጀመረ።
በረከት ጥቂት ቆይቶ ሥራውን መቀየር ፈለገ። ከትውልድ አገሩ ርቆ መሄድ ሲወስን ከቀድሞው የተሻለ ክፍያ እንደሚያገኝ ተነገረው።አላንገራገረም። በፊት በቀን ከሚከፈለው አንድ መቶ ሀምሳ ብር ላይ አሁን የሀምሳ ብር ጭማሪ አግኝቷል።
ከሁሉም በላይ ሥራው አዲስ አበባ መሆኑ አስደስቶታል። በየቀኑ ከከተማ ከተማ መሻገር ልዩ ስሜት እንዳለው ገምቷል። የትውልድ አገሩን ትቶ ለመውጣት ፈጠነ። ከቀናት በኋላ በመኪናው ተገኝቶ ሥራውን ጀመረ። በረከት ከገቢው በላይ በውሎው አጋጣሚዎች መደሰት ያዘ።ሥራውን ወደደው።ከአካባቢው ቢርቅም ቤተሰቦቹን አልረሳም። ገቢው ሲጨምር የሚያስፈልጋቸውን እየላከ ደጎማቸው ።
በረከት በሚሰራበት መኪና ላይ ሁለት ዓመታት አሳለፈ ።ገቢውና የሥራ ውሎው አላስከፋውም። ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ያለው ቀረቤታ መልካም የሚባል ነው። አንድ ቀን ግን እንጀራ የሚያገኝበት ውሎ በድንገት ሊቋረጥ ግድ አለ። መኪናው ደብረጽጌ ከተባለ ስፍራ ከአንድ ከባድ መኪና ጋር ተጋጭቶ ጉዳት አገኘው።
መኪናው ባጋጠመው ጉዳት ሲቆም ።በረከት ሌላ እንጀራ ፈላለገ። በቆየበት ልምዱ የሚመጥን ሥራ አላጣም። በተመሳሳይ ሙያና ልምድ በሌላ መኪና ላይ የረዳትነት መንበሩን ይዞ ከቦታ ቦታ መዘዋወሩን ቀጠለ።
የአዲስ አበባው ባልንጀራ…
ሚኪ አበበ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ደንበል ከሚባለው አካባቢ ነው። ሚኪን ወላጆቹ ትምህርት ቤት ያስገቡት በዕድሜው ነበር።እንደ እኩያ ጓደኞቹ ደብተር ይዞ ቀለም ቆጥሯል። ለትምህርቱ እምብዛም ፍላጎት የሌለው ታዳጊ እንደምንም እስከ ሰባተኛ ክፍል ተምሯል።
ስምንተኛ ክፍል መግባት ሲገባው ገንዘብ ማግኘት የፈለገው ሚኪ ቀለም የመቀባትና ጂብሰም የመስራት ልምድ አዳብሮ በየቤቱ ተዘዋውሮ መስራት ለመደ። ይህ አጋጣሚ ግን አብሮት የኖረውን የእጅ ዓመል ያወጣበት ያዘ። ማንነቱን የጠረጠሩ አንዳንዶች ከሚፈጽመው ድርጊት ተነስተው የስርቆት ልማድ እንዳለው ያሙት ነበር።
ሚኪ የገንዘብን ጥቅም በወጉ ሲያውቅ ከአንድ ኮንስትራክሽን በቅጠር ገብቶ ደመወዝ ማግኘት ጀመረ። በሥራ ሲባዝን መዋሉ ብቻ ባህሪውን አልደበቀውም። በየቀኑ በስርቆት መጠርጠር ልምዱ ሆነ።ማንነቱን የለዩ ብዘዎች ይፈሩት ፣ይርቁት ጀመር።
አንድቀን ሚኪ በሚጠረጠርበት የስርቆት ወንጀል ለክስ ቀረበ ። ድርጊቱ ቢረጋገጥበትም በወቅቱ የነበረው ዕድሜ ለፍርድ የሚያበቃው አልነበረም።ያም ሆኖ በወጣት ጥፋተኞች ተሀድሶ ገብቶ ከመቆየት አላመለጠም። በስፍራው መገኘቱ ክፉ ባህረይውን ለማረቅና ለስነምግባር ለመገዛት ነበር።
ሚኪ ከወጣት ማዕከሉ ከወጣ በኋላ ህይወትን እንደአዲስ ጀመረ።ለጥቂት ጊዚያትም በቀድሞ ሥራው ተሰማርቶ ቆየ ።ጠበኝነት፣ተደባዳቢነቱ ግን ከሰው ያጋጨው ያዘ። በውሎው ሰላም አጣ ፤ከብዙዎች ለመግባባት ተቸገረ። በየአጋጣሚው አላርፍ የሚለው እጁ ‹‹ሌባ ›› የሚል ስያሜ አሰጥቶ በጎሪጥ ያሳየው ጀመር።
ከቀናት በአንዱ ቀን ሚኪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ። ፖሊሶች ሁኔታውን አጣርተው ለክስ አቀረቡት ። ጉዳዩ በምስክርና በማስረጃ ተደግፎ ድርጊቱ ከጥርጣሬ በላይ ሆነ። ሚኪ የተመሰረተበት የውንብድና ወንጀል ተጠያቂ አደረገው።ግራቀኙን ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤትም የጉዳዩን አደገኝነት አስተውሎ ሁለት ዓመት ከሁለት ወር በእስር እንዲቆይ ወሰነበት።
ሚኪ የእስር ጊዜውን ለመጀመር ከማረሚያ ቤት ወረደ። ቀናት፣ሳምንታት፣ወራት ነጉዱ። የእስር ጊዜው ተጠናቀቀ።ከሁለት ዓመታት በላይ ወህኒ የቆየው ወጣት ዳግም ከሌሎች ሊቀላቀል ከእስር ተፈታ።ከማረሚያ በኋላ ራሱን ለመቀየር ሞከረ።ውሎና ድርጊቱን ከቆየበት ክፉ ልማድ አላቆ ባህሪይውን ሊለውጥ ጣረ።
የሚኪ አዲስ ስሜት የሥራ ፍላጎቱን አነቃ፤ከሌሎች ወጣቶች ጋር ተሰማርቶ በመኪና ፓርኪንግ ሥራ እንጀራ ሊያገኝ ታሪኩን ሊቀይር ወሰነ።ያሰበውን አላጣም፣ የሥራው አካልና አጋር ሆኖ በጥረቱ ቀጠለ።እንደሌሎች ጊዜና ጉልበቱን እየከፈለ ከጥቅሙ ሊካፈል ትጋቱን አሳየ።
በጥር ወር 2009 ዓ.ም ግን ሌላ አጋጣሚ ተፈጠረ።ሚኪ በሰው መግደል ወንጀል ሙከራ ተጠርጥሮ ፖሊስ ጣቢያ ተገኘ። ጉዳዩ በምስክሮችና በማስረጃዎች ተጣራ።ለቀናት በእስር የቆየው ተከሳሽ የዋስ መብቱ ተጠብቆ ከእስር ተፈታ።ሚኪን ያዩት ሁሉ ይፈሩት፣ ይጠረጥሩት ያዙ ።በዓይኖቹ መቅበዝበዝ ፣በእጆቹ አላርፍ ባይነት ታወቀ ።ያወቁት ተጠነቀቁት።ያላወቁት የድርጊቱ ሰለባ ሆኑ ።
ነሐሴ 20 2009 ዓ.ም
በዚህ ቀን ሚኪና የደብረሊባኖሱ በረከት ተገናኝተዋል። ዕለቱን በዝናብ የዋለው ቀን ምሽቱን እንደከበደው አይተዋል።ያመሹበት አካባቢ የዘወትር መዋያቸው ነው ።የደንበል ጀርባንና ዙሪያውን አሳምረው ያውቁታል።ይህ ስፍራ ለአንዳንዶች መቃሚያ፣መጠጫና ነጥቆ መሮጫ ነው።
ሰዓቱ እየገፋ እኩለ ሌሊቱ መጋመስ ሲጀምር ሚኪና በረከት በስፍራው ነበሩ።በዚህ አካባቢ ጥቂት የማይባሉት መኪኖቻቸውን በክፍያ ያስጠብቃሉ።ንብረቶቻቸውን በአደራ የሚረከቡት ጠባቂዎች ዓይናቸውን ሳይነቅሉ ኮሽታና ኮቴ ሲያዳምጡ ያነጋሉ።
እነሚኪ ሌሊት 7 ሰዓት ከ 30 አንድ መኪና ፍጥነቱን ቀንሶ ለመቆም ቦታ እየፈለገ መሆኑን አስተዋሉ። የመኪናውን መቆሚያ ያየው ሚኪ ውስጡ ነቃ።አርቆ እያሰበ ብዙ ዕቅዶችን ደረደረ ። ባለመኪናው መብራት አጥፍተው በር ዘግተው እስኪርቁ አያቸው ።ዙሪያ ገባውን ቃኘ።ጠባቂዎቹ በቦታቸው ቆመዋል።
ሌሊት 9 ሰዓት ከ30 ሲሆን ሁለቱ ወጣቶች ተሽሎክሉከው መኪኖቹ መሀል ተገኙ።ያያቸው ም ሆነ ኮቴያቸውን የሰማቸው የለም።ሚኪ ከያዛቸው በርካታ ቁልፎች አንዱን መዞ ወደ መኪናው በር አስገባ ።ተመሳሳዩ ቁልፍ ያላንዳች ችግር ከፈተለት።ከፊት ተቀምጦ ሞተሩን አስነሳ።አላስቸገረውም።በረከትን ከጋቢና አስቀምጦ ወደፊት ገሰገሰ።
ጥቂት እንደተጓዙ የፊት መብራት አልሰራ አለው። በግምት እየነዳ ወደላንቻ አመራ። ጋቢና ያለው በረከት አነዳዱ አስፈርቶታል።ፍጥነቱን ያልገታው ሚኪ መኪናውን እያንገዳገደ ይጓዛል ።ድንገት ከፊት ለፊታቸው አንዳች ነገር መቆሙን አስተዋሉ።መኪናው ሊያልፈው አልቻለም። በመጣበት ፍጥነት ከብረቱ ተጋጭቶ ቆመ።
ከደቂቃዎች በኋላ መኪናው ደም በደም መሆኑን አዩ። ጋቢና የነበረው በረከት ጭንቅላቱ ክፉኛ ተጎድቷል። አፍታ ቆይተው ራሳቸውን ከመኪናው አወጡ። በዋዛ መቆም ያልቻለው የበረከት ደም አስጨነቃቸው። በእግራቸው ተራምደው ከአንድ ጤና ጣቢያ ደረሱ። በቂ ህክምና አላጡም።
የፖሊስ ምርመራ…
ፖሊስ ከአመልካቹና ከአካባቢው ያገኘውን መረጃ ይዞ ምርመራውን ቀጠለ።ተፈላጊዎቹን አላጣቸውም ።በቁጥጥር ስር አውሎ ቃላቸውን ተቀበለ። ሁለቱም ያደረጉትን አልካዱም።መርማሪው ዋና ሳጂን ወንደሰን አበራ የተጠርጣሪዎቹን ዕምነት ክህደት በወንጀል መለያ ቁጥር 181/09/10 ላይ በአግባቡ መዝግቦ አጠናቀቀ።
ውሳኔ…
ግንቦት 9 ቀን 2012 ዓም በችሎቱ የተሰየመው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተከሳሾቹ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮው ተገኝቷል። ሁለቱ ግለሰቦች በተመሰረተባቸው ክስ ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጧል። በዕለቱ ባሳለፈው ውሳኔም ሰዎቹ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ የአምስት ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጡ ሲል በይኗል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2013