
‹‹ኢትዮጵያን እናልብስ›› በሚል መሪ ቃል እየተከናወነ ባለው ሦስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር አሻራውን ለማሳረፍ ከልጅ እስከ አዋቂ ተነሳስቷል። ተቋማት ሠራተኞቻቸውን በማሳተፍ ብቻ ሁሉም በየአካባቢው የሚታየው እንቅስቃሴ ያስደስታል፡፡ አሻራን የማኖር አካል ለመሆን ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን የተገነዘብኩት የተዘጋጀላቸው መኪና አምልጧቸው በኮንትራት ታክሲ(ራይድ) በሥፍራው ተገኝቶ አሻራን እስከማኖር የደረሰ ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን አርአያነታቸውን ያሳዩት የአካባቢ፣የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ሠራተኞች ነበሩ፡፡ሠራተኞቹ አሻራቸውን ያኖሩት በመናገሻ ሱባ ጥብቅ ደን ውስጥ ነበር፡፡በሥፍራው እንደደረስንም ችግኞች ይዛ ከሠራተኞቹ መካከል የተገኘችው ታዳጊም እይታዬን ከሳበው መካከል አንዱ ነበር፡፡
ታዳጊዋ ኪያ ቦኪ በመናገሻ ሱባ አካባቢ ነዋሪ ናት፡፡ኪያ አረንጓዴ የለበሰች ሀገር እንድትኖራት የእርሷም ድርሻ መኖር እንዳለበት በማመን ከአካባቢው ነዋሪ ጋር በሥፍራው እንደተገኘች ከልጅነት አንደበቷ ተረድቻለሁ፡፡የዕድሜ እኩዮችዋ እንደርሷ በአካባቢያቸው ችግኝ እንዲተክሉ መልዕክት አስተላልፋለች፡፡
የኮሚሽኑ ሠራተኞች የችግኝ ተከላ መርሐግብር ያከናወኑበት ሥፍራ በአዲስ አበባ ከተማ ኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ሆለታ ወልመራ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው ሰበታ መናገሻ ሱባ ጥብቅ ደን ውስጥ ነው። የሱባ ጥብቅ ደን በክልሉ በደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ሥር የሚተዳደር ሲሆን፣በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ነው። የቱሪስት መዳረሻም ሆኖ የበለጠ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል ዕድሜ ጠገብ ደን እንደሆነም ከተለያዩ መረጃዎች ለመረዳት ችያለሁ፡፡ የችግኝ ተከላ መርሐግብሩ ተሳታፊዎች የተከሉትን ችግኝ እየተከታተሉ በደንብ ያልተተከለውን በማረም፣ ችግኙ የተዘጋጀበት ፕላስቲክም አብሮ እንዳይቀበር እርሳቸውም እየተከሉ ሲሳተፉ ያገኘኋቸው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ደጉ አባተ ከሌሎቹ በተለየ ለመንቀሳቀስ የተነሳሱት እርሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪ ከደኑ ከፍተኛ ተጠቃሚ በመሆናቸው ነው፡፡ በአካባቢው በኢንተርፕራይዝ የተደራጁት የደረሰውን ዛፍ ቆርጠው ለገበያ በማቅረብ ይጠቀማሉ፡፡ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን በመረዳታቸውም በየጊዜው ችግኝ በመትከል የተቆረጠውን ይተካሉ፡፡ከሚያገኙት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በተጨማሪ የአካባቢያቸውን ሥነምህዳር በመጠበቅም ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ‹‹ደንን ህይወቴ፣እስትንፋሴ፣ፈውሴ›› ሲሉም የሰጡትን ልዩ ትኩረት ይገልጻሉ፡፡
መናገሻ ሱባ ቀደምት የነበሩት መሪዎችና ነዋሪዎች ያቆዩት ቅርስ ብቻ ሳይሆን ለዜጎች ጥቅምም እየሰጠ ያለ መሆኑን በማስታወስ በዚህ ወቅት ያለው ትውልድም ትኩረት ሰጥቶ በአካባቢው አሻራውን ለማኖር መነሳሳቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡የተተከሉት ችግኞች ጸድቀው የበለጠ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖራቸውና የአካባቢውም ሥነምህዳር እንዲጠበቅ የተከሏቸውን ችግኞች እንዲንከባከቡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ተደጋግሞ እንደተነገረው በየአካባቢው የሚተከሉ ችግኞች መልሰው ለማህበረሰቡ ጥቅም ላይ መዋል ይኖርባቸዋል፡፡ተገቢውን እንክብካቤ አግኝተው የሚፈለገው ደረጃ ላይ የሚደርሱትም ማህበረሰቡ ሲጠቀምባቸው ነው።ከዚህ አንጻር መናገሻ ሱባ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
በአካባቢ፣ደንና አየርንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ባለሙያ አቶ ዮናስ ክፍሌ እንደገለጹት ፤በአካባቢው እየለማ ያለው ደን ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል ሲሆን፣ከዘርፉ የአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን በሀገር ደረጃም ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ከፍ ይላል፡፡በመሆኑም የኮሚሽኑ ሠራተኞች ይህንኑ አስተዋጽኦ ከፍ ለማድረግ ነው አስፈቅደው የችግኝ መርሐግብሩን ያከናወኑት፡፡ በኮሚሽኑ ሠራተኞች የተተከሉት ሰባት ሺህ የፈረንጅ የሚባለው ጥድ ችግኞች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ተገቢው እንክብካቤ ተደርጎላቸው ለተጠቃሚዎቹ እንዲውሉ ይደረጋል፡፡የተተከለው ችግኝ ዝርያ ለአካባቢው ተስማሚና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም የጎላ ነው፡፡ ችግኙም እስከ 20 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለቆረጣ እንደሚደርስ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡
የደን ማልማት ሥራ ሳይንሳዊ መሆኑን የጠቀሱት የአካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነም ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን አጉልተው ተናግረዋል፡፡እንደርሳቸው ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የደን ውጤት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ሀገር የገባ ነው፡፡ይሄ መቀጠል የለበትም፡፡ኢትዮጵያ ደን ማልማት እየቻለች ጣውላ ሳይቀር የደን ውጤት ከውጭ ማስገባት ተገቢ አይደለም፡፡ከውጭ የሚገባውን ማስቀረት የሚቻለው ደግሞ በተደራጀ አግባብ ሙያን መሠረት ያደረገ የችግኝ ተከላ መርሐግብር በማከናወን ነው፡፡ ከውጭ ወደ ሀገር የሚገባውን ለማስቀረት ብቻ ሳይሆን ወደ ውጭ በመላክም የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሰራት ይኖርበታል፡፡ ደን ለማር፣ለቅመማ ቅመምና ለሌሎችም ልማቶች፣ለብዝሐ ሕይወት፣ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ፣ግድቦችን ከደለል ለመከላከል፣እንዲሁም አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ፋይዳ ላለው ለአየርና ንብረት መጠበቅ የሚጠቅም ትልቅ ሀብት ነው፡፡ሙያን መሠረት በማድረግ ሳይንሳዊ የደን ተከላን መከተል ከተቻለ ደን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡
በመሆኑም የችግኝ ተከላ መርሐግብሩ በዘፈቀደ ተተክሎ የፀደቀው ይጽደቅ የቀረው ይቅር በሚል መከናወን የለበትም፡፡በተሻለ ጥራት እንዲከናወን በዕውቀት መከናወን አለበት፡፡ኢትዮጵያ የተለያየ ሥነምህዳር ያላት ሀገር በመሆኗ ለየአካባቢው ተስማሚ የሆነ የችግኝ ዘር ከማዘጋጀት ጀምሮ በተከላ ወቅትም ክትትል በማድረግ ሙያን መሠረት ያደረገ ሥራ መሰራት ይኖርበታል፡፡በሙያ የታገዘ ሥራ መሥራቱ እስከ ታች ቀበሌ ድረስ ወርዶ መከናወን አለበት፡፡ህዝቡ ችግኝ በመትከል አሻራውን ለማሳረፍ የሚያደርገው ተነሳሽነት እንዳይቀዛቀዝ በማበረታታትና በመደገፍ የባለሙያዎች ሚና ከፍ ያለ መሆን ይገባል። በተለይም ተመራማሪዎች የተሻለ የጽድቀት መጠን ያላቸውን፣ በኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውም ጥሩ የተባሉ ዝርያዎችን በምርምር በማፍለቅ፣ ከተተከሉ በኋላም ክትትል በማድረግ፣ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን በማፍለቅና የሌሎችንም ሀገሮች ተሞክሮ በመቀመር ለሀገር በሚጠቅም መልኩ በመሥራት ብዙ ተግባራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩልም እንደሚጠቅም ወጣቶች ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ችግኝ ከማፍላት ሥራ ጀምሮ ተንከባክቦ ለውጤት በማብቃትና ችግኙ ዛፍ ሆኖ ከደረሰ በኋላም ለገበያ ቀርቦ ጥቅም እንደሚሰጥ በመረዳት ተሳታፊነታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከዳር እስከዳር ከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄን ፈጥሮ በመከናወን ሦስተኛ ዙር ላይ የደረሰ ቢሆንም አንዳንድ ክፍተቶች ይነሳሉ፡፡ ከነዚህ መካከልም ለደን ልማትና ለእርሻ ሥራ የሚውል መሬትን ለይቶ አለመጠቀም በተደጋጋሚ ከሚነሱት መካከል ይጠቀሳል፡፡
ኮሚሽነሩ ለዚህ በሰጡት ምላሽ፤ ወሳኝ የሆነ ሀሳብ እንደሆነ ይስማማሉ፡፡የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲና ዕቅድ ወሳኝ ነው፡፡በየትኛውም ሀገር የሚሰራበት ነው፡፡በመሆኑም በኢትዮጵያም ፖሊሲና ዕቅድ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራበት ቆይቶ ረቂቅ ፖሊሲው ተጠናቅቆ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ቀርቧል፡፡ መሬትን ለተሻለ ዓላማ ማዋል የሚቻለው በዕቅድ ሲመራ በመሆኑ በዚህ ረገድም ክልል፣ ዞንና ወረዳን ብሎም በሀገር ደረጃ የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ለደን መዋል የሚገባው ለእርሻ፣ ለእርሻ መዋል የሚገባው ለግንባታ ከዋለ እንደሀገር ከመሬቱ መገኘት ያለበትን ጥቅም ማግኘት አይቻልም፡፡
የደን ልማቱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኝ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተናበበ ሥራ መሥራትም ሌላው ትኩረት ማግኘት ያለበት ጉዳይ በመሆኑ በዚህ ላይም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ በዘርፉ ላይ ባለሀብቶችን ማትጋትና ማልማት የሚል በደን አዋጅ ላይ ተቀምጧል፡፡ በአጠቃላይ ሊያሳልጡ የሚችሉ የአሰራር ሥርዓቶች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በችግኝ ተከላ ወቅት ችግኞቹ የሚዘጋጁባቸውን ፕላስቲኮች አብሮ መትከልና በአካባቢው ላይ ጥሎ መሄድ ይስተዋሉ ከነበሩ ክፍተቶች መካከል ነበሩ፡፡የኮሚሽኑ ሠራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች ችግኙ የተዘጋጀበት ፕላስቲክ በአካባቢው እንዳይቀር መሰብሰቢያ በማዘጋጀት በጥሩ አርአያነት ነበር ሲያከናውኑ የታዘብኩት፡፡ባለሙያዎች ደጋግመው እንደተናገሩትና መረጃዎችም እንደሚያመለክቱት ፕላስቲክ በመሬት ውስጥ ከመቶ ዓመት በላይ በመቆየትና የአፈርንም ለምነት በመሳጣት ትልቅ ጉዳት ያስከትላል፡፡
ኮሚሽኑን ተሞክሮ በሌሎችም እንዲለመድ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ ችግኝ በመትከል ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማልበስ ሁሉም ዜጋ ሲነሳሳ በችግኙ ጽድቀት ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥረውንና አካባቢን የሚበክል ነገርንም በመከላከልና በማስወገድ መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡አረንጓዴነት የሚገለጸው በችግኝ ተከላ ብቻ መሆን እንደሌለበትም ተናግረዋል፡፡
ችግኝ መትከልና የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ አብረው ተቆራኝተው የሚሄዱ ተግባራት እንደሆኑ የጠቆሙት ምክትል ኮሚሽነሯ፤ በተለይ በችግኝ ተከላ ወቅት ለችግኝ ማፍላት የዋሉ የፕላስቲክ መያዣዎችን(ችግኙ የተጠቀለለበት ላስቲክ) ከተከላው በኋላ ሰብስቦ የማስወገዱ ተግባር የችግኝ ተከላ መርሐግብሩ አካል አድርጎ መውሰድ ይገባል፡፡ኢትዮጵያን እናልብስ በሚለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር በሀገርአቀፍ ወደ ስድስት ቢሊየን ችግኞች ስለሚተከሉ ተገቢው ጥንቃቄ ተደርጎ ላስቲኮቹን በማስወገድ የተከላ መርሐግብሩ ካልተከናወነ የእያንዳንዱ ሰው ድካም ከንቱ ይቀራል፡፡ እንደሀገር የታሰበው ሀገርን አረንጓዴ የማልበስ መርሐ ግብርን ለማሳካትም ያስቸግራል። ግንዛቤው በዚህ መልክ መሆን ይኖርበታል፡፡
ኮሚሽኑ ችግኝ እንዲተከል ንቅናቄ እንዲፈጠር ብቻ ሳይሆን ጎን ለጎን በተከላ ወቅት መደረግ ሥላለባቸው ጥንቃቄዎች ግንዛቤ በመፍጠር፣ እራሱም አርአያ ሆኖ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነና የችግኝ መያዣ ፕላስቲኮችን በአግባቡ እያስወገዱ የኮሚሽኑ ሠራተኞች ተሳትፎ ማድረጋቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሯ አስረድተዋል፡፡ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ እንዲወገድም አርአያነቱን በማስፋት ግንዛቤውን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የህዝብ ንቅናቄው በዚህ ቀጥሎ መርሐ ግብሩ ስኬታማ ከሆነ እኤኣ በ2030 ዘላቂ የልማት ግብ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ወደ 30 በመቶ ከፍ ይላል፡፡ በአራት ዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብርም 20 ቢሊየን ችግኞች በመትከል የልማት ግብ ዕቅዱን ለመሳካት ነው ርብርቡ፡፡ እንዲህ በሀገር ደረጃ እየተከናወነ ያለው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከጎረቤት ሀገሮች ጋርም ተያይዞ ለማደግ ታሳቢ ያደረ እንደሆነም አይዘነጋም፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2013