ክፍል ሶስት
ባለፈው ሳምንት በቤተሰብ አምድ እትማችን በኢትዮጵያ ያለው የጋብቻና ፍቺ ህጋዊ አካሄድና ውጤቶቹ እንዴት ይታያሉ ስንል በኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር የሆኑትን የህግ ባለሙያውን አቶ እንዳልካቸው ወርቁን አነጋግረን ሁለተኛውን ክፍል ማቅረባችን ይታወሳል። ለዛሬም ከባለሙያው ጋር የነበረንን ሶስተኛ ክፍል እነሆ።
ባልና ሚስት በትዳር ዘመናቸው ወቅት የሚገኘውን ገቢ እያንዳንዳቸው በየራሳቸው ይቀበላሉ። ገቢ ማለት በዚህ አነጋገር ደመወዝ፣ ከግል ንብረት የሚመነጭ እንዲሁም ከጋራ ንብረት የሚመነጭ ማለት ነው። በግል የመነጨውን ገቢ የሚቀበለው የገቢው ምንጭ የሆነው ተጋቢ ነው። ነገር ግን ሌላኛው ተጋቢ ሲጠይቅ ገቢውን የተቀበለው ተጋቢ ያገኘውን የገቢ መጠን ማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት በቤተሰብ ሕጉ አንቀፅ 64(3) ላይ ተገልጿል። የገቢው ምንጭ አንደኛው ተጋቢ ቢሆንም የጋራ ሀብት ስለሆነ ሌላኛው ተጋቢ የማወቅ መብት ይኖረዋል ማለት ነው። ተጋቢዎቹ ከፈለጉ በየግላቸው የሚገኙትን ገቢ የጋራ የባንክ ሂሳብ በመክፈት ማስቀመጥ ይችላሉ።
እዚህ ጋር መታወቅ ያለበት በመርህ ደረጃ የገ ቢው አመንጪ ገቢውን ቢቀበልም በልዩ ሁኔታ (excepti onally) ግን ሌላኛው ተጋቢ ገቢውን ሊቀበል ይችላል። ይህ የሚሆነው በሁለት መልኩ ነው። አንደኛው የገቢው አመንጪ የሆነው ተጋቢ ለሌላኛው ተጋቢ በውል ገቢውን እንዲቀበል ሲፈቅድለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በፍ/ቤት ትዕዛዝ ነው። ይህ በፍ/ቤት የሚሰጠው ትዕዛዝ ከባልና ከሚስት አንደኛው ስጠይቅ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ገቢው በሙሉ ወይም በከፊል እንዲከበር በፍ/ቤት ሊታዘዝ ይችላል። እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባው ነገር በሌላ ህጎች መከበር የሌለባቸው ገቢዎችና ንብረቶች የማይከበሩ መሆኑን ነው። ለምሳሌ የጡረታ አበል ሊከበር እንደማይችል የጡረታና በሌሎች ህጎች የተመለከተ ነው።እንዲሁም በፍታብሄር ስነስርዓት ሕጉም ውስጥ ሊከበሩ የማይችሉ የንብረት ዓይነቶችና የደመወዝ መጠን በአንቀፅ 404 ላይ ተገልጾ ይገኛል።
በኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀፅ 34(1) ላይ ተጋቢዎች በትዳር ዘመናቸው በሁሉ ነገር ላይ እኩል መብት እንዳላቸው ይገልፃል። እንዲሁም በአንቀፅ 35(7) ላይ ሴቶች ንብረት በማስተዳደር ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው በማለት ደንግጓል። እነኚህ የህገ መንግስቱ መርሆች በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 66(1)ላይ በማካተት ባልና ሚስቱ የጋራ ሀብታቸውን በጋራ ያስተዳድራሉ በማለት ገልጾታል። ስለዚህም በመርህ ደረጃ ባልና ሚስት የጋራ ንብረታቸውን በጋራ ያስተዳድራሉ።
ነገር ግን ባልና ሚስቱ በስምምነት የጋራ ንብረታቸውን አንዳቸው እንዲያስተዳድሩ ማድረግ ይችላሉ። ይህም በውል ለአንደኛው ወገን እንዲያስተዳድር ሲሰጥ ነው። በተለያየ አጋጣሚ (ምክንያት) ከተጋቢዎች አንዱ ችሎታ ሲያጣ ወይም ንብረት የማስተዳደር መብቱ በፍ/ቤት ሊገፈፍ ይችላል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሌላኛው ተጋቢ ንብረቱን የማስተዳደር ተግባር ያከናውናል። በውልም ሆነ ንብረት የማስተዳደር መብቱ በመገፈፉ ወይም ችሎታ በማጣቱ አንደኛው ተጋቢ ንብረቱን በሚያስተዳድርበት ጊዜ ሌላኛው ንብረቱን የሚያስተዳድረው ተጋቢ የንብረቱን አስተዳደር በተመለከተ ለሌላኛው ተጋቢ መረጃ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 67 ላይ ተቀምጧል።
ተጋቢዎች በትዳር ተሳስረው የጋራ ንብረት አፍርተው ሲኖሩ ይህን የጋራ ንብረት በጋራ ማስተዳደር እንዳለባቸው ከላይ በተገለጸው መልኩ ለመረዳት ችለናል። እነዚህን የጋራ ንብረቶች ተጋቢዎቹ በጋራ በሚያስተዳድሩበት ወቅት ንብረቱን መሸጥ መለወጥ ያስፈልጋቸው ይሆናል። ይህ የጋራ ንብረት መሸጥ መለወጥ ከፈለጉ በሌላ የሕግ የተለየ ሁኔታ ካልተደነገገ በስተቀር የተጋቢዎቹ የጋራ ስምምነት አስፈላጊ ነው። በአንቀጽ 68 የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የጋራ ንብረትና ሀብት ወደሌላ ሶስተኛ ወገን በሽያጭ ሆነ በስጦታ የሚቀየረው በተጋቢዎቹ የጋራ ስምምነት ብቻ መሆኑን ይገልፃል። እዚህ ላይ በጋራ ንብረት የሆነውን አንደኛው ተጋቢ ሌላኛውን ተጋቢ ፈቃድ ወይም ስምምነት ሳያገኝ ብቻውን ለሌላ 3ኛ ወገን በሽያጭም ሆነ በሌላ መንገድ ቢያስተላልፍ ሌላኛው ተጋቢ ለፍርድ ቤት በሚያቀርበው ጥያቄ ግዴታው እንዲፈርስ መጠየቅ ይችላል። ይህ ግዴታ እንደፈረሰ የሚጠይቀው ተጋቢ ለፍ/ቤት ጥያቄውን የሚያቀርበው ግዴታው መገባቱን ካወቀበት ቀን ጀምሮ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ወይም በሌላ በማንኛውም ሁኔታ በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው። ይህ የተባለው ጊዜ ካለፈ ይህን ጥያቄ ማቅረብ እንደማይቻል በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 69(2) ላይ ተገልጿል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 38126 በአመልካች ዲያቆን ኃ/ጊዮርጊስ ወንድም እና ተጠሪዎች እነ የሺ ተፈሪ መካከል በነበረው ክርክር የአሁኑ 2ኛ ተጠሪ ከ1ኛ ተጠሪ ባለቤት ከሆኑት የጋራ ንብረታቸው የሆነውን ቤት ለአሁኑ አመልካች በ01/03/1995 ዓ.ም ያለ 1ኛ ተጠሪ ፍቃድ ይሸጥለታል። 1ኛ ተጠሪም በስር ፍርድ ቤት ውሉ ያለ እሳቸው ፍቃድ የተፈጸመ በመሆኑ እንዲፈርስ በማለት በ09/08/1999 ዓ.ም ክስ ታቀርባለች። በዚህ ጉዳይ ላይ የሰበር ችሎት የአሁን 1ኛ ተጠሪ የሆነችው ክስ ያቀረበችው በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 69/2/ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ማለትም ሽያጩን ካወቀችበት ጊዜ ጀምሮ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ወይም በማንኛውም ሁኔታ በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ ክሱን ያላቀረበች ስለሆነ (ክሱን ያቀረበችው ከ4 ዓመት በኋላ ነው) ውሉ እንዲፈርስ ክስ የማቅረቢያ ጊዜ አልፎል። ስለሆነም ውሉ አይፈርስም በማለት ውሳኔ ሰጥቷታል። የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ ሲኖር እለት በእለት ኑሮውን ለመደጎም ወጪዎችን ያወጣል። በትዳር ውስጥም ተጋቢዎ ትዳራቸውን ለማቃናትና ዘላቂነቱን ለማስቀጠል የተለያዩ ወጪዎች ማውጣታቸው የማይቀር ሀቅ ነው። በመሆኑም ተጋቢዎች የትዳራቸውን ወጪ ለመሸፈን እያንዳንዳቸው እንዳቅማቸውና ችሎታቸው አስተዋፅኦ የማድረግ ግዴታ አለባቸው። የህይወት መንገድ ሁልጊዜም አልጋ በአልጋ አይሆንም ውጣ ውረድ በህይወት ውስጥ ማጋጠሙ አይቀርም። በዚህ ጊዜ ወደ ብድር እና እዳ መገባት ሊያጋጥም ይችላል። በትዳር ውስጥም ተጋቢዎቹ ለግላቸው ወይም ለትዳራቸው ሲሉ እዳ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ይህ በሆነበት ጊዜ እዳውን ለመክፈል እዳው ለግል የተወሰደ ከሆነ ከባለእዳው ተጋቢ የግል ሀብት ይሸፈናል። ነገር ግን የግል ሀብቱ ይህን ለመሸፈን የማይችል ከሆነ ተጋቢዎች የመረዳዳትና የመተጋገዝ ግዴታ ስላለባቸው ይህ እዳ ከጋራ ሀብታቸው ይከፈላል። እዳው ግን ለትዳራቸው ጥቅም ከሆነ ከጋራ ሀብታቸው የሚከፈል ይሆናል። ነገር ግን የጋራ ሀብቱ በቂ ካልሆነ ከተጋቢዎቹ የግል ሀብት ይከፈላል።
4. ጋብቻ ቀለብ ከመስጠት ጋር ስለሚኖረው ውጤት
በዚህ ጽሑፍ ክፍል እንደ ውስጥ ዝምድና (የስጋም ይሁን የጋብቻ) በጋብቻ ቅድመ ሁኔታነት የሚታይበትን መንገድና የሚያስከትለውን ሕጋዊ ውጤት ተመል ክተናል። የዚህ የዝምድና ሌላኛው ውጤት ደግሞ በዘመዳሞቹ መካከል የሚፈጠረው ቀለብ የመስጠት ግዴታ ነው። በዚህ ክፍል ትኩረት ሰጥተን የምንመለከተው የጋብቻ ዝምድና የሚያስከትለውን የቀለብ መስጠት ግዴታ ነው።
ቀለብ የመስጠት ግዴታ በሕግ ሲቀመጥ አራት መሰረታዊ መርሆዎችን ከግምት አስገብቶ ነው።
1ኛ/ ቀለብ የመስጠት ግዴታ የሚጣለው እንዲሁ የስጋ ወይም የጋብቻ ዘመድ ነው ለተባለ ሰው ሁሉ ሳይሆን ጠበብ ብሎ በጣም ቅርብ ለሆኑ ዘመዶች ብቻ ነው።
2ኛ/ የግዴታው መጠን ለቀለብ ጠያቂው የእለት ተእለት ኑሮ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን በማቅረብ ላይ እንጂ የቀለብ ጠያ ቂውን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ለማሟላት የሚያስገድድ መሆን አይኖርበትም።
3ኛ/ ቀለብ የመስጠት ግዴታው በቀለብ ጠያቂው ላይ የጥገኝነት ስሜት በሚፈጥር መልኩ ሳይሆን ተቀጥሮ ወይም ስራ ፈጥሮ ራሱን ማስተዳደር የሚችልበት ሁኔታንና ስሜትን በሚፈጥር መልኩ መሆን አለበት።
4ኛ/ ቀለብ ጠያቂው ሠርቶ ለመኖር አቅም የሌለውና የተ ቸገረ መሆን አለበት
በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 198 ላይ ቀለብ የመስጠት ግዴታ የተጣለበትን ሰውና ቀለብ ጠያቂው ማን እንደሚሆን አስቀምጧል። ይህም በቀጥታ ወላጆችና ተወላጆች ማለትም በአባትና ልጅ፣ በእናትና በልጅ እንዲሁም በአያትና ልጅ መካከል አንዱ ነው። ሌላኛው ደግሞ በቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች መካከል ማለትም በባልና ሚስት አባት ወይም እናት ወይም አያት ወይም ልጅ ወይም በሚስትና በባል አባት ወይም እናት ወይም አያት ወይም ልጅ መሃላ ያለ ግዴታው ነው። ይህ አይነቱ በቀጥታ ያለውን የዝምድና መስመር የያዘው ነው።
ሌላኛው ደግሞ ወደ ጎን የሚቆጠር ዝምድና ላይ በወንድምና በወንድም ወይም በወንድምና እህት ወይም በእህትና እህት መካከል ግዴታ የተጣለ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ባልና ሚስት የመረዳዳት የመተጋገዝና የመደጋገፍ ግዴታ እንዳለባቸው ከላይ አይተናል። በመሆኑም ይህን ግዴታቸው አንዱ ለአንዱ ቀለብ የመስጠት ግዴታን የሚያካትት መሆኑን መረዳት ይቻላል። በሕጉ ላይ እንደተመለከተው ባል ለሚስት ወንድም ወይም እህት እንዲሁም ሚስት ለባል ወንድም ወይም እህት የቀጥታ የጋብቻ ዘመዶች ስላልሆኑ እነርሱን መርዳት ግዴታ እንደሌለባቸው ይገልፃል። ነገር ግን የባል ወይም የሚስት ወንድም ወይም የእህታቸውን የመርዳት ቀለብ የመስጠት ግዴታ አለባቸው። ይህን ግዴታ ለመወጣት ደግሞ ከግል ሀብት ወይም ከጋራ ሀብት ወጪ ማድረግ ይችላሉ። በመሆኑም ዞሮ ዞሮ ለባልና ለሚስት እህት ወይም ወንድም ቀለብ የመስጠት ግዴታ ለባልና ሚስቱ የሕግ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
የቀለብ ሰጭው ግዴታ እንደባለጉዳዮቹ (ቀለብ ሰጪውና ተቀባዩ) ሁኔታና እንደ አካባቢው ልማድ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት እንደሆነ በአንቀጽ 197 ላይ ተገልጿል። ይህም ማለት እንደ ቀለብ ሰጪውና ቀለብ ተቀባዩ አቅምና ፍላጎትን መሠረት ባደረገ መልኩ የሚከናወን ነው። እነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቶች ምግብ፣ መኖሪያ፣ ልብስ፣ ጤናውን እንዲጠብቅ እና ትምህርት ናቸው። ስለሆነም የቀለብ ሰጭው አቅምና የቀለብ ተቀባዩን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ ቀለብ የመስጠት ግዴታው ይፈፀማል ማለት ነው። ለምሳሌ የአንድ አቶ አበበ የተባለ ግለሰብ የሚስቱ አባት የራሳቸው መኖሪያ ያላቸው ነገር ግን የሚበሉትና የሚለብሱት ከቸገራቸው የአቶ አበበ ግዴታ ትምህርት እንደሚማሩ ወይም እንዲታከሙ ማድረግ ሳይሆን እንደ አቅሙ የሚመገቡትን ምግብና የሚለብሱትን ልብስ መስጠት ይሆናል።
ቀለብ ጠያቂው ከቀለብ ሰጪው ጋር የቅርብ ዘመድ (በሕጉ በተቀመጠው መሠረት) መሆኑ ከተረጋገጠና ሰርቶ እራሱን ለማስተዳደር አቅም የሌለውና ችግር ላይ የወደቀ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው ቀለብ መጠየቅ የሚችለው። ይህም ማለት ቀለብ የመጠየቅ መብት ስራ በማግኘትና ባለማግኘት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን የመስራት አቅም መኖር እና አለመኖር ላይ መሆኑን ከሕጉ መረዳት ይችላል። በመሆኑን መስራት አቅም እያለው ስራ ያላገኘ ሰው ቀለብ መጠየቅ አይችልም።
በጋብቻ የተዛመዱ ሰዎች ጋር የቀለብ መስጠት ግዴታው የሚቆረጥበት አጋጣሚ አለ። ይህም ጋብቻው በፍቺ ወይም የጋብቻ ቅድመ ሁኔታዎች ባለመሞላታቸው ጋብቻው ከፈረሰ ቀለብ የመስጠት ግዴታው ቀሪ ይሆናል። ነገር ግን ጋብቻው የፈረሰው በሞት ምክንያት ከሆነ ግዴታው ቀሪ አይሆንም ( የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 199)። ይህም የሆነበት ምክንያት ጋብቻው የፈረሰው ከአቅም በላይ በሆነ ሀይል በመሆኑ እንጂ በተጋቢዎቹ ቤተዘመዶች መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ መሆኑን ስለሚያሳይ ነው። ሌላው ቀለብ የመስጠት ግዴታ ቀሪ የሚሆንበት ምክንያት ቀለብ ጠያቂው ቀለብ ሰጪው ወይም በቅርብ ዘመዶቹ ህይወት ወይም ንብረት ላይ የወንጀል ተግባር የፈጸመ ወይም ለመፈጸም ሙከራ ያደረገ እንደሆን ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ከፍትህ መርሆች አንዱ “ማንም ሰው ከራሱ ጥፋት አትራፊ (ተጠቃሚ) መሆን የለበትም” (No one can benefit from his own fault) የሚል በመሆኑ ነው።
ቀለብ የመስጠት ግዴታ የተጣለበት ሰው ይህን ግዴታውን ባይወጣ ቀለብ ተቀባዩ ወደ ፍ/ቤት ጉዳዩን በማቅረብ ቀለብ ያልሰጠው ባለግዴታ ግዴታውን እንዲወጣ ማስወሰን ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ ቀለብ አለመስጠት የወንጀል ሃላፊነትም ያስከትላል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2013