
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ሂደት ውስጥ የክትባቶች መገኘት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትልቅ እፎይታን የፈጠረ ቢሆንም የቫይረሱ በየጊዜው ዝርያውን እየቀያየረ መምጣት ደግሞ ተጨማሪ ራስ ምታት ሆኗል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትም እስከአሁን ድረስ በሰባት ሀገራት የተከሰቱ አዳዲስ የኮቪድ ዝርያዎችን ይፋ አድርጓል፡፡
ድርጅቱ በእንግሊዝ የተከሰተውን ‹‹አልፋ››፣ በደቡብ አፍሪካ ‹‹ቤታ››፣ በብራዚል ‹‹ጋማ››፣ በህንድ ‹‹ዴልታ››፣ በድጋሚ በአሜሪካ የተከሰተውን ‹‹ኤፕሲሊዮን››፣ የብራዚሉን ‹‹ዜታ››፣ የፊሊፒንሱን ‹‹ቴታ›› እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ በአሜሪካ የተከሰተውን ‹‹አዮታ›› እንዲሁም በህንድ ለሁለተኛ ጊዜ የታየውን ‹‹ካፓ›› ሲል ሰይሞታል፡፡
በተለያዩ ሀገራት የተለያየ ዝርያ ያላቸው የኮቪድ- 19 ቫይረሶች መከሰታቸው ታዲያ በሁለንተናዊ መልኩ ጉዳት እንዳያስከትሉ በመላው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ስጋት ፈጥሯል፡፡ክስተቱ በተለይ ደግሞ በዓለም አቀፍ ምጣኔ ሀብት ላይ ከባድ ስጋት መደቀኑን የቡድን ሃያ ሀገራት የፋይናነስ ሚኒስትሮች ከሰሞኑ በጣሊያን ባደረጉት ስብሰባ ላይ ማስጠንቀቃቸውን ዘ ኢኮኖሚክ ታይምስ በድረ ገፁ አስፍሯል፡፡
ከአዳዲስ የኮቪድ-19 ዝርያዎች መከሰት ጋር ተዳምሮ እና በታዳጊ ሀገሮች ካለው ደካማ የክትባት አቅርቦት ጋር ተያያዞ እያገገመ የመጣው የዓለም ምጣኔ ሀብት አደጋ እንደተጋረጠበት የቡድን ሃያ ሀገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች ቅዳሜ እለት በጣሊያን ባደረጉት ስብሰባ ማስታወቃቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ የአባል ሀገራቱ የፋይናንስ ሚኒስትሮች በጣሊያን ቬኒስ ባደረጉት የገፅ ለገፅ ስብሰባ ባወጡት መግለጫ በሚያዝያ ወር ካደረጉት ስብሰባ ወዲህ የክትባት ስርጭት በስፋት በመካሄዱና የኢኮኖሚ ድጋፍ ማእቀፎች በመደረጋቸው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አመለካከት መቀየሩን ማስታወቃቸውን ዘገባው አትቷል፡፡ይሁንና በፍጥነት እየተሰራጩ የመጡ አዳዲስ የኮቪድ 19 ዝርያዎችን በተለይ ኮቪድ 19 ዴልታን በመግታት ረገድ ድክመት መታየቱን አባላቱ ባወጡት የመጨረሻ አቋም መግለጫ መናገራቸውንም አመልክቷል፡፡
ኢኮኖሚያዊ ማገገሙ ከሀገር ሀገር ልዩነት የሚታየበት ስለመሆኑና በአዳዲስ የኮቪድ 19 ዝርያዎች ከፍ ማለትና የክትባት ስርጭት ፍጥነት ልዩነት ምክንያት ለአደጋ የታገለጠ ስለመሆኑም በመግለጫው መናገራቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡መግለጫው የክትባት ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ ክፍፍል ድጋፍን በሚመለከት አጥብቆ ያሳሰበ መሆኑንና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ ፣ በዓለም ባንክ፣ በዓለም ጤና ድርጅት እና በዓለም ንግድ ድርጅት አማካይነት ለ 50 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር አዲስ ክትባት ፋይናንስ ድጋፍ እንዲደረግ የቀረበውን ሃሳብ እውቅና በመስጠት ተጨባጭ ዕርምጃዎች እንዳልተወሰደ ማብራራቱም ተገልጿል፡፡
‹‹በዓለም ዙሪያ ሁላችንም የክትባት አፈፃፀማችንን ማሻሻል አለብን›› ሲሉ የፈርንሳዩ የገንዘብ ሚኒስትር ብሩኖ ሊ ማሪ ለጋዜጠኞች መናገራቸውን የገለጸው ዘገባው፤ በተለይ የቡድን ሃያ ሀገራት ምጣኔ ትምበያ ጥሩ የሚባል ቢሆንም ወደ ፈጣን እና ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ መልሶ ማገገም በሚወስደው መንገድ ላይ ሊያጋጥመው የሚችለው ብቸኛ መሰናክል አዲስ የኮቪድ 19 ዝርያ ሞገድ አደጋ ነው›› ሲሉ መናገራቸውን ጠቅሷል፡፡
በክትባት ስርጭት በኩል በድሆችና ሀብታም ሀገራት መካከል ሰፊ ልዩነት ስለመኖሩ በቡድን ሃያ አገራት የአቋም መግለጫ መጠቀሱንም የገለጸው፤ ዘገባው፤ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ልዩነቱን “የሞራል ቁጣ” ሲሉ መግለጻቸውንና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሰፊ ጥረቶችን የሚያዳክም ሲሉ መናገራቸውንም ተናግሯል፡፡
አንዳንድ ሀብታም ሀገራት በአሁኑ ጊዜ ቢያንስ አንድ ክትባት ሁለት ሦስተኛ ለሚሆኑ ዜጎቻቸው ቢሰጡም ይህ ቁጥር ለብዙ የአፍሪካ አገራት ከአምስት በመቶ በታች መሆኑም በዘገባው ተጠቁሟል፡፡ ይህ ሁኔታ በድሃ ሀገራት ህይወትን ከማሳጣት በዘለለ በሀብታሞቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ አዳዲስ የቫይረስ ዓይነቶችን እንደሚጨምርም ብራንደን ሎክ የተባሉና ዋን ካምፔይን በተሰኘ ለትርፍ ባልተቋቋመ የህብረተሰብ ጤና ቡድን ውስጥ የሚሠሩ የተናገሩትን ሃሳብ ጠቅሷል፡፡
አዲስ የኮቪድ – 19 ኢንፌክሽኖች በ 69 ሀገሮች ውስጥ ከፍ ማለቱንና ከሰኔ መጨረሻ ጀምሮ የዕለታዊ ምጣኔው ጭማሪ ማሳየቱንና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ 478 ሺህ መድረሱንም ሮይተርስ ያወጣውን መረጃ ዋቢ አድርጎ ዘገባው ጠቁሟል፡፡የዴልታ ኮቪድ 19 ዝርያ ስርጭት ከፍ እያለ በመምጣቱና በተለይ ደግሞ የክትባቱ ስርጭት ዝቅተኛ በሆነባቸው ሀገራት ጉዳቱ ከዚህም በላይ ሊሆን ስለሚችል የጋጠመውን የዓለም ምጣኔ ሀብት ወደ ኋላ እንዳይመልሰው ስጋቶች እያደጉ ስለመምጣታቸውም በዘገባው መቋጫ ተቀምጧል፡፡
የቡድን ሃያ ሀገራት በኢኮኖሚ ያደጉ 19 ሀገራትንና የአውሮፓ ህብረትን የሚያቅፍ ፤ አባል ሀገራቱ ከ80 ከመቶ በላይ የሚሆነውን የዓለም አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት፣ 75 ከመቶ ያህሉን ዓለም አቀፍ ንግድና 60 ከመቶ የሚሆነውን የዓለም ህዝብ እንደሚሸፍኑ ይነገራል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2013