ዐሻራችን ያዋለደህ መንግሥታችን ሆይ!
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተከናወነው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ይበጀኛል ብዬ ላመንኩበት ፓርቲና አደራዬን በትከሻው ላይ ለማስቀምጥበት ዕጩ ተወዳዳሪ ድምፄን ለመስጠት ከቤተሰቤ ጋር የዘመትኩት በወፎች የማለዳ ጫጫታና ዝማሬ ተቀስቅሼ ነበር፡፡በርግጠኝነት የገመትኩት ጥቂት ሰዎች ይቀድሙኝ ካልሆነ በስተቀር በሁለት ዙር የሰልፈኞች ጥምጥም እፈተናለሁ ብዬ አልገመትኩትም ነበር፡፡
የማለዳው ካፊያና ቁር የማይበግረው ያ ተስፈኛ መራጭ የሕዝብ ጎርፍ እንቅልፍ ሳይበግረው ነቅቶና ማልዶ ከምርጫ ጣቢያው የደረሰው ምናልባትም ከእኔና ከቤተሰቡ ቀድሞ በዶሮ ጩኸት አስታዋሽነት ሳይሆን እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡ የነገይቱን ሰላማ ዊትና ከችግር አረንቋ በአሸናፊነት ተወጥታ የሀሴት ዕልልታ እንድታሰማ የሚናፍቃትን ሀገሩንና ሕዝቡን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል በትረ ሥልጣኑን የሚጨብጥ አገልጋይ መንግሥት “እንዲነግ ሥለት” በመመኘት እንዲያ በቁርና በውርጭ ማልዶ የወጣውን የሰው ጅረት ሳስተውል ስሜታዊ ሆኜ ዓይኔ በዕንባ መርጠቡን መሸሸግ አልፈልግም፡፡
እውነት ነው፤ ተስፋን ሰንቆ፣ ብሩህ ነገን ናፍቆ፣ አስገባሪ ጌቶችን ሳይሆን አገልጋይ መሪዎችን (Servant Leaders) በመመኘት፣ በሙስና በከረፉ እጆች ተገልጋዩን የሚጨብጡትን ሳይሆን ዝቅ ብለው ለፈጣሪ፣ ለህሊናቸውና ለወከሉት የፖለቲካ ፓርቲ መርህ ቃላቸውን የሚጠብቁና በንጽህና የሚያገለግሉ ዕምባ አባሽ አገልጋዮችን ለመምረጥ ሕዝቡ ጓጉቶና ማልዶ መውጣቱን በርህራሄ ልብ ላስተዋለ ሰው አይደለም ስሜታዊነት ከዚያም ከፍ ብሎ እዬዬ ቢያሰኝም ተጋንኗል ሊባል አይገባውም፡፡
ሰዓታት በፈጀ ትዕግሥት ጉልበታቸው እየተን ቀጠቀጠ የተሰለፉ አረጋዊያንንና አዛውንቶችን፣ እርግዝናቸው የከበደ እናቶችን፣ በሥራ እጦት ምክንያት ነገን ተስፋ አድርገው የወጣትነታቸውን ቅብጥብጥ ስሜት ለእርጋታ አስገዝተው የተሰለፉ ጎበዛዝት ወጣቶችን በተሰለፉበት ውሎ እየተከባበሩ ሲጨዋወቱና ድካማቸውን በሚያረሳሱ ቀልዶች እየተጎነታተሉ ሲሳሳቁ ማስተዋል እንደምን ልብ በርህራሄ አይነካ?
ሠልፉ ምናልባት ይቀል እንደሆን በማለት ከቤተሰቤ ጋር ወደ ቤት ተመልሰን አፋችንን በማለዳ እህል ካበስን በኋላ አላስችል ስላለንና የከሰዓት በኋላው ቀጠሮ ረዝሞ ስለታየን እንደገና ወደ ምርጫው ጣቢያ እየተጣደፍን ስንደርስ የሠልፉ ርዝመት ከሁለት ዙር ወደ ሦስት ዙር ከፍ ብሎ አካባቢው በሰው ብዛት ተጨናንቆ አስተዋልን፡፡ይሄኔ ነበር ስሜቴን በማረጋጋት በሰውኛ ዘይቤ ኢትዮጵያን ለምስክርነት ከፊት ለፊቴ አቁሜ በውስጥ እኔነቴ መሟገት የጀመርኩት፡፡
“ኢትዮጵያ ሆይ እኒህን የነገን መልካም ቀን ናፋቂ የመሪ ርሃብተኛ ልጆችሽን ትመለከቻቸዋለሽ? እረኛ እንደሌላቸው በጎች ለዴሞክራሲ መስፈን ሲሉ በብርድና በቁር ሲጠበሱስ ህመማቸው አያምሽም?” – እያልኩ በውስጤ በመፈላሰፍ ደቂቆችን በሃሳብ ነጎድኩ፡፡“ትዕግሥት ደጉ” እንዲሉ ፍልስፍናዬ ትንሽ ወሰድ ስላደረገኝ ሰዓቱ ገፍቶ የወረፋውን ርዝመት ስላቃለለልኝ ዐሻራዬን አትሜ ተመልሻለሁ፡፡ምራኝ ብዬ የመረጥኩህ የመስከረሙ መንግሥቴ ሆይ ይህንንና መሰል የብዙኀንን ስሜት ለተመራጮቹ “ልጆችህ” ታስተላልፍልኝ ከሆነ እነሆ መልዕክቴን አድርስልኝ፡፡
የመራር ሃሞት አደራ!
የምርጫው ውጤት ሙሉ ለሙሉ ባይጠናቀቅም ዛሬ ላይ ቆመን ጊዜውን ስናሰላ ሃያ አራተኛ ቀን እንደሆነ ካላንደሩ ይነግረናል፡፡እርግጥ ነው ከጥቂት ቀናት በፊት በምርጫ አስፈጻሚው ኮሚሽን በኩል አብዛኛው ውጤት ለሕዝብ ይፋ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ከምርጫው ዕለት እስከ ዛሬ ብዙ ክስተቶች የተስተናገዱ ቢሆንም በምርጫው ዕለት በእኔና በመሰል መራጮች አውራ ጣት ላይ የተቀባነው የመራጭነት ማረጋገጫ ቀለም (indelible ink or electoral ink) ግን እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ አልደበዘዘም፤ ጨርሶም አልጠፋም።
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝም ይሄው አልጠፋ ብሎ በየደቂቃው የማስተውለውና የምርጫ ዐሻራዬን ለማሳረፌ ማረጋገጫ የሆነው በጣቴ ላይ የታተመው ቀለም ነው። የተለያዩ ሀገራት ተመሳሳይ ቀለም ቢጠቀሙም የጣት ምርጫቸው ግን አውራ ጣት ብቻም ሳይሆን እንደፈለጉ ስለመሆኑ የተረዳሁት ተጨማሪ ንባብ በማድረግ ነው፡፡ የዜጎችን መራጭነት ለማረጋገጥ ሀገራት እንደፍላጎታቸው በተለያዩ የጣት ጥፍሮች ላይ ቀለም መቀባታቸው በስፋት የተለመደ ብቻም ሳይሆን አንዳንድ ሀገራት በአመልካች ጣት ላይ የውስጠኛው ዐሻራ ላይ ሳይቀር የቀለሙን ምልክት እንደሚያሳርፉ ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡
በእኛ ሀገር አውራ ጣት ከእኩዮቹ መካከል ተመርጦና ለዚህ ሀገራዊ የምርጫ ጉዳይ በምን መስፈርትነት ተለይቶ ለሹመት እንደበቃ ለጊዜው በጥልቀት መመራመሩ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል፡፡ ለምን ቢሉ “ከጣትም ጣት ይበልጣል” እንዲል ብሂላችን ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሙግት ከፍቶ በእንኪያ ሰላንትያ መነታረኩ እጅግም ከጉንጭ አልፋነት አይዘለም። ዋናው ጉዳይ ዐሻራችንን በምርጫው ላይ ማሳረፋችን ነው፡፡ ስለ ዐሻራ ጉዳይ ተጨ ማሪ ንባብ ካስፈለገ ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም በዚሁ ጋዜጣ ላይ የታተመውን ጽሑፌን ማንበብ ይቻላል፡፡
“ኢትዮጵያ እንዳሸነፈች” የተነገረለት ታሪካዊ ምርጫ መቶ በመቶ ተጠቃሎ ባይቀር ብም አሸናፊው ፓርቲ የትኛው እንደሆነ ይፋ ተደርጓል። የአሸናፊው “ልጆችም” – “አገኘኋት እንደተመኘኋት” እያሉ ሲገባበዙና ሲጋበዙ ተመልክተን ያልታዘብነው አንዳንዴ ደስታ ሊያሰክር ይችላል ስለሚባል ነው፡፡ እግር በጣለን አንድ ቤተሰብ መካከል በደረስንበት አጋ ጣሚም “እንኳን ደስ አልዎት!” በሚሉ ቤተኞች ውጪ ግቢውን ካደመቀው ፌሽታ “ጠበል ጠዲቁ” ደርሶን “ከሹመት ያዳብር ምርቃት” ያልተናነሰ ቃል በመወርወር ምንተ እፍረታችንን መርቀን ወጥተናል። መመረጥን ማን ይጠላል? በመባባልም “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ሆኖብን እርስ በእርስ ላለመተፋፈር ተጽናንተናል፡፡
ጉዳዩ ከመመረጡ ላይ ሳይሆን ከሚቀመ ጡበት ወንበር ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ስለመሆኑ ለተመራጮቹም ሆነ ለእኛ ይጠፋናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ችግሩ በዚህ ታሪካዊ ምርጫ ወንበር የተሰጣቸው ግለሰቦች ውለው አድረው የትናንቶቹ ባህርይ ተጋብቶባቸው የመረጣቸውን ሕዝብ ቁልቁል መመልከት የጀመሩ ዕለት ነው፡፡
መስከረም ሲጠባ በፓርላማው ወንበሮች ላይ ከሚሰየሙት የአዲሱ መንግሥት “እንደራሴዎች” መካከል የዚህ ጸሐፊ በርከት ያሉ ወዳጆች በለስ ቀንቷቸዋል፡፡ስለ ፖለቲካ ሲያወራ በፍጹም ሰምቶት የማያውቀው አንድ ዕውቀት የጠለቀው አብሮ አደጉ “ትልቁን ፓርቲ ተጠግቶ” ምርጫውን አሸንፏል። ሦስት ያህሉ የትምህርት ቤትና የሙያ ጓደኞቹም የፓርላማው ደጃፍ ወለል ተደርጎ ተከፍቶላቸዋል፡፡ “ለሁለት ፀጉር የደረስኩበት ሙያዬ እጅ እጅ አለኝ እና በጡረታ ዕድሜዬ ያለ ቋሚ ሥራ መቀመጡ ሰለቸኝ” ይሉ የነበሩ የቅርቡ ሰዎችም በአምፖል ብርሃን መሪነት ወደ ፓርላማው መቀላቀላቸው ተበስሯል፡፡“ፖለቲካ ብሎ ነገር ቆዳዬ ይጠየፈዋል!” በማለት ቃል በቃል ይናገሩ የነበሩ አንድ “የተከበሩ” ወዳጁም የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት እንኳን ፋታ ሳያገኙ “ተወዳድረው አሸንፈዋል፡፡” ታሪኩም፣ ትርክቱም ተመጥኖ ካልተገታ በስተቀር እንዲህ በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ብዙ ስለሚያጽፍ እዚሁ ላይ መግታቱ ሳይበጅ አይቀርም፡፡
ያለምንም ክርክር የኢትዮጵያን ሕዝብ የራበው ላገልግልህ ብሎ ጠረኑን የሚያሸትለት መሪ ነው፡፡ ሕዝባችን የጠማው ዝቅ ብሎ ብዙኀንን ለማገልገል እንጂ “እኔ እኮ!” እያለ “በልዩ የተመራጭነት መብቱ” የሚፎክር “ስመ እንደራሴ” አይደለም፡፡ እንጂማ የአምባገነኖች ስብስብ መች ብርቃችን ሆኖ? ህሊናቸውን ሸጠው ከበላይ በሚወሰንላቸው ውሳኔ ያለ ምንም ተቃውሞና የተለየ ሃሳብ ዕልል እያሉ የሚያጨበጭቡ ሴቶችና ወንዶች ወንበረተኞች ለእኛ ሀገር የፖለቲካ ምህዳር መች እንግዳ ሆነው?
ተቅለስልሰው ተመርጠው ሥልጣን ላይ ፊጥ ካሉ በኋላ የብረት በትር አንስተው ሲጨረግዱን የኖሩ በርካታ “ጉልበተኞችን” በተመለከተ ያለቅስነው ዕንባ ወደ ፈጣሪ ፀባዖት ደርሶ የሆነውን ዕድሜና ጊዜ ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል፡፡በብርሃን ምስክርነት ያማለልን መጭው መንግሥትና የመንግሥቱን አጀንዳ የሚያስፈጽሙት “አምፖል ያዦች” ከላይ ለዘረዘርናቸው መሰል እፀፆች ሰለባ ሆነው ዳግመኛ እንደማያስለቅሱን ተስፋ እናደርጋለን፡፡አልቅሱ ቢሉንስ ከደረቀ ምንጭ የቱ ዕምባ ይመነጭና?
በተለይም ቢሯቸውን በስብሰባ የብረት አጥር ከርችመው ውሏቸውን “ዛሬ ጥብቅ ስብሰባ ላይ ናቸው” እያሰኙ ሲሸነግሉን እንደኖሩት “ቁማርተኞች” እንደማይሆኑ እምነት አለን፡፡እንደ ቀደምቶቹ “ሹመኞቻችን” ውሎ አዳራቸውን በየሆቴሉና በየመዝናኛው በማድረግ “እርዬ እርዬ” ሲሉ አድረው ጠዋት ላይ “ዛሬ ቢሮ አይገቡም” የሚባሉ ዓይነት “እንደራሴዎች” እንደማይሆኑም ተስፋ ጥለንባቸዋል። አሸናፊው ፓርቲና ባለድል ተመራጮች በማን ጥላና ስም ተጠልለው በለስ እንደቀናቸው ይጠፋቸዋል ብለን አንገምትም፡፡ይህንን ስጋታችንን ቀድመን የምንተነፍሰው ሁለት ዓይን ተከፍቶ የሚረከቡት ሥልጣን ውሎ አድሮ እንዳያንሸዋርራቸው በመስጋት እንጂ ሐሰተኛ ነብያት ለመሆን ፍላጎቱ ስላለን አይደለም፡፡“እባብ ያየ በልጥ በረዬ” ብሂላችን ተጽእኖ አሳድሮብን ስለመሆኑም ሊረዱን ይገባል፡፡
ዛሬ ዛሬ እያስተዋልን እንዳለነው ለፕሮጀክት ክትትልም ሆነ ለምርቃት የምናስተውለው አንድን ወይንም ውሱን ሰውን ብቻ ሊሆን አይገባም፡፡ችግኝ ለመትከል አንድ ሰው፣ ፕሮጀክት ለመመረቅም እኒያው ሰው ወይንም ሴትዮ፣ ችግረኞችን ለመጎብኘትም ልብሳቸውን ቀይረው እኛው ማለዳ ያየናቸው ሰው ሆነው ሌሎች የመረጥናቸው “እንደራሴዎቻችን የት ደረሱ?” ብለን በመላ ምት ሃሜተኞች እንዳንሆን ሊጠነቀቁልን ይገባል፡፡በድምፃችን የመረጥናቸው፣ በዐሻራችን የለየናቸው የእኛ የምንላቸው “እንደራ ሴዎች” ከተመረጡበት ሠፈርና መንደር ድረስ ዝቅ ብለው ወርደው እንዲጎበኙን እንጂ መኖር ያለመኖራቸውን በቴሌቪዥን ብቻ እንዳናረጋግጥ ከወዲሁ ሊያስቡበት ይገባል፡፡
በሚቀጥለው አዲሱ ፓርላማ ውስጥ ደምቆ የሚሰማው የሕዝብ ድምፅ እንዲሆን፣ በየግድግዳው ላይ የሚታተመውም ቁርና ውርጭ፣ ፀሐይና ንዳድ እያንገበገበው የመረጠው የሕዝብ ዐሻራ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ መስከረም ሆይ በሆት ግባ፡፡ ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2013