“የወደፊቱ ህይወታችን እያደገ ባለው የቴክኖሎጂ ኃይል እና ቴክኖሎጂውን በምንጠቀምበት ጥበብ መካከል የሚደረግ ግብ ግብ ነው።” እንግሊዛዊው የአንፃራዊነት ንድፈ ሃሳብ እና በኳንተም ሜካኒክስ ሊቅ እና የፊዚክስ ኖቤል ሎሬት ስቴፈን ሀውኪንግ በአንድ ወቅት የተናገሩት ነው። ይህ በታዋቂው የፊዚክስ የኖቤል ተሸላሚ የተጠቀሰው ጥቅስ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች በጤናው ዘርፍም ሆነ ከዚያ ባሻገር ያሉባቸውን ታላቅ ዕድሎች እና ተግዳሮቶች ያስታውሰናል። ዕድሎችን ማስፋትና ተግዳሮቶችን መቀነስ ደግሞ የዘመናችን ትልቁ የቤት ሥራ ነው።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተ ሊጀንስ) የጤና አጠባበቅ እና መድሃኒት አቅርቦትን ለማጠናከር እና ሁሉም ሀገሮች ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን እንዲያገኙ ለማገዝ ትልቅ አቅም አለው። የተሻሻለ ምርመራ እና ክሊኒካዊ ክብካቤን፣ በጤና ዙሪያ የሚደረጉ ምርምሮችን እና የመድሃኒት ልማትን ለማጎልበትም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በተጨማሪም ለበሽታ ክትትል፣ ወረርሽኝ ምላሽ እና የጤና ስርዓቶች አያያዝን የመሳሰሉ የተለያዩ የህዝብ ጤና አሠራሮች አመራርን እንደሚያግዝ የዓለም ጤና ድርጅት ሰሞኑን ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያመላክታል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ሀገራት በተለይም በጤና እንክብካቤ እና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ክፍተት ላለባቸው ሀገራት ሰው ሠራሽ አስተውሎት ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ይችላል። በሰው ሠራሽ አስተውሎት መሰረት ባደረጉ መሳሪያዎች በመታገዝ መንግሥታት የጤና አገልግሎቶችን ለማያገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ማስፋፋት ፣ የህዝብ ጤና ቁጥጥርን ማሻሻል እና የጤና አጠባበቅ አቅራቢዎች ህሙማንን በተሻለ ሁኔታ እንዲያገኙ እና ውስብስብ እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ማቅረብ ይችላሉ።
በተመሳሳይ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በህብረተሰብ ጤና ጥበቃ እና በመድኃኒት ዝግጅት ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲኖረው በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች በዲዛይን ፣ በልማት እና ወደ ተግባር በሚገባበት ወቅት የስነምግባር ጉዳዮች እና የሰብዓዊ መብቶች ማዕከል መሆን አለባቸው። ስነ ምግባር እና የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ሊዘነጉ አይገባም። ሰው ሠራሽ አስተውሎት በጤና ዘርፍ ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል፣ ዘር፣ ዕድሜ እና ጾታ መሰረት ያደረጉ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ እና ስርዓት ላይ የተመሰረቱ ስልተ ቀመሮችን (አልጎሪዝም) ለማሰልጠን በተሠራ መረጃ ላይ የተመዘገቡ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ አድሏዊ አሠራሮች መለወጥ አለባቸው።
ሰሞኑን ድርጅቱ ያወጣው ሪፖርት ላይ እንደተብራራው ከመረጃ እና ከግንኙነት ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የነበረውን አካሄድ ማስተካከል የግድ ነው። መንግሥታት ቀደም ሲል የነበረውን የዲጂታል ክፍፍል (ወይም ያልተስተካከለ የመዳረሻ ስርጭትን) ማስወገድ ይኖርባቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ዲጂታል ክፍፍል በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን የሚገድብ ብቻ ሳይሆን የበለፀጉ ሀገራት ውስጥም ጾታ፣ ጂኦግራፊ፣ ባህል፣ ሃይማኖት እና ቋንቋ ወይም ዕድሜን መሰረት በማድረግ የተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍል ከአገልግሎት እና ጤና ስርዓት እንዲገለል የሚያደርግ ነው።
ብዙ የዓለም ትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በመረጃ ክምችት (የጤና መረጃን ጨምሮ) ፣ የስልተ ቀመር (የአልጎሪዝም) ልማት እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ልማት ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሱ እንደሚገኙ ያመላከተው የድርጅቱ ሪፖርት የሰው ሠራሽ አስተውሎት መበራከት የጤና አገልግሎቶች ቁጥጥር በሌለበት እና ቁጥጥር በማይደረግባቸው የጤና አገልግሎቶች አቅራቢዎች እንዲሰጥ በር ሊከፍት ይችላል፤ ይህም በመንግሥት የጤና እንክብካቤ ቁጥጥር ላይ ፈታኝ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችልም ተጠቁሟል።
ስለሆነም የሰው ሠራሽ አስተውሎት ምርቶችን እና አገልግሎቶችን ተጠቃሚ የሆኑ የግሉ ዘርፍ ተጠያቂ እንዲሆኑ እና ጥፋት ሠርተው ሲገኙ ለሠሩት ጥፋት ተገቢውን ካሳ እንዲከፍሉ ለማድረግ ተገቢ ቁጥጥር ስልቶች መዘጋጀት አለባቸው። እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ውሳኔ አሰጣጥ እና አሠራሮች ግልጽ መሆናቸውን በዚሁ ማረጋገጥ ይቻላል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት በጥበብ ሥራ ላይ ከዋለ በሽተኞች እና ማህበረሰቦች የራሳቸውን የጤና ክብካቤ እንዲቆጣጠሩ እና እየተሻሻሉ ያሉ ፍላጎቶቻቸውን በተሻለ እንዲገነዘቡ የማድረግ አቅም እንዳለው ያብራረው የድርጅቱ ሪፖርት፤ ነገር ግን ተገቢው የጥንቃቄ ዕርምጃዎች ካልተወሰዱ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በአቅራቢዎች እና በታካሚዎች ሊደረጉ የሚገባቸው ውሳኔዎች ወደ ማሽኖች ሊተላለፍ እንደሚችልም ጠቁሟል።
ይህም የሰው ልጅ መጠበቅ ያለባቸው የግል ምስጢሮችን አደባባይ ላይ ሊያወጣ ይችላል። ምክንያቱም የሰው ልጅ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ እንዴት በውሳኔ ላይ እንደደረሰ ሊታወቅ አይችልም፤ የጋራ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከቴክኖሎጂ ጋር መደራደርም አይችልም። በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ጤና ጋር በተያያዘ የሰው ልጆች በጤና አጠባበቅ ሥርዓቶች እና በሕክምና ውሳኔዎች ዙሪያ ሙሉ ቁጥጥር ሊኖረው ይገባል።
በአጠቃላይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የበሽታ ምርመራዎችን ለማፋጠን፣ የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን ለማጠናከር፣ መድኃኒቶችን ለማበልጸግ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ፣ የበሽታ ቅኝት ለማካሄድ እና ለድንገተኛ ወረርሽኞች ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም የጤና ሥርዓት አስተዳደሩን ለማዘመን ጥቅም ላይ እንደሚውል ተገልጿል። ሥነ ምግባር የጎደለው የዳታ አሰባሰብ እና አጠቃቀም፣ ዘርን እንዲሁም የሀብት ሁኔታን እና ሌሎች ጉዳዮችን መሰረት ያደረገ በስልተ ቀመሮች የተደበቀ መድሎ እና የሳይበር ደህንነት ከመልካም አጋጣሚዎቹ ጋር ተያይዘው የመጡ ተግዳሮቶች ተብለው ተጠቅሰዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የሰው ሠራሽ አስተውሎት በጤናው ዘርፍ እንዴት ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት የሚያመላክቱ መርህዎችን የያዘ ሰነድ አውጥቷል። ይህ የዓለም ጤና ድርጅት መመሪያ ሰነድ በሳይንስ ክንፍ – ዲጂታል ጤና፣ ኢኖቬሽን እና ምርምር ለጤና በሁለት ክፍሎች የሚመራ የሁለት ዓመት የልማት ሂደት ውጤት ነው። የዓለም ጤና ድርጅት ሰው ሠራሽ አስተውሎት በጤና ዘርፍ ስነ ምግባር ባለው መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻል ከ20 ባለሙያዎች ጋር በመሆን ሲሠራ ቆይቷል።
እነዚህ መርህዎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት መስክ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ የጋራ መግባባት መርሆዎች ናቸው። ድርጅቱ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተግዳሮቶቹን በመቀነስ መልካም አጋጣሚዎቹን በተሻለ ሁኔታ መጠቀም ያስችላሉ ተብሎ የወጡ ስድስቱ የአጠቃቀም መርሆዎች የሚከተሉት ናቸው፡- ምስጢር መጠበቅ፤ የሰው ልጅ ደህንነት እና የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም፤ ግልጽነትን፣ ገላጭነትን እና አስተዋይነትን ማረጋገጥ፤ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን ማሳደግ፤ ሁሉን አቀፍ እና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ እንዲሁም ምላሽ ሰጭ እና ዘላቂ የሆነ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ማሳደግ የሚሉት ናቸው።
እንደ ድርጅቱ ሪፖርት እነዚህን መርሆዎች እና የሰብአዊ መብቶች ግዴታዎች በተግባር ለመተግበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መሥራት አለባቸው። የሰው ሠራሽ አስተውሎት ንድፍ እና ፕሮግራም አውጪዎች፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አቅራቢዎች እና ህመምተኞች እንዲሁም የጤና ጥበቃ ሚኒስትሮች እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሮች በቴክኖሎጂ ዲዛይን ደረጃ ሁሉ የሥነ ምግባር ደንቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ በጋራ መሥራት አለባቸው።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች ልማት እና ስርጭት የስነምግባር ህጎች ፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ እና የህግ ግዴታዎችን በተከተለ መልኩ እየተተገበረ መሆኑን ለማረጋገጥ መንግሥታት ዓለም አቀፍ ሰው ሠራሽ አስተውሎት አስተዳደር ስርዓትን መደገፍ እና አስፈላጊውን ትብብርም ማድረግም አለባቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት፣ ጋቪ፣ የክትባቶች ጥምረት፣ ዓለም አቀፍ የኤድስ፣ ሳንባ ነቀርሳና ካንሰር መከላከያ ፈንድ የመሳሰሉ የዓለም የጤና ዘርፍ አካላት ከሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ እና የሰብዓዊ መብቶች ግዴታዎች መከበራቸውን በሕጋዊ መንገድ ለማረጋገጥ፣ የጥበቃ እና የስነምግባር ደረጃዎች የሁሉም ስልቶች እና መመሪያዎች ዋና ግዴታ ነው ። ይህንን ግዴታ ለመወጣት ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት አለባቸው።
የአውሮፓ ምክር ቤት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመሆን የስነምግባር ተግዳሮቶችን እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለጤና ዘርፍ የመጠቀም ዕድሎችን አስመልክቶ የጋራ እቅድ ማዘጋጀት አለባቸው። ዕቅዱ ከዓለም አቀፍ መርሆዎች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ወጥነት ያለው የህግ እና ቴክኒካዊ አገልግሎቶች አቅርቦትን፣ ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር ግዴታዎችን ማካተት አለበት።
በተጨማሪም መንግሥታት እና ዓለምአቀፍ ኤጀንሲዎች መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እና የማህበረሰብ ድርጅቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ በማድረግ በተለይም ለተገለሉ ቡድኖች የተለያዩ ጥልቅ ትንታኔዎችን ለማቅረብ እንዲሁም፤ ሲቪል ማህበረሰብ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ለጤናው ዘርፍ ለመጠቀም ጥቅም ላይ በሚውሉ ቴክኖሎጂዎች ዲዛይንና አጠቃቀም ላይ እንዲሳተፉ መደረግ እንዳለበት ሪፖርቱ አመላክቷል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2013