
አዲስ አበባ፡– ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ጫናን እንደ አገርና ህዝብ ተቋቁመን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክትን ከጫፍ ማድረስ ትልቅ ስኬት እንደሆነ የውሃ ባለሙያ ዶክተር ዮሃንስ ዳንኤል አስታወቁ።
ዶክተር ዮሃንስ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ከብዙ አለም አቀፍ ጫና በኋላ ሀይል ማመንጨት የሚጀመርበት ሁለተኛው የውሃ ሙሌት መጀመሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ስኬትና ድል ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ አገርና ህዝብ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ጫና አስተናግደናል፤ጫናውን ሁሉ ተቋቁመን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክትን ከጫፍ ማድረስ መቻላችን ለወደፊት ለሚኖረን ሁለተናዊ ልማት እንደ መሰረት ድንጋይ ሆኖ ያገለግላሉ ሲሉ አስታውቀዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከመጀመሪያው አንስቶ እስካሁን ድረስ አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ረገብ የሚል በኢትዮጵያ ላይ ጫና ይደረግ እንደነበር የጠቆሙት ዶክተር ዮሃንስ፤ በተለይ አሁን ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ተከትሎ ግብጾችና ሱዳኖች በጋራና በተናጠል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲያደርግ እየሰሩ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትም በዲፕሎማሲውና የግድቡን ግንባታ በማፋጠን ረገድ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
እኤአ በ2015 ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ የመርህ ስምምነት(ዲክላሪሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ) መፈራረማቸውን ያመለከቱት ዶክተር ዮሃንስ፤ በስምምነቱም በሶስቱ አገሮች መካከል ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም መኖር እንዳለበትና ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት የጎላ ተጽእኖ አለማድረስ የሚሉት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሶስቱም አገራት ይህን የመርህ ስምምነት መሰረት አድርገው እኤአ በ2018 ከየአገራቱ ገለልተኛ የኤክስፐርቶች ቡድን ተዋቅሮ ኤክስፐርቶቹ ተከታታይ ውይይት አድርገው በደረሱት ስምምነት አድርገው መሰረት ባስቀመጡት የጊዜ ሰሌዳ የግድቡ ሁለተኛ ዙር እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።
ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድብ እንደሚጠቅማቸውና እንደማይጎዳቸው ያውቃሉ ያሉት ዶክተር ዮሀንስ፤ ሱዳንና ግብጽ የሚፈልጉት የህዳሴ ግድብ ድርድር እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያን የወደፊት የውሃ አጠቃቀም ለመወሰን አልያም ከቻሉ ጨርሶ ለመከልከል ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወደፊት በአባይ ውሃ የመልማት ዕድሏን አሳልፋ እንደማትስጥ የገለጹት ምሁሩ፤ በሶስቱ አገራት መካከል ሲደረግ የቆየው በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚደረግ ድርድር እንጂ በአባይ ውሃ አጠቃቀምና ክፍፍል የሚደረግ እንዳልሆነ ብዙ ጊዜ እንደተነገራቸው አመልክተዋል።
በአንጻሩ በተለይ ግብጽ አጋጣሚዎችን ተጠቅማ ኢትዮጵያ በውሃ ላይ ሌላ ልማት እንዳታካሂድ መከልከል ወይም 1958 አሳሪ ስምምነትን ተቀባይነት እንዲያገኘ ጥረት እያደረገች ነው ፤ ይህ እንደማይሳካላቸውና ኢትዮጵያም የማትደራደርበት ጉዳይ መሆኑን አስታውቀዋል። ህዝቡ በአንድ መንፈስና በጋለ ሁኔታ ለግድቡ የሚያደርገው ድጋፍ እስከፍጻሜው ድረስ መቀጠል እንደሚኖርበትም ገልጸዋል።
በጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2013