የሃይቲው ፕሬዚዳንት ጆቨኔል ሞይዝ ሰሞኑን ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸው ተሰምቷል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2017 ላይ ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንቱ የተገደሉት በመኖሪያ ቤታቸው ነው።
ባለፈው ረቡዕ የታጠቁ ሰዎች ወደ ፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ቤት ገብተው ጥቃት ፈጽመዋል የተባለ ሲሆን፤ የሀገሪቱ ቀዳማዊት እመቤትም በጥቃቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሀገሪቱ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ክላውዴ ጆሴፍ ተናግረዋል።
የሄይቲውን ፕሬዚዳንት ጆቨኔል ሞይዝን የገደሉት 28 አባላት ያሉት ቅጥረኛ የገዳዮች ቡድን ነው ሲል ፖሊስ አስታውቋል። ከእነዚህ መካከልም ሃያ ስድስቱ ኮሎምቢያዊያን ሲሆኑ፤ ሁለቱ ደግሞ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ሄይቲያዊያን ናቸው ሲሉ የፖሊስ አለቃ ሌዎን ቻርልስ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
ሁለቱ አሜሪካዊያንን ጨምሮ 17 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ቀሪዎቹን ስምንቱን ለመያዝም ፖሊስ እያደነ መሆኑም ተጠቁሟል። በሕይወት ካሉት ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ ዋና መዲናዋ ፓርቶፕሪንስ ውስጥ ከፖሊስ ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ የሞቱ እንዳሉም ታውቋል።
በጥቃቱ ፕሬዚዳንት ጆቨኔል ሞይዝ ሲገደሉ ሚስታቸው ማርቲን ደግሞ ቆስለው ፍሎሪዳ ወደሚገኝ ሆስፒታል ለሕክምና ተወስደው አሁን መልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተሰምቷል። ጥቃቱን ማን እንዳቀደውና ዓላማው ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
ነገር ግን ተጠባባቂው ፕሬዚዳንት ክሎውድ ጆሴፍ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የ53 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ሰለባ የሆኑት “ሥልጣን በጥቂት ሰዎች እጅ መሆኗን” መቃወም በመጀመራቸው ሣይሆን አይቀርም።
ሐሙስ ዕለት ፖሊስ ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል የተወሰኑትን ከእነ ጦር መሣሪያቸውና ፖስፖርታቸው ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርጓል። “የተቀሩትን አራት ሰርጎ ገቦች ለመያዝ ምርመራችንን እንዲሁም የፍለጋ መላችንን እናጠናክራለን” ብለዋል ቻርልስ።
“በጣም የተደራጀ ኮማንዶ ነው። ከስድስት በላይ መኪናዎችና በርካታ ቁሳቁሶች ያለው ነው” ያሉት ደግሞ የሄይቲ ምርጫ ሚኒስትር ማቲያስ ፒዬር ናቸው። ኮሎምቢያ ቢያንስ ስድስቱ የገዳይ ቡድን አባላት ጡረታ የወጡ ወታደሮቼ ሣይሆኑ አይቀሩም ብላለች። ሃገሪቱ ከሄይቲ ጋር ለመተባበር መወሰኗን አስታውቃለች።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በበኩሉ ዜጎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ማጣራት እንዳልቻለ አስታውቋል። መርማሪዎች አሁንም ከጥቃቱ ጀርባ ያሉትን ሰዎች እየፈለጉ ነው።
የፕሬዚዳንቱ ግድያ በአህጉረ አሜሪካ ድህነት የናጣት ሃገር በምትባለው ሄይቲ ተቃውሞ እንዲነሳ አድርጓል። ይህን ተከትሎ የ15 ቀናት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሄይቲ ታውጇል።
ምንም እንኳ የሄይቲ ሕገ-መንግሥት ፕሬዚዳንቱ ከሞቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ይሾማሉ ቢልም ዳኛው በቅርቡ በኮቪድ-19 ምክንያት መሞታቸው ይታወሳል። ከዚህ በኋላ ማሻሻያዎች ተደርገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይምሩ የሚል ሐሳብ መጥቷል። አሪዬል ሄንሪ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቢሾሙም እስካሁን ቃለ መሐላ አልፈፀሙም።
የተባበሩት መንግሥታት ደግሞ ምክትሉ ጆሴፍ በተጠባባቂ ፕሬዚዳንትነታቸው እስከ ምርጫ ድረስ መቆየት አለባቸው ይላል።
11 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሄይቲ 59 በመቶ ሕዝቧ ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖር መረጃዎች ያሳያሉ። የተፈጥሮ አደጋ የማያጣት ሄይቲ በፈረንጆቹ 2010 በተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ 200 ሺህ ዜጎቿን አጥታለች።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2013