ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ በምታገኘው ገቢ እና ለገቢ ንግድ በምታወጣው ወጪ መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት የረጅም ጊዜ ራስ ምታት ሆኖ ቆይቷል። ከለውጡ በፊት በነበሩት አምስት እና ስድስት ዓመታት ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ ከ2 እስከ 3 ቢሊየን ዶላር ነበር። ምርትና አገልግሎቶችን ከውጭ ለማስገባት ግን ከ15 ቢሊየን ዶላር በላይ ስታወጣ ቆይታለች። የንግድ ጉድለቱ ምን ያህል ከፍተኛ እንደነበር ከአሃዞቹ መረዳት ይቻላል።
ሀገሪቱ ወደ ውጭ ሀገራት የምትልካቸው ጥሬ የግብርና ምርቶች መሆናቸው እና ከውጭ ሀገራት የምታስገባቸው ደግሞ የካፒታል ሸቀጦች መሆኑ ከወጪ ንግድ በሚገኘው ገቢ እና ከገቢ ንግድ በሚገኘው ወጪ መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ እንዲሆን ምክንያት ሆኖ መሰንበቱን የምጣኔ ሀብት ሊህቃን ያስረዳሉ። ይህንን አሳሳቢ ሁኔታ ለመቀየር ብዙ ጥረት እየተደረገ እንደነበር ብዙ ቢወራም በተግባር ግን ጠብ የሚል ውጤት አልታየም።
ይሁን እንጂ ከለውጡ ወዲህ ባሉት ሶስት ዓመታት ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እና ለገቢ ንግድ የምታወጣውን ወጪ መጠን ለመቀነስ በተሰሩት ስራዎች ከዓመት ዓመት መሻሻል እየታየ መጥቷል። የሀገሪቱ የወጪ ንግድ በሚፈለገው እና የሚጠበቅበትን ያህል አድጓል ብሎ መናገር ባይቻልም፤ ከዓመታት የቁልቁለት ጉዞ በኋላ የወጪ ንግድ ቀና ማለት ጀምሯል። በ2012 በጀት ዓመት ከስድስት ዓመታት ማሽቆልቆል በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ 3 ቢሊየን ዶላር ማግኘት የቻለች ሲሆን በ2013 በጀት ዓመትም ይሄው መሻሻል ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለህዝብ እንድራሴዎች ምክር ቤት የመንግስታቸውን የ2013 በጀት ዓመት አፈጻጻም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወጪ ንግድ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ኤክስፖርት ገቢ አግኝታለች:: እስካሁን በነበረው ከፍተኛ የኤክስፖርት ውጤት ተገኘበት በሚባል ጊዜ ውስጥ ትልቁ ወደ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የቀረበ ነበር:: አምና ከነበረው ዘንድሮ በ18 በመቶ ማደጉን ያሳያል። በኤክስፖርት ዘርፍ ዘንድሮ የተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ ነው።
ኤክስፖርትን ከማሳደግ ጎን ለጎን ወደሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን እድገት መግታት መቻሉን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጪ ንግድ በበጀት ዓመቱ በ0 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ ማደጉ ጠቁመዋል። በየዓመቱ ከፍተኛ እድገት ያስመዘግብ የነበረውን የገቢ ንግድ እድገት መግታት ትልቅ ስኬት መሆኑን ነው ያብራሩት።
በ2011 በጀት ዓመት በገቢና በወጪ ንግድ መካከል የነበረው ልዩነት 14 ነጥብ 6 በመቶ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በ2012 በጀት ዓመትም በገቢና ወጪ ንግድ መካከል የነበረው ልዩነት የተወሰነ ቅናሽ ማሳየቱን ጠቁመዋል። በ2013 ዓ.ም ደግሞ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ሁኔታ መሻሻል በማሳየት ልዩነቱ ወደ 9 ነጥብ 3 በመቶ መውረዱንም ያብራራሉ ::
በገቢና ወጪ ንግድ መካከል ያለውን የሰፋ ልዩነት ለማጥበብ የተጀመረው ስራ ይበል የሚያሰኝ እና ተጨማሪ ጥረት ቢደረግ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል አመላካች ነው። በየዓመቱ ኤክስፖርት በሁለት አሀዝ እያደገ የኢምፖርት እድገቱን በተወሰነ ደረጃ መግታት ቢቻል በጥቂት ዓመታት ውስጥ በሁለቱ መካከል ያለውን ጉድለት ማጥበብ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው::
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ከአምናው አንጻር ቢታይ የ500 ሚሊየን ጭማሪ አለው። በ2013 በጀት ዓመት በወጪ ንግድ ዘርፍ የታየው መሻሻል በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይም በ2013 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በርካታ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ያስተናገደበት ነው። ሀገሪቱ 75 ከመቶ የሚሆነውን የወጪ ንግድ ገቢ የምታገኝበት የግብርና ዘርፍ አንበጣን፣ ጎርፍን፣ ግጭትን፣ ጦርነትን እንዲሁም ኮሮናን ያስተናገደ ቢሆንም እነዚህን ችግሮችን ተቋቁሞ እድገት ማስመዝገብ ችሏል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በርካታ ሀገራት የተለያዩ እገዳዎችን ጥለው ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት የብዙ ሀገራት ኢኮኖሚ ተዳክሟል። ኢትዮጵያም የተለያዩ እገዳዎችን ጥላ የነበረ ቢሆንም የወጪ ንግድ ጥሩ መሻሻል ማሳየቱ አበረታች ነው።
በማዕድን ዘርፍ፣ በቡና ዘርፍ፣ ሎጂስቲክስ በማሳለጥ እንዲሁም በብሄራዊ ባንክ አካባቢ የነበሩ አሳሪ ህጎችን በማሻሻል ረገድ የተሰሩት ስራዎች የወጪ ንግድ ዘርፍ ላይ ለታየው ስኬት አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በዘንድሮ ዓመት የወጪ ንግድ በ18 በመቶ ሲያድግ ሀገሪቱ ከውጭ ማስገባት የምትፈልጋቸው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም የገቢ ንግድ በ0 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ ስለመምጣቱ አመላካች ነው። ይህ ለረጅም አመታት ተሞክሮ ሳይሳካ የቆየ መሆኑን ያነሳሉ።
እንደ አቶ ዋሲሁን ማብራሪያ፤ በቀጣይ ጊዜያትም ሀገሪቱ የወጪ ንግድን በማሳደግ እና የገቢ ንግድን በመግታት በሁለቱ መካከል ያሉ ልዩነቶችን ለማጥበብ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። ለዚህም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በመጠንና በአይነት ማብዛት እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መጠን መቀነስ አስፈላጊ ነው። ነገ መልሶ ለሚከፍል ለግብርና፣ ለትምህርት፣ ለጤና ዘርፎች አስፈላጊ የሆኑ ወሳኝ ሸቀጦችን ብቻ ከውጭ ሀገራት በማስገባት የቅንጦት እቃዎች እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የጌጣጌጥ ምርቶችን ለመግታት ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግ ምክረ ሀሳብ ያሉትን አጋርተዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2013