ወደ ጆሮ ሲደርስ ልስልስ ብሎ ገብቶ ከራስ ጋር የሚዋሀድ ድምፅ፤ ቢሰሙት የማይጠገብ ለዛ ቅላፄ አቀርቅሬ እየጎረጎርኩት ካለው ስልኬ አባነነኝ። “ሰልፉ የት ነው?” የሚል ድምፅ ስሰማ አንገቴን ቀና አድርጌ የጠያቂውን ማንነት እያየሁ “ፒያሳ” ብዬ ተሰልፌ የምሄድበትን አድራሻ ተናገርኩ። ከኋላዬ ዞራ እስክትቆም በአይኔ ሸኘኋት። ውብ ናት፤ እጅግ የዘነጠች። ቁመናዋ ማራኪ ነው። የወይን ጠጅ ቀለም ያለውና ከውብ ሰውነትዋ ጋር ተጣብቆ እጉልበትዋ ድረስ ወጥ ሆኖ የሚደረሰው ቀሚስዋ ከለበሰው ጫማ ጋር የሚሄድና አይን የሚማርክ አለባበስ ነው።
ረዘም ያለ ሉጫ ፀጉር ራስዋ ላይ ደፍታለች። ጎላ ጎላ ያሉት አይኖችዋ ያሳሳሉ። ምንም አይነት የከንፈር ቀለም ያልደረቡት ክናፍሮቿ ቅርፅና ቅላታቸው ይገርማል። ልቅም ያለች ቆንጆ ናት። ከኋላዬ ቦታ ይዛ እስክትቆም አንገቴ ተጠማዞ ተከተላት። ፊቴን ወደስዋ አዙሬ ላያት ፈለኩ፤ ነገር ግን ሀፍረት ተሰማኝ። አለባበስዋ ደግሞ አንገትን የሚያጣምም እዩኝ እዩኝ የሚል አይነት ነው። አይደለም የኔ ቢጤ ጎረምሳ የሸበተንም አንገት ታስቆለምማለች።
ልቤ ያለወትሮው ድው.. ውድ… ይላል። “እንዴ ምን ነካኝ ኧረ ሳም ተረጋጋ”አልኩት ራሴን፤ በሁኔታዬ ተገረምኩ። ላወራት ፈለኩ ግን ደግሞ ምን ሰበብ ፈጥሬ። በጉጉት ስጠብቀው የነበረው ታክሲ ሳይመጣ እንዲቆይ ተመኘሁ። ምን ብዬ ላናግራት እንደምችል እያሰብኩ “ወንድሜ ታክሲዎች የት ጠፍተው ነው እንዲህ ሰው የበዛው፤ ቶሎ አይመጡም ማለት ነው?” ስትለኝ ከመቅፅበት ወደስዋ ዞሬ አይን አይንዋን እያየሁ አወራት ጀመር።
ከቅድሙ ይበልጥ ውብ ሆነችብኝ። ጀርባዬን ያላበኝ ለካስ በዚህ ውበት ወላፈን ተገርፌ ነው። ታዲያ ምን ይፈረድብኛል። ወሬ እስዋ መጀመርዋን ወደድኩት፤ እንኳን አውርታኝ ቀድሜም በምን ላውራት እያልኩ ነበራ። “ሌላ ጊዜ እንዲህ ቆይተው አያውቁም ዛሬ ጠፉ ምክንያታቸው ግን ምን እንደሆነ እንጃ” ብያት እንደመመለስ ብዬ ከስዋው ጋር መቆየት ፈልጌ ወሬዬን ቀጠልኩ። “ምነው ቸkoለሽ ነው?” አልኳት። ፈገግ ብላ “አዎ ክላስ ከ30 ደቂቃ በኋላ ነው የሚጀመረው፤መድረስ አለብኝ” አለች። በመሀል አንድ ታክሲ መጥቶ ከፊት ለፊታችን የነበሩ 12 ሰዎች ቆጥሮ ጭኖ ሄደ። የተወሰኑ እርምጃዎችን ወደፊት ተጠግተን በድጋሚ ቆምን።
“ኡፍ፤ ሲያናድድ ፤ አሁን ቢመጣ አይደርሰንም ማለት ነው።”ብላ ጥያቄም ምሬትም ያዘለ አረፍተ ነገር አከታትላ በረጅሙ ተነፈሰች። ወሬዬን የምቀጥልበትን ምክንያት ማግኘቴ ደስ እያለኝ በፈገግታ ጥያቄዬን ቀጠልኩ። “አይዞኝ ምን ይደረጋል መታገስ ነው። ደግም አንድ ዙር ብቻ ነው የሚቀረን፤ሁለት ታክሲዎች ተከታትለው ከመጡ ይደርሰናል” አልኳት። ጨዋታችን ቀጠለ።
ታክሲዎቹ ግን የኔ ፀሎት በፈጣሪ ተሰምቶ ወደዚያ ድርሽ እንዳትሉ የተባሉ ይመስል ፈፅሞ ሊመጡ አልቻሉም። ምክንያቱን ስንጠይቅ መስቀል አደባባይ ለሆነ መርሀ ግብር ተፈልጎ በመዘጋቱ ታክሲዎቹ ሌላ አማራጭ ፈልገው በሌላ መንገድ እየተጓዙ እንደሆነ ሰማን።
ጉዳዩን እንደ ሰማን ምን ይሻላል በሚል ስሜት ተያየን። “እስከቻልነው በእግር እንሂድ እንዴ፤ መስቀል አደባባይ ጋ ተሻግረን ቢያንስ አማራጭ አናጣም።” የሚል ሀሳብ ሳቀርብላት ግራ ገብቷት ነበርና አላንገራገረችም። የተገናኘነው ወሎ ሰፈር አደባባዩ ጋ ነው። በእግር ለእንደኛ አይነት የዘመኑ ስስ ሰው ሲታሰብ ይከብዳል፤ ግን ከእስዋ ጋር አብሮነቱ እንዲረዝም ፈልጌ ነበረና አደረኩት። መንገዱን እየሄድን የባጥ የቆጡን አወራን።
በመሀል ምነው .. ምን.. እቱ እስካሁን ስምሽን ደበቅሽ ስላት “ማራኪ እባላለሁ” ብላ እጅዋን ዘረጋችልኝ፤ እውነትም ማራኪ ተፈጥሮ ሳይሰስት ኩሏታል። ደግሞ ቤተሰቦቿ ግፋቸው ለስንት መልከ ጥፉ መጠሪያ ሆኖ መልኩን የሚደግፍ ስም እንዲህ ውብ ለሆነች ልጃቸው ይደርቡባታል። ምነው አለቆ ሌላ ስም ቢሰይሙላት። እንዴ ራስዋም ማራኪ የሆነ ደም ግባት ተችሯት ሳያበቃ ሌላ ማራኪ የሚሉት ስም ማጎናፀፍ ምን ይሉታል።
በማራኪ ብዙ እየተማረኩ ልቤ አስሬ እየደቃ መንገዱን ቀጥያለሁ። አንዳንዴም ከጎኔ ሆና በደንብ ላያት እፈልግና የተዋበው ሞንዳላ ሰውነቷ ለማየት ስላልተመቸኝ ትንሽ ቆም ብዬ አሳልፋትና እከተላታለሁ። “ምነው ደከመህ እንዴ አይዞኝ በርታ” ስትለኝ ደግሞ ፍጥነቴን ጨምሬ እጠጋትና እኩል መራመድ እንጀምራለን። ሁለቴ ሳት ብሎኝ እጄን አንስቼ ላቅፋት ሁሉ ቃጣኝ። ነገር ግን ቀጣዩን ነገር በመፍራት ራሴን ለመቆጣጠር ሞከርኩ። ሀምምም፤ አልገርምም ፤ ምንድነው እንዲህ መጣደፍ። ገና ለገና ፊት ሰጠችኝ ብዬ መንቀዥቀዥ።
በመንገዱ ሁሉ የሚያልፈውን ወንድ ግን ጠላሁት። እንዴት ነው አፍጥጠው የሚያዩዋት። ቅናት ቢጤ አንጨረጨረኝ። ከአጠገባችን የሚያልፈው ሁሉ ከኋላችን ሆኖ ዞር ብሎ ያያታል። እስዋ ለምዳዋላች መሰለኝ ዴንታም አይሰጣት። ብትንሽ ትልቁ ትስቃለች። ጨዋታ አዋቂ መሆንዋን በዚህች አጭር ቆይታዬ ተረዳሁት።
የእኔ ላደርጋት በብዙ ተመኘሁ። ፍቅረኛዬ እንድትሆን በልቤ ብዙ አሰብኩ። ወደፊት ይበልጥ እንዴት እንደምግባባትና የራሴ ለማድረግ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ብዙ አሰብኩ። መሀል ላይ በሀሳብ ትክዝ ስል “ምነው ጥለኸኝ የት እየሄድክ?” ትለኛለች። ይበልጥ ውስጤ ገብታ በእስዋው እየተተራመስኩ እንደሆንኩ አልተረዳችልኝም።
መድረሳችንን ባልወደውም መስቀል አደባባይ ስንደርስ በፌዴራል ፖሊሶች ተፈተሽን። እኔ እየተሽኩ ማራን የሚፈትሿት ሴት ፖሊሶች ላይ አፈጠጥኩ። “ቀስ ብለው አይፈትሿዋትም እንዴ ቆይ ይህቺ የበሰለ ብርቱኳን የመሰለች ልጅ ብትፈርጥባቸውስ” የማስበው ሁሉ ለራሴው ሳቅ ፈጠረብኝ። ፖሊሶቹን አልፈን ተገናኘን። አደባባዩን እንደ ተሻገርን ታክሲ መጠበቂያው ጋ አብረን ቆመን አሁን ታክሲ መጠበቁን ተያያዝን። እኔ ጭራሹኑ የምሄድበትን ጉዳይ ወዲያ ብዬ ከእርስዋ ጋር መቆየት ፈለኩ።
ተንቀሳቃሽ ስልክዋን ከቄንጠኛ ቦርሳዋ ውስጥ አውጥታ ተመለከተች። “አይ የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ አመልጦኛል፤ ለሁለተኛው በደረስኩ” ስትል “አይዞኝ ይደርሳል፤ ምን አልባት ታክሲ አምባሳደር ጋር ማግኘት እንችላለን፤ ወደዚያ እንጠጋ፤ ማኪ” አልኳት። ወይ ጉዴ፤ የኔ ነገር ይኸው ማቆላመጥ ጀመርኩ። አረ ተው ፤ተው፤ ረጋ በል ሳሚ። በድካም ስሜት ተመለከተችኝ። መንገዱ እንዳሰለቻት ገባኝ።
በመሀል አንድ ዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል መጣና አጠገባችን ቆመ። ከውስጥ አንዲት ሴት ወርዳ አመሰግናለሁ መልካም ቀን ብላ በሩን ዘጋችው። መኪናው ግን አልሄደም፤ እዚያው ቆሞ ሲቀር አጮልቄ ሹፌሩን ተመለከትኩት። ሙሉ አይኑ ማራኪ ላይ ነው። አናደደኝና ሄጄ ላንቀው ሁሉ አማረኝ።
“ወይ ጉድ፤ ይች ልጅ ከሰው ጋ አባልታ ልትጨርሰኝ ነው” አልኩ በውስጤ። ፈጣሪ ሆይ ይሄን ሰው ከዚህ አርቅልኝ ብዬ መፀለይ ጀመርኩ። ክላስክ ሲያደርግ ማራኪ ተጠግታው “ወዴት ነው ውንድም ፤ፒያሳ ድረስ…” የልጁ ፊት ሲፈካ ታየኝ። “ችግር የለም ግቢ ግቢ፤ የፈለግሽበት አደርስሻለሁ።”ሲላት ጓደኛዬም አለ። ኦህ ፤ሶሪ፤ አንድ ሰው ነው መጫን ፤ጥቁር አንበሳ ጋ ሌላ የሚብቀኝ ሰው ስላለ።” ብሎ መለሰላት።
ቀና ብላ ስታየኝ ውስጤ በፍራት ቆፈን ተመታ። እንዳትሄድብኝ ሰጋሁ። ያየሁትን ማመን አቃተኝ። ሳሚዬ አመሰግናለሁ ስላካሄድከኝ። ባይ እኔ ስለቸኮልኩ ልሂድ” ብላኝ ወደመኪናው ገባች። መኪናው ተፈተለከ። ታርጋውን እያየሁ ከኋላ መሮጥ አማረኝ። ስረጋጋ ድጋሚ ላገኛት እንኳን እንዳልችል ስልኳን አልተቀበልኳትም። መጀመሪያ በጨዋታዋ ያላበው ሰውነቴ ንፋስ ሲነፍስ ቀዘቀዘኝ። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የራሴ የሆነች ያህል አቅርቤያት የነበረችው ማራኪ ልቤን ማርካው መንገድ ላይ ከትክታው ርቃኝ ሄደች።.. አበቃ
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2013