
በየትኛውም የዓለም ክፍል አካል ጉዳተኞች በርካታ እንቅፋቶች ሲገጥማቸው ይታያል። አካል ጉዳተኞች ከሚገጥማቸው እንቅፋቶች መካከል ምቹ ያልሆኑ የተሽከርካሪ ወንበርና መወጣጫዎች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ ህንፃዎች፣ መፀዳጃ ቤቶችና ሌሎችም በዋናነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ እንቅፋቶች እንዳይገጥሟቸውም ማንኛውም ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲከናወኑ አለም አቀፍ ድንጋጌዎችና ሀገራት ከነዚሁ ድንጋጌዎች የቀዷቸውን ህግጋቶች ያስገድዷቸዋል።
ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹ ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ባደረገ መልኩና አለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ብሎም ሀገራት የሚያወጧቸውን ህጎች ተከትለው መከናወናቸው አጠያያቂ ነው። በእርግጥ አብዛኛዎቹ ያደጉት ሀገራት ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ትኩረት በመስጠት እነሱን ታሳቢ ያደረጉ ግንባታዎችን ያከናውናሉ።
ለአብነትም የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ማእከል የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ወደፈለጉበት ቦታ ለመጓዝ የሚስችላቸውን የካርታ መጠቆሚያ መተግበሪያ ሰርቷል። ከዚህ በተቃራኒ ግን ለማደግ ገና ዳዴ እያሉ ያሉ ሀገራት አለም አቀፍ የግንባታ ድንጋጌዎችን የተቀበሉ ቢሆንም የተቀመጠውን ህግ ተከትለው አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ግንባታዎችን ሲያከናውኑ አይታዩም።
በኢትዮጵያም ህንፃዎችና መንገዶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሆነው እንዲገነቡ የሚያስገድድ ህግ በቅርቡ የወጣ ቢሆንም ህጉን ተከትለው ህንፃዎችንና መንገዶችን የሚገነቡ ጥቂቶች ናቸው። ከህጉ ውጪ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ባላደረገ መልኩ ግንባታዎችን በሚያከናውኑ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃም ጠንካራ አይደለም።
በአዲስ አበባ ከተማ አካል ጉዳተኞች ከሚገጥሟቸው ችግሮች ውስጥ አንዱ ምቹ የመንገድ መሰረተ ልማት አለመኖር ሲሆን በዚሁ ምክንያት በርካታ አካል ጉዳተኞች እንደልብ ለመንቀሳቀስ ሲቸገሩና አለፍ ሲልም ተጨማሪ የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው ይታያል። በተለይ ደግሞ መንገዶች በተለያዩ ምክንያቶች በየጊዜው ስለሚቆፈሩና ከተቆፈሩ በኋላ ወደነበረ ይዞታቸው እንዲመለሱ ስለማይደረግ አካል ጉዳተኞች በነዚህ ጉድጓዶች ውስጥ ገብተው የከፋ የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው ባስ ሲል ደግሞ የሞት አደጋም ጭምር ሲደርስባቸው ይታያል።
ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን እያከናወነ ቢሆንም አሁንም በርካታ ስራዎች እንደሚቀሩ ይነገራል።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሰሎሞን እንደሚሉት፤ የመንገድ ልማት አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ በሚሆን መልኩ መገንባት እንዳለበት ይታወቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣንም በርካታ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። መንገድ ልማቱ አካል ጉዳተኞችንም ጭምር ተደራሽ ማድረግ አለበት ሲባልም ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ምቹና የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚችል የመንገድ ግንባታ እንዲሆን ይጠበቃል።
ከዚህ አንፃር በአዲስ አበባ ከተማ የነበረው አጠቃላይ የመንገድ ግንባታ ሁኔታ ሲታይ አብዛኛዎቹ የመንገድ ግንባታዎች የተከናወኑት በተለያዩ ጊዜያት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል በመንገድ ግንባታ ዘርፍ በከተማዋም ይሁን ከከተማዋ ውጪ ባለው የሀገሪቱ አጠቃላይ የመንገድ ግንባታ አሰራር በዋናነት ተሽከርካሪውን ማእከል ያደረገ የአውራ ጎዳናን ፅንሰ ሃሳብ ብቻ ተከትሎ የሚከናወን ግንባታ የነበረ በመሆኑ ለእግረኞችም ሆነ ለአካል ጉዳተኞች እንቅስቃሴ ምቹ ያልነበረ እንደሆነ ይታወቃል።
ይሁንና አሁን ባለው አጠቃላይ የመንገድ ግንባታ አሰራር ሁኔታ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችንና ሁሉንም የትራፊክ እንቅስቃሴ ባማከለ መንገድ የመንገድ መሰረተ ልማት የማቅረብ ስራ በትኩረት የሚከናወን ሆኗል። ከዚህ አኳያም በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የእግረኛ መንቀሳቀሻ መስመሮች አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በኩል ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ላይም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችና አካል ጉዳተኞችን መሰረት ያደረጉ የመልሶ ግንባታ ስራዎችም ባለፉት አመታት በስፋት ሲከናወኑ ቆይተዋል። በተለይ አይነስውራን ታሳቢ ተደርገው የተሰሩ የእግረኛ መንገዶች የዚህ አንዱ ማሳያ ነው። በተጠናቀቀው በጀት አመትም በተመሳሳይ ወደ 27 ነጥብ 3 ኪሎሜትር ርዝማኔ ያላቸው የእግረኛ መንገድ መልሶ ግንባታ ስራዎች ተከናውነዋል። ከዚሁ ጎን ለጎንም ወደ 16 ኪሎሜትር ርዝማኔ ያላቸውንና በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱ የእግረኛ መንገዶችን መልሶ በመጠገን ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎችና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ ተደርጓል።
በሌላ በኩል ደግሞ በያዝነው አመት ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆኑትና ወደ 24 የሚደርሱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች፤ ወደ 37 ኪሎሜትር በላይ ርቀት ከሚሸፍኑ የአስፓልት መንገዶች ጎን ለጎን አዳዲስ የእግረኛ መንገዶችንም ጥራት ባለው መልኩ ለመስራት ጥረት ተደርጓል።
አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ ከማድረግ አንፃርም በእግረኛ መስመሮች ላይ በተለይ ማየት የተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ስለሚጠቀሙ አይነስውራኑ በሚመሩበት በትር በቀላሉ መስመሩን እየተከተሉ መሄድ የሚችሉባቸው ሁኔታዎችን ለመፍጠር የአካል ጉዳተኞች መንቀሳቀሻ ራሱን የቻለ ታይልስ እንዲነጠፍ ተደርጓል። ከዚህ ውጪ በተሽከርካሪ ወንበር ለሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኞችም ራምፖችን የመስራት ሁኔታዎች አሉ። እነዚህ ስራዎች ሲሰሩ ታዲያ ሁሉም ነገር የተሟላና ለሁሉም የአካል ጉዳተኞች ምቹ ነው ማለት አይቻልም። በዚሁ ልክ የሚጎሉ ነገሮች እንዳሉም ታሳቢ ይደረጋል። በመንገድ ግንባታዎች ሂደት ያሉትን ክፍተቶች በየጊዜው በማረም አካል ጉዳተኞችን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ በባለስልጣኑ በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በከተማዋ ቀደም ሲል የነበሩ አብዛኛዎቹ መንገዶች ለተሽከርካሪዎች ብቻ የተሰሩ እንጂ እግረኞችንና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው የተገነቡ አይደሉም። በዚሁ ምክንያት በአጠቃላይ አካል ጉዳተኞች ብቻ ሳይሆኑ እግረኞችም ጭምር ሲቸገሩ ቆይተዋል። በመሆኑም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በስፋት እየተከናወነ ባለው የእግረኛ መንገድ መልሶ ግንባታ ስራ በርካታ የከተማዋ ቦታዎች ላይ በተለይ ደግሞ በማዕከላዊ የከተማዋ ክፍል የሚገኙ መንገዶች አብዛኛዎቹ ለእግረኞችና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎች በመሰራት ላይ ነው።
ነባር መንገዶችን ደረጃቸውን የማሻሻል፣ የማስፋትና ለእግረኞችና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የማድረግ ስራዎች ተከናውነዋል። ከችግሩ አንፃር በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ያለመና በዛ አቅጣጫ እየተመራ ቢሆንም በአንፃሩ በመልሶ ግንባታም ሆነ በአዳዲስ ግንባታ ባለስልጣኑ የእግረኛ መንገድ እየገነባቸው ባሉ ቦታዎች ላይ በተለያየ መንገድ መንገዱ ጉዳት እየደረሰበት ይገኛል። በተለያዩ አካባቢዎች በእግረኛ መንገዶች ላይ የሚከማቹ የግንባታ ቁሳቁሶችና የግንባታ ተረፈ ምርቶች፣ የጎዳና ላይ ንግድ … አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ በእግረኞች እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ጫናና ችግር ፈጥሯል።
ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የተገነቡ የእግረኛ መንገዶች በተለያዩ ምክንያቶች በቀላሉ ለብልሽት እንዲጋለጡ ሆነዋል። ከዚህ ጉዳት ባለፈ የእግረኛ መንገዱ የውሃ መውረጃም የሚሰራበት በመሆኑ ቦታው ላይ የሚቀመጡ የግንባታ ቁሳቁሶችና ተረፈ ምርቶች ወደ ድሪኔጅ ሲስተም ውስጥ በመግባትና በመድፈን ለአስፓልት መበላሸትም የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። በዚህ ሒደት ውስጥ ሁሉ ታዲያ ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል በበለጠ አካል ጉዳተኞች ተጎጂ ይሆናሉ።
በባለስልጣኑ በኩል የሚከደኑና የድሪኔጅ ሲስተሙን ፅዳት ለማከናወን እንዲሆኑ ተደርገው የሚዘጋጁ የድሪኔጅ መገጣጠሚያ ቦታዎች ላይ የተቀመጡ ክዳኖች የሚሰሩት ከኮንክሪትና ብረት ስለሆነ ለብረት ስርቆት ሲባል የድሪኔጅ መስመሮችን ክዳን ግለሰቦች የመስበርና የማውደም ሁኔታዎች በስፋት ይታያል። ይህም የህብረተሰቡን የጋራ መጠቀሚያ ሀብት ከማውደም ባሻገር አካል ጉዳተኞችም ሆኑ እግረኞው ለከፋ አደጋ እንዲጋለጡ ያደርጋል። ይሄ መጥፎ ልማድና ሊታረም የሚገባ ጉዳይ ሲሉ ያሳስባሉ።
በዚህ ሂደት ውስጥ ከሚጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ቀዳሚዎች አካል ጉዳተኞች በተለይ ደግሞ ማየት የተሳናቸውና በቀላሉ ራሳቸውን ማዳን የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። እንዲህ አይነት ያልተገቡ ነገሮችም መታረም አለባቸው።
በባለስልጣኑ በኩል በበጀት አመቱ የእግረኞችን እንቅስቃሴ ምቹ ለማድረግ እየተሰሩ ካሉ ተግባራት ጎን ለጎን የማኑዋል ክዳኖችንም በስፋት መልሰው እንዲመረቱ በማድረግ የተበላሹ ቦታዎችን መልሶ የማስተካከል ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ይሁንና ችግሩ አዳዲስ ተገንብተው በተመረቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች አካባቢዎችም ጭምር ያጋጠመ በመሆኑ ችግሩን ከመፍታት አንፃር የሚመለከታቸው የፀጥታና የአስተዳደር አካላት እንዲሁም የልማቱ ዋነኛ ባለቤት የሆነው የህብረተሰብ ክፍል ትልቅ ድጋፍና ትብብር ማድረግ ይጠበቅበታል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ሀገሪቱ አሁን ባለችበት የኢኮኖሚ ደረጃ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ፍላጎት ሰፊ ክፍተት አለ። ከዚህ አኳያም በጊዜ ሂደት የሚመለሱ ነገሮች ይኖራሉ። ለአብነትም የከተማዋን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለማዘመን በተለይ ደግሞ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሳደግ ከመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ጋር በተያያዘ የቢ አር ቲ ኮሪደሮችን ማስፋት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ይህ ግንባታ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችንም ጭምር አካቶ የሚገነባና አካል ጉዳተኞችንም ጭምር ታሳቢ ያደረገ ነው። በመሆኑም ፍላጎቱ ሰፊና ብዙ ስራዎችን መስራት የሚጠይቅ ቢሆንም ያለው የሀብት ውስንነትና እስካሁን ያልተገፉ ስራዎችን በቀጣይ በጥናት ላይ በመመስረት በባለስልጣኑ በኩል የሚከናወኑ ይሆናል።
በከተማዋ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተገነባ ባለው የቢ አር ቲ ኮሪደር ላይ ከሚገነቡ ነገሮች አንዱ ለብዙሃን ትራንስፖርት ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች መረጃዎችን በየፌርማታዎቹ የሚያገኙባቸው ቴክኖሎጂዎችም አብረው ይገነባሉ። ይህም አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2013