ጉዳት ማለት በሰው ጥቅም ወይም ሀብት ላይ የሚደርስ ጉድለት ወይም ኪሳራ ነው ( የአካል ጉዳትንም ጨምሮ)፡፡ በውል ሕግ ላይ ማብራሪያ የፃፉት ፕሮፌሰር ጆርጅ ቺቺኖብችም ጉዳት በሰው ጥቅም ላይ የሚደርስ ኪሳራ ነው የሚል ትርጉም ሰጥተውታል፡፡ ይህም የገንዘብ ወይም የኅሊና ጥቅምን የሚነካ ወይም የሚያጎድል ሊሆን ይችላል፡፡ የገንዘብ ጉዳት የተጎጂውን ኪስ ያራቁታል፡፡ የኅሊና ጉዳት ደግሞ የተጎጂውን ስሜት ይነካል፡፡ በተጎጂው ላይ የደረሰው ጉዳት ሀብቱን ያሳጣው ወይም ገቢው እንዳይጨምርና ሀብቱ እንዳያድግ ያገደው ሊሆን ይችላል፡፡
ይህ ጉዳት አሁኑኑ የደረሰ ወይም ገና ወደፊት የሚደርስ ጉዳት ሊሆን ይችላል፡፡ ለአብነት ተጎጂው በሬው ሞቶበት ወይም ቤቱ ተቃጥሎበት ወይም የሚነግድበት አውቶብስ ከጥቅም ውጭ ሆኖበት ወይም ቋሚ የአካል ጉዳት ደርሶበት ሊሆን ይችላል፡፡ ባለቤቱ እነዚህን ንብረቶቹን እያከራየ ገቢ ያገኝባቸው ከነበረ የንብረቶቹ ዋጋ ተከፍሎት የማከራየቱን ስራ እስኪጀምር ድረስ በየቀኑ ወይም በየወሩ ኪሳራ ይደርስበታል፡፡
ጉዳቱ የአካል ጉዳት ከሆነም ሥራ እየሰራ ያገኝ የነበረው ገቢ ሊቋረጥበት ይችላል፡፡ ይህ ጉዳት የመስራት አቅሙ እስከሚደክም (እስኪሟጠጥ) ድረስ ላለው ዘመን ሁሉ የሚቀጥል ነው፡፡ ወደፊት የሚደርስ ጉዳት የምንለው እንዲህ ዓይነቱን ጉዳት ሲሆን ጉዳቱ እንደሚደርስ እርግጠኛ ከሆነ፣ ጉዳቱ እስኪደርስ መጠበቅ ሳያስፈልግ አስቀድሞ ካሳው እንዲከፈል ማድረግ ይቻላል፡፡
የጉዳት መነሻዎችና ምንጮች
በውል ግንኙነት የመብት ወይም የግዴታ ምንጭ የሰዎች ስምምነት ሲሆን፤ ከውል ውጭ ለሚደርስ ኃላፊነት ደግሞ የግዴታው ምንጭ ሕግ ነው፡፡ በውል የጉዳት መነሻ የሚሆነው የውሉ አለመፈፀምና የውል መፍረስ ሲሆን፤ ውል ባለመፈፀም ስለ ሚደርስ ጉዳት በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1790፣ ስለ ውል መፍረስ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1697 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ውል ባለመፈፀሙ እና ውል ሲፈርስ የደረሰው ጉዳት ኪሳራ መጠየቅ የሚቻል ሲሆን፤ ኪሳራውና ልኩ በፍትሐብሔር ሕግ ከውል ውጪ ስለሚደረስ ኃላፊነት በሚለው ምዕራፍ በተፃፉት ድንጋጌዎች መሰረት ይወሰናል በማለት በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1790 ንዑስ ቁጥር 2 ስር ተደንግጓል፡፡
ሌላው ከውል ውጭ የሚደርስ ጉዳት ኃላፊነት ምንጮች በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2027 ስር እንደተዘረዘረው ሶስት ዓይነት የጉዳት ምንጮች (የጉዳት መነሻ ነገሮች) ያሉ ሲሆን እነርሱም በራስ ጥፋት በሌላሰው ጥቅም ወይም መብት ላይ ጉዳት ማድረስ፣ ጥፋት ሳይኖር የሚደረስ ጉዳት ኃላፊነት ሲኖር እና ሌላ ሰው ስለሚያደርሰው ጉዳት ኃላፊነትን መውሰድ የሚመለከት ነው፡፡
በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ስር የሥራ ስንብት፣ ያለ ማስጠንቀቂያ ሥራ ማስለቀቅና መልቀቅ (ከሕግ ውጪ የሆነ የስራውል ማቋረጥ) እና በሥራ ላይ የሚደረስ የአካል ጉዳት መነሻዎችና ምንጮች ሲሆኑ የጉዳት ካሳ (ክፍያ) የሚከፈልባቸው ናቸው፡፡
የጉዳት ዓይነቶች
በፍትሐብሔር ሕግ ውስጥ ጉዳት ግልጽ የሆኑ ጉዳቶች እና የኅሊና ጉዳት በመባል በሁለት ተከፍሎ እናገኛለን፡፡ ግልጽ የሆኑ የጉዳት አይነቶችን ስንመለከት ጉዳት የደረሰበት ወገን በንብረቱ አልያም የገንዘብ ጥቅሙ በቀጥታ የሚነካ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በሀብትና ንብረቱ ላይ ጉዳት ከደረሰ ይኸው ሀብትና ንብረት በገንዘብ ተተምኖ ወይም ተመሳሳይ ንብረት በመመለስ ይካሳል፡፡ አንድ ሰው በደረሰበት የአካል ጉዳት ምክንያት የደረሰውን ጉዳት ወደነበረበት ለመመለስ አልያም ለማገገም የተለያዩ ለሕክምና የሚወጡ ወጪዎች ይኖራሉ (የአልጋ፣ የመድኃኒት፣ የአልሚ ምግብ እና የትራንስፖርት)፡፡ ከዚህ አንጻር ግልጽ የሆኑ ጉዳቶች በሁለት የሚከፈሉ ሲሆን እነርሱም የደረሱ ጉዳቶችና ወደፊት የሚደርስ ጉዳት በመባል ይከፈላሉ፡፡
የደረሱ ጉዳቶች ማለት ጉዳት በመድረሱ በተጎጂው ላይ በእርግጠኝነት የደረሰውን የገንዘብ ኪሳራ ለማመልከት ነው፡፡ ለአብነትም አንድ የአካል ጉዳት የደረሰበት ሰው ለሕክምና ያወጣው ወጪ እንዲሁም የንብረት ጉዳት የደረሰበት ሰው በጉዳቱ ምክንያት የንብረቱ ዋጋ መቀነስ ወይም ሙሉ ለሙሉ ዋጋ ማጣት ጉዳት ሊሆን ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ወደፊት የሚደርስ ጉዳት ማለት በጉዳት ምክንያት ተጎጂው ለወደፊቱ የሚያወጣው ወጪን የሚመለከት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሾፌር በደረሰበት ጉዳት ሳቢያ ሽባ ከሆነ እንደቀድሞው ሰርቶ ገቢ የማግኘት ዕድል የለውም ሊባል ይችላል፡፡ ስለሆነም ከጉዳቱ በፊት ያገኝ የነበረውን ገቢ ለወደፊቱ ያጣ ስለሚሆን ወደፊት የሚደርስ ግልፅ ጉዳት ደርሶበታል ይባላል፡፡
በአጠቃላይ ግልፅ የሆኑ ጉዳቶች (የደረሰ እና ለወደፊት የሚደርስ ጉዳት) ካሳ ሊያስከፍሉ የሚችሉ በእርግጠኝነት የሚታዩ ሲሆን ብቻ ነው ( የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2102(2) እና 2092)፡፡ እነዚህ ጉዳቶች መኖራቸው የሚረጋገጠው በማስረጃ ሲሆን በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2041 መሰረት ተጎጂው ሕጋዊ ማስረጃን በማቅረብ የደረሰበትንና ለወደፊቱ የሚደርስበትን ጉዳት ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ተከሳሹ ጉዳቱን በግልጽ ባያስተባብልም እንዳመነ ተቆጥሮ ማስረጃ ያልቀረበበት ጉዳት ካሳ ሊወሰንለት ስለ ማይችል ከሳሹ ጉዳቱን እና የጉዳት መጠኑን የሚያሳይ ማስረጃ አቅርቦ ማረጋገጥ አለበት (የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 83 ላይ በግልጽ ተቀምጧል)፡፡
ሁለተኛው የጉዳት ዓይነት የኅሊና ጉዳት ሲሆን ይህ ጉዳት የተጎጂውን የገንዘብ አቅም ወይም ኪሱን የሚጎዳ ሳይሆን ሊጎዳ የሚችለው ስሜቱን ነው፡፡ ተጎጂው የደረሰበትን ጥልቅ የስሜት መጎዳት ፣ሀዘንና ሀፍረት መሰረት በማድረግ እንደ ጉዳቱ ዓይነትና ባህሪ ደረጃ የኅሊና ጉዳት ካሳ ሊከፈል ይችላል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ባለው የኅሊና ጉዳት ካሳ በምንም ቢሆን ከአንድ ሺህ ብር እንደማይበልጥ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2116 (2) ይገልፃል፡፡
በሌላ በኩል ግን በቅጅና ተዘማጅ መብቶች አዋጅ ቁጥር 410/96 አንቀጽ 34(4) መሰረት የተለያዩ ጽሁፎች፣ሙዚቃዎች እና ፊልሞች በሌላ አካል ከተሰረቀባቸው የተሰረቀባቸው ዘፋኞች ወይም ደራስያን ከደረሰው ጉዳት ጋር በማመዛዘን የሞራል (የኅሊና) ጉዳት ካሳው ከ100 ሺህ ብር የማያንስ እንደሚሆን ተደንግጓል። ይህም በዚህ ዘርፍ ሊደርስ የሚችለውን የኅሊና ጉዳት ካሳ ከሌሎች የኅሊና ጉዳቶች ካሳ በልዩ ሁኔታ የተቀመጠ መሆኑን ያሳያል፡፡
ሦስተኛው የአካል ጉዳት ሲሆን በተጎጂው ላይ የሚደርሰው የአካል ጉዳት በገንዘብና በኅሊና ከሚደርሱ ጉዳቶች ሁሉ የከፋና የጉዳት ካሳውንም ለማስላት አስቸጋሪ ሲሆን የኅሊና ጉዳትንም ከገንዘብ በበለጠ መልኩ የሚያደርስ ነው፡፡ ጊዚያዊ፣ ዘላቂ ከፊል እና ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት አይነቶች ያሉ ሲሆን ጊዚያዊ የአካል ጉዳት ጊዚያዊ የሆነ ሕመምና ስቃይ ቢያስከትልም እንኳ ቁስሉ የሚድንና ስብራቱም ከትንሽ ጊዜ በኋላ የሚጠገን በመሆኑ ሥራን እንደወትሮው ሁሉ ለማከናወን የሚስችል ነው፡፡
ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት ደግሞ ሥራን እንደ ድሮው አቀላጥፎ ለመስራትና እንደልብ ለመስራት የማያስችል ቢሆንም ቅሉ ቀለል ያሉ ሥራዎችን ከመስራት አይከለክልም፡፡ በአንጻሩ ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ጉዳቱ የደረሰበትን ሠራተኛ የመስራት ችሎታ የሚቀንስ፣ የማይድን ጉዳት ማለት ነው፡፡ ይህ ከሁለም የጉዳት ዓይነቶች ከባዱ ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውንም ዓይነት ሥራ ለመሥራት አያስችልም፡፡ ይህ ዓይነት ጉዳት የደረሰበት ሰው ዕድሜ ልኩን የግል ህይወቱን ለመምራት ስለማይችል የሌሎች ሰዎች እርዳታ ያስፈልገዋል፡፡
በአጠቃላይ አንድ ሰው ሙሉ የአካል ጉዳት ደረሰበት ሲባል ግለሰቡ በጊዜያዊነትም ሆነ በዘላቂነት ለዕለት ኑሮው ማድረግ የሚገባውን እንደወትሮው ለማከናወን፣ ተደስቶና በተፈጥሮ በመጠኑም ቢሆን እረክቶ ለመኖር ይቸገራል፡፡ ውድ አንባቢዎቻችን በቀጣይ ሳምንት ደግሞ የጉዳት ካሳ አይነቶችንና ከዚሁ ጋር ተያያዠ የሆኑ የህግ ፍሬ ነገሮችን ይዘንላችሁ የምንቀርብ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2013