
ምዕራብ አውሮፓዊቷ ሀገር ፈረንሳይ ግዙፍ ኢኮኖሚ ከገነቡ አስር የዓለማችን ሀገራት ውስጥ አንዷ ናት። ከጀርመንና ከእንግሊዝ ቀጥሎ ትልቁ ኢኮኖሚም የእርሷ እንደሆነ ይነገራል። ልክ እንደ ብዙሃኑ የአለማችን ሀገራት ሁሉ የእርሷም ምጣኔ ሃብታዊ እድገት በኮቪድ-19 ክፉኛ ተፈትኗል። ሀገሪቱ በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት በርከታ ዜጎቿንም ተነጥቃለች።
የኮሮና ክትባት ከመጣ ወዲህ በርካታ ዜጎቿን የከተበቸው ፈረንሳይ ቫይረሱ መልኩን በመቀያየር እየተሰራጨ መሆኑን ተከትሎ አሁንም ወረርሽኙ ስጋት ከደቀነባቸው ሃገራት መካከል አንዷ ሆናለች። ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ታዲያ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት በፍጥነት እንደሚያገግም ሲ ኤን ቢ ሲ ኒውስ ከትናት በስትያ በድረ ገፁ አስፍሯል።
ቫይረሱ በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ መምጣቱን ተከትሎ ፈረንሳይ አሁንም በወረርሽኙ ስጋት ውስጥ የምትገኝ መሆኗን የጠቀሰው ሲ ኤን ቢ ሲ ኒውስ፤ የመንግስት ሀላፊዎችና የቢዝነስ መሪዎች በመጪው ግዜ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በፍጥነት እንደሚያገግምና የፈረንሳይን መፃኢ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ሊያመላክት የሚችል መሆኑ አትቷል። ይሁንና በዚህ ሂደት ሀገሪቱ ከወዲሁ ቀሪ የቤት ስራዎችና ችግሮች እንዳሉባት አያይዞ ጠቁሟል።
‹‹የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ማገገም በጣም ፈጠንና እንደውም ከአምናው አመት በበለጠ የፈጠነ መሆኑንና በዚህም ደስተኛ ነን›› ሲሉ በፈረንሳይ ትሬዠሪ ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሞያ የሆኑት ቤኒሲዬ ኬሪ የብሄራዊ ስታትስክስ ቢሮ የፈረንሳይን የ2021 እድገት 6 ከመቶ እንደሚሆን ያወጣውን ትንበያ ጠቀሰው ለሲ ኤን ቢ ሲ መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል።
ቤኒሲዬ ኬሪ ‹‹ስለውድቀቱ ስለምናስብ የሃገሪቱ የ2021 ይፋዊ ትንበያ አሁንም 5 ከመቶ ነው›› ያሉ ሲሆን ልውጥ የኮሮና ቫይረስ በሀገሪቱ መኖሩ አንዳንድ ገደቦች እስከ አመቱ ፍፃሜ ድረስ እንዲቆዩ ተደርገዋል ሲሉ መናገራቸውንም አስታውቋል። እስካሁን ድረስ ይህን ትንበያ አልቀየርንም፤ በመሆኑም የ2022ን በጀት መገንባት ሲኖርብን የሚፈጠረውን እናያለን›› ሲሉ ኢኮኖሚስቱ መደመጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ከ 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውንና ወረርሽኙ በፈረንሣይ ብዙ ጥፋቶችን ማስከተሉን ፤ እስከዛሬ ድረስም ከ111 ሺ በላይ ሰዎችን መግደሉን ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የተገኘውን መረጃ ዋቢ በማድረግ ዘገባው አያይዞ አብራርቷል።
እንደ ሌሎች ሀገሮች ሁሉ ፈረንሣይ በወረርሽኙ ወቅት ኢኮኖሚን ፣ ንግዶችን እና ሥራን ለመደገፍ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን አስተዋውቃለች እናም አሁን ቀደም ሲል ሲደረግ የነበረው ድጋፉ መገባደድ የስራ ማጣት ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉና አንዳንድ ድርጅቶችም በዚሁ ድጋፍ መቋረጥ ምክንያት ሊዘጉ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው የምጣኔ ሃብት ባለሞያው መናገራቸውን በዘገባው ተመላክቷል።
መንግስት “ስለዚህ ጉዳይ በጣም ጠንቃቃ” ነው ሲሉ መናገራቸውንና በአሁኑ ወቅት የስራ ገበያው ግን ጠንካራ ስለመሆኑ መናገራቸውንም ተጠቁሟል። ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ የፈረንሳይ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያገገመ ነው ሲሉ ዋና የምጣኔ ሃብት ባለሙያው መናገራቸውንም ዘገባው ጠቅሷል።
‹‹በበጋው ወቅት ድጋፉ ቀስ በቀስ የእቀነሰ መጥቷል። ከዚህ አኳያ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ መቅረፅ ያስፍልጋል። አሁንም ተጨማሪ ድጋፎች ያስፈልጋሉ። ለአብነትም የረጅም ጊዜ የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ አዲስ መርሀግብር መዘርጋት ያስፈልጋል ሲሉም ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቤኒሲዬ ኬሪ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል።
ይሁንና በአንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ ቀድሞውኑ ከነበረው የችግር ቀውስ በላይ መሆኑንና አንዳንድ እንደ ቱሪዝም ያሉ ዘርፎችም ወደ ኋላ መቅረታቸውን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አስምረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ እኩል ያልሆነ የኢኮኖሚ ማገገም እንዲኖር ከሚያደርጉ ችግሮች መካከል የፈረንሳይ የእዳ ክምር ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማደጉ መሆኑንም ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ማስታወቃቸውን ዘገባው ጠቁሟል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የፈረንሣይ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ጽሕፈት ቤት ባወጣው ሪፖርት መሰረት የመንግሥት ዕዳ ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት መጠን በ2019 ከነበረበት 97 ነጥብ 6 ከመቶ እ.ኤ.አ. በ 2020 መጨረሻ በ 115 ነጥብ 7 ከመቶ ላይ ደርሶ እንደነበርም በመረጃው ለትውስታ መቀመጡንም ዘገባው ገልጿል።
ፈረንሳይ ያለባትን የብድር እዳ እንዴት እንደምትከፍል ለአሁኑ አጠራጣሪ ቢሆንም ከፕሬዚዳንታዊ ምርጫው አስር ወር አስቀድሞ ግብርን ከፍ ለማድረግ በኢማኑኤል ማክሮን መንግስት በኩል ተስፋ እንዳለ በዘገባው መቋጫ የተቀመጠ ሲሆን ኢማኑኤል ማክሮን የፈረንሳይን የጡረታ ስርዓት ለማሻሻል የሚያደርጉት ጥረት ቢኖርም በዚሁ ተለዋዋጭ የኮቪድ ወረርሽኝ ሁኔታ ምክንያት የስራው ውጤታማነት አጠራጣሪ ስለመሆኑም ተነግሯል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2013