ክፍል ሁለት
ባለፈው ሳምንት በቤተሰብ አምድ እትማችን በኢትዮጵያ ያለው የጋብቻና ፍቺ ህጋዊ አካሄድና ውጤቶቹ እንዴት ይታያሉ ስንል በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር የሆኑትን የህግ ባለሙያውን አቶ እንዳልካቸው ወርቁን አነጋግረን የመጀመሪያውን ክፍል ይዘን ቀርበናል። ለዛሬም ከባለሙያው ጋር የነበረንን ሁለተኛ ክፍል እነሆ።
1. የጋብቻ ውል
ከላይ እንደተገለጸው የተወሰኑ የጋብቻ ውጤቶች በውል ሊቀር ወይም ሊሻሻል ይችላል። ይህ ውል የጋብቻ ውል ተብሎ ይጠራል። ከተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 42(1) እና (2) እንደምንረዳው የጋብቻ ውል ተጋቢዎቹ የንብረት ግንኙነታቸውን እና አልፎ አልፎም ግላዊ ግንኙነታቸውን አስመልክተው የሚፈራረሙት ውል ነው።
ይህ የጋብቻ ውል 1ኛ አስገዳጅ የሕግ ድንጋጌዎችን ሊቃረን አይገባውም። ይህ ሆኖ ከተገኘ ውሉ ፈራሽ ነው። 2ኛ ይህ ውል መፈጸም ያለበት ጋብቻው ከመፈፀሙ በፊት ወይም ጋብቻው በሚፈጸምበት ዕለት ነው። 3ኛ ይህ ውል በጽሑፍ ሆኖ አራት ምስክሮች ሁለቱ ከባል ወገን ሁለቱ ደግሞ ከሚስት ወገን መሆን አለበት። 4ኛ የውሉ ቅጅ በፍ/ቤት ወይም በክብር መዝገብ ሹም ዘንድ ሊቀመጥ ይገባል። 5ኛ ይህ ውል በሌሎች ሶስተኛ ወገኖች ግዴታ የሚያስከትል ስምምነቶችን ማድረግ አይችሉም። እንዲሁም ተጋቢዎቹ የጋብቻ ውሉንም በጥቅሉ በአንድ ሀይማኖት ወይም ባህል ወይም ሀገር ሕግ በመጥቀስ ብቻ ተስማምተናል ማለት አይችሉም። 6ኛ ተጋቢዎች የጋብቻ ውላቸውን ለማሻሻል ወይም በጋብቻ ውስጥ እያሉ አዲስ ውል ቢፈራረሙ እንዲህ ዓይነቱን ማሻሻያ ወይም አዲሱን ውል ፍ/ቤት ቀርቦ መጽደቅና ተቀባይነት ማግኘት አለበት።
እነዚህ ከላይ የሰፈሩት ስድስቱ ነጥቦች የጋብቻ ውል በተጋቢዎች ሲፈጸሙ መሞላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሞሉ የጋብቻ ውል ፈራሽ ይሆናል ወይም ውሉ እንዳልተደረገ ይቆጠራል። ነገር ግን በ4ኛ ደረጃ ላይ የተገለጸው የውሉ ቅጅ በፍ/ቤት ወይም በክብር መዝገብ ሹም ጋር ሊቀመጥ ይገባል የሚለው ላይ ሁለት የተለያዩ ሀሳቦች አሉ። አንደኛው ሃሳብ ይህ ውል በተጠቀሱት ተቋማት ዘንድ እንዲቀመጥ ሕጉ በግልጽ የደነገገ ስለሆነ ይህ ተደርጎ ባይገኝ ውሉ ሕጋዊ ውጤት አይኖረውም የሚል ነው።
ሁለተኛው ሀሳብ ደግሞ ይህ ውል በተጠቀሱት ተቋማት ዘንድ እንዲቀመጥ ያስፈለገበት ምክንያት ለጥንቃቄና ለሶስተኛ ወገኖች ጥቅም ተብሎ በመሆኑ ሦስተኛ ወገኖች ላይ ውጤት እንዳይኖረው በማድረግ በተጋቢዎቹ ላይ ግን ሕጋዊ ውጤቱ እንዳለ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል የሚል ነው። በዚህ ነጥብ ላይ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አቋም የሁለተኛው ሀሳብ ነው።
ምክንያቱም በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 45 ላይ የውሉ ሰነድ ስለሚቀመጥበት ቦታ ሲገልጽ የሚቀመጥበትን ቦታ ከመግለጽ ውጭ ይህ ሆኖ ባይገኝ የውሉን ውጤት ሳይገልጽ ነው ያለፈው። ነገር ግን ስለ ውሉ ፎርም እና ውሉን ለመዋዋል ስላለው የነጻነት ወሰን በአንቀጽ 44 እና 46 ላይ ሲገለጽ በሕጉ አባባል መሠረት ውሉ በጽሁፍ ካልሆነ እና ተጋቢዎች በውላቸው ውስጥ ለሌላ ሶስተኛ ወገኖች ላይ ግዴታ የሚያስከትል ስምምነት ቢፈጽሙ ውሉ ውጤት አይኖረውም በማለት ይገልጻሉ። በአንቀጽ 45 ላይ ግን ይህን አላደረገም። ውሉ በተጠቀሱት ተቋማት ዘንድ መቀመጣቸው ግዴታ ማድረግ ቢፈልግ ኖሮ ሕጉ በግልጽ እንደ ሌሎች ሁሉ በግልጽ ያስቀምጥ ነበር። በመሆኑም የሁለተኛው ሀሳብ ሚዛን የሚደፋ ነው።
በሕጉ እምነት ተጋቢዎች የጋብቻቸውን ውጤት በውል ከወሰኑና የጋብቻ ውሉም አስገዳጅ የሕግ ድንጋጌዎችን ያልተቃረን ከሆነ የጋብቻ ውሉ የግልም ሆነ የንብረት ግንኙነታቸውን እንዲገዛ ይደረጋል። ነገር ግን በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተነስተን ስንመለከት አብዛኛውን ጊዜ ተጋቢዎች የጋብቻቸውን ውጤት በውል አይወስኑትም። በጥቂት ሁኔታዎች እንኳን ውል ሲዋዋሉ ውሉ በሕጉ የሚፈለገውን መመዘኛ አሟልተው የሚፈጽሙት እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው። በመሆኑም ውሉ ውጤት አይኖረውም። እንደነዚህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር ደግሞ ይህን ክፍተት የመድፈን ሀላፊነት የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ነው። በዚህም የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ የተጋቢዎችን ግላዊ እና ንብረት ነክ ግንኙነቶች የጋብቻ ውል በሌለበት ወይም ውሉ በሕግ ፊት ውጤት አልባ በሆነ ጊዜ የሚመራበትን የሕግ ድንጋጌ አስቀምጧል።
2. ጋብቻ ግላዊ ግንኙነት ላይ ስለሚኖረው ውጤት
ጋብቻ ተጋቢዎቹ በማህበረሰቡ ውስጥ በፊት ከነበራቸው ማህበረሰባዊ ቦታ ማለትም ለአቅም አዳም እና ሄዋን ደርሰው ከነበሩበት ወንደላጤነት እና ሴተላጤነት ወደ ሌላኛው ማህበረሰባዊ ቦታ አባወራ እና እማወራ የሚቀየሩበት እና የማህበረሰብ መሠረት የሆነውን ቤተሰብ የሚመሰርቱበት ነው። ይህ የሚመሰረተው ጋብቻ ተጋቢዎቹ በፊት ከነበራቸው ግላዊ ህይወት ወደ ጋራ የሆነ ህይወት የሚያዘዋውራቸው ነው። በዚህ የጋራ የሆነ ህይወት ውስጥ ግላዊ ግንኙነታቸው ዘላቂ እና የተረጋጋ እንዲሆን ይጠበቃል። ይህም ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው መከባበር፣ መተጋገዝና መደጋገፍ አለባቸው። ይህ የመተጋገዝ፣ የመከባበር እና የመረዳዳት ግዴታ በምንም ሁኔታ ተጋቢዎቹ ሊያስቀሩት የማይችሉት ግዴታቸው ነው። (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 49)።
ተጋቢዎቹ ቤታቸው በፍቅር የደረጀ፣ መከባበር፣ መተሳሰብ እና መተጋገዝ የሰፈነበት እንዲሆን ባል እና ሚስት ቤትን በማስተዳደር እኩል የሆነ ሚና ሊኖራቸው ይገባል። በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 34(1) ላይ “ተጋቢዎች በጋብቻ አፈፃፀም፣ በጋብቻው ዘመንና በፍቺ ጊዜ እኩል መብት አላቸው” ይላል።
ይህ የሀገራችን የሕግ ሁሉ የበላይ የሆነ ህገ መንግስት ባል እና ሚስት በትዳራቸው እኩል መብት እንዳላቸው ይገልፃል። የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 50 ላይም ባል እና ሚስት በቤተሰብ አመራር፣ ልጆች አስተዳደር እና የቤተሰቡን ደህንነት ጥቅም በማስከበር ላይ እኩል መብት ያላቸው መሆኑን ይገልፃል። በመሆኑም ቀደም ባሉት ጊዜያት በሰፊው ይስተዋል የነበረው ሴቶችን በጋብቻ ውስጥ የበታች አድርጎ የሚወስድ አስተሳሰብ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በማያሻማ ሁኔታ እንዲወገድ ተደርጓል።
ጋብቻ በተጋቢዎች ግላዊ ግንኙነት ላይ የሚፈጠረው ሌላኛው ውጤት አብሮ የመኖርን ግዴታ ነው። ተጋቢዎች በፊት ከነበራቸው ማህበራዊ ቦታ ከላጤነት ወደ ጋራ የሆነ ህይወት ሲዘዋወሩ ዋነኛው መገለጫው አብሮ መኖራቸው ነው። ቤተሰብ ተመሰረተ የሚባለውም ተጋቢዎቹ በጋራ መኖር ጀምረው ጤናማ የሆነ የሩካቤ ስጋ ግንኙነት በማድረግ ልጆች በማፍራት የማህበረሰቡን ቀጣይነት ሲያረጋግጡ ነው። ይህን አብሮ የመኖር እና ለጤንነታቸው አደገኛ እስካልሆነ ድረስ የሩካቤ ስጋ ግንኙነት መፈጸም ግዴታ በባል እና ሚስት ላይ የተጣለ ግዴታ ነው። ይህን የሚቃረን የማናቸውም ስምምነት ማድረግ አይችሉም። (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 53)።
በጋራ የመኖር ግዴታቸውን ሲወጡ የጋራ መኖሪያ ቦታቸውን በጋራ ተጋቢዎቹ ይወስናሉ። በአንደኛው ተጋቢ ስምምነት ብቻ የመኖሪያ ቦታን መምረጥ አይቻልም።
ከላይ እንደተገለጸው በትዳር ውስጥ ተጋቢዎች በጋራ የመኖሪያ ቦታቸውን መርጠው አብረው የመኖር ግዴታ አለባቸው። ነገር ግን ባልና ሚስት ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ተለያይተው ለመኖር ሊስማሙ ይችላሉ። ይህ የሚሆነው በተለያየ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በስራ ምክንያት ባል አዲስ አበባ ቦሌ፣ ሚስት ደግሞ ባሌ ሊኖሩ ይችላሉ።
3. ጋብቻ በንብረት በኩል ስለሚኖረው ውጤት
ጋብቻ ከሚያስከትላቸው ሕጋዊ ውጤቶች አንደኛው በንብረት ወይም በሀብት ላይ የሚያስከትለው ውጤት ነው። ማንኛውም ሰው የፈለገው ስራ ላይ ተሰማርቶ ሀብትና ንብረት ማፍራት መብት እንዳለው በህገ መንግስታችን አንቀጽ 41(1)ና(2) ላይ በግልጽ ተቀምጧል። በመሆኑም ማንኛውም ሰው ፍላጎቱ በሆነ ስራ ላይ ተሰማርቶ ሀብትና ንብረት ማፍራት ይችላል። በዚሁ መሠረት አንድ ሰው ወደ ጋብቻ ከመግባቱ በፊት በላቡና በወዙ ሰርቶ ያገኘው ወይም በስጦታ ወይም በውርስ ያገኘው ሀብትና ንብረት ሊኖረው ይችላል። ይህን ከትዳሩ በፊት ያገኘውን ሀብትና ንብረት ወደ ትዳር ሲገባ የግል ንብረቱ ሆነው ይቀጥላል። በትዳሩ ውስጥ ከገባ በኋላም ለግሉ በስጦታም ወይም በውርስ ያገኘው ንብረት የግል ንብረት ሆኖ ይቀጥላል። ነገር ግን ተጋቢዎች የግል ንብረታቸው የሆነውን የጋራ ንብረት ነው በማለት ሊስማሙ ይችላሉ።
ተጋቢዎች ትዳር የሚፈጽ ሙት እስከ መጨረሻው አብሮ ለመኖር መሆኑ እሙን ነው። በዚህ በትዳር ባሉበት ጊዚያት በግል ንብረትነት ይዘዋቸው ያሉ ንብረቶችን መሸጥ መለወጥ አይቀሬ ጉዳይ ነው። እነዚህ የግል ንብረቶችና ሀብቶችን በመሸጥ ወይም በመለወጥ የሚገኘው አዲስ ንብረትና ሀብት የግል ንብረት ይሆናል። ነገር ግን እነዚህ በግል ሀብት የተገዙ ወይም የተለወጡ ንብረቶች የግል ሀብትና ንብረት እንደሆኑ የግል ንብረቱ ባለቤት ለፍ/ቤት የግል ይባልልኝ በማለት ጥያቄ ማቅረብ እና ማፅደቅ አለበት። የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 58(1)ና(2) ይህን ይገልፃሉ። ይህ ካልሆነ ግን በአንቀጽ 62/2/ መሠረት የጋራ ንብረት ተደርጎ ይቆጠራል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 37275 ላይ አመልካች ሻ/ባሻ ገዛኸኝ ድልነሳው እና ተጠሪ ወ/ሮ ተዋበች ደመቀ መካከል በነበረው ክርክር የአመልካች የግል ንብረት የነበረ ቤት በትዳር ባሉበት ጊዜ ሸጠው በተሸጠው ገንዘብ ሌላ አዲስ ቤት ገዝተዋል ነገር ግን አመልካች አዲስ የገዙትን ቤት የግል ይባልልኝ በማለት ጥያቄ ለፍርድ ቤት ያላቀረቡ እና ያላጸደቁ በመሆኑ የጋራ ንብረት ነው በማለት ወስኗል።
ኑሮ በትዳር ውስጥ የጋራ ቢሆንም ከላይ በተገለጸው መልኩ ተጋቢዎቹ የግል ንብረቶቻቸውን ይዘው በትዳር መቀጠል ይችላሉ። በዚህ ጊዜ እነዚህ ንብረቶችም የሚተዳደሩት በግል የንብረቱ ባለቤት በሆነው ሰው ነው። በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 59 ላይ እያንዳንዱ ተጋቢ የግል ሀብቱን እራሱ ለማስተዳደርና ገቢውንም ለመቀበል ይችላል። እንዲሁም የግል ሀብቱን ራሱ ሊያዝበት ነፃነት አለው በማለት ይገልፃል። ነገር ግን የግል ንብረቱ ባለቤት የሆነው አንደኛው ተጋቢ የግል ንብረቱን በሙሉ ወይም በከፊል ሌላኛው ተጋቢ እንዲያስተዳድርለት እና እንዲያዝበት በጋብቻ ውላቸው ሊወስን ይችላል።
ይህ በሚሆንበት ጊዜ የግል ንብረቱ ባለቤት የሆነው ተጋቢ ሌላኛውን ተጋቢ ስለንብረቱ አስተዳደር ዓመታዊ የሂሳብ መግለጫ መጠየቅ ይችላል። ይህ ሲሆን ሌላኛው ተጋቢ ሲጠይቅ ይህንኑ የመስጠት ግዴታ አለበት (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 60(2) )። እንዲሁም ከተጋቢዎቹ አንዱ የግል ንብረቱንና ሀብቱን በሙሉ ወይም በከፊል እንዲያስተዳድርለት ለሌላኛው ተጋቢ ውክልና መስጠት እንደሚችል በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 61 ላይ ተቀምጧል።
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በጋብቻ ውስጥ ተጋቢዎች የግል ንብረት ሊኖራቸው ይችላል። ይህን ንብረት በዋነኛነት የንብረቱ ባለቤት የሚያዝበትና የሚያስተዳድረው መሆኑን እንዲሁም የግል ንብረቱ ባለቤት የሆነው አንደኛው ተጋቢ ሌላኛው ተጋቢ እንዲያስተዳድርለት በጋብቻ ውል ወይም በውክልና መስጠት እንደሚችል ተረድተናል። (በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ከአንቀጽ 57-61)
ተጋቢዎች በትዳር ከተሳሰሩበት እለት ጀምሮ ህይወታቸውን በጋራ ሲመሩ የጋራ ንብረት ማፍራታቸው አይቀሬ ነው። በጋብቻ ውላቸው ተጋቢዎች ከትዳር በፊት የነበራቸውን የግል ንብረት የጋራ ንብረት ማድረግም ይችላሉ። በጥቅሉ በትዳር ዘመናቸው ተጋቢዎች የግል ንብረትና ሀብት እንደሚኖራቸው ሁሉ የጋራ ንብረትና ሀብት ሊኖራቸው ይችላል።
ከተሻሻለው የቤተሰብ ህጋችን አንቀጽ 57 እና 58 ለመገንዘብ የምንችለው ነገር በትዳር ውስጥ የተፈሩ ሀብቶችና ንብረቶች፣ ለተጋቢዎቹ በጥቅሉ በውርስ ወይም በስጦታ የተሰጧቸው ሀብትና ንብረቶች በተጨማሪም የግል ሀብትና ንብረት ተሸጦ ወይም ተለውጦ የተገኘ ንብረት ሆኖ የግል ንብረቱ ባለቤት በፍርድ ቤት ቀርቦ የግል ንብረት መሆኑን ያላጸደቃቸው ንብረቶችና ሀብቶች ሁሉ የጋራ ንብረት እንደሆኑ ይቆጠራል።
ከዚህ በተጨማሪ በአንቀጽ 62(1) ላይ ባልና ሚስት ከግል ጥረታቸውና ከግል ወይም ከጋራ ንብረታቸው የሚያገኟቸው ገቢዎች ሁሉ የጋራ ሀብቶቻቸው እንደሚሆኑ ይገልፃል። የግል ንብረት የግል ቢሆንም ከንብረቱ የሚገኝ ገቢ ግን የጋራ ነው።
የንብረት ባለቤትነት የሚገለጹባቸው መንገዶች የተለያዩ ናቸው። በሀገራችን የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እንደ ቤቶችና መኪና የመሳሰሉት ባለቤትነታቸው የሚረጋገጠው በባለቤትነት የምስክር ወረቀት ነው። በጋብቻ ውስጥ የተጋቢዎች የጋራ ንብረት በአንደኛው ተጋቢ ስም ብቻ ተመዝግቦ ሊገኝ ይችላል።
በዚህ ጊዜ አንደኛው ተጋቢ የግል ሀብቱ መሆኑን ካላስረዳ በስተቀር ማንኛውም ንብረት በአንደኛው ተጋቢ ስም ብቻ የተመዘገበ ቢሆንም እንኳን የጋራ ሀብት እንደሆነ ይቆጠራል። (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 63(1))ሳምንት ይቀጥላል::
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2013