
አዲስ አበባ፡- ክልሉን ከማናቸውም የአሸባሪው ትህነግ ጥቃት ለመመከት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ። የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቡድኑ የሁሉም ጠላት መሆኑን አውቀው አደብ እንዲገዛ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቀረቡ።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ትናንት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፤ አሸባሪው ትህነግ ባለፉት ዓመታት በሕዝብ ላይ በደል ሲፈጽም መቆየቱንና አሁንም በአማራና በመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሽብር ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
በፌደራል መንግሥት የተደረሰበት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ከአማራ ክልል አንጻር ያለውን አንድምታ በመገምገም አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ እየተሠራ መሆኑን ያስታወቁት አቶ አገኘሁ፣ ክልሉን ከማናቸውም የአሸባሪው ትህነግ ጥቃት ለመመከት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል። የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሀገር እንድትሆን እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
አሸባሪው ትህነግ ዋጋውን ያገኘበት የሕግ ማስከበር ዘመቻ መከናወኑን ያስታወቁት ርእሰ መስተዳድሩ፣ አሁን ለሀገሪቱ ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። መከላከያው ከትግራይ ሲወጣ ለላቀ ግዳጅ ራሱን ለማዘጋጀት መሆኑን እንደሚረዱም ጠቁመዋል።
የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔው የትግራይ ሕዝብ ወደ ልማት እንዲገባ እድል የሚሰጥ ነው። ውሳኔው ኃላፊነት ከሚሰማው መንግሥት የሚጠበቅ ነው ያሉት አቶ አገኘሁ፣ አሸባሪው ትህነግ የአማራን ሕዝብ የቻለውን ሁሉ አድርጎ በድሎታል፤ ቡድኑ ጸረ አማራ መሆኑን በግልጽ አውጥቶታል ብለዋል።
በህግ ማስከበር ዘመቻው ጥቃት የማድረስ አቅም የሌለው ደረጃ ላይ ቢሆንም ጠላቴ ብሎ በሚጠራው የአማራ ሕዝብ ላይ ደግሞ ሂሳብ አወራርዳለሁ የሚል አጉል ፉከራ እያሰማ መሆኑን አመልክተዋል።
ከስህተቱና ከሽንፈቱ የማይማረው አሸባሪው ትህነግ ንቀት የተመላበት እብሪት እያሳየ እንደሆነ የተናገሩት ርእሰ መስተዳድሩ፣ የሕዝብ ጠላት በመሆኑ ምቹ ሁኔታ ካገኘ፣ በአማራ ሕዝብ ላይ ማናቸውንም ነገር ለማድረግ ወደኋላ እንደማይል እናውቃለን ብለዋል። ከዚህ አንጻር ለሚመጣው ሁሉ የአማራ ሕዝብ ዝግጁ ነው ብለዋል።
“የአማራ ሕዝብና መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ሂሳብ አያወራርድም፣ የትግራይ ሕዝብ ጠላታችን አይደለም” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ አሸባሪው ትህነግ ግን ጠላት በመሆኑ “የአማራ ሕዝብ ለማንኛውም ነገር በሥነልቦና ዝግጁ ነው ብለዋል።
ወልቃይት ጠገዴና ራያ የማን እንደሆኑ የታወቀ ነው፤ ቦታዎቹ የተወሰዱት በማጭበርበርና በጉልበት ነው። ለማንነት ጥያቄው ሕዝብ ዋጋ ከፍሏል፣ አካባቢዎቹ የአማራ ግዛት ናቸው፤ በአማራ ክልል ሥር እያስተዳደርናቸው ነው፤ ወልቃይት ጠገዴንና ራያን በጉልበት እንወስዳለን የሚለው ጉዳይ የማይሳካ መሆኑንም አሳስበዋል።
ወልቃይት ጠገዴንና ራያን በጉልበት ለመውሰድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ካለ ማናቸውንም ዋጋ እንከፍላለን። አሸባሪው ትህነግ በእነዚህ የአማራ ግዛቶች ላይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ቀልድ ነው፤ አይሳካለትም፤ ዋጋ ያስከፍላል ብለዋል።
ቡድኑ አማራን ሊያጠቃ እየተንቀሳቀሰ ያለ ጠላት ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፣ እንደ አመጣጡ ለመመለስ ለሚደረገው ጥሪ ሁሉም እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅርበዋል። የማህበራዊ አንቂዎች ትክክለኛውን መረጃ በመያዝ እንዲሰሩና በተሳሳተ መረጃ የተሳሳተ ታሪክ እንዳይሰሩም አሳስበዋል።
አሁን ላይ የፖለቲካ ልዩነት ጉዳይ አይደለም ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ፣ የክልሉ መንግሥት ጠላትን ለመመከት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
የአማራ የጸጥታ ኃይል የትህነግ አሸባሪ ቡድን የሚያደርገውን ጥቃት በአግባቡ እንደሚያስተናግደው እርግጠኞች ነን ያሉት አቶ አገኘሁ፣ ሕዝቡም በተልእኮ ላይ ያሉ የጸጥታ አካላትን ቤተሰቦች በማገዝ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል። ኢኮኖሚን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ማኅበረሰቡ አንድም ቀን ከሥራው ወደኋላ እንዳይል አሳስበዋል።
የአሸባሪው ትህነግ ዋነኛ ዓላማ የትግራይ ሕዝብን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር መነጠል መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ቡድኑ ሥርዓት ካልያዘ ሀገርን መልሶ እንደሚያተራምስ አመልክተዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አሸባሪው ትህነግ የሁሉም ጠላት መሆኑን አውቀው አደብ እንዲገዛ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም