በኃይሉ አበራ
ዴሞክራሲ የህዝብ ውክልና ያለው አስተዳደር ቢሆንም፣ እኩልነት ነጻነትና ደህንነት የዴሞክራሲ አንኳር አሴቶች በመሆናቸው እነዚህን መንከባከብ እና በትውልዱ ውስጥ ማሳደግ ያስፈልጋል። በመሆኑም ዴሞክራሲ ላይ ህይወት የሚዘራው ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ በማካሄድ ነው። ይህም ተግባራዊ የሚደረግበት መንገድ ድምጽ በመስጠት ነው። በምርጫ ድምጽ መስጠት ደግሞ ዋነኛው የዜግነት ኃላፊነት በመሆኑ ተማሪዎች በስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ብቻ መወከልና መወከልን ሊማሩ አይችሉም። ነገር ግን ተግባራዊ በሆነ መልኩ በመራጭነትና በተመራጭነት የክበባት መሪዎቻቸውን በየዓመቱ እንዲመርጡ በማድረግ ማሸነፍንና መሸነፍን የለመዱ፣ መምራትና መመራትን የለዩ፣ ማስረከብና መረከብ የማይቸግራቸው ልጆችን ማፍራት ያስፈልጋል።
“ቮት ለኢትዮጵያዬ በጎ አድራጎት ድርጅት” መስራችና ስራ አስኪያጅ ስምኦን ከበደ ተሰማ “ልጄ ወደፊት ምን መሆን እንደምትፈልግ ስጠይቃት ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን እንደምትፈልግ ነገረችኝ፤ ምላሿን ስሰማ ደነገጥኩኝ። መደንገጤን አይታም “ሴቶች ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን አይችሉም?” ስትል ጠየቀችኝ። ይችላሉ ነገር ግን ጠንካራ ሰራተኛ፣ አንባቢ መሆን ያስፈልጋል አልኳት።”
እንደ አቶ ስምኦን ከበደ ኢትዮጵያ በስልጣኔና በነጻነት ፈር ቀዳጅ እንደነበረች ሁሉ የራሳችንን ችግር በራሳችን በመፍታት፣ ዴሞክራሲን ባህል በማድረግ ለተቀሩት የአፍሪካ ሀገሮች ማስተማር ይኖርብናል። ኢትዮጵያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖራት ትውልዱ ላይ መስራት ይገባል። በመሆኑም የዴሞክራሲ ትምህርት ሀገራዊ አጀንዳ መሆን አለበት። በመሆኑም ከታችኛው ደረጃ ጀምሮ ትውልዱ ላይ በመስራት በሰለጠነ መልኩ መሪዎቻቸውን የሚመርጡ፣ ማሳመንና ማመን የሚችሉ ዜጎችን ማብቃት፤ በኃይል ስልጣን መያዝን የመጠየፉ፣ እርስበርስ ያሉ ቅራኔዎችን መፍታት የሚችሉ ወዘተ ዜጎችን ለማፍራት የሚያግዝ ስራ እየተሰራ ነው።
ልጆችን ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ የምርጫ ሥርዓትን እንዲማሩ፤ የዴሞክራሲ ትምህርት ሀገራዊ አጀንዳ እንዲሆን ትውልዱ ላይ መስራት ይጠበቃል። ቮት ለኢትዮጵያዬም እንደ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ተጨባጭ ለውጥ አምጪ፣ ተጸዕኖ ፈጣሪና ጠንካራ ዜጎችን መፍጠር የሚያስችል ትውልድ ለማፍራት እና ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖራት ለማስቻል የተቋቋመ ነው።
ተማሪዎች በቮት ለኢትዮጵያዬ በኩል የምርጫ ሂደት ላይ ልምምድ እንዲያደርጉ በአምስት ክበባት (ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የኪነጥበብ፣ የአከባቢና ጤና፣ የጤናና ሰውነት ማጎልመሻ እና የስነዜጋና ስነምግባር) ክበባት ኃላፊዎችና ጸሃፊዎችን በፍትሃዊ ምርጫ የሚወክሉበት አሰራር በመዘርጋት የምርጫ ሂደትንና ዴሞክራሲን በተግባር እንዲማሩ እየሰራ ይገኛል። ይህንንም በመደገፍ አብረው የሚሰሩ አራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ሲኖሩ የሳይንስና ኢኖቬሽን በወረቀት የሚደረገውን ምርጫ ኮድ ጽፈው መተግበሪያ አበልጽገው የኤሌክትሮኖኒክ የምርጫ ዘዴ የሚፈጥሩበት መንገድ ለማበረታታት ከአይሲቲ ፓርክ ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ነው አቶ ስምኦን ከበደ የሚናገሩት።
የኪነጥበብ ዘርፉም ወጣቶች ላይ ሰርጾ የሚገባ በመሆኑ የብሔር ብሔረሰብ ቋንቋና አለባበስን ለማስተማር ብቻ ሳይሆን ከዚያም ባለፈ ስለግብር ትርጉምና ዓይነትና የአጀማመር ታሪክ ከልጅነት ጀምሮ ማስተማር፤ ገንዘብ ከመፈጠሩ በፊት ግብር እንደነበረና ግብርን የማይከፍል ዜጋ እንደሀገር ጠላት የሚጸየፉ ዜጎችን በልጅነት ለማፍራት በድራማ፣ በትያትርና በስነጽሁፍ ማስተማር ተገቢ ነው የሚሉት ዘቶ ስምኦን በጤናና ሰውነት ማጎልመሻ በኩልም ልጆች ከታችኛው የትምህርት ደረጃ እስከ ላይኛው የትምህርት ደረጃ አባል የሚሆኑበትን ቡድን በማቋቋም፤ ጠንካራና አቋማቸው ተመጣጣኝ የሆኑ ቡድኖችን በመፍጠር ግጥሚያዎችን እንዲያደርጉ በማድረግ፤ ተማሪዎች ክሂሎታቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑንም ይናገራሉ።
እንደ አቶ ስምኦን ከበደ የቮት ለኢትዮጵያዬ ፕሮጀክት ተማሪዎች የህግ የበላይነትን ከልጅነት ጀምረው እንዲያውቁ፣ መሸነፍን ከግላዊነትና ከስሜታዊነት በጸዳ መልኩ እንዲቀበሉ፣ ማሸነፍን ለአገልጋይነት ብቻ መሆኑን አውቀው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለማስተናገድ የማይቸገሩ ዜጎች የሚቀረጽበት ነው።
አልፎ አልፎ ለሚከሰቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ለውጦች በቀላሉ የሚላመዱ ዜጎች የሚፈጠሩበት፤ እንዲሁም የሚከሰቱ ግጭቶችና ቅራኔዎችን በውይይት የመፍታት ሥርዓትና ደንብ የሚማሩበት፤ ሳይንሳዊ ሃሳብና ሙግት ከልጅነት ጀምሮ የሚለማመዱበትና ምክንያታዊ ዜጎች የሚቀረጹበት ነው።
በደጃዝማች ወንድራድ ትምህርት ቤት ከ2ሺህ 150 ተማሪዎች በላይ ተምረዋል። እንዲሁም በኮከበ ጽባህ አጸደ ህጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ700 በላይ ተማሪዎች ተግባራዊ ትምህርት የወሰዱ ሲሆን በዚህ ዓመት ብቻ በሀገራችን በሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶች ለ11ሺህ 200 ተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ከስራ አስኪያጂጁ ገለፃ መረዳት ተችሏል።
“ቮት ለኢትዮጵያዬ” በዚህ ዓመት በአራት ክልሎች (በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሲዳማ) በመንቀሳቀስ እና ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመፈተሽ በቀጣይ በ2025 ሁሉንም የኢትዮጵያ ክልሎች ለማዳረስ በ2030 ደግሞ አፍሪካን ለማዳረስ መታቀዱን ስራ አስኪያጁ አቶ ስምኦን ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም