በየካቲት 1966 ዓ.ም የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ በሀገሪቱ አብዮት መፈንዳቱ ይታወቃል። ለአብዮቱ መምጣት ተማሪዎችን ጨምሮ የበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፣ ስልጣኑን ግን ቀስ በቀስ ወታደሩ ጠቅላሎ እንደያዘው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሰራዊት አባላትን ይወክላሉ የተባሉና ከተራ ወታደር እስከ ሻለቃ ድረስ ማዕረግ ያላቸው 120 የጦሩ አባላት ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም በአራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ ተሰብስበው ‹‹የጦር ኃይሎች፣ የክብር ዘበኛ፣ የፖሊስ ሰራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ›› የተባለ ቡድን አቋቋሙ። ይህ ኮሚቴ ስያሜውንም ‹‹ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ›› ብሎ በመቀየር ስልጣን ይዞ ኅብረተሰባዊነት (Socialism)ን የፖለቲካ-ኢኮኖሚ መርሁ አድርጎ አገር መግዛት ጀመረ። መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ከዙፋናቸው አወረደ።
ደርግ ወደ ሥልጣን ከመጣበት እለት ጀምሮ ለሶስት ወራት የእለት ተእለት ስራውን ለመከወን ሲጠቀምባቸው የነበሩት ስፍራዎች በአራተኛ ክፍለ ጦር ውስጥ የሚገኙትን ቢሮዎች ነበር። በጥቅምት አጋማሽ 1967 ዓ.ም ደርግ ወደ ታላቁ ቤተመንግሥት ተዛውሮ ሀገር መግዛቱን ቀጠለ። ከዚሁ ጊዜ አንስቶም የደርግ አባላት በሙሉ ስብሰባ ያደረጉ የነበረው ዙፋን ቤት ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የቀድሞ ባለስልጣናት ታስረው የነበረው የዚሁ አዳራሽ አካል በሆነው ምድር ቤት ውስጥ ነበር።
በዚሁ አዳራሽ በተደረጉ ስብሰባዎች በርካታ ታሪካዊ ውሳኔዎች ተላልፈዋል። ከእነዚህም ታሪካዊ ውሳኔዎች መካከል በየካቲት 25 ቀን1967 ዓ.ም «የገጠር መሬት አዋጅ» እና ሐምሌ 19 ቀን 1967 ዓ.ም «የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ» በመባል የሚታወቁት ሁለት አዋጆች ተጠቃሽ ናቸው።
በሌላ በኩል በተለምዶ «ስልሳዎቹ» ተብለው የሚታወቁት የቀድሞቹ የንጉሠ ነገሥቱ ባለሥልጣናት የሞት ፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው በዚሁ ዙፋን ቤት አዳራሽ በተደረገ ስብሰባ ነበር።
ቆይቶም ሊቀመንበሩ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆኑ፤ በአገዛዝ ዘመናቸው የመሰረተ ልማት አውታሮችን በተለይ ደግሞ ትምህርትን ለማስፋፋት ከተደረገው ጥረት ቢደረግም፣ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ እስራትና ስርዓት አልበኝነት የአገዛዙ መለያዎች ሆኑ። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ ደግሞ በኤርትራ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ጦር በተሸነፈ ቁጥር ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃ/ማርያም የሚወስዱት እርምጃ፣ ግትርነታቸው እንዲሁም ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ተደምረው በግንቦት 1981 ዓ.ም የጦሩ መሪዎች በፕሬዚዳንቱ ላይ ጥርሳቸውን ነከሱባቸው፤ በዚህ ሳይገቱም ያልተሳካ ደም አፋሳሽ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አካሄዱባቸው።
ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው በኋላ በተወደሰው እርምጃ ኢትዮጵያም በርካታና ‹‹በአፍሪካ ደረጃ ምርጥ ነበሩ›› የተባሉ የጦር መሪዎቿን አጣች። የፕሬዚዳንት መንግስቱ አገዛዝም የደመ ነፍስ ጉዞውን ቀጠለበት። ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ከግንቦት 1981 መፈንቅለ መንግስት ቢተርፉም፣ መንግስታቸውን ክፉኛ ሲፈታተን በቆየው ኢህአዴግ ጦር ግንቦት 1983 መሸነፋቸውን ሲረዱ ግንቦት 13 ቀን 1983 አገር ጥለው ሸሹ። ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ኢትዮጵያን የባሕር በር ያሳጣው፣ በዘር የከፋፈለው፣ የዜጎች እስር ቤት እንዲሁም የሙስናና የብልሹ አስተዳደር መነኻሪያ ያደረገው … የብሔር ፖለቲካ ስርዓት አሸንፎ ቤተ መንግሥት ገባ።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2013