ስለባህልማዕከል ሲነሳ በአብዛኞቻችን አእምሮ ውስጥ ቶሎ የሚታወሰው የአንድ አካባቢ የባህል ምግብ አዘገጃጀት፣ አልባሳቶቻቸው፣ ዘፈናቸው፣ ጭፈራቸው፣ የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶችና ሌሎችም እሴቶች ናቸው። ነገር ግን የባህል ማዕከል ከሚታሰበው በላይ ሰፊ የሆነ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ባህልና ታሪክ የያዘ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የታሪክ ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ ከፍችው በመነሳት እንዲህ አብራርተዋል። ማንኛውም ይሄ ባህል አለኝ የሚል ህብረተሰብና ክልል አለፍ ብሎም በሀገር ደረጃ የሚገለጽ ሲሆን፣ እሴቶቹን የሚያሳድግበት፣ የሚጠብቅበት፣ ለሌላው የሚያስተዋውቅበት፣ በባህል ላይ ጥናትና ምርምር የሚደረግበት፣ ባህል ሀብት በመሆኑ ደግሞ የሚለማበት፣ የሀብት ምንጭ የሚፈጠርበት፣ ይሄን ሁሉ አካቶ የሚሰራ ነው ባህል ማዕከል።
በኢትዮጵያ ባህል ማዕከልን ማቋቋም በቅርብ ጊዜ የመጣ አዲስ አይደለም። የመጀመሪያው የባህልማዕከል በአፄኃይለሥላሴ ዘመን ቀድሞ ቀዳማዊኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ በሚጠራው ውስጥ ነበር የተቋቋመው። ማዕከሉ አሁንም አለ። በወቅቱ ሲቋቋም ባህሎች፤ በባህል ውስጥ ያሉ አላባውያን እንደ ሙዚቃ፣ ቲያትር፣ሥነግጥም፣ በአጠቃላይ በሥነጥበብ ዘርፉ ያሉትን አካቶ ከፀጉር አሰራር ጀምሮ አለባበስ፣ምግብና ሌሎችም አካባቢን የሚገልጹ የሚገኙበትና ብዙ ሥራዎች ሲሰራበት የቆየ ብዙ ባለሙያዎችንም ያፈራ የባህል ማዕከል ነበር።
የሥነሥዕል ኤግዚቢሽኖችን በማካሄድ፣በዚህም ከሰአሊያን እነአለፈለገ፣ የዓለምሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ በቲያትሩ አርቲስት ደበበ እሸቱና ሌሎች ባለሙያዎችንም በማፍራት የጎላ ሚና ነበረው። በተጨማሪም ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ የተባለው የሙዚቃ ቡድን በተለይ የሀገረሰብ የሙዚቃ ሥራዎች በማጎልበት፣ዘመንን የሚዋጁ ማህበረሰብን የሚገነቡ፣ ዘመናዊነትን ከትውፊት ጋር እንዴት አያይዞ መሄድ እንደሚቻል፣ ለህብረተሰብ በማስተማርም የነበረው አስተዋጽኦ አይዘነጋም። የኪነጥበብና ሥነጥበብ ትልቁ ድርሻ ህብረተሰብን ሳያስጨንቅ እያዝናና ያስተምራል።
ያስገነዝባል። በዚህ ረገድ የተዋጣለት ሥራ ተሰርቷል። ይሁን እንጂ እንደአመሰራረቱና እንደሥራው አልቀጠለም። የንጉሱ ሥርዓት ተለውጦ የተተካው የደርግ አገዛዝ ሥርዓት ሶሻሊዝም የሚባለውን ርዕዮት የሚያራምድ በመሆኑ የባህል ማዕከሉን እንቅስቃሴ አዳከመው። የነበረው ሥርዓት የኪነት ቡድንን በማቋቋም የርዕዮተ ዓለም ማጎልበቻ አድርጎ ይጠቀምበት ነበር። ከደርግ ሥርዓት በኋላ የመጣው መንግሥት ከ1983 ዓ.ም በኋላ በቁጥር በዛ ያሉ የባህልማዕከሎች አቋቁሟል።
በዚህ ወቅትም የነበረው መንግሥት የመረጠውንና የራሱ የሆነውን ዘፈኑን፣ ምግቡን፣ መጠጡን አልባሳቱን በማሳየት ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር።ቲያትር አልፎ አልፎ ካልሆነ ከነዚህ ውጭ ያሉት አይቀርቡም። ከባህል አላባዎች አብዛኛው ማህበረሰብ የሚጋራቸው ይኖራሉ። ከነዚያ ተነስቶ ባህል ልውውጥ የማድረግና የማስተዋወቅ ሥራ አይሰራም። ጥናትና ምርምር አይካሄድባቸውም። በጥቅሉ ባህል ማዕከላቱ ሚናቸውና ፋይዳቸው ሲመዘን ግላዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ከማተኮር ባለፈ የማልማት ሥራ አልተከናወነባቸውም።
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አሁን ላይ ለውጦችን እያዩ ቢሆንም አብዛኞቹ የባህልማዕከሎች ሥነጥበብን ያሟላ ሥራ የሚሰሩ አላጋጠማቸውም። በተለይ ሰዓሊያን ሥራዎቻቸውን በማዕከላቱ የማቅረብ ዕድል አያገኙም። በዚህ ረገድ በውጭ ሀገር ዜጎች የተቋቋሙት አልያንስኢትዮፍራንሴ፣ ጎቴ ተብለው የሚጠሩት የባህልማዕከሎች ናቸው የሚያስተናግዷቸው።
በኢትዮጵያኑ የተቋቋሙት ግን ዘፈን ላይ ያተኮረ ሥራ ነው የሚቀርብባቸው። እነዚህም ቢሆኑ ቱባው የባህል ጭፈራ ሳይሆን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ያላቸው የሙዚቃ ሥራ ወይንም ውዝዋዜዎች ናቸው የሚታዩት። ማዕከላቱ ባህልን እንዲጠብቁ፣ እንዲንከባከቡና እንዲያለሙ ተልዕኮ ተስጥቷቸው የሚሰሩ ከሆነ በዘፈኑም ማንነትን የሚገልጹ አልባሳት፣ ምግቦች ሁሉም የባህል እሴቶች እውነተኛውን የሚያንጸባርቁ መሆን መቻል አለባቸው።
ማዕከላቱ መደራጀት ያለባቸው የሙዚቃ፣ የቲያትር፣ የሥነቃል፣ እንዲሁም ጌጣጌጥና አልባሳት ሽያጭ የሚካሄድባቸው ፣የማዕከሉን ሥራ የሚያግዝ ጥናትና ምርምር ክፍል በማቋቋምና በባህል ዘርፍ የሰለጠኑ ወይም የተማሩ ሙያተኞችንም በማሟላት ግብና ተልዕኮ ይዞ በመከታተልና በመደገፍ መሆን ይኖርበታል። ባህልን ማልማት ማለት ገቢ መፍጠር በመሆኑ የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ከሀገር ውስጥም ከውጭም ጎብኚዎችን በመሳብ ገቢ ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል በመፍጠር የበጀት እጥረታቸውን ማቃለል ይችላሉ።ጠንክረው ከተንቀሳቀሱ ከሳምንት እስከ ሳምንት ገቢ መፍጠር ይችላሉ።
አንዴ ቴአትሩን፣ ሌላ ጊዜ የሥዕል ኤግዚብሽን፣ የፋሽን ትርኢት፣ የግጥም፣ የሙዚቃ ዝግጅቶችንና ሌሎችን ጥበባዊ ሥራዎች በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ከፍ በማድረግ የተቋቋሙበትን ዓላማ ሊያሳኩ ይችላሉ። ነገር ግን አብዛኞቹ የባህል ማዕከሎች በዚህ መልኩ ሳይሆን በወቅታዊ የስብሰባና የተለያዩ ዝግጅቶች የተጠመዱ ናቸው። ክፍተቶችን ለይቶ በመሙላትና ጠንካራ ጎናቸውን ደግሞ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በቢሮ ደረጃ የተቋቋሙትም በተለያየ መልኩ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
‹‹የባህል ማዕከል ሲመሰረት ዓላማ አለው። የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህል፣ ታሪክ፣ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ በውስጡ የሚይዝና የአካባቢውን ማህበረሰብ ግንኙነት የሚያሳይ፣ አንድን ማህበረሰብ ለመረዳት የሚያስችል፣ጥንታዊ ስልጣኔዎች የሚታዩባቸው፣የቱሪዝም መዳረሻ ሆኖ ጥቅም እንዲያስገኝ ብቻ ሳይሆን ዕውቀትንም ያስተላልፋል። እንዲህ ያለው አሰራርም ዓለም አቀፋዊ ነው›› በማለት የረዳት ፕሮፌሰር አበባውን ሃሳብ ያጠናከሩት በኦሮሚያ ባህል ማዕከል የባህል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ኃይሌ ናቸው።
አቶ አለማየሁ የባህልማዕከል አስተማሪነቱን በምሳሌ እንዳስረዱት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥ ንጉሥ አባጅፋር በሥነጽሁፍ፣ በዕደጥበብ እንዲሁም በዲፕሎማሲው መስክ በዘመናቸው ብዙ ሥራዎችን ሰርተዋል። በምዕራብ ኢትዮጵያም እንዲሁ ኩምሳ ሞረዳ የተባሉ ንጉሥ ከአፄዳግማዊ ሚኒልክ ጋር የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች፣ ከጎጃሙ ንጉሥ ተክለኃይማኖት ጋር ያደረጓቸው ግንኙነቶችና የፈጸሟቸው ውሎች፣ ሌሎችም የታሪክ ሰነዶች ተተኪው ትውልድ ይማርባቸዋል። የባህልማዕከል ለተመራማሪዎችም የመረጃ ምንጭ በመሆን ፋይዳው የጎላ ነው።
ከእንጨት፣ ከድንጋይ፣ ከወርቅና ከብረት የተሰሩ በጥንት ጊዜ ህብረተሰቡ የሚጠቀምባቸው የወግ ዕቃዎች በወቅቱ የነበረውን የዕድገት ደረጃ የሚያሳዩ በመሆናቸው አሁን ላይ ላለው ማህበረሰብ ግንዛቤ ይሰጣሉ። ሰዎች በአይነህሊናቸው ወደኋላ መለስ ብለው አባቶቻቸው፣ አያቶቻቸው በአጠቃላይ ቤተሰቦቻቸው በምን ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ለማወቅ ያስችላቸዋል። ባዩትም ይማራሉ። ይዝናናሉ። በወታደራዊ አቅምም እንዲሁ በዚያን ወቅት ከጦር መሳሪያው ጀምሮ ያለው ነባራዊ ሁኔታ፣ በተለይም ለመጓጓዣ ይጠቀሙባቸው የነበሩ የጋማ ከብቶ፣ የመንገዱን ሁኔታ፣ የውጊያውን አድካሚነትና ጠቃሚነቱን የሚያሳይ እንዲሁም በወቅቱ የነበሩ መሪዎች ከሌሎች ሀገሮች ጋር የሚያደርጉት የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች በማዕከሉ ውስጥ ከሚገኙት የተለያዩ ሀብቶች አንዱ የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ሲሆን፣ በገዳ ሥርዓት ውስጥ የማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ ይታያል።፣በአጠቃላይ ገላጭ በሆነ መልኩ በስዕላዊና በጽሁፍ ታግዞ በባህል ማዕከሉ ውስጥ መገኘቱ የኋላው ታሪክ አሻራዎች ናቸው። በአጠቃላይ በኦሮሞ ባህል ማዕከል ውስጥ ሃይማኖታዊ፣መንፈሳዊና ቁሳዊ ወጎችን የያዙ ይገኛሉ። ከዚህ አንፃር የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ እያገለገለ ነው። በባህልማዕከሉ ውስጥም በተለያየ ክፍል ውስጥ ተደራጅተዋል።
ባህል ማዕከሉ በውስጡ ከያዛቸው የተለያዩ የባህል መገለጫ እሴቶች በተጨማሪ የባህል ማዕከሉ ኪነ ህንፃ ባህልማዕከል መሆኑን የሚያሳይ ወይንም ገላጭ ነው ወይ? ለሚለው ጥያቄ አቶ አለማየሁ በምላሻቸው የህንፃው ሥራ ሲጀምርም ለግንባታ ከተመረጠው ቦታ ጀምሮ የባህል ሰዎች አልተካተቱም። በመካከል ላይ ግን ገብተው አንዳንድ ነገሮችን ለማስተካከል ጥረት አድርገዋል። ህንፃው ዘመናዊ ከመሆኑ በስተቀር ጎልቶ የሚታይ ገላጭ የሆነ ነገር አይታይበትም። ሆኖም ግን በመካከል ላይ የገቡት የባህል ሰዎች በህንፃው ቅጥረ ጊቢ ውስጥ የኦሮሞን ባህል የሚገልጹ ነገሮች ተሰርተዋል። ከመገለጫዎቹ አንዱ በማዕከሉ መግቢያ በር ላይ የተሰራው የኦሮሞ ገዳ ሥርዓትን የሚያሳየው ቅርጽ ይጠቀሳል።
‹‹ኢኮኖሚን ከሚያመነጩ አንዱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በመሆኑ የባህልማዕከሉ ይህንንም ታሳቢ ባደረገ ይሰራል›› ያሉት አቶ አለማየሁ፤ እንደ እሬቻና በሌሎችም ክብረበዓላት ወቅት የጎብኚዎች ቁጥር ከፍ ያለ ቢሆንም ተማሪዎች፣ሰራተኞች በጋራ፣ግለሰቦች ይጎበኛሉ። ባህልማዕከሉ እንደተመሰረተ ለአንድ ዓመት ያህል ጎብኚዎችን በነጻ ሲያስተናግድ ነበር። መልሶ ለማልማት እንዲችል ለተማሪና ለአዋቂ በተመጣጣኝ ክፍያ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ገቢውን ከፍ ለማድረግም በጊቢው ውስጥ ባዛሮች ይዘጋጃሉ።በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ገቢ በማግኘት ማዕከሉ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ ግን የጎብኚዎች ቁጥር በመቀነሱ ገቢውም ተዳክሟል።ባህል ማዕከሉም ከተመሰረተ አጭር ጊዜ በመሆኑ ገቢ በማስገኘት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ነው ለማለት አያስደፍርም።
የባህል ማዕከሎች ወቅታዊ በሆኑ ዝግጅቶች ላይ እንደሚጠመዱና በዚህም ጥበቃና እንክብካቤያቸው እደንደሚጓደል ከተለያዩ ሰዎች ስለሚቀርበው ትችትም አቶ አለማየሁ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የወግ ዕቃዎችም ሆኑ ታሪክ ነክ ቁሳቁሶች በተዘጋጀላቸው ማስቀመጫ ውስጥ የሙዚየም መስፈርቶችን መሠረትባደረገ መንገድ ነው እንዲቀመጡ የተደረገው። ጎብኚዎችም እንዳይነኳቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግላቸዋል።የሚያሰጎበኙ ባለሙያዎችም ከጉዳት እንዲጠበቁ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።
የአስጎብኚዎች አለመሟላትና በተለያየ ቋንቋም የሚጠቀሙ አለመኖራቸው በጎብኚዎች ከሚነሱ ቅሬታዎች አንዱ እንደሆነም ለቀረበው ጥያቄ አቶ አለማየሁ በምላሻቸው በሀገር ውስጥ ቋንቋ በኦሮምኛና በአማርኛ ከውጭ ቋንቋ በእንግሊዝኛ ገለጻ ሚያደርጉ ብቁና ብቁ ባለሙያዎች ተሟልተዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ባህል ማዕከል በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ የባህል ማዕከሎች እገዛ በማድረግ ረገድም ይሰራል ያሉት አቶ አለማየሁ በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የባህል ማዕከል የተደራጀው ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተሰበሰቡ የባህል ሀብቶች እንደሆነ ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ ከተማ የባህል ማዕከል እንድትሆን ለተለያዩ ክልሎች ለግንባታ የሚሆን መሬት የከተማ አስተዳደሩ በመስጠት እያበረታታ ይገኛል። በዚህ ላይ ረዳት ፕርፌሰር አበባው፤ እንዳሉት መገንባቱ አንድ ነገር ሆኖ ሚናን መወጣት ሌላ ተልዕኮ ነው።አዲስ አበባ ከተማ ትንሿ የባህል ማዕከል ለመሆን ስታቅድ በተለይም የኮንፈረንስ ቱሪዝም (ማይስ) የሚባለውን ዕድል ለመጠቀም ያስችላል። አዲስ አበባ ከተማ ላይ ቆይቶ መመለስ የሚፈልግ ቱሪስት የትኛውም ክልል ሳይሄድ በከተማዋ የተቋቋሙትን የባህል ማዕከሎች በመጎብኘት ሀሴት አድርጎ ወደመጣበት መመለስ ይችላል።
በጥቅም ደረጃም ማዕከላቱ ሳቢ የሆነ ነገር ካቀረቡ የቱሪስቱን ቆይታ ማራዘም ይችላሉ። ቱሪስቱ ቀኑን ሲያራዝም ተጠቃሚ የሚሆኑት የባህልማዕከላቱ ብቻ ሳይሆኑ በመስተንግዶ ላይ የተሰማሩት ሁሉ የጥቅሙ ተጋሪ ይሆናሉ። ጥቅሙ ሲደመር ደግሞ ሀገራዊ ይሆናል። ‹‹ባህላችን ትልቅ ሀብት ነው። ሀብቱ ደግሞ ሸጠን የምንጠቀምበት ነው። ስለዚህ ሁሉም ቢሰራና መንግሥትም ትኩረት ቢሰጠው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ማግኘት ይቻላል›› ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰሩ አስምረውበታል።
የባህል ማዕከሎች ያላቸው ጥቅምና አስፈላጊነት ባለሙያዎቹ እንዲህ ቢያስረዱም ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው ትልቅ ዓላማ ይዘው የተገነቡ አንዳንድ የባህል ማዕከሎች ያለጥቅም ባክነው ይስተዋላሉ። የማዕከላቱ መባከን አንዱ የበጀት አለመሟላት ነው። አስፈላጊነታቸው ከታመነባቸው የተቋቋሙበትን ዓላማ ማሳካት ይኖርባቸዋል። በባህል ማዕከሎች ቅኝቴ ብዙ ሥራዎች እንደሚጠይቁ ተገንዝቤያለሁ። ፓርኮችንና አረንጓዴ ልማትን ለማጠናከር የተሰጠው ትኩረት ለባህል ማዕከሎችም በተመሳሳይ ቢተገበር ማዕከላቱ የተቋቋሙበትን ዓላማ ሊያሳኩ ይችላሉ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2013