“ሃሜት” የሚመለከተው ወይም ባለጉዳዩ በሌለበት ስለ እዛ ሰው የሚወራ ወሬ ማለት ነው፡፡ወይም የባለጉዳዩን አለመኖር ተገን በማድረግ ሰውዬውን በተመለከተ አሉታዊ ሃሳብ መለዋወጥም ጭምር እንደማለት ነው፡፡ለመሆኑ ሀሜት በማህበራዊ ግንኙነታችን ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ወይንም የሚያሳድረው ጫና ምን ይሆን ስንል የዘወትር ተባባሪያችን የሆኑትን የማህበራዊ ሳይንስና አመራር ባለሙያ አቶ ዘላለም ይትባረክን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
አቶ ዘላለም እንደሚያብራሩት የኢንግላንድ የስነልቦና እድገት መጽሄት እንደሚያስቀምጠው ከሆነ የሰው ልጅ እድሜው ከ10 ዓመት በታች ካለበት ጊዜ ጀምሮ ሃሜት ይጀምራል፡፡ሰዎች በቀን ውስጥ 52 ደቂቃ በአማካኝ እንደሚያሙ፤ ከዚህም ውስጥ ሶስት እጥፍ የሚሆነው ሀሜት በጾታ ስለሚመሳሰላቸው ሰው መሆኑን የ”ማህበራዊ ስነልቦናና ስብዕና” መጽሄት ያስተናገደው ጥናት ይናገራል፡፡በአንዳንድ ማህበረሰብ ዘንድ ሀሜት የሴቶች ባህሪ ብቻ ተደርጎ የሚወሰደው ግን ስህተት ነው፡፡
የሃሜት መንስኤ
የሃሳብና የእውቀት ድርቀት፤ ድህነት፤ ስራ ፈት ወይም አጥ መሆን፤ ስንፍና፤ ቀናተኛ መሆን መበለጥ ወይንም መቀደም እንዲሁም በበታችነት ስሜት መጠቃት፤ ወረተኛነት፤ የራስን ክፍተት ለመሸፈን ወይም ለመርሳት የሚደረግ ጥረትና ምስጢር አባካኝ መሆን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
ሁለቱ ሀሜት አመጣሽ ጉዳቶች
አንደኛው – ከስራ ይልቅ ማውራትን፣ ወሬን እንዲመርጡ ያደርጋቸዋል፤ የሰዎችን መልካም ጎን መመልከት እንዲሳናቸው ስለሚያደርጋቸው ከሰዎች ልምድንና መማር ያለባቸውን እንዳይማሩ ያደርጋቸዋል። ጊዜን በአግባቡ የማይጠቀሙ አባካኝ ይሆናሉ። ለተስፋ መቁረጥና ቸልተኝነት ወይም ዳተኝነት ይዳርጋቸዋል፤ ጓደኝነትን፣ ቤተሰብን፣ ወዳጅን፣ ትዳርን በማፍረስ ጠላት ያበዛባቸዋል፤ እምነትን ያሳጣቸዋል።
ሁለተኛው – የሚታማው ሰው ላይ ደግሞ ምን ይሉኛል በሚል ለስኬት የሚደረግን ጥረት ያስቆማል፤ ለበጎ የሚደረግን መነሳሳትንና መበረታታትን ያዳክማል፤ ፈሪ፣ ይሉኝተኛ፣ አስመሳይ፣ አድርባይ፣ ውሸታም ወዘተ ያደርጋል፤ የብርቱ ሰዎችን ጉልበት ያላሽቃል፤ ህብረትን፣ የቡድን ስራንና አንድነትን ይንዳል፤ ጥገኛ፣ ተለጣፊ ወዘተ ያደርጋል፤ ልብ ይሰብራል። ባጠቃላይ የተግባርና የተሞክሮ እስራት ነው፤ የግለሰቡን በራስ መተማመን በመናድ ለድባቴ፣ ለውጥረትና ለጭንቀት ከመዳረግ ባለፈ ራስን እስከ ማጥፋት ሊዳርግ ይችላል፡፡
ሃሜትን ለማቆም መፍትሔው ምንድን ነው?
• ራስን መለየት
በዚህ ተግባር ከተያዙ ሰዎች ወይም ሃሜት ማውራት ሲጀምሩ ራስን ከቦታውና ከጊዜው መነጠል ወይም ተነስቶ መሄድ ተመካሪ ነው፡፡በርግጥ በመጀመሪያ ተው/ተይ ማለት ያለብን ሲሆን በዚህ የማያቆሙ ከሆነ ግን ራስን መለየት ወይም መነጠል የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ለዚህም ትኩረትን ከሌሎች ላይ አንስቶ ወደ ራስ ማድረግ፣ ወደ ውጭ አሻግሮ በግምትና ውሸት ስለሌሎች ለማወቅና ለማውራት ከመሞከር ይልቅ ራስን ለማወቅና ከራስ ለመመካከር የሚያስችል እድልን ይሰጣል፡፡ስለዚህ ከሃሜተኞች ጋር መደባለቅ ሃሜተኛ ስለሚያደርግ መለየትና መራቅ አለብን፡፡ይህም መጽሀፉ እንደሚለው ብርሃን ከጨለማ ህብረት እንደሌለው ሁሉ ከሃሜት ተግባር መውጣት የሚፈልግም ሁሉ ህብረቱን ጥሎ መለየት አለበት፡፡ላለማማት ብቻ ሳይሆን ሃሜትንም ላለመስማት የተሻለውም መንገድ ይሄው ነው፡፡
• መከሰት እና ማጋለጥ በድምሩ አለመተባበር
ከውሸት፣ ከጨለማና ከክፉ ወሬ ጋር ላለመተባበር እና ለማጋለጥ ሀሜተኛውን፤ እራሱን እውነቱን ጨክነን መጠየቅ ስንጀምር ሃሜትን ለማቆም ጉልበት እናገኛለን፡፡ለዚህ ደግሞ “መከሰት” እና “ማጋለጥ” ጥሩ መፍትሄዎች መሆናቸው ተመስክሮላቸዋል።
“መከሰት” ስንል አላውቅም፣ በቦታው አልነበርኩም፣ አላየሁም ወዘተ በማለት ባለቤቱ በሌለበት ከምናወራ ይልቅ እሱ ባለበት ብናወራ ይሻላል የማለት ልምድ ሲሆን፤ “ማጋለጥ” ደግሞ የታማው ሰው ሲገኝ ጠብቆ “እነ እንትና እንደዚህ እያሉ ነበር እውነት ነው እንዴ?”፤ ወይም የታማበትን ጉዳይ እንዲያብራራ በፊት ለፊታቸው ማፍረጥ መቻል ነው፡፡በርግጥ ይህን ስናደርግ ወይም ሃሜተኞችን አለመተባበርን እንደአማራጭ ስንጠቀም አጣቸዋለሁ፣ ይቀየሙኛል፣ ይሸሹኛል፣ ያገሉኛል ወዘተ የሚል ፍርሃት ብቻ ሳይሆን ሊያደርጉትም ይችላሉ፡፡
የስራ ሰው መሆን
የሃሜት ዋነኛ መንስኤው ስራ ፈትነት በመሆኑ ስራ መስራት ስንጀምር ለወሬና ለሃሜት ጊዜ እንድናጣ ያደርገናል፡፡ይህም ስራ ፈት አዕምሮ የሰይጣን የስራ ቦታ ይሆናል እንደሚባለው ነው! ስለዚህ ለሌሎች የምንሰራውን በስራ ቦታ ያለውን ስራ ብንጨርስም እንኳ ራስን በመስራት ወይም ለራስ በመስራት ልንጠመድ ይገባል፡፡ስራ ቦታ ስራ ስንጨርስ ከስራ ጋር የተያያዙ፣ ለሁሉም ጠቃሚ የሆኑትን የሚያሳትፍ የእረፍት ወሬዎችን በመምረጥ ማውጋት መልመድ የሚቻል ሲሆን ለራስ መስራት የሚቻልበት ሁኔታ ሲመቻችልን ደግሞ መጽሀፍትን ማንበብ፣ በራስ ጉዳይ መወያየት፣ በእውቀትና ጠቃሚ ጉዳዮች ዙሪያ ማውራት ወዘተ ራስን ማስለመድ ከሃሜት ለመዳንም ሆነ ሃሜትን ለማቆም ተመካሪ ብልሃት ነው፡፡
ራስን መገደብ ወይም መከልከል
በምናውቀው፣ በሚያገባን፣ በሚመለከተን፣ ባለድርሻ በሆንበት፣ በነበርንበት፣ በተጠየቅንበት ወዘተ ጉዳይ ላይ ብቻ ለመሳተፍ ወስኖ መተግበር ከሃሜት ያድናል፡፡በተቃራኒው በሁሉ የምንዘነኩር ከሆነ ግን ለሃሜት ተጋላጭ እንሆናለን፡፡ምንአልባት ያልገባን ጥያቄ የሆነብን ጉዳይ ካለም ከባለጉዳዩ ውጭ ከማይመለከታቸው ጋር ከመፈትፈት ራስን በመገደብ ባለጉዳዩን በመጠበቅ እንዲያብራራ እድል መስጠትንም ያካትታል፡፡እናም ገደብ አልባ፣ ለከት አልባ፣ ወሰን የለሽ ወዘተ ከመሆን ራስን መገደብም ሆነ መከልከል ከሃሜት ያድነናል፡፡በሰዎች ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት እንደማለት ነው፡፡
ምስጢር መጠበቅን መልመድ
የሰዎችን ገበና ለማይመለከታቸው አለመናገር ምስጢር ጠባቂ ያሰኛል፡፡ጓዳኛ፣ ቤተሰብና ወዳጅ ብለው አቅርበው ያካፈሉ ያወያዩንን ምስጢራቸውን መጠበቅ አለብን፡፡ምስጢር በወዳጆች መካከል የሚዘረጋ የአብሮነት ገመድ በመሆኑ በሃሜት የተነሳ ስናባክነው ወዳጅ የሚያሳጣን ሲሆን ስንጠብቀው ደግሞ ወዳጅን ያስገኝልናል፡፡
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2013