ሰሞኑን በማህበራዊ ድረገጾች ሳይቀር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የጎበኟቸው አቅመደካሞችን ስሜት የሚጋሩ ሀሳቦች ሲንሸራሸሩ ተመልክተናል:: በእነዚህ አቅመ ደካሞች ሀገርና ህዝብ ተመርቋል:: ብዙዎችም የወላጆቻቸውን፣ የጎረቤቶቻቸውንና የአካባቢያቸውን ሽማግሌዎች ምርቃት ወደኋላ መለስ ብለው በማስታወስ ስሜቶቻቸውን ያንፀባረቁበት ነበር:: ምርቃትና አሜን ብሎ መቀበል አንዱ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ነው::በየትኛውም እምነት ምርቃት ከፍ ያለ ቦታ ይሰጠዋል:: ሰው ከቤቱ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ትዳር ሲመሰርት ትዳሩ እንዲሰምር፣ ልጆች እንዲያድጉ፣ ኑሮ እንዲቃና፣ ምርት ተትረፍርፎ ጥጋብ እንዲሆን፣ ሰውም እንስሳውም በአጠቃላይ ሀገር ሰላም እንዲሆን፣ ለሁሉ ነገር ቸር እንዲሆን መመረቅና መመረቅ ይወደዳል::
ምርቃት ለማግኘት ሲሉም በጎ ነገር ለማድረግ የሚነሳሱ ሰዎችም አሉ:: ምንም እንኳን ምርቃት በዕድሜ የሚገደብ ባይሆንም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ሲመርቁ ግን ልብ ይሞላል::ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በጎ መሥራት ብቻ ሳይሆን፣ እንዲህ መልካም እሴት ያለው ምርቃትም እንዳይዘነጋ አስታዋሽ ያጡትን በመጎብኘት እርሳቸውም ተመርቀው ምርቃት እንዳይዘነጋ ማድረጋቸው ያስመሰግናቸዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በሚኖሩበት አካባቢ ሲወጡና ሲገቡ በሚያዩዋቸው የተጎሳቆሉ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ አቅመደካሞች ቤት እንዲታደስ ቤቱን በማፍረስ ነበር የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃግብርን ያስጀመሩት:: እንዲህ ያለው በጎ ሥራ ጧሪና ደጋፊ፣ ተመልካች ለሌላቸው አቅመደካሞች ትልቅ ትርጉም አለው:: በውስጣቸው የሚፈጠረው ደስታ በዕድሜያቸው ላይ አንድም ቀንም ቢሆን የመኖር ተስፋቸውን ያለመልምላቸዋል:: እንኳንስ ኑሮአቸውን የሚለውጥ በጎ ነገር መፈጸም በመጎብኘት ወገናዊነትን ማሳየት በራሱ ትልቅ ዋጋ አለው:: ሰው ሆኖ ሰው የሚናፍቅ መኖሩ ሊዘነጋ አይገባም:: በተለይ ደግሞ አንድ ሀገር መሪ ዜጎቹን የትናችሁ፣ ምንስ ጎደላችሁ ብሎ ሲጎበኝ የሚሰጠው ዋጋ ከፍ ይላል:: ሰዎች የመጨረሻ ምሬት ላይ ሲደርሱ ‹‹መንግሥት አላየኝም::ተዘንግቻለሁ:: የመንግሥት ያለህ›› አይደል የሚሉት:: ኑሮአቸው የሚመሰክረውን ሰዎች በመብራት ፈልጎ ለመደገፍ መነሳሳትና እነርሱም ሲደሰቱ ከማየት በላይ ምን የሚያስደስት ነገር አለ?
የበጎፈቃደኝነት አገልግሎት ጽንሰሀሳብ እንደየ ህብረተሰብ የዕድገት ደረጃ አካባቢያዊ ሁኔታ የሚለያይና አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም ባይኖረውም በራስተነሳሽነት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ የግል ኃላፊነት በመወጣት ሰብአዊ ተግባር መፈጸም እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ:: ሰብአዊነት ያለው ተግባር አለፍ ሲልም ሀገራዊና ብሄራዊ ግዴታዎች እንዳሉትና ለሀገርና ለወገን ያለውን ፍቅር ማሳያም እንደሆነ ብዙዎች ሀሳብ ይሰጣሉ::
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባደጉት ሀገራት የተለመደ ነው:: ከራሳቸው አልፈው ወደተለያዩ ሀገራት በመሄድ ጭምር በተለያየ መንገድ ነፃ አገልግሎት ሲሰጡ ይስተዋላል:: ኢትዮጵያም በአንድ ወቅት በትምህርት ዘርፍ ተጠቃሚ የሆነችበት ጊዜ አይዘነጋም:: በተለይም ከአሜሪካን ሀገር በጎፈቃደኛ ወጣቶች በወቅቱ ፒስኮር ተብለው የሚጠሩ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በማስተማር ነፃ አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር ይታወሳል::
ምናልባትም ያደጉት ሀገሮች ምንም ሳይጎልባቸው በጎ ፈቃደኝነቱ ከየት መጣ ትሉ ይሆናል::የበጎ ፈቃድ ተግባር የግድ ከኢኮኖሚ አቅም ጋር ብቻ መያያዝ የለበትም:: ከጎናቸው የቅርብ ሰው የሌላቸውንም መጎብኘት ዋጋ አለው:: ለዚህም ነው የበጎፈቃድ አገልግሎት አንድ ትርጉም ብቻ የማይሰጠው:: ግለኝነቱ በበዛበት ያደጉ ሀገሮች የሚጎበኝ ሰው ያስፈልገዋል::እንደሚታሰበውም ሁሉም ኢኮኖሚያዊ አቅሙ ያደገም አይደለም:: በእነርሱ ቋንቋ ሆምለስ (ቤት አልባ)የሆኑና የሰው እጅም አይተው የሚያድሩ አሉ:: ስልጣኔው የበዛ በመሆኑ ሰዎች የተረፋቸውን ምግብ ለምስኪኖች መስጠት ከፈለጉ የሀገሩ መንግሥት ለዚሁ ተግባር ባዘጋጀው የማቀዝቀዣ ቤት (ፍሪጅ) ውስጥ ያኖሩላቸዋል:: ይህን ሀሳብ በአንድ ወቅት ጠቅላይሚኒስትር ዶክተር ዐብይም አንስተውት ነበር:: በኢትዮጵያም በተለይ እንደ አዲስአበባ ከተማ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ቢለመድ በቀን አንዴ እንኳን ምግብ የማያገኙ ወገኖች ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ነበር ሀሳብ ያነሱት:: በአካባቢያችን እንደምናስተውለው ገና የቤተሰብ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ታዳጊዎች አዳራቸው ጎዳና ምግባቸው ደግሞ ከገንዳ ውስጥ ነው:: እንዲህ ያሉ ወገኖችን መታደግ ትልቅ የበጎተግባር ሥራ ነው::
እንዲህ በተለያየ መልኩ የሚገለጽ ብዙ ነገር ይጎላቸዋል ተብሎ በሚታመንባቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገሮች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቢለመድ ብዙ ማትረፍ ይቻላል:: የነፃ በጎፈቃድ አገልግሎት በኢትዮጵያም እየተለመደ መምጣቱን ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል:: ባለፉት ሶስት አመታት በሀገሪቱ እዚህም እዛም በተፈጠሩ ሁከቶችና ግርግሮች በነበረው አለመረጋጋት የበጎፈቃድ አገልግሎት ቢቀዛቀዝም በችግር ውስጥ ተኮኖም የተለያዩ የበጎ ሥራዎች ተሰርተዋል:: ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በወጣቶች ተሳትፎ ያረጁ ቤቶች የማደስ ሥራ ተከናውኗል:: ጣናን ሥጋት ላይ የጣለውን የእምቦጭ ዓረም በትብብር ለማስወገድ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጡ በጎፈቃደኞች ተሳትፈዋል::በተቆርቋሪነት የተደረገው ጥረት ሀገራዊ ስሜትን ያሳደረ ነበር:: ቀደም ባሉት አመታት ደግሞ እንቅስቃሴው የሰፋ ነበር::
ሰኔ ግም ብሎ ክረምቱ ሲገባ ከአፀደ ህፃናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአመቱን የትምህርት መርሃግብር ሲጨርሱ የበጎፈቃድ አገልግሎቱ ሥራ ይከተላል:: በተለይ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወደየአካባቢያቸው ሲመለሱ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሁለት ወር ክረምት በማስተማር ያግዟቸዋል:: በዚህም ተማሪዎች የትምህርት ውጤታቸውን በማሻሻል ተጠቃሚ ሆነዋል:: በከተሞች ደግሞ የትራፊክ አገልግሎት ላይ በመሰማራት አደጋን ለመቀነስ የተደረገው ጥረትም አይዘነጋም:: የትራፊክ ፍሰቱ እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት በተለይም እንደአዲስ አበባ ከተማ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በሰፋበት በመደበኛ የትራፊክ አገልግሎት ሰራተኛ ብቻ ክፍተቱን መሙላት አይቻልም:: ወጣቶቹ የዝናብ መከላከያ እንኳን ሳይኖራቸው የሚሰጡት አገልግሎት ያስመሰግናቸዋል::
በጎ ሥራ መጎልበትን እንጂ መቀዛቀዝ የለበትም:: አሁን በሀገራችን እየታየ ያለው ሰላምና መረጋጋት ብዙዎችን አረጋግቷል:: የበለጠ እንዲረጋገጥ ደግሞ ከእያንዳንዱ ዜጋ ብዙ ይጠበቃል:: አሁን ወደኋላ ተመልሰን እኩይ የሆኑ ተግባሮችን የምናስብበት ወቅት ላይ አይደለንም:: ፊታችንን ወደልማትና በጎ ተግባር ሥራ ማዞር ይኖርብናል:: በተለይም ተፈጥሮ በነበረው ሁከትና ግርግር ብዙ ሀብት ጠፍቷል:: በዚህም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ተፈጥረዋል:: በተለይም ተማሪዎች በተፈጠረው አለመረጋጋትና በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ምክንያት ተጎድተዋል:: የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ያንን የሚያካካስ ሥራ ቢሰሩ የዜግነት ግዴታቸውን ተወጡ ማለት ነው:: መልሶ መጠገኑን መንግሥት ለብቻው የሚወጣው ብቻ ሳይሆን የበጎ ተግባር ትብብር ያስፈልገዋል:: በተለይም ወጣቶች ብሩህ የሆነውን አዕምሮአቸውንና ትኩስ ጉልበታቸውን ለበጎ በማዋል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል:: የክረምት ወቅቱ በጎ ተግባር የምንፈጽምበት እንዲሆን መልካሙን ሁሉ ይግጠመን::
ክረምቱ ተማሪዎች የሚያርፉበት ጊዜ በመሆኑ በዚህ ወቅት ላይ ብቻ ትኩረት የተደረገ እንጂ በጎ ተግባር በጊዜ መገደብ እንደሌለበትም መዘንጋት የለበትም::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2013