ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ገና ከጥንስሱ ብዙ አዎንታዊና አሉታዊ ሀሳቦችን ያስተናገደ ቢሆንም የአውሮፓውያኑ እና የአሜሪካኖቹ የ‹‹እኔ አውቅልሀለሁ›› ውትወታ ግን ከነበሩ ሀሳቦች ከብዙ በጥቂቱ ጎልቶ፣ ከፍቶና ከርፍቶ የታየበት ወቅት ነበር። ከእነ እኔ አውቅልሀለው ባዮቹ ነጮች አስተያየት እጅግ በጣም ያናደደኝና ይህን ፅሁፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ አንዳንድ የአገሬ ምሁራን ሟርት መሳይ ደቀ መዝሙራዊ ንግግር በመነሳት ነው።
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ምዕራባውያኑ በገመቱልን ሳይሆን ‹‹ቅኔ›› የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ባሰበውና ባቀደው ልክ፤ አንድ አገራዊ ምርጫ ቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ ወቅት እና ድህረ ምርጫ ሊያሟላው የሚገባውን መስፈርት አሟልቶ የተገኘ ነው። ምርጫውም ምዕራባውያኑን እስኪገርማቸውና እስኪደንቃቸው ‹‹ላም ባልዋለበት…›› የሚባለው አባባል እውን ሆኖ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ ተጠናቋል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በውጤት መጠባበቅ ድባብ ላይ እንገኛለን።
የሁለቱ ምርጫዎች ወግ
አገሪቱ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ባካሄደችው አገራዊ ምርጫ የአንድ ቡድን ሀሳቦች ብቻ ቦታ እየተሰጣቸው እንዲጓዙ የተደረገበት ልምድ የሚዘነጋ አይደለም። በመሆኑም ምርጫ በየ አምስት አመቱ ሊካሄድ በታሰበ ቁጥር በሶስቱም የምርጫ ምዕራፎች ውስጥ የነበረው ኢ-ፍትሀዊነት አይን ያወጣ ነበር። ፓርቲዎች አለን የሚሉትን ሀሳብ ለህዝብ ለመሸጥ የነበራቸው እድልና የሚሰጣቸው የመገናኛ ብዙሀን የአየር ጊዜ እና የጋዜጣ አምድ ፓርቲዎች ቀደም ባለው ምርጫ ባገኙት የምክር ቤት መቀመጫ ቁጥር ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ደግሞ አዲስ ፓርቲን ካለማበረታታቱ ባለፈ ነባሮቹንም ቢሆን የሚደረግላቸው የፋይናንስ ድጋፍ ጭምር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም።
በቅድመ ምርጫው ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የነበረው የውድድር ሜዳ እጅግ የጠበበ ነው። በአንፃሩ ሜዳው ለራስ ሲቆርሱ ነውና ለኢህአዴግ ሙሉ ነበር። የመንግስትን ሀብት ለፓርቲ ጥቅም በሚገባ ከመጠቀም ጀምሮ የቅስቀሳ ምህዳሩን በብቸኝነት በመያዝ በሚገባ ተጠቅሞበታል። ስብሰባ ለመጥራት የሚከለከሉ ተቃዋሚዎች በርከት ያሉ ናቸው። ከዚህ የከፋው ግን ሀሳብን በነፃነት የመጠቀም መብታቸውን በመነፈግ ለእስር የሚዳረጉ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ብዛት ቤት ይቁጠረው።
ሁለት አገራዊ ምርጫን ያደረገው ህዝቡ በ1987 እና 1992 ዓ.ም ባገኘው ተሞክሮና ትዝብት መነሻነት በ1997 ዓ.ም ባደረገው ምርጫ የመምረጥ መብቱን በመጠቀም ህወሓት-ኢህአዴግን ለመቅጣት ያሰበው ድርጊት ህዝቡን ብዙ ዋጋ እንዲከፍል አድርጎታል። በ97 የምርጫ ወቅት ቅድመ ምርጫው ላይ የነበረው ነፃነት ካለፉት ሁለት ምርጫዎች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ነበር። ከአየር ሰዓት እና ጋዜጣ አምድ አጠቃቀም ውጭ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተቃዋሚዎች ሀሳባቸውን በሚገባ ለህዝብ የሸጡበት በመሆኑ ልዩነት ፈጥረዋል። በምርጫው ወቅትም ህዝቡ በነቂስ በመውጣት ድምፁን ሰጥቷል። በዚህም ህዝቡ ኢህአዴግን በሚገባ የቀጣበት መሆኑን የተረዳው የአቶ መለስ አስተዳደር የተፈጠረ ችግር ባልነበረበት ሁከት በመፍጠር የህዝብን ድምፅ ለመስረቅ ባቀዱት ልክ የበርካታ ወጣቶችን ነፍስ በልቶም ለዲሞክራሲ የነበረው እድል ጅማሮ በከፋ ሁኔታ ተጨናገፈ። አቶ መለስ በዚህ ድርጊታቸው ‹ኢህአዴግ አፈር ልሶ፣ አፈር አልሶ› እንዲነሳ አደረጉት።
በአንፃሩ የዘንድሮ ምርጫ ልዩነት የፈጠረ ነው ሲባል ምዕራባውያኑ እና አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳሟረቱት ሳይሆን በግልፅ እንደታየው በሶስቱም የምርጫ ምዕራፎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሳይቀሩ የተሳካ ነበር። በርካታ የምርጫ ታዛቢዎች ሰላማዊና ነፃ መሆኑን የመሰከሩትን የዘንድሮ ምርጫ ከ97ቱ ምርጫ ጋር እያስተያየን አሳጥረን የምርጫ ወጎችን እንጨዋወት። ይህን ወግ የምናወጋው በተጨባጭ መረጃ ላይ እንጂ በሟርት ላይ ተመስርተን አለመሆኑን ልብ ይሏል።
በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በቅድመ ምርጫው ወቅት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን ለመሸጥ የተሰጣቸው የአየር እና የጋዜጣ አምድ ድልድል እንደ 97ቱ ምክር ቤት ባገኙት ወንበር ልክ ሳይሆን ለሁሉም ፓርቲዎች ገዢ ፓርቲውን ጨምሮ እኩል ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ተደልድሎላቸው ነው። በፓርቲ ደረጃ በነበራቸው ቅስቀሳም ቢሆን የመንግስት ሀብት ለፓርቲ የመጠቀም ሁኔታ አልተስተዋለም። ይህ ሁኔታም የቅድመ ምርጫውን ሜዳ እኩል እና ፍትሀዊ አድርጎታል። ይህን እድል በሚገባ የተጠቀሙ ፓርቲዎችም ሂደቱን ከማመስገን ባለፈ ‹‹ትልቅ ልምድ የተገኘበት ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል።
በመሰረቱ ይህ ለአገሪቱ አዲስ እና መልካም የዲሞክራሲ መሰረት የጣለ ነው። በዚህ ጊዜ ፓርቲዎች ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው ነበር ማለት እንዳልሆነ ግን ልብ ሊባል ይገባል። ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ችግር በገጠማቸው እና መስተካከል አለበት በሚሉት ጉዳይ ለመንግስትም ሆነ ለምርጫ ቦርድ በማሳወቅ ችግርን በጋራ እየፈቱ የተጓዙበት መንገድ እጅግ አመርቂ ነበር። በምርጫ ወቅትም በድህረ ምርጫው ወቅት ከሁሉም አካል የተስተዋለው ሁኔታ 97 ተፈፅሞ ከነበረው ሴራ ጋር ፍፁም የሚነፃፀር አይደለም።
ዘንድሮ ህዝቡ የመምረጥ መብቱን ለመጠቀም የነበረው ተነሳሽነት ምርጫ ቦርድ የድምፅ አሰጣጡ እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት እንዲራዘም ያስገደደ ነበር። በማግስቱም ቢሆን መንግስት የህዝብ ድምፅ ለመስረቅ ያደረገው ተግባር አልነበረም፤ሁከት እና ግርግር በመፍጠር የተወሰደ ሳጥን የለም፤ ሰላም የሚያደፈርስ አዲስ ኮሽታም አልነበረም። ከ97ቱ በተለየ አጨራረስም ህዝቡ በዘንድሮው ምርጫ በነፃነት የሰጠውን ድምፅ ውጤት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ግን የምርጫውን አጠቃላይ ሁኔታ ለማደናቀፍ በገሀድም ሆነ በድብቅ ሲሰሩ የነበሩ አገራት እና ድርጅቶች እንዳወሩት ሟርት እና እንደ ሄዱበት የሁከት እና ትርምስ የመፍጠር ተግባር ሳይሆን ህዝብና መንግስት ተናበው ባከናወኑት ልክ ምርጫው ሰላማዊ፣ነፃና ዲሞክራሲያዊ በመሆኑ እጅጉን እንዲያፍሩ አድርጓቸዋል።
ምዕራባውያኑ ካቋቋሙዋቸው መገናኛ ቡዙሀኖቻቸው ጋር ተዳምረው ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የምርጫውን አጠቃላይ ሁኔታ ለማጠልሸት የሄዱበት ርቀት በእርግጠኝነት በምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ ከመጠናቀቅ አኳያ ራሳቸውን የታዘቡበት እንደሆነ ብዙ ማሳያዎች አሉ። ከላይ ያነሳናቸው መገናኛ ብዙሀን ‹‹የመረጃ ምንጮቻቸው እነማን ናቸው?›› ብሎ ለሚጠይቅ ብልህ ኢትዮጵያዊ የሚሰጠው ምላሽ አሊያም የሚቀርቡለት ምንጮች አÕጊ ናቸው። አንዳንዶቹ የጁንታው ሰዎች እና ተቋማት ይሆኑና እንደ እነ አፈቀላጤው ጌች እና ደብሪፅ በረሀ ገብተዋል የሚል ተረት ተረት መልሶችን ታገኛለህ። በአንፃሩ ደግሞ ‹‹ምሁራንን›› አነጋግረናል በሚለው ገፅታቸው ደግሞ እነ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን የመሰሉ ምሁራን ተብዬዎችን እናገኛለን። እኝህን ሰው ምንጭ በማድረግ ረገድ በርካታ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሀን ይጠቀሳሉ። በተለይ በምርጫው ሰሞን ከቤቲ ሾው ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ላይ ያነሷቸውን ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› አይነት ሀሳቦች በሚገባ ተጠቅመዋል።
የእንጀራ ምሁራን
‹‹ምሁራን ማለትን በትክክል ያሳወቀን የለም…›› ይላሉ ነብሳቸውን ይማር እና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም። እኚህ አባት በአንድ ወቅት በህወሓት-ኢህአዴግ ዘመን ምሁራን ተብዬዎች የሚናገሩት እና የሚከውኑት ሁሉ ግራ ቢያጋባቸው ‹‹ዛሬስ የምሁራን ትክክለኛ ትርጉም ምን ይሆን?›› ሲሉ አንጀታቸው እያረረ በቁጭት ያነሱትን ሀሳብ ላካፍላችሁ ወደድኩ።
‹‹እኔ ሆዱ ሰፊ የሆነ እና ስምንተኛ ክፍል ጨርሶ በፌስቡክ ላይ የሚፅፍ ሁሉ ምሁር ነው ብዬ እነሳለሁ። ከዚያ በላይ በ12ኛ ክፍል በኩልም ይሁን በሌላ አቋራጭ መንገድ የሚገኙትን የትምህርት መጠሪያ ጌጦች ሁሉ ከእነ ዝባዝንኪያቸው የታቀፉ ሁሉ ምሁራን ናቸው፤ ቄንጠኛ ባርኔጣ ያደረጉና ጥቁር መነፅር የሚያደርጉትንም እጨምራቸዋለሁ፤ የሚሽሎከለኩም ይኖሩ ይሆናል።›› ሲሉ ሀሳባቸውን ተንፍሰዋል።
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተለይ ምዕራባውያኑን ያሳፈረ ቢሆንም የምእራባውያኑ አምላኪዎች እና ተላላኪዎች ስለ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻና ዲሞክራሲያዊነት የተጓደለ አድርጎ ብቻ ሳይሆን አስመስሎ ቆሻሻ ቀብቶ ለማቅረብ እንኳን ምንም እድል ያልሰጠ በመሆኑ ስለ ምርጫው ህፀፅ ማውጣት አልተቻላቸውም። ነገር ግን ከህግ ማስከበር ጋር እያስታከኩ በትግራይ ክልል እየተከናወነ ባለው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታና ድጋፍ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት መካከል ዥዋዥዌ የሚጫወቱት አለም አቀፍ ረድኤት ድርጅቶች እና አንዳንድ አገራት ሁኔታውን ከምርጫው ተአማኒነት ጋር በማገናኘት ጎዶሎ ነገር ፍለጋ ብዙ ፈልገው ቢያጡም ሀሰት ከመናገር አላገዳቸውም። በምርጫው ዲሞክራሲያዊነት እና ፍትሀዊነት ላይ የሚነሳ ጉዳይ ባለመኖሩ ወሬና ሟርቱ ሁሉ የአገሪቱን መፃኢ እድል መተንበይ ላይ ሊያተኩር ተገዷል።
የምዕራባውያኑን ዱካ የተከተሉት ፕሮፌሰር መረራ በቤቲ ሾው ላይ በነበራቸው ቃለ ምልልስ ያለምንም የፀጥታ ችግር የተጠናቀቀውን ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሊያወጡለት የሚችሉት እንከን ባለመኖሩ ዛሬም ‹‹ብሄራዊ መግባባት›› ያስፈልጋል ሲሉ በኢህአዴግ ዘመን ያነሱዋቸውን የተለያዩ አማራጮች አቅርበዋል፤ ዛሬም በምርጫው ማግስት የቆረቡበትን ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል በሚል ያነሱዋቸው ሀሳቦች አሉ።
ፕሮፌሰሩ የሚመሩት የፖለቲካ ድርጅት ኦፌኮ በኦሮሚያ ክልል ባለመሳተፉ ቅድሚያ ተጠያቂ አድርገው ማንሳት ያለባቸው የውስጥ ችግርን ነው። ኦነግም ቢሆን በተደጋጋሚ በሰጠው መግለጫው ‹‹የውስጥ ችግር ስላለብኝ በምርጫው አልሳተፍም›› ብሎ በይፋ መግለጫ ሰጥቷል። ኦፌኮም በዋናነት የራሱ የውስጥ ችግር እንጂ ሌላ የሚለው ባለመኖሩ ‹‹እኛ ያልተሳተፍንበት ምርጫ ምርጫ አይደለም›› ሲሉ መደመጣቸው ለከፍተኛ ትችት ጥሏቸዋል። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ ሲያሳድዳቸው ከኖረው ‹‹ከኢህዴግ የወረሱት ነው›› ሲሉ ሌሎች ምሁራን ይተቻሉ።
ከሳር ቤት ክዳን ላይ ‹‹አንድ ሳር ቢመዘዝ ውሀ አያፈስም›› ሲሉ የአገሬ አባቶች ይናገራሉ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ የፕሮፌሰር መረራን ያህል እድሜ ሲቃወም ብቻ የኖረ አለ ቢባል የሚገኝ አይመስለኝም። ነባር ምሁራን ነባር ሁኔታው ላይ የተኙ በመሆናቸው ለውጥን አይደግፉም። የእነሱን እንጀራ ለማያወፍር ለውጥ ተቃዋሚ እንጂ ደጋፊ ሊሆኑ አይችሉም። በመሰረቱም የእንጀራ ምሁራን ከለውጥ ጋር የሚሰለፉት የተሻለ ወፍራም እንጀራ የሚያቀርብላቸው ሲሆን ነው።
በአገሪቱ በተለይም በኦሮሚያ ክልል የተካሄደው ምርጫ ፍትሀዊነት እና ዲሞክራሲያዊነት ማውራት ይቻላል። በተለይ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ እስከ ምሽት ሶስት ሰዓት የመምረጥ መብቱን ለመጠቀም የሄደው ርቀት በእርግጥም አንድ ሳር የተመዘዘበት እንኳ አይመስልም። ህዝብ በምርጫው ያልተሳተፈ ፓርቲ ያለ እስከማይመስል ድረስ ነፃ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ አልፏል።
በእኔ እድሜ እንደተገነዘብኩት እንደ እነ ፕሮፌሰር መረራ አይነቱ ምሁር ራስን ከፍ ለማድረግ ሌላውን ዝቅ አድርጎ መገመት መነሻቸው ይመስለኛል። በመሆኑም ‹‹እኛ የምናውቀውን አያውቁም፤ እኛ የምናየውን እነሱ አያዩም፤ እኛ የምንሰማውን እነሱ አይሰሙም›› የሚል የሀሳብ አባዜ የተጠናወታቸው ናቸው። በመሆኑም በዘንድሮ ምርጫ ከመነሻው እስከ መድረሻው በምርጫው የተወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርገዋታል። እነርሱም አሸናፊ ናቸው።
ኢትዮጵያ አትፈርስም
ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግ መነሳት እና ኢትዮጵያ እንድትፈርስ መስራት ሁለቱ የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት እንዳላቸው ለአንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሚደበቅ ሀቅ አይደለም። በዚህ ምርጫ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ሶስት ምዕራፎች የነበራቸው የተሳካ ጉዞ ራሳቸው የመሰከሩለት ነው። ከእነዚህ ፓርቲዎች አብዛኞቹ አሸባሪ የተባሉ፤ ፀረ ህዝብ እና ፀረ አገር ተብለው በህግ ጭምር አገር እንዳይገቡ የተከለከሉ ነበሩ።
እነዚህ ፓርቲዎች ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው አይደለም ምርጫውን ያከናወኑት። የሚከሰቱ ችግሮችን በግልፅ በማንሳት እንዲስተካከል በማድረግ ዋጋ እየከፈሉ እንጂ ችግር በተገኘ ልክ ተቃዋሚ ሆነው በመገኘት አይደለም። በዚህ ጥረታቸውም በፅሞና ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ቃለ ምልልስ እንዳይተላለፍ በማድረግ ያቀረቡት ቅሬታ ተቋማዊ ነጻነቱን ተጠቅሞ የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን እንዳይተላለፍ አድርጓል። ይህ አንዱ ማሳያ ሲሆን በርከት ያሉ ተመሳሳይ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል።
መቼም የኢትዮጵያን መፍረስ እና መፈራረስ በመመኘት ‹‹ትፈርሳለች›› ያሉ አገራት እና ግለሰቦች የበዙበት ዘመን ቢኖር አሁን ያለንበት ዘመን ለመሆኑ ብዙ አስረጅ ማቅረብ አያዳግትም። ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያን የማፈረስ ህልማቸው ጥቅማቸውን አሊያም አልታዘዝ ባይነታችን ያመጣብን ጣጣ ነው ብዬ ልውሰድ። ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ሆኖ በተለይ ምሁራን ጎራ ውስጥ ከገቡ ጎምቱ የፖለቲካ ሰዎች ሲገኙ ግን ‹‹ምን ይሆን ጥቅማቸው?›› በማለት ለማነሳው ጥያቄ ምላሽ አይገኝም።
እውነት ለመናገር የዘንድሮ ምርጫ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለት ይቻላል በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሳካ ዝግጅት አድርገው ሀሳባቸውን በነፃነት ለህዝብ ሸጠዋል። ‹‹የእናቴ መቀነት…›› በሚለው ምክንያት በምርጫው ያልተሳተፉ እንደ እነ ኦነግ እና ኦፌኮ ያሉቱ ለቀጣይ ምርጫ ለመዘጋጀት ማቀድ እንጂ የዚህን ህዝብ የዲሞክራሲ ጥማት በመብቱ የማረጋገጥ ጅማሮ ለማንኳሰስ መሞከር ከወደቁበት ላለመነሳት የሚደረግ ከንቱ ድካም እንዳይሆንባቸው ፈራሁ። ምክንያቱም ህዝብ ፈርዷልና።
እናት ከመሳለሚያ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2013