የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን በጠቅላላ አቢይ አጀንዳቸው በሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን። የግድቡ ግንባታ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት በሀገር ቤትም በውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ከግብጽ ጋር በተያያዝነው ግብግብ እና የግድቡን ግንባታ የመጨረሻ ምዕራፍ ለማድረስ በሚደረገው ጥረትና ርብርብ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራኑን የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል። በአንድ ካርታ ብቻ የማትጫወተው ግብፅ አንዱ የሚመክን ሲመስላት በአንዱ እየተካች የማያልቀውን ሴራዋን በማክሸፍ ረገድ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራኑ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። በዚህ ረገድ ባለፍት ዓመታት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱና ምሁራኑ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ረገድ የነበራቸው የተሳትፎ ደረጃ እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ በርካታ ሊቃውንት ይናገራሉ። በሀገር ውስጥ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩ ምሁራን፤ በፖለቲካል ሳይንስና ውሃ እንዲሁ በታሪክ ጥልቅ እውቀት ያላቸው ምሁራን፣ በተለያዩ ተቋማት በግልም ጭምር የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን የግብጽን ሴራ ሲያጋልጡ መቆየታቸው አይካድም። ነገር ግን ተቋማትና ምሁራኑ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ምርምሮችን፣ ጥናቶችን በማድረግ፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እውቀትን መሰረት ባደረገ መልኩ በመከራከር ረገድ ተሳትፏቸው ደካማ መሆኑን ከሚናገሩት መካከል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበር እና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች የሚኒስትር አማካሪ እና የኢትዮጵያ የድርድር ቡድን የሕግ አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም እንድሪስ አንዱ ናቸው።
አምባሳደር ኢብራሂም፤ ታላቁን የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ግብጽና ሱዳን የጥቅም እና ፍላጎት በተፃረረ መልኩ አስገዳጅነት ያለው ስምምነት እንዲደረግ የቻሉትን ጥረት እያደረጉ ናቸው። ሀገራቱ በተሳሳተ አካሄድ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በተለይ ምዕራባውያኑን ከጎናቸው ለማሰለፍ ጫናዎችን እያሳደሩ እንደሚገኙ ይገልጻሉ። በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ዘንድ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን እውነት እውቀትን መሰረት ባደረገ መልኩ ግንዛቤ አለመፈጠሩ ለጫናዎቹ መወለድ ምክንያት መሆኑን ያመላከቱት አምባሳደሩ፤ ስለዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራን የተፈጠረውን ብዥታ በሳይንሳዊ እውቀትና በእውነት ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችን በማቅረብ የማጥራት ኃላፊነታቸውን በሚገባ ሊወጡ ይገባቸዋል” ሲሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱና ምሁራኑ ኃላፊነታቸውን በሚፈለገው ደረጃ እየተወጡ አለመሆኑ ነው ያመላከቱት።
ይህንን ሀሳባቸውን በማጠናከርም “በአባይና በህዳሴ ግድብ ላይ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ የሚስተዋሉ የግንዛቤ ክፍተቶች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ምሁራኖች በቂ ስራ ያለመስራታቸው ውጤት ነው” ሲሉ ሀሳቡን የሚያጠናክሩት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ዲንና መምህር አቶ ልጃለም ጋሻው ናቸው። አቶ ልጃለም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉትን የግንዛቤ ብዥታዎች በማጥራት ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራኖች ሚና ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ጥናትና ምርምርን መሰረት ባደረገ መልኩ ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ያሰበቻቸውና እየሰራቻቸው የሚገኙት ስራዎች የማንንም መብት እንደማይጋፋ፣ አብሮ የመበልፀግ፣ አብሮ የማደግ ፍላጎት እንዳላት፤ ይኼም ብሔራዊ መብቷ መሆኑን እንዲሁም የሉዓላዊነት ጉዳይ እንደሆነ በትክክል ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማስረዳትና ማሳወቅ እንዳለባቸው ይናገራሉ። ነገር ግን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቶቹ እና ምሁራኑ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ አለመሆኑን ያመላክታሉ።
‹‹የዓባይ ጉዳይ የውሃ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የኢትዮጵያ እድገት፣ የብልጽግና በር ቁልፍ ነው›› ያሉት አቶ ልጃለም፣ ሁሉም ማህበረሰብ፣ ተቋም፣ ዜጋ ግዴታውን መወጣት እንዲችል በማንቃት እንዲሁም ከውጪ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ተገቢ በሆነ መልኩ ምሁራዊ ምላሾችን በመስጠት ረገድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን ያለባቸውን ትልቅ ኃላፊነት መወጣት አለባቸው። በዚህ ረገድ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ባለሙያዎች በተገኘው አጋጣሚ የድርሻቸውን ለመወጣት በምርምር ስራ፣ በሳይንስ እና በዲፕሎማሲው ላይ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም ይጠቁማሉ። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታላቁን የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ስለመሆኑ ሌላው ማሳያ በዩኒቨርቲው የህግ ትምህርት ክፍል የዓለም አቀፍ የውሃ ህግ ፕሮግራም በድህረ ምረቃ ደረጃ እየሰጠ መሆኑን ነው።ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሀገራችን ብቸኛው የውሃ ህግ እና የአካባቢ ጥበቃ ላይ እያስተማረ የሚገኝ መሆኑን ያመላከቱት አቶ ልጃለም፤ ̋ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ዓመት የዓለም አቀፍ የውሃ ህግ ትምህርት ፕሮግራምን ለማጠናከር ወደ ሦስተኛ ዲግሪ የማሳደግ እቅድ ይዟል። ይህ መሆኑ ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁ የሆኑ በርካታ ተመራማሪዎች እንዲኖሯት ያደርጋል። በአባይ ዙሪያ ዓለም አቀፍ ተደራዳሪዎችን ለማፍራት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻችን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ትኩረት አድርጎ መስራት የሚገባ መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባቸው ያመላከቱት አቶ ልጃለም፤ “ይህ መሆን እንደሚገባው ከግብጾች ልንማር ይገባናል። ግብጾች ከየትኛውም የትምህርት ዘርፍ የውሃ ፖለቲካቸው በጣም ጠንካራ ነው፤ ምክንያቱም የኢኮኖሚያቸው፣ የልማታቸውና የማደጋቸው እንዲሁም የስልጣኔያቸው ሁሉ መሰረት ውሃ ስለሆነ በረጅም ዘመን ሂደት ውስጥ ተገንብቷል። በመሆኑም በእኛም አገር ተመሳሳይ ሁኔታ ሊኖር ይገባዋል” ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠቃልላሉ።
በዓገር አቀፍ ደረጃ ወጣቱ ትውልድ ስለ ዓባይ ወንዝና ስለ ህዳሴ ግድቡ እውነታ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማስቻል ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ ትምህርት መሰጠት እንደሚገባም ያመላከቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሥራት አፀደወይን ኢትዮጵያ የዓባይ ምንጭ ብትሆንም ጉዳዩን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ከማሳወቅ አንፃር ብዙ ክፍተቶች ያሉ መሆኑን ይገለጻሉ። “ይህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አመላካች ነው። በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያለውን መጓተት ወደ ትክክለኛው መስመር በማምጣት ረገድ የኢትዮጵያ ብቻ ሣይሆን የአፍሪካ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራን ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው “ይላሉ። በዚህ ረገድ ደግሞ የሌሎችን አህጉራት ተሞክሮ ይጠቅሳሉ። የአውሮፓ ምሁራን በአውሮፓ አገሮች መካከል ሊኖር ስለሚገባው ሁሉን አቀፍ ትብብር በመጻፍና በመምከር ያደረጉትን አስተዋጽኦ እናውቃለን። በተመሳሳይ መልኩ የኢስያ ምሁራን ‘አሲያን’ የተባለው ትብብር እንዲፈጠር ብዙ ደክመዋል። ስለዚህ ከአፍሪካ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ምሁራን ብዙ የሚጠበቅ መሆኑን ይናገራሉ። የአፍሪካ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ምሁራን በተለይ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየደረሰ ያለውን ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች ለመቋቋም እና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማስፈን እየተደረገ ያለው ጥረት እንዲሰምር በአብሮነት በመሥራት ሚናቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል” ሲሉ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የሚነሱ መጓተቶችን ለመፍታት የአፍሪካ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ምሁራን ኃላፊነት ጭምር መሆኑን በማመላከት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ያሳሰቡት።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን የህዳሴው ግድብ መሰረት ከተጣለበትና ከዲዛይን ጀምሮ ከፍተኛ የእውቀትና የክሂሎት ጉዳዮችን በማፍለቅ አስተዋጽዖ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያስታወሱ ሲሆን፤ ተቋማቱም ሆኑ ምሁራን ከመሰረቱ ጀምሮ አበርክቶ የነበራቸው ቢሆንም፤ ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ በውጪ ኃይሎች የሚደረገውን ጫና ለመመከት በሚደረገው ርብርብ ላይ ያላቸው ተሳትፎ በቂ ነው ለማለት የማያስደፍር አለመሆኑን ተናግረዋል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ‹‹ከአባይ ጋር ተያይዞ የሚወጡ የተዛቡና የተጣመሙ አካሄዶችን በእውቀትና በእውነት መሞገት እንዲሁም ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ የጋራ ድምጽ ማሰማት የግድ ይላል›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የኢትዮጵያ ምሁራኖቻችን በዓለም አቀፍ መጽሔቶች እውነትና እውቀትን መሰረት በማድረግና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ስለ አባይ መጻፍ፣ መሞገት፣ ምላሾችን መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በዚህ አግባብም ‹‹ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ የሚሰነዘሩ ጫናዎችን መመከት አለባቸው። በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲዎቻችን ለኢትዮጵያ የሚጠቅሙ ፕሮግራሞችን፤ በተለይ ደግሞ በዓለም አቀፍ ውሃ ህግ፣ በውሃ ቴክኖሎጂ፣ በውሃ ፖለቲካ ዙሪያ የሚሰሩ የትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሞች በጣም አስፈላጊ ናቸው። በዚህ ረገድ የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ተሞክሮ እንደ አርአያ በመቁጠር ወደ ተግባር ሊሸጋገሩ ይገባል” በማለት ሀሳባቸውን ይቋጫሉ።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2013