ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ባለሙያዎች መብቶቻቸውን እና የፈጠራ ስራዎቻቸውን ለማስጠበቅ እንዲያስችሏቸው ስራዎችን ለመስራት ማህበር አቋቁመዋል። በአሁኑ ወቅትም ይህን ማህበር አንጋፋው ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ በፕሬዚዳንትነት ይመራዋል። እርሱና የሙያ አጋሮቹም በተለይ መብቶቻቸውን ለማስከበር ህጎች እንዲወጡ ሲሰሩ ቆይተዋል።
በተለይ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የኮፒ ራይት ህግ እንዲወጣ በማድረግ ረገድ የእርሱ ሚና እንደ ማህበር ፕሬዚዳንትነቱ አንፃር ትልቅ ነበር። ይህ ህግም ተግባር ላይ እንዲውል ከባልደረቦቹ ጋር በቅንጅት ሰርቷል። ከዚህ መነሻም የሙዚቀኞች የኮፒ ራይት የሮያሊቲ ክፍያ ተጠቃሚ ለማድረግ የዜማ ደራሲን፣ ግጥም ፀሃፊን፣ አቀናባሪንና ድምፃዊን ያካተተ የሙዚቀኞች “ኮፒ ራይት ሶሳይቲ” ከመሰረቱ ሁለተኛ ዓመታቸውን አስቆጥረዋል። ከሚቀጥለው ዓመት በኋላም ሙዚቀኞች ከሮያሊቲ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደላድሎች ተሰርተዋል። አንጋፋው ሙዚቀኛና የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንት የዛሬው “የዝነኞች የእረፍት” እንግዳችን ነው።
ስለ አንጋፋው ሙዚቀኛ
ብዙዎች “በዘመናዊ ሙዚቃ ቅብብሎሽ ውስጥ ገና በለጋነት እድሜው ራሱንና ዘመኑን በሙዚቃ ዓለም ጥልቅ ባህር ውስጥ ያኖረ አንጋፋው የሙዚቃ ተጫዋችና አቀናባሪ” ይሉታል ዳዊት ይፍሩን። የ11 ዓመት ታዳጊ እያለ በቀድሞው ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ቲአትር ወይም በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲአትር ቤት መቀላቀሉን ይናገራል፡፡
የ11 ዓመት ልጅ በነበረበት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ቲአትር ለመማር በመጣበት ወቅት ህፃናት ባለማወቅ በጥፊ መቱት። ለሙያው ያለው ፍቅር ከፍተኛ ስለነበረ ከመቱት በኋላ ትዕግስተኝነትን በመላበስ ከቲአትር ቤቱ ጀርባ ተቀምጦ ማልቀስ ይጀምራል፡፡ በዚህ ጊዜ የሙዚቃ መምህር የነበሩት ሙሴ ነርሲስ ናልባንዲያ አባብለው ወደ ሙዚቃ ትምህርቱ መልሰውት ዛሬ ላይ ለደረሰበት እውቅና ቅጽበታዊ አጋጣሚ ተፈጠረለት፡፡ ያን ጊዜ ተስፋ ቆርጦ ከህልሙ ቢገታ ኖሮ የዛሬውን አንጋፋውን ሙዚቀኛ አናገኘውም ነበር። በሁለት ወር የትምህርት ቆይታ ልዩ ችሎታን የተላበሰው ዳዊት ወደ ኦርኬስትራ በመቀላቀል የዘመኑን ታላላቅ የቲአትር ቤቱ ድምፃዊያንን ማለትም የምኒሊክ ወሰናቸውንና የመልካሙ ተበጀን ስራዎችን አቀናበረ፡፡
የቀለም ትምህርቱን ከሙዚቃ ሙያው ጋር አብሮ በማስኬድና በንግድ ስራ ኮሌጅ በመመረቅ ለተወስነ ጊዜ በአዋሽ ሸለቆ ባለስልጣን በሒሳብ ሰራተኝነት (አካውንታት) በማገልገልና በማታው ጊዜ በሀገር ፍቅር ቲአትር ቤት የሙዚቃ ትምህርት ስልጠና ይሰጥ ነበር፡፡
ለሙዚቃ ስራዎች ልዩ ፍቅር በመስጠት ከአምስት የሙዚቃ ባለሙያ ጓደኞቹ ጋር በመሆን በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የመጀመሪያውን ‹‹ኤኬኤተርስ›› የተሰኘው ባንድ አቋቋሙ፤ በመቀጠልም ቬነስ ባንድ፣ ቬነስ ናይት ክለብ፣ ዳህላክ ባንድ ግዮን ሆቴል ውስጥ ኢትዮ ስታር ባንድ፣ ዋልያስ ባንድ እንዲሁም አይቤክስ ባንድ በማቋቋም ሰሩ፡፡ በኋላም ዳህላክና አይቤክስ ባንድን ያጣመረ ሮሃ ባንድ ተፈጠረ፡፡
ሮሃ ባንድ በወቅቱ በሚሰራቸው የሙዚቃ ስራዎች ከፍተኛ እውቅና የነበረው ሲሆን፤ ባንድ በዘመኑ ከ200 በላይ ካሴቶችን ወይም ከ2000 በላይ የሙዚቃ ስራዎች በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ የአመራርነት ሚናና የቅንብሩን ስራ ላይ ዳዊት ይፍሩ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ማህበር ኘሬዚዳንት ዳዊት ይፍሩ በህይወት ዘመኑ ለዘመናዊ ሙዚቃ እድገት ለስራቸው ሥራዎች ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ለሁለተኛ ጊዜ ተማሪዎችን ባስመረቀበት ወቅት ለዓለም ህዝብ ያበረከተውን ሙያዊ ብቃቱን በመገንዘብ የክብር ዶክትሬት መስጠቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
አንድነት፣ ሠላምና አርበኝነት በሙዚቃ ውስጥ
ቀደም ባሉ ጊዜያት ሙዚቀኞች አገራዊ ጉዳይን በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነትና ሉዓላዊነትን የተመለከቱ ስራዎች በፍቃደኝነትም ሆነ በግዳጅ ይሰሩ ነበር። በዚህ ውስጥ የአንጋፋው ኪ ቦርዲስትና አሬንጀር ዳዊት ተፅዕኖም አለበት።
እርሱ አሁንም ድረስ ይህን መሰል ሥራዎች እንደሚሰሩና እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ ይናገራል። ይሁን እንጂ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት መሰል ሙዚቃዎች ቢሰሩም ወደ መገናኛ ብዙሃን ባለመድረሳቸው ሚናቸው ያን ያህል እንዳልጎላ ነው የሚገልፀው። ነገር ግን በእነርሱ ዘመን በሠላምና በአገር ጉዳይ የተሰሩ ሥራዎች አሁንም ድረስ ሰፊ አድማጭ እንዳላቸው ይገልፃል። ይህ ዓይነት በጎ ምግባርም ከምንም በላይ መበረታታት እንዳለበትና ማህበራቸውም እንደሚደግፈው ነው የሚገልፀው።
መዝናናትና ዳዊት
አንጋፋው ሙዚቀኛ ዳዊት “ሁሌም ቢሆን ሙዚቀኛ ራሱ በሰራው ሥራ አይዝናናም” ይላል። እርሱም እንደዚያው ነው። ሥራዎቹ አንድ ጉድለት አላቸው ብሎ በማሰቡ ምክንያት ሙዚቃውን ሰምቶ ከመዝናናት ይልቅ የጎደለውን ነገር ማሰብ ይቀናዋል። ከዚያ ይልቅ ጥልቅ ሃዘንና ማሰላሰል ውስጥ ሲገባ ሙዚቃን መጫወት ያስደስተዋል። ከዚያ በተረፈ ዳዊት ከሥራ መንፈስ ራቅ ብሎ ለመዝናናት በሚያስብበት ወቅት ጋዜጦችን ማንበብ፣ ዜና መከታተልና መፅሃፍትን ማንበብ ያስደስተዋል።
አንጋፋው ሙዚቀኛ ታሪካዊ ቦታዎችን የመጎብኘት ልምድ አለው። በሥራ አጋጣሚም ሆነ አስቦበት የአገሩን ባህል፣ ቅርስና ታሪካዊ ሥፍራዎች ይመለከታል። እርሱ እንደሚለው “በፅሁፍና በትምህርት የሚታወቀውን በአካል ተገኝቶ ማየትና ሥሜቱን መጋራት ያስፈልጋል”። ዳዊት ወደ ወሎ ከሄድን ላሊበላን፤ ወደ ጎንደር ከተጓዝን የነገሥታቱን ቤተመንግሥት፤ ወደ ትግራይ ስናመራ የአክሱም ሐውልትና ታሪካዊ ቦታዎች፣ ወደ ደቡብ ሲኬድ ደግሞ በርካታ የአገሪቱን ባህላዊ ሥርዓቶችና ልምላሜ መመልከት እንችላለን ይላል። አይናችን ወደ ውጪ ከሚባዝኑ እነዚህን መሰል የአገራችን ሃብቶች ላይ ማተኮሩ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልፃል።
የዳዊትን መንገድ ለመከተል
ራእይ ሊኖረን ይገባል። ይሁን እንጂ “የግል ስኬት ላይ ለመድረስ ሁሉም በአንድ ሌሊት አይሳካም” ይላል አንጋፋው ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ። ህልማችንን ለመኖር ትዕግስት፣ ጥንካሬና የአላማ ፅኑነትን መካን እንደሚኖርብን ከበርካታ ዓመታት የህይወት ልምዱ ያገኘውን ትምህርቱን ያጋራናል።
የጥበብ ሰው በተፈጥሮ ካገኘው ሥጦታ በላይ ራሱን ሥኬት ላይ ለማድረስ ሁሌም ቢሆን ለመሻሻል ዝግጁ መሆን እንዳለበት ይናገራል። በማንኛውም ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ይህንኑ ሊከተሉ ይገባል የሚል ምክርም ይለግሳል። ወጣቶች ላመኑበት ነገር ሙት መሆን አለባቸው ይላል፤ አንድ ጊዜ በመውደቃቸው ብቻ ተሥፋ ሳይቆርጡ ደጋግመው (መቶ ጊዜም ቢሆን) መሞከር ይኖርባቸዋል የሚል እምነት አለው። ይኼ ፅናት በድምሩ አገር ይሰራል ሲል ይገልፃል። ሠላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20 ቀን 2013 ዓ.ም