የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የአፍሪካ መዲናም ጭምር የሆነችው አዲስ አበባ በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነቶች የሚከወኑባት ትልቅና የኢትዮጵያውያን ሁሉ መናሸሪያ ናት። ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በየጊዜው ወደ ከተማዋ የሚገቡ ዜጎች እንዲሁም በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ባለው የሀገሪቷ የህዝብ ቁጥር ምጣኔ የተነሳ የከተማዋ የህዝብ ቁጥር በብዙ እጥፍ እያደገ ይገኛል።
አዲስ አበባ ከተለያዩ የሀገሪቷ ክልሎች ወደ ጉያዋ የሚመጡ ዜጎቿን መቀበል የሚያስችል ቁመና ባይኖራትና ዝግጁነቷም ባይረጋገጥ ሁሉን አቅፋ ማደር የምትችል ሆደ ሰፊ ከተማ በመሆኗ ብዙዎች ወደ ጉያዋ ይገባሉ። በልቶ ጠጥቶ የሚያድር የማይመስለው የህዝብ ቁጥር ሁሉ ሲመሻሽ ወደ ማደሪያው ገብቶ ሲነጋጋ ደግሞ ከየጉራንጉሩ ብቅ ብቅ ሲል መታየቱ ገመና ሸፋኝ ከለላ ሰጪ መሆኗን ያሳያል። ታድያ ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል እንዲሉ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየኖሩ ከመቃብር ባልተናነሰና እጅግ በተጎሳቆለ ቤት ውስጥ ከሚኖሩ ነዋሪዎች አንስቶ እጅግ ዘመናዊና ቅንጡ በሆኑ የመኖሪያ አፓርትመንቶች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችም አሉ።
በከተማዋ የሚገኙ ዜጎች እጅግ የተራራቀ የኑሮ ደረጃ ያላቸው በመሆኑ ጥቂቶች ጫፍ የወጡ ባለጸጎች ሆነው ቅንጡ የሆነ ኑሮ ሲኖሩ፤ አብዛኛው የከተማዋ ህዝብ ግን እጅግ በተጎሳቆለ የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ሆኖ በችግር ይጠበሳል። ይህም በሀገሪቷ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ያለመኖሩን የሚያሳይ ስለመሆኑ ብዙዎች ያነሳሉ። በተለይም በአዲስ አበባ ከተማና በክልል ከተሞች የሚስተዋለው የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እጥረት እና የፍላጎት መበራከት እጅግ ሊጣጣሙ ያልቻሉ ጉዳዮች ሆነው ሰንብተዋል።
ከዚህም በላይ በከተማዋ ያሉት በርካታ መኖሪያ ቤቶች ዘመን ያለፈባቸውና ያረጁ ያፈጁ ለነዋሪዎች ምቹ ያልሆኑ የስጋት ምንጮች ስለመሆናቸው በግልጽ የሚታይ ሀቅ ነው። በዚህም ነዋሪዎች ዘርፈ ብዙ ለሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሲጋለጡ ይስተዋላል። በተለይም ክረምት በመጣ ቁጥር ዝናብ ወደ ቤት ገባ አልገባ እያሉ በሰቀቀን ኑሯቸውን የሚገፉ የአዲስ አበባ ከተማ አቅመ ደካማ ነዋሪዎችን ቤቱ ይቁጠራቸው።
ብዙ አቅመ ደካማ አዛውንቶች የቤታቸው ጣራ የክረምቱን ዝናብ መመከት አቅቶት በዝናብ ወጨፎ እየራሱ፣ በንፋስና ውርጩ እየተርገበገቡ ኑሮን ይገፋሉ። ቤት አይባል ቤታቸውን ከላይ ከጎን ላስቲክ ሸፍነው በላስቲክ ውስጥ ተደብቀው የክረምቱን ማለፍ በጉጉት ይጠባበቃሉ።፡ እነኚህ አቅመ ደካማ ነዋሪዎች ምርጫ የላቸውምና የባሰ እንዳይመጣ ፈጣሪያቸውን በመማጸን አንድ ቀን ይሳካ ይሆናል በሚል ተስፋ ኑሮን በሰቀቀንና በስጋት ሲገፉ ኖረዋል። አሁንስ እነዚህ አቅመ ደካማ ዜጎቻችን ባዘመሙ ጎጆአቸው ይቀጥሉ ወይስ እንድረስላቸው የሚለው ነው ወቅታዊው ጥያቄ።
እርግጥ ነው ከተማዋም እያደገችና እየሰፋች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ አዳዲስ የመኖሪያ መንደሮች እንደሚያስፈልግ ሁሉ ያረጁ ቤቶችን በአዲስ የመቀየር ሥራን መስራት የግድ ይላል። ለዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን የተለያዩ ተግባራትን በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ዋል አደር ብሏል።
ምንም እንኳን ከተማዋን ቀፍድዶ ከያዛት የመኖሪያ ቤት ችግር በአንድ ጊዜ መንጭቆ ማውጣት ባይቻልም ከተማ አስተዳደሩ ቀስ በቀስ ችግሩን ማቃለል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል። ከተማ አስተዳደሩ ተግባራዊ እያደረጋቸው ካሉት የቤት ልማት ፕሮግራሞች በተጨማሪ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ የተጎሳቆሉና ያዘመሙ የአቅመ ደካማ እናቶችን ቤት ማደስና ማቅናት አንዱ ነው።
በከተማዋ የሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው አቅመ ደካማ እናቶች ቀድሞውኑ በከፋ ድህነት የተጎዳው ሕይወታቸው በቤታቸው ጣሪያና ግድግዳ መጎሳቆል የተነሳም የከፋ ችግር ላይ ወድቀው ይታያሉ። እነዚህ ዜጎች ታድያ በአቅም ማነስ የዘመመ ጎጆአቸውን ማቃናት የሚያስችል አቅም ባይኖራቸውም ፈጣሪያቸውን እየተማጸኑ ከችግራቸው ጋር ለመኖር ተገድደዋል። የቤቶቹ ጣሪያና ግድግዳ የክረምቱን ዝናብ መመከት አቅቶት ጎጇቸው ከዘመመባቸው የአዲስ አበባ ከተማ መንደሮች መካከልም በቤተ መንግስት ዙሪያ የሚገኘው አቧሬ ተብሎ የሚጠራው ሰፈር አንዱ ነው።
ምንም እንኳን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሚፈራረቁባት አዲስ አበባ ከተማ በእጅጉ የተጎሳቆሉና እድሳት ሳያገኙ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችን ማየት የተለመደ ቢሆንም ሁሉም ሰው አካባቢውን ቢያጸዳ ሀገር ትጸዳለች እንደሚባለው ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ከሪፐብሊካን ጋርዶች ጋር በጋራ በመተባበር በአካባቢያቸው የሚገኙ የተጎሳቆሉ ቤቶችን ለማደስ የጀመሩት ሥራ በሁሉም አካባቢ ቢተገበር ሀገር በብዙ ትለወጣለች።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ከዛሬ ሶስት ዓመት ጀምረው ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተለያዩ በጎ ተግባራትን ግንባር ቀደም መሪ ሆነዋል። ለሌሎችም መልካም ተሞክሯቸውን በማካፈል መተባበርንና መደጋገፍን በስፋት አስተምረዋል። በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራቸውም 15 የሚደርሱ የአቅመ ደካማ እናቶችን ደሳሳ ጎጆ ለማደስ ሥራውን አስጀምረዋል።
ቤቶቹን የማደስ ሥራ በተጀመረበት አቧሬ አካባቢ የሚገኙት ነዋሪዎችም የክረምቱ መምጣት በእጅጉ ያስጨነቃቸውና ከዘመመ ጎጆቸው ሥር ከችግር ጋር የሚታገሉ አቅመ ደካማ እናቶች ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም እየከበደ የመጣውን ክረምት ቀድመው 15 ለሚደርሱ የአቅመ ደካማ እናቶች መኖሪያ ቤት ለማደስ ባሳለፍነው ሳምንት ሥራ ጀምረዋል። በወቅቱም ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውና ገቢያቸው እንኳንስ የሚያፈስ ጣራቸውን ለመቀየር በልቶ ጠጥቶ ለማደርም የማይቻላቸው እናቶች ስለተደረገላቸው ነገር በብዙ ሲያመሰግኑና ሲደሰቱ ታይተዋል።
ቤታቸው እድሳት ሊያገኝ ከተመረጡት 15 ቤቶች መካከል የወይዘሮ ይርገዱ ከበደ ደሳሳ ጎጆ አንዱ ነው። ወይዘሮ ይርገዱ ደካማና ችግርተኛ እናት ከመሆናቸው በተጨማሪ ማየት የተሳናቸው እናት ናቸው። ታድያ እጅግ በተጎሳቆለው ደሳሳ ጎጇቸው ውለው ቢያድሩና ዘመናትን ቢያስቆጥሩም የክረምቱ መምጣት ግን እንደ ሁልጊዜው አስጨንቋቸው ሰንብቷል። የቤታቸው ጣራ ዝናቡን መመከት ያቃተውና የሚፈስባቸው ሲሆን ግድግዳውም እንዲሁ የፈራረሰ በመሆኑ ብርድና ቁሩ ይፈራረቅባቸዋል። የተቦጫጨቀ ዲሪቶ የሚመስለውን ግድግዳቸውንም ከጎረቤቶቻቸው ካርቶን ወረቀት ለምነው ለመሸፈን እንደሞከሩ ይናገራሉ። ቢሆን ብለው እንጂ ካርቶን ያውም በክረም መቼ ከዝናብ ያድናል። ብቻ ዝም እንዳይሉ ከንፋስ አያስጥል ከጎርፍ የሆነውን ቤት ሸፈን ሸፈን አድርገዋል።
እንደ ወይዘሮ ይረገዱ ሁሉ በዚሁ አቧሬ አካባቢ የሚገኙና ክረምት በመጣ ቁጥር ለሀሳብና ጭንቀት የሚዳረጉ ሌሎች እናቶችም ከችግራቸው ጋር እየታገሉ አንድን ቀን ተስፋ በማድረግ ዘመናቸውን ሙሉ አሳልፈዋል። ያማሩ ቤቶችን አይተውና ተመኝተው። ችግሩ ሊለመድ የማይችል ፈታኝ ከመሆኑም በላይ በተለይም የክረምት ወቅት ኑሯቸውን የከፋ አድርጎታል። ታድያ ዛሬ እነዚህ እናቶች ለዓመታት ከገቡበት የክረምት መጣ ጭንቀት ኑሮ ሊላቀቁ ሆነና እጅጉን ተደስተዋል። ምንም እንኳን ጉልበታቸው ቢዝልና አቅማቸው ቢደክምም ከዘመናት ጭንቀታቸው ተላቅቀው፤ በእፎይታ ሊያድሩ ነውና ልባቸው በተስፋ ተሞልቷል።
በተለይም እነዚህን አቅመ ደካማ እናቶች ካሉበት ችግር ለማላቀቅ ከደሳሳ ጎጇቸው ደጅ ተገኝተው የተዳከሙና የዘመሙ ጎጇቸውን የማቅናትና የማደስ ሥራን በግንባር ቀደምትነት ላስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እነዚሁ እናቶች ‹‹ከጭቃና ከጭለማ አወጣን›› በማለት የላቀ ምስጋናና ምርቃት ሲያደርሱ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡበት ከዛሬ ሶስት ዓመት ጀምረው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በተግባር ሲያሳዩ ተስተውሏል። ከዚህም ባለፈ ይህን በጎ ተግባር አጠቃላይ ማህበረሰቡን ጨምሮ ሌሎች አካላትም ተሳታፊ እንዲሆኑ በብርቱ የሰሩ በመሆኑ በርካቶችም የዚሁ በጎ ተግባር ፈለግ ተከታይ ማድረግ ችለዋል።
በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አቧሬ አካባቢ በሚገኙ የተጎሳቆሉ ቤቶችን ለማደስ በዕለቱ ሰባት ደሳሳ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማፍረስ የእድሳቱ ስራ ተጀምሯል። ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ የተጎሳቆሉና የዘመሙ ቤቶችን ለማደስ አቅደው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የበርካታ አቅመ ደካማ እናቶች ቤት እንደሚሞቅና እፎይታን እንደሚያገኙም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። አያይዘውም አቅመ ደካሞችን የመርዳት ተግባር ሁሉም ሰው ሊተገብረው የሚገባና አስፈላጊ እንደሆነ ሲናገሩ፤ ‹‹በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ባላቸው አቅም በትብብር አቅም የሌላቸውና በዕድሜ የገፉ እናቶችን እየለዩ አቅም ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ከተማ አስተዳደሩን ጨምሮ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም እንዲሁ ቢተባበሩና የዘመሙ የእናቶችን ቤት ቢያቀኑ ኢትዮጵያ በብዙ ትጠቀማለች። ከዛም በላይ አቅመ ደካማ እናቶች እፎይ ብለው አርፈውና ከስጋት ተላቅቀው ሲተኙ ይመርቃሉ። ምርቃታቸውም ለሁላችንም ጠቃሚ ነው ። ስለማንተባበር እንጂ ስለሌለን አይደለም የምንቸገረው›› በማለት ከመተባበር በሚገኘው ውጤት ተጠቃሚ እንደሆነ ጥሪ አቅርበዋል።
የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ የክረምት በጎ ፍቃድ ስራን ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስተሩ፤ የተዳከሙና የተጎሳቆሉ አቅመ ደካሞችና የእናቶችን ቤት ለማደስ አቅደው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ውለው ማደራቸውን አንስተዋል። ከሪፓብሊካን ጋርድ አባላት ጋር በመሆን የጀመሩት ቤቶችን የማደስ የክረምት የበጎ ፍቃድ ስራ ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ በተለያዩ ጊዜያት በክረምት ወቅቶች ተግባራዊ ሆኗል።
ባለፉት ጊዜትም የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስና ለህብረተሰቡም ተመሳሳይ ጥሪ በማቅረብ በርካታ ቤቶች እንዲታደሱ አድርገዋል። አሁንም በተመሳሳይ ለመላው ኢትዮጵያውያን ባቀረቡት ጥሪ እንዲህ አይነቱን የመረዳዳት ባህል በማጠናክር፤ ለልማት ትኩረት በመስጠት የአገሪቱን ብልፅግና ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል። የመገናኛ ብዙሀን አካላትም ሁነቱን ከመዘገብ ባለፈ እነርሱም በአካባቢያቸው ላሉ አቅመ ደካሞች ተመሳሳይ ተግባር እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጠይቀዋል።
አቅመ ደካሞችን መደገፍ ፣ ደሳሳ ጎጆአቸውን ማደስ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው የዘንድሮ ክረምት የበጎ አድራጎት አንዱ ስራ ነው፤
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2013