ሰዎቹ ጠዋት ማታ ይጨቃጨቃሉ። በየምክንያቱ በየአጋጣሚው የሚጋጩበት አያጡም። ሁሉም ከዓመታት በፊት ስለነበራቸው ቅርበት አይረሱትም። እንደዛሬ በየሰበቡ ጥርስ ሳይናከሱ ውሎና መክረሚያቸው በአንድ ነበር። የዛኔ በጋራ የሚገናኛቸው፣ አብሮ የሚያከርማቸው ጉዳይ አጣልቶ አጋጭቷቸው አያውቅም።
ጪሞ ኡስማን አርሲ አካባቢ የምትገኝ የገጠር ቀበሌ ናት። በዚህች ቀበሌ ዓመታትን የገፉ ነዋሪዎች ክፉና ደጉን በእኩል ሲጋሩ ቆይተዋል። በመስኩ የሚግጡ ከብቶች፣ በእርሻው የሚውሉ ገበሬዎች፣ በሜዳው የሚሮጡ እረኞች ለስፍራው የየዕለቱ ገጽታዎች ናቸው።
ከጠዋት እስከማታ ከእርሻው የሚውሉ ገበሬዎች ሁሌም ስለወቅቱ ምርትና ገበያ ያወጋሉ። ከሚያገኙት መልካም ፍሬ ተነስተውም ስለከርሞው ማውጋት፣ ስለሚሻለው ማቀድ ልምዳቸው ነው። ከዓመት እስከ ዓመት ምርት የሚያገባው መሬታቸው የሕይወታቸው መሠረት ስለመሆኑ አያጡትም።
እነሱ ሁሌም በከብቶቻቸው ሲሳይ ሕይወትን ይገፋሉ። ከብቶቹ ለእነሱ የተለዩ በረከቶች ናቸው። ሲሻቸው ወተት እያለቧቸው፣ ሲሻቸው ከእርሻ እያዋሉ የፍላጎታቸውን ያደርሳሉ። ገበሬዎቹ እስከዛሬ በከብቶቹ ትከሻ ቀናትን ተሻግረዋል። ጎጆ አቅንተው፣ ቤተሰብ አፍርተዋል። ልጆች አሳድገው፣ ኩለው ድረዋል።
ነዋሪዎቹ ውሃና ግጦሽ ፍለጋ ከብቶቻቸውን አርቀው አይወስዱም። በሰፊው የተንጣለለው የጢሞ ኡስማን መስክ በየቀኑ የአካባቢውን ከብቶች እንዳሻው አሰማርቶ ይውላል። ከብቶቹ ለዓመታት ከዚሁ ሜዳ ግጦሽ ሲያገኙና ሲቦርቁ ቆይተዋል። በዚህ ችግር የቀለላቸው አርሶአደሮችም ዘወትር ዕድለኝነታቸውን ሲያወጉና ሲናገሩ ዓመታትን ተሻግረዋል።
6 ሄክታር መሬት የሆነው የግጦሽ ስፍራ ዛሬም በረከቱን ሳይነፍግ፣ ያለውን እየሰጠ ነው። አሁንም አርሶአደሮቹ በጪሞ ኡስማን ቀበሌ ከብቶቻቸውን እንዳሻቸው ያሰማራሉ። ከብቶቹም ከግጦሽ ውለው ውሃ ለመጠጣት ወንዝ ይወርዳሉ። በቀበሌው ኑሮና ሕይወት በቀድሞ መልኩ ቀጥሏል። የአርሶ አደሮቹና የከብቶቹ ውሉ ያለአንዳች ከልካይ በመስመሩ እንዳለ ነው።
ከዓመታት በኋላ …
ዓመታት አልፈዋል። የመንደሩና የነዋሪዎቹ ሕይወት እንደነበረ ቀጥሏል። አሁንም ከታረሰውና ከተዘራው መሬት ምርት በወጉ እየታፈሰ ነው። በስፍራው ዓመታትን በአብሮነት የገፉ ነዋሪዎች ፍቅር ግን ውሃ ገብቶታል። እንደቀድሞው ከብቶቻቸውን በአንድ አያውሉም። እንደፊቱ ተሳስቦ ማደርና መግባባት ካቆሙ ጊዜያት ተቆጥረዋል።
የጪሞ ኡስማን የግጦሽ መሬት ከዓመታት በፊት በነበረው ገጽታ አይደለም። በእሱ ደረት ሲጋፉ፣ ሲተራመሱ፣ ሲግጡ፣ የሚውሉ ከብቶች ዛሬ ቁጥራቸው ተመናምኗል። በእነሱ አጀብ ሲተራመስ የሚውለው የጪሞ ኡስማን ቀበሌም አሁን የጥቂቶች ብቻ መገኛ እየሆነ ነው።
አቶ ረጋሳ ስዩምን ጨምሮ አስራ ሰባት ሰዎች ፍርድቤት መመላለስ ከጀመሩ ሰንብተዋል። አስራሰባቱ ሰዎች የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው። ፍርድቤት የመገኘታቸው ዋንኛ ምክንያት የጪሞ ኡስማን የግጦሽ መሬት ጉዳይ ሆኗል።
ሰዎቹ ፍርድቤት አቁመው በተከሳሽነት ያቀረቧቸው በቁጥር አስር የሚሆኑ የአካባቢውን ነዋሪዎች ነው። ከሳሽና ተከሳሾቹ እንደዛሬ የሁለት ቡድን ባላንጣዎች አልነበሩም። ፍርድቤት ተካሰው ከመቆማቸው በፊት በግጦሽ መሬቱ የእኩል ተጠቃሚዎች ሆነው ከጥቅሙ ሲጋሩ፣ ቆይተዋል።
አስራሰባቱ ሰዎች (እነ አቶ ረጋሳ) በቁጥር አስር የሚሆኑ እነአቶ ሙስጠፋ ከድርን ሲከሱ የግጦሽ መሬቱን የጋራ ተጠቃሚነት እንደምክንያት በማንሳት ነው። ከሳሾች 6 ሄክታር መሬት የሆነው ጪሞ ኡስማንንና አዋሳኙን ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ በጋራ ሲጠቀሙበት እንደነበረ ያስረዳሉ። ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ግን አስሩ ሰዎች የግጦሽ መሬቱን በይገባኛል በመያዝ እየተጠቀሙበት ነው።
ሁለቱ ቡድኖች ወደክስ ከማምራታቸው አስቀድሞ በውዝግብ ሲከራከሩ ቆይተዋል። አስሩ ሰዎች መሬቱን ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ሲጠቀሙበት እንደቆዩ አይክዱም። ይህን ሲያደርጉ ግን የይዞታ ማረጋገጫ ከሚመለከተው አካል በአግባቡ በመውሰዳቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ማረጋገጫው በእጃቸው መገኘቱና ባለቤት መሆናቸው በመሬቱ የተጠቃሚነት መብታቸውን እንደሚያረጋግጥ ይጠቅሳሉ።
በአስራ ሰባቱ ሰዎች ክስ የቀረበባቸው አስሩ ሰዎች በየቀኑ መሬቱን ልቀቁ በሚል የሚነሳባቸውን ውዝግብ አይቀበሉትም። በእጃቸው የሚገኘውን የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ በማስረጃነት እያሳዩ ሕጋዊነታቸውን ያስረዳሉ። ከዚህ በኋላ የግጦሽ መሬቱ ከእነሱ እጅ እንደማይወጣ በመግለጽም ማንም የመጠየቅና የመከራከር መብት እንደማይኖረው ይናገራሉ።
አስራ ሰባቱ ተሟጋቾች ጉዳዩን በድርድር መፍታት እንደማይቻል ከገባቸው ቆይቷል። የመሬት ይገባኛል ክርክሩን አሸንፈው በሕግ አግባብ ለመፍታትም አማራጫቸውን ፍርድቤት ላይ አድርገው አቤት ማለት ጀምረዋል። የክስ ማመልከቻው የደረሰው የአርሲ ወረዳ ፍርድቤት አመልካቾች የሚያነሱትን ጥያቄ በጥልቀት መርምሮ ተጠሪዎችን አስቀርቦ ጠየቀ።
አስሩ ግለሰቦች በእነ አቶ ሙስጠፋ መዝገብ ከፍርድቤቱ ችሎት ተገኙ። ፍርድቤቱ ከአመልካቾች የቀረበውን ክስ አስመልክቶ ጥያቄ አቀረበ። ተጠሪዎቹ ‹‹አሉን›› የሚሏቸውን የሰነድ ማስረጃዎች አቅረበው በመሬቱ ላይ የባለቤትነት መብት ያላቸው እነሱ ብቻ እንደሆኑ አስረዱ።
ፍርድቤቱ የተጠሪዎቹን የሰነድ ማስረጃ አጣርቶ አመልካቾች ተገቢው ማስረጃ ይኖራቸው እንደሆነ ጠየቀ። አስራሰባቱ ሰዎች በተባለው መሬት ላይ ባለቤት የሚያደርጋቸው አንዳች ማስረጃ በእጃቸው እንደማይገኝ ገለጹ።
ፍርድቤቱ የግራቀኙን ሀሳብና እማኝነት መርምሮ ውሳኔ ካለው መቋጫ ደረሰ። የአመልካቾችንና የተጠሪዎችን ሀሳብ ለብቻው መዝኖም ‹‹ይበጃል›› ከሚለው ውሳኔ ደረሰ። ሁለቱም ወገኖች ለየብቻቸው ያሰሙትን ቃልና ያቀረቡትን መረጃ ለየቅል ፈርጆም የመጨረሻውን ብይን አሳለፈ።
ፍርድቤቱ በውሳኔው ከሳሽ ሆነው ከቀረቡት አስራሰባት አመልካቾች ይልቅ ተጠሪ ሆነው የተከሰሰሱት አስሩ ሰዎች የግጦሽ መሬቱ ይዞታ ይገባቸዋል ሲል ብይን ሰጠ። ለዚህ ውሳኔውም ተጠሪዎች በዋቢነት ያቀረቧቸው ማስረጃዎች ማሳያ ስለመሆናቸው አስታወቀ።
አስራ ሰባቱ አመልካቾች ውሳኔው ለአስሩ ሰዎች መተላለፉን ባወቁ ጊዜ ዳግም ሰብሰብ ብለው መከሩ። ሁሉም የፍርድቤቱን ውሳኔ በይሁንታ ለመቀበል አልፈቀዱም። አሁንም የቀድሞ ይዞታቸውን መልሰው በጋራ መጠቀም እንዳለባቸው ተስማሙ።
ስምምነቱ ቃላቸውን አቀናጅቶ ለቀጣዩ እርምጃ አዘጋጃቸው። ፍርድቤቱ ያሳለፈውን ውሳኔ ለመቀልበስም ይግባኝ ማለት እንደሚኖርባቸው አመኑ። ጊዜ አልወሰዱም። የይግባኝ ማመልከቻውን አዘጋጅተው ለአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድቤት ‹‹አቤት›› አሉ።
ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድቤት ሁለቱን ወገኖች በእኩል አቅርቦ ሀሳባቸውን አደመጠ። ከዓመታት በፊት በይዞታው ላይ የነበራቸውን ተጠቃሚነት አውቆም ለሁለቱም ወገኖች ተገቢ ነው ያለውን ጥያቄ አነሳ። ሁለቱም በግጦሽ መሬቱ ላይ የጋራ ጥቅም እንደነበራቸው አስረዱ።
ፍርድቤቱ ለተጠሪዎች መሬቱን በሕጋዊ መንገድ ስለመያዛቸው በማስረጃ እንዲያረጋግጡለት ጠየቀ። የቀረበውን ማስረጃም በአግባቡ አጢኖ ለየ። በተመሳሳይ አመልካቾች መሬቱን ሲጠቀሙበት ስለመቆየታቸው የሚያስረዳ ማሳያ ስለመኖሩ ከሚመለከተው ክፍል በደብዳቤ ጠየቀ። ከክፍሉ ከተሰጠው የመልስ ደብዳቤ ተነስቶም ከመጨረሻው ውሳኔ ደረሰ።
ፍርድቤቱ አመልካቾቹ ከዚህ ቀደም ይዞታውን ሲጠቀሙበት ስለመቆየታቸው በመረዳት በኦሮሚያ የገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 130/99 አንቀጽ 25 መሰረት ክስና ክርክር የተነሳበትን ይዞታ ሁለቱም ወገኖች በጋራ ሊጠቀሙበት ይገባል ሲል ውሳኔውን አሳለፈ።
አስራ ሰባቱ አመልካቾች ከዞኑ ፍርድቤት የተሰጣቸውን የፍርድውሳኔ ተቀብለው የአፈጻጸሙን ተግባራዊነት ጠበቁ። በተሰጣቸው ፍትህም እንደቀድሞው ሊሆኑ ዳግም ከመሬታቸው ሊገናኙ ራሳቸውን አዘጋጁ። ከብቶቻቸው እንደፊቱ ከግጦሽ መሬቱ ውለው ምሽቱን ወደቤት የሚመለሱበትን ቀን ናፈቁ።
አስሩ ሰዎች ተጠሪ ሆነው በቀረቡበት የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድቤት የተላለፈባቸው ውሳኔ ከገመቱት በላይ ሆኗል። እስካሁን በእጃችን አለ የሚሉት የይዞታ ማረጋገጫ ከሕግ ፊት እንዳላዋጣቸው አውቀዋል። እነሱ በተላለፈባቸው የፍርድ ውሳኔ መብታቸውን ማሳለፍ መሬቱን መልሶ ማጋራት አይሹም።
አስሩ ሰዎች ይህ ሀሳብ የሁሉም ስሜት ስለመሆኑ በጋራ ተማምነዋል። ይህ አመኔታ ገዝፎም ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድቤት ማሳለፍ እንደሚኖርባቸው ወስነዋል። አሁን አስሩ ተጠሪዎች ይግባኝ ባሉበት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት ተገቢውን ምላሽ እንደሚያገኙ ገምተዋል።
አመልካቾቹ የሚሰጣቸው ብይን ቀድሞ ከተላለፉት ውሳኔዎች አብላጫ ሆኖ የፍርድ ሚዛኑ ለእነሱ እንደሚያደላ እያሰቡ ነው። ውሳኔው እንዳሰቡት ሆኖ ከተጠናቀቀ ደግሞ የሚሹትን መሬት አስከብረው መብታቸውን ይጠቀማሉ። ከጭቅጭቅና ውዝግብ ርቀውም ሰላማቸውን ያገኛሉ።
በሁለቱ ወገኖች መሀል የተጀመረው የሕግ ክርክር ቀጥሏል። ሁለቱም ቡድኖች ውሳኔው ለራሳቸው እንዲያደላ እየጠበቁ፣ እያሰቡ ነው። ሁሉም ከውሳኔው በኋላ በሚኖረው ሂደት መሆን መከወን ስለሚገባው ጉዳይ እርስ በርስ ይወያያሉ።
ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት ‹‹ይግባኝ›› ሲሉ አቤቱታ ያቀረቡት አስሩ ሰዎች ማመልከቻቸውን ከማስረጃዎች አጣምረው አቀረቡ። ጠቅላይ ፍርድቤቱ በተለመደው የሕግ አካሄድ አሁን ላይ ተጠሪ የሆኑትን የአስራ ሰባት ሰዎች ጉዳይ አንስቶ ምርመራዎችን አጣራ።
ጠቅላይ ፍርድቤቱ በሁለቱም ወገኖች በኩል ያገኘውን መረጃ በእኩል መዝኖ ለውሳኔ ሀሳብ ደረሰ። የመጨረሻ ብይኑ ለተከራካሪ ወገኖች ሲደርስ ቀድሞ የነበሩ ውሳኔዎችን ሳይሸራርፍ ነበር። ፍርድቤቱ ቀደምሲል በዞኑ ፍርድቤት የተላለፈውን ውሳኔ አጽንቶ ሁለቱ ወገኖች መሬቱን በእኩል ሊጠቀሙበት ይገባል ሲል ብይን ሰጠ።
አስሩ ሰዎች አሁንም በተላለፈው ውሳኔ አልተስማሙም። ቀጣዩን የፍርድ ሂደት ለመጀመር ማመልከቻቸውን አዘጋጅተው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድቤት ባሳለፈው ውሳኔ ‹‹አቤት›› ለማለት ወደክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አመሩ።
ሰበር ሰሚ ችሎቱ የአመልካቾችን አቤቱታ ተቀብሎ ጉዳዩን መረመረ። አስሩ ሰዎች የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው ስለመሆኑ ማስረጃ ማቅረባቸውን አስተዋለ። ከዚህ ተነስቶም ግለሰቦቹ ለመሬቱ ባለቤት የመሆን ሙሉ መብት አላቸው ሲል የዞኑና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤቶች ያሳለፉትን ውሳኔ በውሳኔው ሻረ።
ሰኔ 9 ቀን 2007 ዓ.ም…
አስራሰባቱ አመልካቾች የሰበር ችሎቱን ውሳኔ ካወቁ በኋላ ማመልከቻ ጽፈው አዘጋጁ። የአሁኑ ማመልከቻ እንደተለመደው ወደመደበኛ ወደፍርድ ቤቶች የሚመራ አልሆነም። አመልካቾቹ ከፊል አርሶአደሮች መሆናቸውን ጠቅሰው የሕገመንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ባስገቡት አቤቱታ ለረጅም ጊዜ በግጦሽ መሬቱ ሲጠቀሙ እንደነበር አነሱ።
አመልካቾቹ የወል መሬቱን አስመልክቶ በተለያዩ ጊዜያት በፍርድቤቶቹ በተሰጡት ውሳኔዎች ይዞታው የተጠሪዎች ስለመሆኑ መወሰናቸውን ጠቅሰው ድርጊቱ አግባብ ባለመሆኑና የሕገመንግሥቱን አንቀጽ 9 40/5/ መሠረት እና 50 የሚጥስ በመሆኑ ትርጉም እንዲሰጥልን ሲሉ ጠየቁ።
ጉባኤው በጉዳዩ ላይ ማስረጃዎችን ከያዘ በኋላ ፍርድቤቶቹ የሰጧቸው ውሳኔዎች ከተጠቀሰው የሕገመንግሥቱ ድንጋጌ ጋር የሚቃረን መሆን ያለመሆኑን መርምሯል።
አመልካቾች ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን የመሬት ይዞታ በተመለከተ ጉባኤው ለክልሉ የገጠር መሬትና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ በላከው ደብዳቤ በአንድ ይዞታ ላይ ሁለት የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዴት ሊሰጥ እንደቻለ ማብራሪያ ጠይቋል። ቢሮው በበኩሉ በሰጠው ምላሽ ክርክር ወደተነሳበት ስፍራ ባለሙያዎችን በመላክ ማጣራት ስለማድረጉ ጠቅሷል።
በዚህም መሠረት መሬቱ በ1996 ዓ.ም በተደረገው የመሬት ልማት የጋራ መሬት ተብሎ ስለመለካቱ የሰፈሩንና የአካባቢ ሽማግሌዎችን በመጠየቅ ማረጋገጥ መቻሉን ለማወቅ ተችሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም መሬቱ ‹‹ይገባናል›› ሲሉ የሚከራከሩት አስር ሰዎች ‹‹አለን›› ያሉት የመሬት ማረጋገጫ ማስረጃ ከትክክለኛው አካል ያልተወሰደና አግባብነት የሌለው እንደሆነ ተረጋግጧል።
ጉባኤው ባደረገው ተጨማሪ ማረጋገጫ በአስሩ ሰዎች እጅ አለ የተባለው የይዞታ ማረጋገጫ ስርዝ ድልዝ ያለውና መረጃዎቹ ተፍቀው የተሞሉ ናቸው። በተመሳሳይ በሚመለከታቸው ክፍሎች ያሉ ሰነዶችም አንድ ዓይነት ይዘት ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል።
የመሬት ይዞታውንና የተጠሪዎችን ጉዳይ ለማጣራት በተደረገው ጥረት የተባሉት የማስረጃ ይዘቶች በሙሉ ሕገወጥና ተቀባይነት የሌላቸው ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
ውሳኔ…
ጉባኤው አመልካቾች ከፊል አርሶአደሮች ስለመሆናቸው አረጋግጧል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ክርክር የተነሳበት መሬትም የውል የግጦሽ መሬት ስለመሆኑ አውቋል። እስከዛሬ በተለያዩ ጊዜያት በፍርድቤቶቹ የተሰጠው የፍርድ ውሳኔ ተገቢ ያለመሆኑን የተረዳው ጉባኤ ውሳኔው የአመልካቾችን ሕገመንግሥታዊ መብትን የሚጥስ በመሆኑ ተፈጻሚነት ሊኖረው አይገባም ሲል ብይን ሰጥቷል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2013