የተወለዱት በቀድሞው አጠራር ወላይታ አውራጃ ዳሞት ወይዴ ወረዳ ደጋጋ ሌንዳ ቀበሌ ውስጥ ነው። በቃለህይወት ሚሽን ስር ይተዳደር በነበረው በዴሳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ወላይታ ሶዶ ሊጋባ በየነ ትምህርት ቤት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተማሩ። ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ገብተውም በእንግሊዘኛ ትምህርት ዲፕሎማቸውን አገኙ። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኝ ነሲቡ በተባለ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሁለት ዓመታት አገለገሉ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመማር እድሉን አገኙና በእንግሊዘኛ ቋንቋና ስነ-ፅሁፍ ትምህርት ተከታትለው በከፍተኛ ማዕረግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀበሉ። ከፍተኛ ውጤት በማምጣታቸውም ከሌሎች ተማሪዎች መካከል ተመርጠው እዛው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ቀርተው የማስተማር እድሉን አገኙ። በመማር ማስተማሩ ሂደት ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም በዛው የትምህርት ዘርፍ የሰሩት እንግዳችን በዚህ ሳይወሰኑም በፖለቲካ ሳይንስና አለምአቀፍ ግንኙነት ለማግኘት ችለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመጡ ከተቋቋሙት አዳዲስ ትምህርት ክፍሎች ውስጥ አንዱ የሆነው የሰላምና ደህንነት ተቋምን እንዲመሩ ኃላፊነት ተሰጣቸው። ላለፉት 20 ዓመታት ተቋሙን በአመራርነትና በመምህርነት ሲያገለግሉ የቆዩት እንግዳችን በመካከሉም በእንግሊዝ ብራድፎርድ ዩኒቨርስቲ የትምህርት እድል አግኝተው ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በሰላምና ደህንነት ጥናት ዘርፍ ሰርተዋል። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመመለስ የሰላምና ደህንነት ተቋምን ዳግመኛ መምራት ቀጠሉ። የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር ዮናስ አዳዬ በዚህ ተቋም ውስጥ ተምረው አገርን በከፍተኛ ሥልጣን ከመሩና እየመሩ ያሉ ባለስልጣናትን ማፍራት ችለዋል። እንደሀገርም ለሰላምና ደህንነት ዘርፉ መጠናከርም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለማበርከታቸው ይጠቀሳል። ከእንግዳችን ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡– የምርጫን ምንነትና ለአንድ ሀገር ያለውን ፋይዳ ያብራሩልንና ውይይታችንን እንጀምር?
ዶክተር ዮናስ፡– የቃሉ ጥሬ ትርጉም ካሉት ነገሮች ውስጥ አንዱን መምረጥ ወይም መለየት ማለት ነው። ወደ ፖለቲካው ስንመጣ ደግሞ ሁሉም የፖለቲካ ሃይል ሀገርን መምራት ስለማይችል ይወክለኛል ወይም ያስተዳድረኛል የምንለውን ለይተን የምንመርጥበት ሂደት ነው። የተሻለ የምንለውን ካሉት ጋር አወዳድሮ አንዱን መወሰን እንደማለት ነው። ምርጫ በፖለቲካ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና አለው። በመሰረቱ ምርጫ ለእኛ ለአፍሪካውያን አዲስ አይደለም። እንደአሁኑ ዘመናዊ መንግስታዊ መዋቅር ሳይስፋፋ በፊት የጎሳ መሪዎቻችን እንመርጥ ነበር። ይህም ማለት አፍሪካውያን በቀኝ ግዛት ሳይዙ በፊት የምርጫ ስርዓትን አስቀድመው ያውቁና ይከተሉ እንደነበር ማሳያ ነው። ምርጫ የተፈጥሮ ሂደትም ነው። የህይወት ፍልስፍናም ነው። ስለዚህ ምርጫን አውሮፓዊ አስተሳሰብ ብቻ እንደሆነ ማሰብ ከአላዋቂነት ያስቆጥራል። ምክንያቱም ማንኛውም ሰው የሆነ ሰው በዕለት ተዕለት እንቅሳቀሴው የሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ በምርጫው ላይ የተመሰረተ ነው። በአጠቃላይ ለእኔ ምርጫ የህይወት አካል እና ሊደረግ የሚገባው ነው።
አዲስ ዘመን፡– በእርሶ እምነት ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ብቸኛ መንገድ ነው? ከዚህ አኳያ ያለፉት አምስት ምርጫዎች እንዴት ይታያሉ?
ዶክተር ዮናስ፡– እኔ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ምርጫ ቁልፍ መሳሪያ እንደሆነ አምናለሁ። ነገር ግን ብቸኛ መንገድ ነው ብዬ አላምንም። የዲሞክራሲ ተቋም ካልገነባን፤ አስተሳሰቡንም ማስረፅ ካልቻልን ምርጫ ብናካሄድም የተመረጠው አካል ሊመራ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በተለይም ምርጫ ቦርድን የመሰሉ የዲሞክራሲ ተቋማትን በአግባቡ ካልገነባናቸው ዲሞክራሲ ገደል ይገባል። በአጠቃላይ ዲሞክራሲ እውን የሚሆነው ነፃ የፍትህ ተቋማት ሲኖሩን እና ሰላም በመላው ህብረተሰብ ውስጥ ባህል ሲሆን ነው። በተለይም ልጆች ከቤተሰብ ጀምሮ ሰላምን በሰላማዊ መንገድ እንዲያገኙ ስናስተምራቸው ነው።
ከዚህ አኳያ ያለፉትን አምስት ምርጫዎች ዋቢ ማድረግ እንችላለን። እኔ ቅዱስ መፅሃፍ ‹‹ እውነትን ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ( ነፃነት) ያወጣችኋል›› እንደሚለው እውነትን ስናውቅና ስንከተል ህሊናችን ከወቀሳ ነፃ እንደምንሆን አምናለሁ። መነጋገር መሸነፍ ሳይሆን መሰልጠን መሆኑን ስንገነዘብ ነው። በእኔ እምነት ያለፉት ምርጫዎች ከስም የዘለለ ፋይዳ ነበራቸው ብዬ አላስብም። እርግጥ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫዎች ተካሂደዋል። ግን ምርጫ ብቻ ማድረግ ወደ ዲሞክራሲ እንዳላደረሰን በተግባር አይተናል። ምርጫ መፍትሔ ቢሆን ኖሮ በደርግ ጊዜም ምርጫ ተካሂዶ ነበር፤ ግን ዲሞክራሲን አላመጣልንም። ምርጫ ከተደረገ በኋላ ኩዴታ ተፈፅሞ በብዙ ጦርነት ውስጥ የገቡ አገራት አሉ።
በሌላ በኩል ግን የማይካደው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 27 ዓመታት በተቋም ግንባታ ረገድ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። ለምሳሌ የልማት አውታሮችን ብንመለከት በአለም መዝገበ ቃላት የማይታወቁ የአገራችን አካባቢዎች የዩኒቨርስቲ ባለቤት ሆነዋል። የህክምና ተቋማት፣ መንገዶች በየቦታው ተሰርተዋል። እነዚህ መሰረተ ልማቶች ለብልግናችን መሰረቶች ናቸው። ከዚሁ ጎን ለጎን ምርጫዎች ተካሂደዋል። ግን ሃቀኛ ምርጫዎች ነበሩ ወይ? የሚለው ነገር ህዝቡ ራሱ ይፈርዳል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በእርስዎ እምነት እነዚያ ምርጫዎች ሃቀኛ እንዳይሆኑ ያደረጉዋቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ዮናስ፡– ከመሰረቱም ቢሆን ህወሓት ምርጫን ያመጣው በትግል ወቅት ለአውሮፓውያኑ የገባውን ቃል ለማክበር ሲል ነው። ከሃያላን ሃገራቱ ድጋፍ ለማግኘት ከተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ምርጫ ስለነበረና የገባውን ቃል ለማክበር ሲል እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዳይ አስጨንቆት ወይም አሳስቦት አይደለም። ከዚህ አንፃር የተደረጉት አምስቱም ምርጫዎች ከላይ ወደ ታች ጫና የተደረገባቸው ነበሩ። ከውስጥ የመነጨ ወይም የህዝቡ
ፍላጎት የተተገበሩበት አይደለም። እንደዛም ሆኖ ምርጫዎቹ እውነተኛ አልነበሩም። በእኔ አተያይ መቶ በመቶ አሸንፈሽ እውነተኛ ምርጫ ተካሂዷል ማለት አትችይም። ኢህአዴግ 99 ነጥብ 6 በመቶ አሸነፍኩኝ እያለ በምን መልኩ ነው ብዝሃነት ሊያከብር የሚችለው? ሁሉም አብዮታዊ ዲሞክራሲን ብቻ እንዲያስቡ፣ እንዲናገሩ፣ ስለእሱ ብቻ እንዲያቀነቅኑ ሆኖ እንዴት አይነት ምርጫ ሊካሄድ ይችላል? ለራሳቸው ህሊናም የሚከብድ ነገር ነው። እኔ ይህን በድፍረት የምናገረው ከጀርባዬ ፖለቲካ ስላለ አይደለም፤ ይልቁንም የማመልከውን ፈጣሪና እውነት መሰረት በማድረግ ነው። በመሆኑም በንፁህ ህሊና የምታዬው ከሆነ ምርጫ ይካሄድ የነበረው የምዕራባውያን እርዳታ እንዳይቋረጥ ስለሚፈለግ ነው። ይህ ደግም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ባላደጉ አገሮች ምዕራባውያን የሚያደርጉት ጫና ነው። ያንን ካላደረጉ የመንግስት ለውጥ እስከማድረግ የሚደርሱበት ሁኔታ አለ። ጋዳፊ ለምዕራብውያን አልገዛ ሲሉ የደረሳባቸውን አይተናል። እናም እንዲህ አይነት ኢ- ፍትሃዊ የሆነ አለም አቀፍ የቁጥጥር ስርዓት በመዋቅራችን ውስጥ በመኖሩ ነው ትክክለኛ ምርጫ ማካሄድ ያልቻልነው። የተደረጉት አምስቱም ምርጫዎች የይስሙላ ምርጫዎች ነበሩ ማለት ይቻላል።
ይሄ ብቻ አይደለም፤ የነበሩት ባለስልጣት ስልጣናቸውን መልቀቅ ስለማይፈልጉና ለኢትዮጵያ ህዝብ ደንታ ስላልነበራቸው በምርጫ ወቅት ህዝቡን የሚያስጨንቁበትና ጫና የሚያሳድሩበት ሁኔታ ነበር። መሪዎች ራሳቸው ትክክለኛ ምርጫ ተካሂዶ እውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ቅንነቱ አልነበራውም። ደርግን ደምስሰው ስለመጣታቸውና ስልጣናቸውን ስለማስቀጠላቸው እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ መርጣቸው፤ አልመረጣቸው አያስጨንቃቸውም ነበር። በእኔ እምነት ሃይል የእግዚአብሄር ነው፤ ለዘላለም እንዳሸነፈ የሚቀጥለውም ፈጣሪ ብቻ ነው። ዛሬ መልካም ነገር ዘርተን ከሄድን ከዘመናት በኋላ በቅሎ እናየዋለን። በንፁህ ህሊና ከሰራን ቢያንስ ቢያንስ የህሊና እረፍት እናገኛለን። ከዚህ አኳያ ምርጫዎቹ ይካሄዱ የነበሩት በንፁህ ህሊና ላይ ተመስርተው አይደለም። በመሰረቱ ህወሓት የተመሰረተበት ማኒፌስቶ አንድን ማህበረሰብ በጠላትነት ፈርጆ የተነሳ መሆኑ በራሱ በዚህች ሃገር ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማምጣት ቀርቶ ህዝብንም በእኩል እንዳይመራ አድርጎታል። በሌላ በኩል የህዝቡ የፖለቲካ ባህልም ያለማደጉ የራሱ አስተዋፅኦ አለው። በጥቅሉ ከጥፋት ነፃ የሚሆን የለም። ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ውጤታማ ያለመሆን የሁላችንም ሚና አለው ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የዲሞክራሲ ተቋማት ተገንብተዋል ቢሉም፤ ሌሎች ግን አይቀበሉትም። ምክንያታቸው ደግሞ ተቋማቱ ቢገነቡ ኖሮ ዲሞክራሲው በጥቂቱም ቢሆን ማበብ ይችል ነበር የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ዮናስ፡- የእኔ መልስ አወንታዊ ነው፤ አዎ ኢህአዴግ ከሰራቸው መልካም ነገሮች አንዱ የተቋማቱ ግንባታ ተጠቃሽ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው የመጣው። እርግጥ ነው በኢህአዴግ ጊዜ የነበረው ምርጫ ቦርድ ሙሉ ለሙሉ ለገዢው ፓርቲ ያደላ እንደነበር ይታወቃል። በወቅቱ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የምርጫ ቦርድ የበላይ ጠባቂ የነበሩት አንድ ግለሰብ ነበሩ። የተበደለ ግለሰብ ወደ ፍርድ ቤት ቢመጣም የሚከሰውም ሆነ ፍርድ እንዲበይንለት የሚጠይቀው አንድ አካል ሆኖ እያለ እንዴት ነው ፍትህ ሊመጣ የሚችለው? ራሳችንን ካላታለልን በስተቀር የከሰስነው አካል መልሶ ለእኛ ሊፈርድልን የሚችልበት ሁኔታ የለም። ያም ሆኖ ተቋማቱ በራሳቸው መኖራቸውን በመልካምነት ነው የማየው። ግን ደግሞ ማስተካከልና ወደሚፈልገው ደረጃ ማድረስ ይገባል። አሁን ላይ ቦርዱን የሚመሩት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ከዩኒቨርስቲ ጀምሮ አውቃቸዋለሁ። በዚያ ወቅት እንኳ በጣም የሚያነቡና በእውቀት ላይ ተመስርተው የሚከራከሩ ጠንካራ ስብዕና ያላቸው ግለሰብ ናቸው። በተጨማሪም ሰብሳቢዋ በብዙ ጭንቀትና መከራ ውስጥ ያለፉ እንደመሆናቸው በእሳት እንደተፈተነ ወርቅ የነጠረ አመራር እንደሚሰጡ እሙን ነው። ለዚህም ነው ለቦርድ ሰብሳቢነት ሲታጩ በገዢውም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት የቻሉት። በመሆኑም ተቋሙ ቢቋቋምም የሚመሩት ሰዎች ለህዝቡ ትክክለኛ ዲሞክራሲ ለማምጣት የቆረጡና የጀገኑ ካልሆኑ እውን ሊሆን አይችልም። ሰላም በሰላማዊ መንገድ ለማምጣት ከመነጋገር ይልቅ ነፍጥ አንስቶ ወደ ጫካ የሚገባ አለ። ስለዚህ ያንን ለማስቀረት እንዲህ አይነቷን በህይወት እሳት የተፈተነች ብቁ ሴት ወደፊት ማምጣት ያስፈልጋል።
ሌላው ጉዳይ ደግሞ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ወቅት ያለውን የውጭ ጫና ያውቃል። በተለይም በግብፅ አማኝነት የሚደረግብን አለምአቀፍ ጫና ለመቋቋምና ሉላዊነት ለማስከበር በህዝቡ ውስጥ ቁርጠኝነት አለ። ይህንን ለመመከትም ትክክለኛ ምርጫ አካሂዶ በህዝብ የተመረጠ መንግስት መመስረት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ አሁን ላይ ህሊናዊ እረፍት የሚሰጥ ሁኔታ አለ። ለዚህም ነው ህዝቡ ለመምረጥ ፀሃይና ዝናብ ሳይበግረው ለመምረጥ ተሰልፎ ውሎ ያመሸው። ስለዚህ በህዝቡ ውስጥ ያለውን ቁርጠኝት ሲታይ ህሊናዊ ሁኔታዎች ተሟልቷል ብሎ መናገር ይቻላል። በነገራችን ላይ እኔ የምናገረው ያየሁትን ነው። ማንንም ለመደገፍ ሳይሆን ያለውን እውነታ መግለፅ አለብኝ ብዬ ስለማምን ነው።
አዲስ ዘመን፡– የዘንድሮ ምርጫ በብዙ ችግሮች ታጅቦ መካሄዱ በራሱ አወንታዊና አሉታዊ ሚናው ምንድን ነው ብለው ይላሉ?
ዶክተር ዮናስ፡– በፍልስፍና ሳይንስ ፅንፍ የያዘ አመለካከት አይፈቀድም ወይም አይመከርም። ሌላው ቀርቶ ሴት መቶ በመቶ ሴት አይደለችም፤ ወንድም እንዲሁ። ምክንያቱም በውስጣቸው የሚያመሳስላቸው ነገሮች አሉ። ፍፁም የሚባል ነገር በምድር ላይ የለም። ሁሉም አንፃራዊ ነው። ሁልጊዜ የሚታየው በንፅፅር ነው ። በመጀመሪያ ይህንን መሰረታዊ ሃሳቡን በግልፅ መገንዘብ ይገባናል። የትም ሀገር ፍፁም የሆነ ዲሞክራሲ የለም። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ምርጫው ተራዝሟል። በምርጫው ወቅት እንኳን የተስተዋለባቸው ቦታዎች ላይም ተሰርዟል። ይህ መደረጉ ተገቢ ነው። አሁን ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ ደግሞ አስቀድሜ እንዳልኩሽ በእሳት ውስጥ ያለፉ በመሆናቸው ችግር በታየባቸው ቦታዎች ላይ ምርጫውን ለመሰረዝ ወደ ኋላ እንደማይሉ እሙን ነው። አዳማ ላይ ምርጫውን ያወከ ግለሰብ ተከሶ ወዲያውኑ እንደተፈረደበት ስታይ ህግ እየሰራ መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም።
ግን ደግሞ አብሮ የሚነሱ ችግሮች አሉ። ከምርጫው የወጡ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች መኖራቸው ለዲሞክራሲው ግንባታ እንቅፋት መሆኑ አይቀርም። ያም ቢሆን ካለፉት ምርጫዎች በብዙ መልኩ የተሻለ ምርጫ ነው ለማለት እችላለሁ። ለዚህ ደግሞ በምርጫው እለት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የሰጡት ምስክርነት አንዱ ማሳያ ነው። በአጠቃላይ ምንግዜም መንገድ ስታቋርጪ በእርግጠኝነት ያለምንም እንቅፋት እሻገራለሁ ብለሽ አታስቢም። ምርጫውም ያለምንም እንከን ይካሄዳል ተብሎ አይታሰብም። ግን ደግሞ በአንፃራዊ መልኩ የተሻለ ነባራዊ ሁኔታ ነበር ማለት ይቻላል። በነገራችን ላይ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ማለፋችን የበለጠ ጠንካራ ነው የሚያደርጉን። እያንዳንዱ ሰው ደግሞ በእኔነት መንፈስ ከሰራ የምንናፍቀው ሰላምም ሆነ ዲሞክራሲን ማምጣት እንችላለን። በመሰረቱ በየትኛው አገር ያለችግር የመጣ መንግስትም ሆነ ስርዓት የለም። በድምሩ ምርጫው ብሄራዊ ውይይት እንዲፈጠር አግዟል። ያም ቢሆን ግን ምርጫው በራሱ ሁሉንም ችግሮች ይፈታልናል ተብሎ አይጠበቅም። ደግሞም በእርግጠኝነት የምነግርሽ በሚቀጥሉት ሶስትና አራት ወራት ችግሮቹ ባሉበት አይቀጥሉም። ይቀየራል።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ይህንን ምርጫ ማካሄዷ የውጭ ጣልቃ ገብነት ለማስቀረት ምን ፋይዳ አለው?
ዶክተር ዮናስ፡– በመጀመሪያ ደረጃ ይሄ ምርጫ እኛ ነፃና ሉዓላዊ ሀገር መሆናችንን ያስገነዝባል። እንደሚታወቀው በየሀገሩ የእጅ አዙር ቀኝ አገዛዝ አለ። ለምሳሌ ማሊ ውስጥ ችግር ቢፈጠር ቀድሞ የሚደርሰው ፈረንሳይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ከተፈጠረ በተመሳሳይ መልኩ ጣልቃ ለመግባት የቋመጡ አገራት አሉ። እዚህም ሀገር ሆነውም ቢሆን የኮሶቮ አይነት የውጭ ሰላም አስከባሪ ሃይል ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመጣ የሚናፍቁ አሉ። ስለዚህ እኛ ምርጫውን ያለምንም ተፅዕኖ ማካሄዳችን ይህ ቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ ምርጫ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ ያካሄደችው በመሆኑም ማንም ሃይል በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት አይችልም። በኢትዮጵያ ነፃ አገር ስለመሆንዋ የነበረውን ብዥታ ያጠራልም ብዬ አምናለሁ። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ገጠመኝ ልንገርሽ፤ ሲዋዚላንድ በምትባል አፍሪካዊ ሀገር በስራ አጋጣሚ ሄጄ በኢትዮጵያ ስም የተሰየመ ቤተክርስቲያን መኖሩን ተመለከትኩና እንዴት ሊሆን እንደቻለ ስጠይቅ ኢትዮጵያ ቅድስት ሀገር ናት ብለው ስለሚያስቡ እንዲሞክራሲ ለዚያ ደግሞ ከነጭ ወራሪዎች ብቻዋን ታግላ ነፃ የወጣች ሀገር በመሆንዋ እንደተምሳሌት ስለሚያይዋት እንደሆነ አስረድተውኛል። አሁንም ቢሆን ይህ ምርጫ ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያውያን ማካሄዳቸው ዲሞክራሲን በሃገራቸው ለማስፈን ያላቸውን ቁርጠኝነት ነው የሚያሳየው። የምስራቅ አፍሪካ ታዛቢ ሃይልም ይህንኑ ነው ለአለም የመሰከረው።
በሌላ በኩል ከውጭ ሃይል ጋር አብረው ምርጫውን ለማወክ አቅደው ለነበሩ ሰዎችም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነ አምናለሁ። በተጨማሪ ያኮረፉ አካላትም መልሰው ራሳቸውን እንዲያዩ ያደርጋል። ከዚህ ባሻገር እንደ አውሮፓ ህብረት ያሉ የውጭ ታዛቢዎችም ሲከተሉት የነበረው ስትራቴጂ ትክክለኛ እንዳልነበር ያስገነዘባቸው እንደሆነም እረዳለሁ። ከዚህም አልፎ ተርፎ ከምርጫ ጎን ለጎን ችግኝ የመትከል መርሃግብር መኖሩ ለሀገራችን ልማት እርስ በርስ እንድንቀራረብና እንድንረባረብ እድል ፈጥሮልናል ብዬ አስባለሁ። በአጠቃላይ ውስጣዊ አንድነታችንን የበለጠ ያጠናክርልንናል።
አዲስ ዘመን፡– የዚህ ምርጫ በሰላም መጠናቀቅ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ያለው ፋይዳ ምን እንደሆነ ያብራሩልኝ?
ዶክተር ዮናስ፡– እንዳልሽው የዚህ ምርጫ ፋይዳ ብዙ ነው። በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ያለን ሀገራት በባህልም ሆነ በቋንቋ ከሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት በላይ የተሳሰርን እንደመሆናችን የአንዱ ሰላም ማጣት ለሌላው ጠንቅ መሆኑ አይቀርም። ጎረቤታችን ያለው እሳት እኛ ቤት አለመግባቱን ማናችንም እርግጠኛ መሆን አንችልም። ሰላማችን የተሟላ ይሆን ዘንድ ጎረቤቶቻችን ሰላም መሆን አለባቸው። ስለዚህ ለቀጠናው አንድነት መሰረት ጥሏል የሚል እምነት አለኝ። ከዚህም ባሻገር ለመላው የአፍሪካ ህዝብ የሚያስተላልፈው መልዕክት አለ። በተለይም ያለምዕራብያውያን ተፅዕኖ ለራሳችን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ መኖሩ የሚያስገነዝብ ነው። እኛ አፍሪካውያን ከተባበርን ብዙ ታዓምር መስራት እንደምንችልም መልዕክት ሰጥቷል። በመሰረቱ እኛ አፍሪካውያን ማህበራዊ ትስስሩ ጠንካራ የሆነ የአኗኗር ባህል ነው ያለን። አንዳችን ካለአንዳችን ምንም ነን። ስለዚህ ወደፊት የምናስባትን የበለፀገችና ለህዝቦቿ የምትመች አህጉርን ለመፍጠር እርስበርስ ሰላማችንን ማስጠበቅ ይገባናል። ለዚህ ደግሞ ፍትሃዊና ሰላማዊ ምርጫና የስልጣን ሽግግር ወሳኝ ሚና አለው።
አዲስ ዘመን፡– አንድአንድ ሰዎች አኩርፈው የወጡና በህግ ጥላ ስር ያሉ የፖለቲካ አመራሮች ባለቡት ሁኔታ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ውስጥ እንደሚገባ ይናገራሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ዶክተር ዮናስ፡– እውነት ለመናገር በህግ ጥላ ስር ያሉ ፖለቲከኞች በምርጫው እንዲወዳደሩ መደረጉ በራሱ ትልቅ ነገር ነው ባይ ነኝ። እኔ በፍርድ ውሳኔ ውስጥ መግባት አልፈልግም። ይሁንና እነዚህ ሰዎች ወንጀለኝነታቸው እስከሚረጋገጥ ድረስ በምርጫው እንዲሳተፉ ማድረጉ በራሱ የፍትህ ተቋማቶቻችን አሰራር ምን ያህል እየተሻሻለ መምጣቱን ያመለክታል። በነገራችን ላይ በእስር ሆኖ በምርጫ የመወዳደር ጉዳይ በእኛ አገር የተጀመረ አይደለም። የደቡብ አፍሪካዊው መሪ ኒልሰን ማንዴላም በእስር እያሉ ነው በፓርቲያቸውና ደጋፊዎቻቸው ቅስቀሳ ሲደረግላቸው የነበረው። በተመሳሳይ የበርማ ተቋዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩት አንሳንሱቺ እስር ቤት እያሉ ነበር ብዙ ቅሰቀሳና እንቅስቃሴ ሲያደርጉና ሲደረግላቸው የነበረው። በእኛ ሀገርም እነዚህ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ህግ ተማምነው ወደ ፍርድ ቤት አቅርበው ህጉ በሚፈቅደው መሰረት እንዲወዳደሩ መደረጉ በራሱ ለእኔ ትልቅ እምርታ ነው። ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፍትህ አሰራር እየጎለበተ መምጣቱን ነው የሚያሳየው። የምርጫ ቦርድን ታዓማኒነት ነው የሚያስረዳን። ስለዚህ በእኔ በኩል ይሄ የሚያስወቅስ ጉዳይ አይደለም።
በሌላ በኩል መጀመር በራሱ ስራውን በግማሽ እንደማጠናቀቅ ይቆጠራል። እኔ ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ ሁኔታዎችን ስከታተል ነበር የቆየሁት። እንዳልሽው በሁላችንም ዘንድ ከነበው ስጋት አንፃር በሰላም መጠናቀቁ የሚያስደስት ነገር ነው። ምክንያቱም የደህንነት ስጋትና ለግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የምርጫ ጉዳይ ነው። ከምርጫ ቅስቀሳ ጀምሮ በአጠቃላይ የምርጫው ሂደት የሀገሪቱ ህዝብም ሆነ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃላፊነት መንፈስ በመንቀሳቀሳቸው ነው ምርጫውን በሰላም ማጠናቀቅ የተቻለው። ትልቁ ጉዳያችን መሆንም የሚገባው ኢትዮጵያን ማሻገር ሊሆን ነው የሚገባው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የለችም እያሉ ጠላቶቻችን ብዙ ሲፎክሩብን ነበር። በቅርቡ ተከታትለሽ ከሆነ የግብፅ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ህገመንግስት ዋቢ በማድረግ ሁሉም ክልል እንዲገነጠልና ራሱን ችሎ ሀገር እንዲሆን ሲቀሰቅሱ ነበር። በነገራችን ላይ በአለም ላይ እንደ ኢትዮጵያ ያለና መገንጠልን የሚፈቅድ ህገመንግስትም ሆነ መንግስት የለም። ይህ በራሱ ጠላቶቻችን በልዩነቶቻችን ተጠቅመው እንዲከፋፍሉን እድል ሰጥቷቸዋል ብዬ ነው የማምነው። በአጠቃላይ ጠላቶቻችን ይመኙልን እንደነበረው በምርጫው ግጭት አለመከሰቱ በመጀመሪያ ፈጣሪ በመቀጠል ደግሞ ፖለቲከኞችንና መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ማመስገን እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በትግራይ ክልል ምርጫ አለመካሄዱ በራሱ ከህግ አንፃር ክልሉን ለማስተዳደር አዳጋች አያደርገውም? በህዝቡስ ላይ አሉታዊ ስሜት አይፈጥርም?
ዶክተር ዮናስ፡– አስቀድመን እንዳነሳነው በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ተካሂዷል። አንዳንድ የፀጥታ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ጳጉሜ 1 እንደሚካሄድ ይታወቃል። እንደትግራይ የፀጥታ ችግር ያለባቸው ቦታዎች በተመሳሳይ መረጋጋት ሲሰፍን ምርጫ ይካሄዳል ብዬ እጠብቃለሁ። ምርጫ ባለመካሄዱ የተለየና አሉታዊ ሁኔታ ይኖራል ብዬ አላስብም።
ያነሳሽው ትክክለኛና ተገቢ ጥያቄ ነው። ግን ደግሞ አሁን ላይ ትግራይ ክልል ምርጫ አልተካሄደም ማለት ይቀራል ማለት አይደለም። ለምሳሌ በሌሎችም አካባቢዎች ገና የጊዜ ሰለዴ ወጥቶላቸው የሚካሄድባቸው አሉ። እንዳልሽው ክልልንም ሆነ ሀገርን የሚያስተዳድረው የተመረጠ መንግስት ነው። ትግራይ ክልል ያለ ችግር መላውን ኢትዮጵያ ይነካል። ምክንያቱም አንዳችን ከአንዳችን ጋር እርስበርስ የተሳሰርን ነን። ስለዚህ አሰርግጬ ልነግርሽ የምችለው በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በጊዜ ሰለዴው መሰረት ምርጫ እንደሚካሄድ ነው። ነገር ግን በህግ ማስከበሩ ስራ አሁን የሚቀሩ ነገሮች መኖራቸው እንዲሁም በአካበቢው ያለው ማህበረሰብም ለመረጋጋት ጊዜ የሚስፈልገው በመሆኑ፤ ያ እስኪሆን ድረስ ደግሞ መጠበቅ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– የድህረ ምርጫው ሂደትም ሰላማዊ እንዲሆን በተለይም የምርጫውን ውጤት በፀጋ ከመቀበል አኳያ ከአሸናፊውም ሆነ ከተሸናፊ ፓርቲዎች ምን ይጠበቃል?
ዶክተር ዮናስ፡– በዚህ አጋጣሚ መናገር በእስከዛሬ የምርጫ ሂደታችን አይተነው በማናቀው መልኩ በፓርቲዎች ላይ ፍፁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በማየቴ የተሰማኝን ደስታ ለመግለፅ እወዳለሁ። ከምንም በላይ ኢትዮጵያን ማስቀደማቸው እጅግ አስደንቆኛል። በተለይም ከኢዜማ፣ ከባለደራስ እና ከአብን ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በፀጋ እንደሚቀበሉ መናገራቸው ለሀገር ህልውና የሚኖረው ፋይዳ በቀላሉ አይታይም። የፈለገው አይነት ችግር ቢኖር ችግሩን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመወያየት እንጂ ወደ ነውጥ እንደማይገቡ ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አንደበት አዳምጠናል። ይህም ለእኔ ትልቅ ለውጥ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በህዝብ ፊት ቃል የገቡ በመሆናቸውም ጭምር ምን አልባት ከአቋማቸው ቢያፈነግጡ እንኳን ህዝቡ ራሱ ነው የሚጠይቃቸው። ሚዲያውም ሌላው ፓርቲም ሆነ ህዝቡ በተመሳሳይ ውጤቱን በፀጋ ተቀብሎ አገርን ማስቀጠል እንደሚገባው ማስገንዘብ ይገባዋል ባይ ነኝ። ምክንያቱም ሁላችንም ለሀገራችን ሰላም የዜግነት ድርሻ አለብን። አንዱ ሰው ላይ ብቻ ጣት አንቀስርም። በተለይ ፓርቲዎች በገቡት ቃል መሰረት ላሸነፈው ፓርቲ መልካም የስራ ዘመን ተመኝቶ በጋራ አገርን ለማቅናት መዘጋጀት ይገባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡– አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫው ወቅት በገዢው ፓርቲ አመራሮች ህገወጥ ተግባራት እንደተፈፀሙባቸው ጠቅሰዋል። ከዚህ አኳያ ስህተቱ ተፈጥሮ ከሆነ በምን መልኩ ነው ሊታረም የሚገባው ይላሉ?
ዶክተር ዮናስ፡– በነገራችን ላይ ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ለሌሎች ሚዲያዎችም በተደጋጋሚ አቋሜን በግልፅ አስቀምጫለሁ። እኔ የምናገረው ለውጥ መምጣት አለበት ብዬ ስለማስብና ላለችን የጋራ አገር ይበጃል ብዬ ስለማምን ነው። በዚህ ረገድ በገዢው ፓርቲ በኩል ከሚታዩ ችግሮች መካከል በዋናነት የወጥነት ችግር ነው። ይህም ማለት አንዱ የሚናገረውን ሌላው ያፈርሰዋል። ከላይ ያለው አመራር የሚሰጠው መመሪያ ታች ሲወርድ ይቀየራል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ብዙ ችግሮች ሲፈጠሩ አስተውለናል። ይህንን በሚመለከት ኢዜማም በማስረጃ አስደግፎ ያቀረበው ሪፖርት የሚታወስ ነው። በርካታ ችግሮች እያሉም ቢሆን እነዚህ ፓርቲዎች በሰላምና በህግ አግባብ ለመንቀሳቀስ መሞከራቸው በእኔ በኩል በበጎ የሚወሰድ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ገዢውም ፓርቲ ሰላምና ፍትህ እንዲሰፍን ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት።
እርግጥ ነው ፤ ለዚህ የሚያስፈልጉ ምቹ ሁኔታዎችን አስቀድሞ ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። በተለይም እንደምርጫ ቦርድ ያሉ የፍትህ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ እንዲሆኑ ማድረጉ በበጎ ጅምር የሚታይ ነው። ነገር ግን በውስጡ መጥራት የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ። ያሉት አመራሮች ሃላፊነታቸውን በሚገባ ያልተወጡባቸው ሁኔታዎችን አይተናል። ስለዚህ እነዚህ ጉዳዮችን ማረምና ውስጡን መፈተሽ ይገባዋል። በተለይም በታችኛው መዋቅር ላይ ያሉ ድክመቶችን በአፋጣኝ ሊያስተካክል ይገባል ብዬ አምናለሁ። ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁኔታዎች እንዳልተመቻቸላቸው አሳማኝ የሆኑ ሪፖርቶች ያሳያሉ። ይህ ደግሞ በተለያዩ አካላት ሲገለፅ የነበረ ጉዳይ ነው። እነዚህ ነገሮች ካልታረሙና ካልተፈተሹ ውጤቱን በፀጋ ለመቀበል እንቅፋት ስለሚሆን የመንግስት አመራሮች በገቡት ቃል መሰረት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተስፋ እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡– ምንአልባት ውጤት ላይ አለመግባባት ቢፈጠርና ጉዳያቸው ወደ ፍርድቤት ቢሄድ ከፍትህ አካላት ምን ይጠበቃል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ዮናስ፡– በአሁኑ ወቅት በፍትሕ ተቋሞቻችን አንፃራዊ የሆነ ገለልተኝነትና ነፃነት አለ ብዬ አስባለሁ። በሃላፊነት ላይ ያሉ የህግ አካላትም ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ሙያቸውን አክባሪና ለፍትህ ተገዢ ናቸው ብዬም አምናለሁ። ይህንን የምልሽ ዝም ብዬ አይደለም፤ አንዳንዶቹንም በቅርበት ስለማውቃቸው ጭምር እንጂ። አብዛኞቹም የኢኮኖሚ ችግር የሌለባቸው ግለሰቦች ናቸው። ለምሳሌ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጊዜ የእንደራሴ ምርጫ ሲካሄድ ሃብት ያላቸው ሰዎች ነበሩ ወደ ስልጣን የመጡት። ይህም የተደረገበት ምክንያት ሃብት ከሌላቸው ወደ ሙስና ይገባሉ ተብሎ ስለሚሰጋ ነው። ይህንን ስልሽ ሃብታም ብቻ ነው ወደ ስልጣን መምጣት ያለበት ማለቴ አይደለም። ይሁንና ሌሎች ከጥገኝነት ነፃ ሆነው መናገር እንዲችሉ ነው። በሙያቸው በትክክል ሃገርን ለማገልገል የሚችሉ መሆናቸውንም በተግባር እያየን ነው። ያ ማለት መቶ በመቶ ከስህተት የፀዳ ነው ማለቴ አይደለም። አንፃራዊ የሆነ መሻሻሎች በመኖራቸው የሚቀርቡ ክሶችን በአግባቡ ፈትሸው ትክክለኛ ፍትህ ይሰጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በተለይም ዳኞች ከማንኛውም ሃይል ተፅዕኖ ውጭ ሆነው መዳኘት ይጠበቅባቸዋል። በጭብጥና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የክርክር ሂደትም ሊኖር ይገባል። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በንፅህናና በፍፁም ራስ መተማመን መንፈስ ጉዳያቸውን ወደ ፍርድቤት ይዘው መምጣት ይኖርባቸዋል።
በሌላ በኩል ግን ለአዲሱ መንግስት ምስረታ ሰላማዊ ሂደት ሁሉም ፓርቲዎች በገቡት ቃል መሰረት መሄድ እንዳለባቸው ለማስገንዘብ እወዳለሁ። በነገራችን ላይ እነሱ የገቡትን ቃል ማክበራቸው ለአዲሱ መንግስት ምስረታ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማስቀጠልም ወሳኝ ሚና አለው። እያንዳንዱ የፓርቲ አባል የሚመሰርተው መንግስት የእገሌ ፓርቲ ደጋፊዎችን ብቻ የሚጠቅም አድርጎ ሊወስድ አይገባም። ይልቁንም በኢኮኖሚም ሆነ በዲሞክራሲ የበለፀገችውን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የሚያስችል ጅማሮ መሆኑን ተገንዝቦ ለሰላማዊ የመንግስት ግንባታ በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ ለማሳሰብ እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼ እና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ዮናስ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2013