የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መንግሥት ባመቻቸላቸው የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ተጠቅመው የተለያዩ ምርቶችን አምርተው ወደ ገበያ በማቅረብ ኅብረተሰቡን እያገለገሉ ያሉበት ሁኔታ
አለ፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በአገር ኢኮኖሚ ላይ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡
የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ ባለፉት ዓመታት ለዘርፉ ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂና ፖሊሲ ተቀርጾ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል። የኢንተርፕራይዞች የቴክኖሎጂ፣ የገበያ እና የፋይናንስ ፍላጎትም እያደገ በመምጣቱ ከፍተኛ የመነሻና የማስፋፊያ የካፒታል እጥረት መኖር አንዱ የዘርፉ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በመሆኑም ጥቂት የማይባሉ ኢንተርፕራይዞቹ ከመንግሥት በሚደረግላቸው ድጋፍ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ተጠቃሚ በመሆን ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ መሸጋገር ችለዋል፡፡ በተመሳሳይም ኢንተርፕራይዞቹ በሚያጋጥማቸው የፋይናንስ እጥረት በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ተጠቅመው ውጤታማ ሳይሆኑ የቀሩና ወደ ቀጣዩ ደረጃ ያልተሸጋገሩም አሉ፡፡
ስለሆነም የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ለማስፋፋት የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን በፋይናንስ ድጋፍ ለመቅረፍ፤ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ባንክ በሚል ባንክ ለማቋቋም የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል።
የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉና በዋናነትም የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ስለመኖሩ በተደጋጋሚ የሚነሳና በተግባር በጥናት የታየ ስለመሆኑ የፌዴራል የከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ በሀይሉ ንጉሴ ያስረዳሉ፡፡
እንደሳቸው ማብራሪያ በዘርፉ የሚያጋጥመውን የፋይናንስ እጥረትን በዘላቂነት ለመፍታት ኤጀንሲው ጥናት አጥንቷል፡፡ የጥናቱ አስፈላጊነትም የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚያጋጥማቸውን የመነሻ ካፒታልና የማስፋፊያ ገንዘብ እጥረት እራሳቸው በሚመሰርቱት የፋይናንስ ተቋም በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው፡፡ በዚህም ባንክ በማቋቋም የቁጠባ ብድር እና የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መንገድ ማግኘት የሚስችላቸውን የራሳቸውን ባንክ መመስረት እንዲችሉ የሚያስችል ጥናት ተጠንቷል፡፡
ኤጀንሲው የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በራሳቸው አቅም ባንክ ማቋቋም የሚችሉበትን መንገድ በመዘርጋት አስቻይ የሆኑ ዝግጅቶችን አድርጓል፡፡ አስፈላጊውን ጥናት በማድረግም ጥናቱን ለሚመለከታቸው አካላት ማለትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ከሥራ ፈጠራ ኮሚሽን፣ ከመካከለኛና አነስተኛ ተቋም የመጡ አመራሮች በተገኙበት እንዲሁም የተለያዩ የማይክሮ ፋይናንስ አመራሮችም ተሳትፈውበታል፡፡ በውይይቱ በተለይም ብሔራዊ ባንክ የሰጠውን ጥቂት ማስተካከያዎች በማሻሻል ባንኩን መመስረት የሚያስችል ቁመና መኖሩን አቶ በሀይሉ አስረድተዋል፡፡
የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ባንክ መመስረት አስፈላጊ መሆኑን ያካፈሉን አቶ በሀይሉ፤ በተለይም ጀማሪ ኢንተርፕራይዞች ቢዝነሳቸውን ለማስፋፋት የሚያስፈልጋቸውን ከፍተኛ ገንዘብ በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ የባንኩ መቋቋም የግድ መሆኑን አጋርተውናል፡፡ ባንኩ የሚቋቋመውም ኢንተርፕራይዞቹ በሚያዋጡት ገንዘብ በመሆኑ ባንኩ የራሳቸው ባንክ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ከኢንተርፕራይዞች ውጪ ያለ ማንኛውም ዜጋ አክሲዮን በመግዛት አባል መሆን የሚችል ይሆናል፡፡
የውጭ አገር ተሞክሮም የሚያሳየው ይህንኑ እንደሆነ አቶ በሀይሉ አንስተው ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ እጥረት ማቃለል የሚችሉት በራሳቸው አቅም ባንክ በማቋቋም የባንኩ ባለቤት በመሆን ነው፡፡ ለአብነትም ቻይና፣ ኮርያ የሚጠቀሱ ሲሆን አፍሪካ ውስጥም ናሚቢያና ጋና በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ ባቋቋሙት ባንክም ውጤታማ ሆነው በፋይናንስ በኩል የሚገጥማቸውን ችግር መፍታት ችለዋል፡፡ ዘርፉ ካለው ፋይዳ አንጻር እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢንተርፕራይዞችና ፍላጎት በአገር ውስጥ በመኖሩ የባንኩ ምስረታው የዘገየ ስለመሆኑ አቶ በሀይሉ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ባንኩ ወደ ሥራው ለመግባትም የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎች አሉት፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት ድጋፍም እንዲሁ ያላቸው በመሆኑ ባንኩ ሲቋቋም በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው አስተዋጽኦው የጎላ ይሆናል፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ ከሚያጋጥማቸው የፋይናንስ እጥረት በተጨማሪ የብድር አቅርቦት በተቀላጠፈ መንገድ ማግኘት ካለመቻላቸው ባለፈ ከፍተኛ የወለድ መጠን በመኖሩ መንግሥት ኢንተርፕራይዞቹ ላይ በሚፈለገው ደረጃ አልሰራም በመሆኑም ባንኩ ሲቋቋም ከዘርፉ የሚጠበቀው ውጤት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምክንያቱም አብዛኞቹ ኢንተርፕራይዞቹ እያጋጠማቸው ባለው የፋይናንስ እጥረት በሙሉ አቅማቸው ተጠቅመው የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ ነገር ግን ጥቂት የማይባሉ ኢንተርፕራይዞች ደግሞ የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ ዕጥረት በራሳቸው ጥረት ከቤተሰብ እና ከተለያዩ አካላት በማግኘት ቢዝነሳቸውን በማስፋፋት የተሻለ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ በዚህም ዕውቅና አግኝተው ተሸላሚ መሆን የቻሉ ኢንተርፕራይዞችም አሉ፡፡
መንግሥታዊ ከሆኑ አቅርቦቶች መካከል የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን ማቅረብ፣ ብድር ማመቻቸትና የተለያዩ ሥልጠናዎችን የመስጠት ሥራዎች የሚሰሩ ቢሆንም ውስንነቶች እንዳሉ አቶ በሀይሉ አንስተዋል፡፡ ለዚህም ከመንግሥታዊ ድጋፎች አንዱ የሆነውን የፋይናንስ አቅርቦት በማመቻቸት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ባንክ ለማቋቋም በተዘጋጀው የፍላጎት ዳሰሳ ረቂቅ ጥናት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ተጨማሪ መረጃዎችንና አስተያየቶችን በመሰብሰብ ሰነዱን በማዳበር፤ በቀጣይ ባንኩ ስለሚቋቋምበት የአዋጭነት ጥናትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ መድረኩ መዘጋጀቱን አቶ በሀይሉ ተናግረዋል፡፡
ኤጀንሲው በመዝገብ የሚያውቃቸው ኢንተርፕራይዞቹ ከ750 ሺ በላይ ሲሆኑ፤ እነዚህ ኢንተርፕራዞች በተጨባጭ ስለመኖራቸውም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማረጋገጥ ሥራ ይሰራል፡፡ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ባንክን የሚያቋቁሙት እነዚሁ ኢንተርፕራይዞች ሲሆኑ በተጨማሪም ከኢንተርፕራይዞቹ ውጪ የሆኑ ዜጎችም አክሲዮን ገዝተው ተሳታፊ መሆን የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩን አቶ በሀይሉ ተናግረዋል፡፡
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2013