የሚጥል ህመም /Epilepsy በአለም ላይ 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን የሚያጠቃ ስር የሰደደ እና ተላላፊ ያልሆነ የአንጎል ህመም ነው። ይህ ህመም ተደጋጋሚ በሆነ እና መቆጣጠር በማይቻል ንዝረታዊ የሰውነት እንቅስቃሴ (የተወሰነውን የአካል ክፍል ወይም ሙሉ የአካል ክፍልን ሊያጠቃ ይችላል) የሚገለጽ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም እራስን መሳትና ሽንትና ሰገራን የመቆጣጠር ችግር ሊኖረው ይችላል። ንዝረታዊ የሰውነት እንቅስቃሴዎች በተወሰኑ ወይም በሁሉም የአንጎል ክፍሎች ከፍተኛ የሆነ የነርቭ ኤሌክትሪካል መልዕክት መለቀቅ ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው ። ይህም የተለያዩ የአንጎል ክፍሎች የመልዕክቱ መነሻ ሊሆኑ ሲችሉ ችግሩም ከአነስተኛ የሀሳብ መሰረቅ እና የተወሰነ የሰውነት ክፍል እንቅስቃሴ እስከ ብዙ
ደቂቃ የሚቆዩ የሰውነት ማንቀጥቀጥ ሊደርስ ይችላል። ይህ ህመም በአመት አንድ ጊዜ መከሰት እስከ በቀን ለብዙና ተደጋጋሚ የማንቀጥቀጥ ችግር ሊደርስ ይችላል። አንድ ጊዜ ብቻ የሚከሰት ንዝረታዊ የሰውነት ማንቀጥቀጥ የመጣል ህመምን ላያመለክት ይችላል ፤ ስለዚህም እንደ አለም ጤና ድርጅት ትርጉም የመጣል በሽታ ለመባል ሁለትና ከዚያ በላይ የሆነ ቀስቃሽ የሌለው የሰውነት ማንቀጥቀጥ መኖር እንደሆነ ይገልፃል። የሚጥል ህመም ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ችግር እንደሆነ እና ከክርስቶስ ልደት 4ooo ዓመት በፊት ጀምሮ ይታወቅ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። የዚህ ህመም ተጠቂዎች በተሳሳተ አመለካከት እና በግንዛቤ እጥረት ምክንያት በፍርሀት እንዲኖሩ፣ መገለል እና መድልኦ እየደረሰባቸውና ህክምና ባለማግኘት ለኑሮ መመሰቃቀል ተዳርገዋል።
ምልክቶች
• የህመሙ ምልክቶች ከተነሳበት የአንጎል ክፍል አንፃር እና ከሚያጠቃው የአንጎል ክፍል ስፋት አንፃር የተለያየ ነው። ይህም ጊዜያዊ የሆነ እራስን መሳት፣ የእንቅስቃሴ መዛባት፣ ለእይታ መቸገር ( ብዥታ)፣ የመስማትና እና የመቅመስ ችግሮችን ያጠቃልላል።
• የሚጥል ህመም ከማንቀጥቀጡ ጋር ተያይዞ በሚከሰት አካላዊ የሆነ ጉዳትን (ስብራት፣ የቆዳ መጫጫር) ያስተናግዳሉ፤ ከዚህም በተጨማሪ ለድባቴ፣ ለጭንቀት እና ለመሳሰሉት የአእምሮ ህመሞች ተጋላጭ ይሆናሉ።
• ችግሩ በሚከሰትበት ጊዜ በሚፈጠሩ (መውደቅ፣
ውሀ ውስጥ መስመጥ፣ እሳት ላይ መውደቅ እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ማንቀጥቀጥ) ምክንያቶች ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ።
ምን ያህል ሰው ያጠቃል?
• በየአመቱ 5 ሚሊዮን ሰዎች ይጠቃሉ፤
• በአደጉ ሀገራት 49/100,000 ሰዎች በዚህ ህመም ሲጠቁ፤ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ደግሞ 139/100,000 ሰዎችን ያጠቃል።
• ይህም ከፍተኛ ከሆነ ወባና ሌሎች አንጎልን የሚያጠቁ ችግሮች መኖር፣ የመኪና አደጋ፣ ህፃናት ሲወለዱ በሚደርስ ችግር እና የህክምና እጦት ጋር የተያያዘ ሲሆን ይህም 80 በመቶ የህመሙ ተጠቂዎች ዝቅተኛ ገቢ ባለላቸው አገሮች እንዲኖር አድርጓል።
የሚጥል በሽታ በምን ይመጣል ?
የሚጥል ህመም ከሰው ወደ ሰው የማይተላለፍ ሲሆን የተለያዩ ይህን ችግር የሚያመጡ ምክንያቶች ቢኖሩም 50% የሚሆነው ግን ምክንያቱ የማይታወቅ ሲሆን፤ ከ50 በመቶ ምክንያቶቹ መካከል፤
• በእርግዝና እና በወሊድ ጊዜ በሚፈጠሩ የአንጎል ጉዳት (ኦክስጅን ማጣት)
• የአንጎል የአፈጣጠር ችግር
• ከፍተኛ የጭንቅላት ጉዳት (መውደቅ፣ መጋጨት)
• የአንጎል ምት (Stroke)
• አንጎልን የሚያጠቃ ኢንፌክሽን (ማጅራት ገትር፣ ወባ፣ ኢንሴቫላይቲስ)
• የዘረመል ችግር
• የጭንቅላት እጢ
አልኮል
ህክምናው
• 70% የሚሆኑት ታማሚዎች ተገቢውን ህክምና ካገኙ ከንዝረታዊ የሰውነት ማንቀጥቀጥ መዳን ይችላሉ።
• መድሀኒቶች – lamotrigine, topiramate, valproic acid, zonisamide, phenytoin, carbamazepine, ethosuximide, A ketogenic diet, Vagal nerve stimulation እና ቀዶ ጥገና በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው።
መከላከል
• እራስ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን መቀነስ (ሄልሜት ማድረግ)
• የእርግዝና ክትትል ማድረግ እና ሆስፒታል መውለድ ችግሩ መች እንደሚከሰት ስለማይታወቅ ከዚህ በፊት ከነበረ አደገኛ ከሆነ ነገሮች መቆጠብ፤ የውሀ ዋና እና ሌሎችም።
ምንጭ ፦Doctor M Home Ccare service
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2013