የምንገኝበት የክረምት ወር እና ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ መገጣጠሙ ለሶስተኛው ዙር ‹‹ኢትዮጵያን እናልብሳት›› በሚል ለሚካሄደው ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ እስከሚቀጥለው የምርጫ ጊዜ የሚመራውን በምርጫ ካርዱ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ የወሰደ ሁሉ እግረ መንገዱን ችግኝ በመትከል በአረንጓዴ አሻራ በመሳተፍ የማይረሳ ታሪክ አስቀምጧል፡፡
ኢትዮጵያ በአምስት ዙር ካካሄደችው ሀገራዊ ምርጫ ስድስተኛውን ዙር ለየት የሚያደርገውም ይኸው አጋጣሚ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እንደሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት ለሚደረግ ጥረት ችግኝ ተከላውና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ ተደርገው መወሰዳቸው እንደሆነ ብዙዎች ብለውታል፡፡በመሆኑም ህዝቡ ከመንግሥት በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በአንድ እጁ የምርጫ ካርድ በሌላኛው ደግሞ የዛፍ ችግኝ በመያዝ ለአረንጓዴ አሻራና ለዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የቀረበለትን ሀገራዊ ጥሪ በተግባር አረጋግጧል፡፡
‹‹እየመረጥን ችግኝ እየተከልንም ታሪክ እንሰራለን››፣ ‹‹እመርጣለሁ አረንጓዴ አሻራም አኖራለሁ››፣ ‹‹ችግኝ እየተከልን ዴሞክራሲን እንተክላለን›› የሚሉ የተለያዩ አስተያየቶች በተለያዩ ሰዎች በስፋት ሲሰጥ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ችግኝ የመትከሉ መርሃ ግብር ዓላማ በምርጫው ተፎካካሪ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም አንድ ያደረገ ነበር ማለት ይቻላል፡፡አንድ ተፎካካሪም ችግኝና ዴሞክራሲ ሁለቱም ሥር እንዳላቸውና ሥሩ በደንብ ካልያዘ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡እነዚህ ሁለት ጠንካራ መሠረት ያላቸው ነገሮች ትኩረት ሊያገኙና ተተኪውም ትውልድ ሊያስቀጥለው እንደሚገባ ነበር ሲናገሩ የተደመጡት ፡፡
ከሀገራዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ጎን ለጎን ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመሳተፍ ኢት ዮጵያን እናልብስ በሚለው መሪ ሀሳብ ላይ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከልም በአማራ ክልል አዊ ዞን ጓንጓ ወረዳ ቻግኒ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ወጣቶች ይጠቀሳሉ፡፡በሥፍራው ለምትገኘው የአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ ሀሳባቸውን ያካፈሉት ወጣት ይልቃል መልኬ እና እንድሪስ ዓሊ እንደገለጹት፤ እነርሱን ጨምሮ አስራ አምስት የሚሆኑ የአንድ አካባቢ ወጣቶች ያለማንም ግፊት እንደሀገር የተያዘውን መርሃግብር ለማሳካት ችግኝ በመትከልና በካርዳቸውም ይበጀናል ያሉትን እጩ ተወዳዳሪ በመምረጥ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡
ወጣቶቹ እንዳሉት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ አነሳሽነት ስለተጀመረና እርሳቸው ስላሉ ብቻ ሳይሆን አረንጓዴ አሻራ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ተገንዝበው ጭምር ነው፡፡ የሚመራቸውን መሪ በምርጫ ለመለየት ጥረት እንዳደረጉት ሁሉ የሰውን ልጅ ህይወት ለማስቀጠል ትልቅ ቦታ ያለውን ችግኝም መትከል የማይነጣጠል ተግባር ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ወጣቶቹ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ለማሳካትም የተለያየ ዝርያ ያላቸው 300 ችግኞችን በአካባቢያቸው ተክለዋል፡፡ ቀሪውን የክረምት ጊዜም በዚሁ ተግባር በመሳተፍ እንደሚያሳልፉ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ባለሀብቶችና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ውስጥ ችግኝ በመትከል በከተማዋ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ችግኝ መትከል ሰላም መትከል መሆኑን ነው የገለጹት ፡፡ ምክትል ከንቲባዋ ለሁሉም ነገር መሠረት የሆነውን ሠላም ያሰመሩበት በጊዜያዊ አለመግባባት በመካከላቸው ቅራኔ የተፈጠረ ሰዎች ችግሮቻቸውን ለመፍታት በዛፍ ጥላ ሥር ነው የሚገናኙት በማለት ነው ባለውለተኛነቱን ያስታወሱት።
‹‹አሸማጋዮችም ዳኝነት ለመስጠት የዛፍ ጥላ ሥርን ይመርጣሉ፡፡በጫንቃቸው ሞፈርና ቀንበር ተሸክመው መሬቱን በማረስ ለዘር የሚያለሰልሱት በሬዎችም ከድካማቸው የሚያርፉት በዛፍ ጥላ ሥር ነው፡፡በአጠቃላይ የደከመን ጥላ ሆኖ ከድካሙ የሚያበረታ፣ድርቅን በመከላከል ለአረንጓዴ ልማቱ አስተዋጽኦ ያለው የዛፍ ችግኝ ተከላ በዚህ የምርጫ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ልዩ ትኩረት አግኝቷል፡፡›› ሲሉ ጠቅሰዋል።
የአረንጓዴ ልማት ሥራ ለኢትዮጵያ አዲስ ባይሆንም አንዳንዴ የታሪክ ግጥምጥሞሽ ነገሩን ለየት ሲያደርገው በተለየ ሁኔታ ይነሳል ትኩረት ለመስጠት የፈለግነውም ለዚሁ ነው ፡፡ይህንን አጋጣሚ የጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ስለሺ ደገፋ እንዲህ ሲሉ ይገልጻሉ ፡፡ምርጫውና የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ትልቅ አጀንዳ እና የዜግነት ግዴታም ነው፡፡በግላቸው ለአረንጓዴ አሻራትኩረት መሰጠቱ አስደስቷቸዋል፡፡ ካለፉ ምርጫዎች እንዲህ ያለ ተሞክሮ አልተለመደም፡፡
ምርጫን ተቃውሞ የተለያዩ ጎጂ የሆኑ ነገሮች ሲፈጸሙ በተለይም ወጣቱን በመጠቀም ይደረጉ የነበሩ እኩይ ተግባሮችን ነው የሚያስታውሱት፡፡በአሁኑ ምርጫ እኩይ ተግባርን ከማየትና ከመስማት ይልቅ ጠቃሚ በሆነ ነገር ላይ ዜጎች ማሳለፋቸው ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በተለይም ምርጫው እንዳይሳካ ግፊት ሲያደርጉ የነበሩ የውጭ ኃይሎችን አንገት የሚያስደፋ መሆኑ ደግሞ የበለጠ የደስታ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ሀገርንም ያኮራ ተግባር ነው፡፡ መላው ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደረግ አጀንዳ ሆኖም ተገኝቷል፡፡
የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል እንደ ሀገር ከሁለት አመት በፊት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሲሳተፍ ቢቆይም በተለይም ለምርጫው ተብሎ በተዘጋጀው ኢትዮጵያን እናልብሳት በሚል መርሃ ግብር በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ከከተማ አስተዳደሩ ተፋሰስና አረንጓዴ ልማት፤ ከአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ጋር በጋራ በማቀድ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ነው ወደተግባራዊ እንቅስቃሴው የተገባው፡፡ በዕቅዱ መሠረትም ወደ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊየን ለመምረጥ ምርጫ ካርድ የወሰደው የከተማዋ ነዋሪ እያንዳንዱ ሁሉት ችግኝ ቢተክል በከተማዋ ወደ ሶስት ሚሊየን የሚጠጋ ችግኝ ይተክላል ተብሎ ቅድመ ዕቅድ ላይ ቢቀመጥም የማይመርጥ ሊኖር እንደሚችል ግምት ውስጥ ገብቷል፡፡ ያም ሆኖ ግን 90 በመቶ የሚሆን መራጭ ቢሳተፍ ወደ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ችግኞች ይተከላሉ፡፡ በዚህ መሠረት ለማሳካት ጥረት ተደርጓል፡፡እስከ ምርጫው ዕለት ባለው መረጃም ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊየን ችግኞች በሁሉም የከተማዋ ክፍለ ከተሞች ተተክለዋል፡፡
በዜጎች የሚጠበቀው ሀገራዊ ምርጫ በተካሄደበት ወቅት ጎን ለጎን አረንጓዴ ልማት መካሄዱን መሠረት አድርገው ባስተላለፉት መልዕክትም አረንጓዴ ልማቱ ከየትኛውም የሀገሪቱ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ጋር ተቀናጅቶ መከናወን ይኖርበታል፡፡ለአብነትም የአረንጓዴ ልማቱ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ላለው የከተማ ማስዋብ ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ሁኔታ በመጎዳት ላይ በመሆኗ በተለይም ቆላማው የሀገሪቱ ክፍል በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ነው፡፡
የሀገሪቱ ብዝሃ ህይወትም በመመናመን ላይ ይገኛል፡፡የአረንጓዴ ልማቱ መጠናከር እንዲህ ያለውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ያግዛል፡፡በአጠቃላይ ለአርሶአደሩ፣አርብቶአደሩናለከተማው ነዋሪ የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ዜጎች ሀገር በቀል ችግኝ በመትከል እንደተረባረቡት ሁሉ ችግኞቹ ጸድቀው የታለመው ዓላማ ከግብ እንዲደርስ ተንከባክቦ ችግኞችን በማጽደቅ በኩልም ጥረት እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡በሶስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ በአዲስ አበባ ከተማ ወደ ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊየን ችግኞች ለመትከል መታቀዱንም ዶክተር ስለሽ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን በየአመቱ በማሳደግ በማከናወን ላይ ስትሆን፣በመጀመሪያው ዙር እንደ ሀገር የተያዘው ዕቅድ አራት ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ሲሆን፣ክልሎች የየራሳቸውን ዕቅድ አካተው በመፈጸማቸው አተገባበሩ ግን ከዚያም በላይ እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡በሁለተኛው ዙር መርሃ ግብር ደግሞ አምስት ቢሊየን ችግኝ ነው የተዘጋጀው፡፡ በአሁኑ በሶስተኛው ዙር ስድስት ቢሊየን ችግኞች እንደሚተከሉ በመንግስት እቅድ ወጥቶ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቋል። የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬም ተካትቶ መከናወኑ ደግሞ ጥቅሙን የጎላ አድርጎታል፡፡
ከሶስት አመት በፊት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሲጀመር በአንድ ቀን 300 ሚሊየን ችግኝ በመትከል በዓለምአቀፍ ደረጃ ተይዞ የነበረውን ክብረሰወን ኢትዮጵያ መውሰዷ ይታወሳል፡፡ክብረወሰኑን በመስበር የታላቅ ታሪክ ባለቤት ከመሆንም በላይ በደን መጨፍጨፍና በተለያየ ምክንያት ተራቁቶ የነበረውን የደን ሽፋን መልሶ እንዲተካ በማድረግ አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ነበር፡፡ የሙቀቱ ማየል ዓለምን ሥጋት ላይ በጣለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማቱ ርብርብ ማድረጓ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት አድርጓታል፡፡
የአረንጓዴ አሻራንና የአዲስ አበባ ከተማን በማስዋብ እንደስሟ አበባ ለማድረግ እየተከናወነ ስላለው ተግባር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ እንደተናገሩት መንግሥት እሰራለሁ ብሎ ቃል የገባውንና ለዜጎች የሰጠውን ተስፋ በተግባር በመፈፀም አቅም በፈቀደ መጠን በመትጋት ቃሉን በተግባር ማዋል ይኖርበታል፡፡ አዲስ አበባ ከተማን እንደስሟ አበባ ለማድረግ እንቅስቃሴው ሲጀመር ቤት አፍርሶ ከማልማት አዲስ ከተማ ቢመሰረት የተሻለ እንደሆነ በብዙዎች አስተያየት ሲሰጥ እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡እርሳቸው እንዳሉት መንግሥት አጥር አጥሮ ሰፊ መሬት በመያዝ እንደ አዲስ አበባ ከተማ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ይሄን የወል መሬት ጥቅም ላይ በማዋል አዲስ አበባ ከተማን መለወጥ ይቻላል የሚለው አንዱ የመንግሥት ቁርጠኝነት ማሳያ ነበር፡፡
ሌላው አብዛኛው የአዲስ አበባ ከተማ ቤት አለው ለማለት አያስደፍርም፡፡መጸዳጃ ቤት በሌለው በተጎሳቆለ ቤት ውስጥ የሚኖር በመሆኑ የቤቶቹ መፍረስ ቁጭት ውስጥ የሚከቱም አይደሉም፡፡በተጨማሪም አዲስ አበባ ከተማ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማዕከል መሆኗም እንዲሁም መልክአ ምድሩ ለልማት ምቹ መሆኑና ሌሎችም ተደምረው ልዩ ትኩረት እንድታገኝ አድርጓታል፡፡እነዚህን ሁሉ መነሻዎች በማድረግ አዲስአበባ ከተማ ላይ የተጀመረው ከተማዋን የማስዋብ ሥራ ሌሎች ከተሞችንም በተመሳሳይ ለማስዋብ ዕድል ይሰጣል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2013