የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምርጫውን በሰላም መጠናቀቅ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት”እንደ ሀገር ሉዓላዊነታችንን ለዘመናት ሳናስደፍር ኖረናል ። እንደ ሕዝብ ግን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትና ምንጭ አልነበርንም።…” በማለት ነጻነታችን የሕዝብን ሉዓላዊነት ያላካተተ እንደነበር አውስተዋል። ይህ መልዕክታቸው በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆነው ሬይሞንድ ጆናስ” አፄ ምኒልክና የአድዋ ድል”፣ በተሰኘው ማለፊያ መጽሐፍ ፤”ልንታደለው የሚገባን ነፃነት ልንከላከለው የሚገባ መሆን እንዳለበት አድዋ ያስታውሰናል፡፡”ያለበትን አውድ እንዳሰላስል አድርጎኛል።
የአድዋን ድልም ሆነ ከሶስት አመት በፊት በጭቆናና በአፈና ላይ የተቀዳጀነው ድል ልንከላከለውና ልናስቀጥለው የምንችለው ሕዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆኑን ስናረጋግጥ ነው። ይህ ከድህረ አድዋ እስከ 2010 ዓ.ም ለውጥ ድረስ ሳይሆንልን ቀርቷል። በዚህ የተነሳ ነጻነታችን ግምሽ እንጂ ሙሉ ስላልነበር አልጠበቅነውም ። በለውጡ ማግስት ግን የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባትና በዚህ መሰረት በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጻ ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ ከሶስት አመት በፊት የተቀዳጀነውን ድል መከላከልና መጠበቅ ሀ ብለን ጀምረናል። ቢያንስ እኔ የመራጭነት ካርድ በወሰድሁበትና ድምጼን በሰጠሁበት ምርጫ ጣቢያ ይሄን አረጋግጫለሁ። ብርድ ብርድ ሲለው በከረመው ብቸኛውን ሀገራዊ ሉዓላዊነት ላይ የሕዝብ ሉዓላዊነት በሰሞነኛው ምርጫ ጋቢ ደርቧል።
ሀገራችን ከ3ሺህ አመታት በላይ ሊወሯት ቅኝ ሊገዟት የመጡ ጠላቶቿን አሳፍራ ድል አርጋ መልሳለች ። ግብጽ፣ ደርቡሽ፣ ቱርክ፣ ጣሊያን፣ ሱማሊያ ፣ ወዘተረፈ በተለያዩ ጊዜያትና በተደጋጋሚ ሀገራችንን የመውረርና ቅኝ ተገዥ የማድረግ ከንቱ ምኞታቸው በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ተጋድሎና አልበገርባይነት መክኗል ። አንጸባራቂው የሰው ልጆች ድል አድዋ እና የካራማራ ድል ትውልዶች ሲቀባበሏቸው ከኖሩት የነጻነት ፣ የሉዓላዊነትና የአትንኩኝ ባይነት ችቦዎች መሀከል ይጠቀሳሉ ።
በተለይ የአድዋ ድል ጥቁር ሕዝብ እስከ አፍንጫው የታጠቀን የአውሮፓን እብሪተኛ ወራሪ ማሸነፍ እንደሚቻል ያስመሰከረ ፋና ወጊ ታሪካዊ ክስተት ነው ። ሆኖም እነዚህ አንጸባራቂ ገድሎቻችን የሀገርን ሉዓላዊነት አስከበሩ እንጅ የሕዝቡን ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የቻሉ አልነበሩም። እስከዚህ ምርጫ ድረስ ሉዓላዊነታችን ግማሽ እንጅ ሙሉ አልነበረም። አዎ ! ዜጋው በቅኝ ገዥዎች ባይሆንም በገዛ ልጆቹ ነጻነቱና መብቱ ተረግጦና ተጨፍልቆ ለዘመናት ሲማቅቅ ኖሯል። ሕዝቡ ከጥንት እስከ ዛሬ ከላይ ከፈጣሪ ተመርጠን የተቀባን ስዩመ እግዚአብሔር ነን ከሚሉት አንስቶ በነፍጥ መንበር ላይ የተቀመጡ ገዥዎች ለዘመናት ሲፈራረቁበት ኖረዋል ። በገዛ ሀገሩ ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ ኖሯል። ብቸኛ ሉዓላዊ የስልጣን ምንጭ ቢሆንም ይህ መብቱ ተከብሮ አያውቅም። እኔ አውቅልሀለሁ እየተባለ አበሳውን፣ ፍዳውንና መከራውን ሲያይ ኖሯል። በግርማዊነታቸው፣ በደርግ፣ በህወሓት/ኢህአዴግ የተደረጉ መረጣዎች/selections/እንጅ ምርጫዎች/elections/ አልነበሩም።
የ97ቱ ቅድመም ሆነ ድህረ ምርጫ ሒደት በዜጎች ተስፋ ተሰንቆበት የነበር ቢሆንም የሕዝብ ድምጽ በቀን በአደባባይ ተዘርፏል ። ቅንጅት አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በአብላጫ ድምጽ አሸንፏል ተብሎ ቢታመንም በአፈሙዝና እንደ ምርጫ ቦርድ ባሉ በአምሳሉ ጠፍጥፎ በሰራቸው ተቋማት ጀሌነት የሕዝብ ድምጽ ተሰርቋል። በሰላማዊ ሽግግር ስልጣን መያዝ የሚገባቸው የቅንጅት አመራሮች ባልዋሉበት ታርጋ ተለጥፎላቸውና በሀሰተኛ ክስ ዘብጥያ ወርደዋል። አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ለጅምላ እስር ፣ ለግርፊያ ፣ ለድብደባና ለተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተዳርገዋል።
በየከተሞች ድምጻችን ይከበር ያሉ ሰላማዊ ሰልፈኞች በግፍ ተገለዋል ። አካላቸው ጎሏል ። በተለይ በአዲስ አበባ ድምጻችን ይከበር ያሉ ከ200 በላይ ወጣቶችና ህጻናት በአንድ ቀን በመለስ ትዕዛዝ በአግዓዚ ልዩ ኃይል አልሞ ተኳሾች በግፍ ተገድለዋል። የበርካቶች አካል ጎድሏል ። በዚህ ጭልጭል የነበረች የዜጎች ተስፋ ጨልማለች ። ህወሓት/ኢህአዴግ የ2007 ዓ.ም ምርጫን መቶ በመቶ አሸነፍሁ ባለ አመት ባልሞላ ጊዜ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተቀጣጠለ ሕዝባዊ አመጽ እና በግንባሩ ውስጥ ባሉ ለውጥ ፈላጊዎች በተካሄደ ተመጋጋቢና የተንሰላሰለ ትግል በመጋቢት 2010 ዓ.ም የለውጥ ኃይሉ ወደ ኃላፊነት ሊመጣ ችሏል ።
የዛን ጊዜው የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር እጅን በአፍ የሚያስጭኑ ፈጣን ለውጥ ከማሳየታቸው ባሻገር ነጻ ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ በገቡት ቃል መሰረት ከ38 ነጥብ 2 በላይ ዜጎች የተሳተፉበት ምርጫ ያለአንዳች ኮሽታ ተካሂዷል ። በዚህ አጋጣሚ ምርጫ ቦርድና ታዛቢዎች ወደፊት የሚያረጋግጡት ሆኖ እኔ ድምጼን በሰጠሁበት የምርጫ ጣቢያ ምርጫው ነጻ ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን በአስር ጣቴ የማረጋግጥ ቢሆንም በበነጋው የተለጠፈው ጊዜያዊ ውጤትም እምነቴን ያጸና ሆኖ አግኝቸዋለሁ ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳም፤”ከሞላ ጎደል ምርጫው ሰላማዊ ነው። የመራጩ ተሳትፎ ልብን ያሞቃል ።”ብለዋል ።
ይህ ምርጫ ከምርጫም በላይ የሀገሪቱን መጻኢ እድል የበየነ ውሳኔ ሕዝብ /referendum/ ነው ። ሕዝቡ ማንንም መረጠ ማንን ዴሞክራሲን መርጧል ። ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት ከዘመናት ውጣ ውረድ በኋላ የመጀመሪያዋን የዴሞክራሲ መሰረት ጡብ አስቀምጧል ። ሉዓላዊነቱን ሙሉ ለማድረግ የሚያስችለውን እርምጃ አሀዱ ብሏል ። በሀገሪቱ ታሪክም በወሳኝ መታጠፊያነት/critical juncture/ በትውልድና በታሪክ ሲወሳና ሲዘከር ይኖራል። የሰው ልጅ ከፍ ሲልም ሀገርና ሕዝብ በያለፉበት መንገድና በየተገለጡበት ገጽ የየራሳቸው የሆነ ወሳኝ መታጠፊያ አላቸው።
ቀጣይ እጣ ፈንታቸውን በአዲስ የሚበይንና የሚለውጥ ሁነት አልያም አጋጣሚ ይከሰታል። ዛሬ በአለማችን እየተመለከትነው ያለ የኢኮኖሚ ብልፅግና የዴሞክራሲያዊነት ልዩነት ጥንስስ የተበጀው የአለምን ግማሽ ሕዝብ እንደጨረሰ በሚነግርለት እኤአ በ1346 ዓ.ም በተከሰተ ጥቁሩ ሞት ወሳኝ መታጠፊያ ሳቢያ ነው። ዳረን አኪሞግሉ እና ጄምስ ሮቢንሰንን በጣምራ በዘጋጁት፤” WHY NATIONS FAIL” በተሰኘ ግሩም ድንቅ መጽሐፍ ገጽ 101 ላይ ስለ ወሳኝ መታጠፊያ ፤”…ጥቁሩ ሞት የወሳኝ መታጠፊያ ጉልህ ማሳያ ነው ። ወሳኝ መታጠፊያ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ መስተጋብሮች እንደ አዲስ የሚበይኑና የሚጠረምሱ ዓበይት ሁነቶች ናቸው።…”ይላል።
በቅኝ ግዛት መያዝም ሆነ ነጻ መውጣት ወሳኝ ምዕራፍ ነው። ሀገራት ነጻነታቸውን ሲቀዳጁ ወይም ሲያገኙ መንታ መንገድ ይገጥማቸዋል። ከግል ጥቅም ይልቅ ሀገርንና ሕዝብን የሚያስቀድመውን አሳታፊ ፓለቲካዊ ስርዓትና አካታች ኢኮኖሚያዊ ፈለግ መከተል የመጀመሪያው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አሮጌውን አፋኝና በዝባዥ አገዛዝ በአዲስ መተካት ነው። አሮጌ ወይን በአዲስ አቀማዳ እንዲሉ። በድህረ ቅኝ ግዛት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጡ ሀገራት መልሰው በአምባገነናዊ አገዛዝ መዳፍ ስር ወድቀዋል። አፍሪካን ብንወስድ ከቦትስዋና በስተቀር ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ነጻ እንደወጡ በሀገሬው አምባገነናዊ መሪ ተተክተዋል። ብዝበዛውም ተባብሶ ቀጥሏል።
በአንጻሩ በ1966 ዓ.ም ከእንግሊዝ ነጻነቷን ያገኘችው የዛን ጊዜዋ ቤኩዋናላንድ የዛሬዋ ቦትስዋና ወሳኝ መታጠፊያዋን ሳታባክን በአግባቡ በመጠቀሟ አካታች ስርዓትን መምረጧና የዴሞክራሲያዊና የነጻ ገብያ ተቋማትን መገንባት መቻሉ ከአህጉሩ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ተደጋግማ በአርዓያነት ትጠቀሳለች።
በፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ፣ “ A History Of Modern Ethiopia ,1855 – 1991 “ በተሰኘው ድንቅ መፅሐፍ ላይ ደጃች ካሳ ሀይሉ / ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ / የዘመነ መሳፍንት የስልጣን ሽኩቻንና የቱርኮች ወረራ በመመከት የዘመናዊ ኢትዮጵያ ጥንስስ እንደጣሉ ያወሳሉ ፡፡ ይሄን የዘመናዊት ኢትዮጵያ ዘመን በአብነት ብንወስድ አፄ ቴዎድሮስ ፣ አፄ ዩሐንስ ፣ አፄ ምንልክ ፣ እቴጌ ጣይቱ ፣ ልጅ ኢያሱ ፣ ንግስት ዘውዲቱ ፣ አፄ ሀይለስላሴ ፣ ደርግና ትህነግ/ኢህአዴግ የሀገራችንን መጻኢ እድል በአዎንታ መለወጥ የሚችሉ ወሳኝ መታጠፊያዎች በእጃቸው ገብተው የነበረ ቢሆንም በአግባቡ ሳይጠቀሙባቸው ባክነው ቀርተዋል።
ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን አንስቶ በጊዜው አውድ አሳታፊ የሆነ ፓለቲካዊ ስርዓት እና አካታች ኢኮኖሚያዊ ስልት ተነድፎ በተከታታይ እየተደመረበት ዛሬ እስከምንገኝበት ዘመን ድረስ ቢቀጥል ኖሮ ሀገራችን በብልፅግና ጎዳና መሪ ትሆን ነበር ። የቀደሙትን አገዛዞች ትተን ደርግ ወይም ትህነግ አሳታፊ ፓለቲካዊ ስርዓትና አካታች ኢኮኖሚያዊ ፓሊሲን ቢከተሉ ኖሮ ዛሬ በምንገኝበት አረንቋ ባልተዘፈቅን። የሀገራችን ቀውስ፣ ፈተና፣ አሳርና ፍዳ ሳይፈታና መፍትሔ ሳያገኝ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲንከባለል መጥቶ ህልውናዋ ላይ አደጋ ባልደቀነ ነበር።
ከለውጡ በፊት የነበሩ ሶስት ፈታኝ ተከታታይ አመታት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመቀጠሏ ነገር ጥያቄ ላይ መውደቁን ያመላከቱ ነበር ። ሕዝባዊ አመጹና በትህነግ/ኢህአዴግ ውስጥ የተነሳው የለውጥ ኃይል አሸናፊ ሆኖ ወደ ስልጣን እንደመጣ የቀደመውን አገዛዝ መንገድ ልከተል ቢል ኖሮ ሀገራችን ዛሬ ድረስ ስለመዝለቋ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም ነበር ። በድጋሚ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የተመራው የለወጥ ኃይል ምስጋና ይግባውና በህይወቱ ተወራርዶ ይሄን ወሳኝ መታጠፊያ እንደ ቀደሙት አገዛዞች ሳያባክን አሳታፊ የፓለቲካ ስርዓት ፤ አካታች የኢኮኖሚ ፈለግን መከተል መምረጡ እና በሀገራችን ጥንታዊ ታሪክ ይህን ወሳኝ ምርጫ ማካሄዱ ሀገራችንን ከማያበራ ቀውስና ፍርሰት ታድጓታል።
እንደ መቋጫ
የለውጥ ኃይሉ ከሀገር ውስጥም ከውጭም በማያባራ ጫና ስር ሆኖ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አዕማድ የሆኑ ተቋማትን ቅድሚያ በመስጠት ማሻሻያዎችን አድርጓል። የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የፍትህና የዳኝነት ስርዓቱ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ኮሚሽን፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ፣ የብሔራዊ ደህንነትና የመረጃ ተቋም፣ ፌደራል ፓሊስ፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የሲቭል ማህበራት ኤጀንሲን፣ ወዘተረፈ ላይ የተፈጠሩ የአደረጃጀትና የአመራር ለውጦችን በአብነት ማንሳት ይቻላል።
የለውጥ ኃይሉ በምርጫ ዋዜማ ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ፤ ክብርት መዓዛ አሸናፊን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፤ አቶ ዳንኤል በቀለን (ፒኤችዲ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነርነት መሾሙ የለውጥ ኃይሉ የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፈንታ በዴሞክራሲ፣ በፍትሕ፣ በእኩልነትና በነጻነት ለመዋጀት የቆረጠ መሆኑን ያረጋግጣል ።የዴሞክራሲያዊ ተቋማት አዕማድ የሆኑ እነዚህን ተቋማት በኃላፊነት እንዲመሩ የተሾሙ ሰዎች ገለልተኝነትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብት መከበር ያላቸው ቁርጠኝነት የለውጥ ኃይሉ ሀገሪቱን ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አርነት ለማውጣት መወሰኑን በተግባር አረጋግጧል። ይህ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና የወጣችበት ምርጫ ሊሳካ የቻለው ባለፉት ሶስት አመታት የተሰሩ ስራዎች እርሾ ሆነው በማገልገላቸው ነው።
የምስራች!
ኢትዮጵያ አሸነፈች። ኢትዮጵያዊያን አሸነፉ።
በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2013