የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ በተለያየ ወቅት በሚተከሉ ዛፎች አረንጓዴ መሆን ከጀመረች ሰነባብታለች። ይህ ልምላሜ ዓይናችን ውበትን እንዲያይ እያደረገ ነው። እንጦጦ ላይ ብንወጣ ብቻ ይህንን ማረጋገጥ ይቻላል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሲሳይ ጌታቸው እንደሚሉት፤ አዲስ አበባ አረንጓዴ እንድትለብስ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ወደ አንድ ቢሊዬን ብር በጀት መድቦ መሥራት ችሏል። ይህ ደግሞ ለ 24 ሺ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ ነበር። ከ24 ሚሊዬን ችግኞች በላይ በሁለት ዓመታት ውስጥ ተክሎ 83 በመቶ ያህሉን ማጽደቅ ልምላሜን ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚነትንም አሳድጓል።
በዘንድሮው የችግኝ ተከላ ወቅትም ይህንን ሁኔታ በተቻለው ሁሉ ከፍ ለማድረግ ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዬን ችግኝ ለመትከል ተዘጋጅተናል የሚሉት ኮሚሽነሩ፣ ለዚህም ከቦታ ዝግጅት ጀምሮ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ይላሉ።
እንደ አቶ ሲሳይ ገለፃ፣ከስምንት መቶ ሄክታር በላይ ቦታ ተለይቶ ከሁለት ሚሊዬን በላይ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል። ከ12 ሚሊዬን በላይ ችግኝም በማህበራት ብቻ እየፈሉ ናቸው። ስለዚህም በምርጫው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የችግኝ ተከላው የሚጀመር ይሆናል። በዕለቱም ከ2 ነጥብ ስድስት ሚሊዬን በላይ ችግኝ ለመትከል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
የአረንጓዴ ልማት ሥራ በየጊዜው እየታየ የሚስተካከል ነው የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ በተደረገው እንቅስቃሴ ብዙ ችግኞችን ተክሎ ማጽደቅ ቢቻልም ሁሉም መጽደቅና ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው። በዚህም በዘንድሮው ዓመት ክፍተቶችን ለመድፈን ከእንክብካቤ ባለፈ ከቦታ መረጣ አንጻር የነበረውን ችግር ለመፍታት እንደተሠራ ይገልፃሉ። ለዚህም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ እየተመራ በቴክኒክ ቡድን አማካኝነት የሥራ እንቅስቃሴውም ቀደም ብሎ መጀመሩንም ያስረዳሉ።
የአየር ንብረት ለውጥን በማምጣት ደረጃ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዲኖረውም እየተሠራ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሲሳይ፤ ከአፈር እስከ ችግኝና የቦታ ጥናት ተደርጎ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅቱ መጠናቀቁን ፤ አገር በቀል ችግኞችና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም ይገልፃሉ። አሁን እየጨመረ ያለውን የአየር ብክለትና የሙቀት መጠን ለመቀነስ ሁነኛ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል።
የአረንጓዴ አሻራ ጉዳይ የኢትዮጵያን ተብሎ የሚወሰንም ሊሆን አይችልም። የዓለም ሁሉ የህይወት ዋስትና የሚረጋገጥበት ጉዳይ ነው። ስለዚህም ልማቱ ወገን ለይቶ የሚጠቅም አይደለምና ለራሳችን ብለን በመሥራት ለሌሎችም እንትረፍ ይላሉ። ከዚህ የበለጠ ነገር ብንሠራ ደግሞ ብዙ ማትረፍ እንችላለን። ስለሆነም የአረንጓዴ አሻራችንን የችግሮቻችን መፍቺያ እናድርገው ሲሉም ያሳስባሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ልማትና ጥናት መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ አለሙ በበኩላቸው ፤ አሁን ያለው የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ አዲስ አበባ ከተማ ከተፈጥሮ ችግር በፍጥነት እንድታገግም ሊያደርጋት የሚችል ነው። በካይ ነገሮችን በመቀነስ የሰው ጤንነት እንዲጠበቅ፣ የተለያዩ የመዝናኛና ማህበራዊ ክዋኔዎችን በስፋት የምናደርግባቸው ማራኪ ቦታዎች እንዲኖርም ዕድል ሰጥቷል ይላሉ።
የችግኞች ዝርያ የተመረጡና አገር በቀል መሆናቸውም የአፈር ለምነትን ጨምሮ ምርታማነት እንዲስፋፋ ፤ከዚህ ቀደም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የጠፉ የእጽዋት ዝርያዎች ዳግም እንዲመለሱ ማድረጉም አንዱ የአረንጓዴ ልማቱ ገጸ በረከት ነው የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ በዚህ ሁኔታ ልማቱ ከቀጠለ በወንዞች አካባቢ ያለ የአፈር መሸርሸር ይቀንሳል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የማይለማና ልምላሜ የማይታይበት ቦታ አይኖረንም። ስለዚህም የአንጓዴ ልማቱ ላይ መረባረቡ ጊዜ የሚሰጠው መሆን እንደሌለበት ይገልጻሉ።
በአረንጓዴ ልማት ጤናማ የዝናብ መጠን በከተማ ውስጥ እንዲኖር ያደርጋል። ይህ ደግሞ የከተማውንም ሆነ የገጠሩን ነዋሪ ምርታማነቱን በመጨመር ኑሮውን ከማሻሻል አንጻር የማይተካ ሚና አለው ሲሉ ያስረዳሉ። በውጭ ምንዛሪ ችግር ውስጥ እንዳትገባ ያግዛታል። ስለሆነም ለውጥ የእያንዳንዱ ዜጋ ልማት የእያንዳንዱ ጸጋ መሆኑን አምኖ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2013