የኑሮ ውድነቱ የእያንዳንዳችንን ኪስ አንኳኩታል።ፍላጎታችንን ቀንሰን እንደ አቅማችን ለመኖር ተገደናል። ያማረንን ሁሉ ትተን በአይናችን አይተንና ጠግበን እንድናልፈው ሆነናል። ‹‹ከጮማው ቁረጥ፣ ከቀዩ፣ ኧረ ከጎድኑ…›› የሚሉ የሸማች ድምጾች የጥቂቶች ብቻ እየሆኑ ነው። አብዛኛው ስጋ አፍቃሪ የሽሮ ቁርጥ ፍላ መማተሩን ቀጥሏል።ሽሮ ለምኔ ቢል አይችልማ። የስጋ ዋጋና ኪሳችን አራምባና ቆቦ ።
ሰሞኑን ምርጥ የሚባለው የነሐረርና ጅሩ ሠንጋ አንድ ኪሎ ሥጋ አዲስ አበባ ወደ አንድ ሺህ ብር ጠጋ ያለ ሂሳበ አውጥቷል ሲባል ሰማሁና ይሄ ነገር ከየት ነው የሚመጣው? በውጭ ምንዛሬ ነው የሚገባው? ብዬ ለመጠየቅ ዳዳኝ።
‹‹ምነው ይሄን ያህል ዋጋ ለስጋ ነፍስ መቀጠያ ነው ››ያሉን ዶሮ ማነቂያ ሥጋ ቤት አካባቢ ስጋ ለመግዛት ሄደው በሰሙት የተጋነነ ዋጋ የደነገጡት ወይዘሮ መስትዋት አረጋ ናቸው።
‹‹ ሥጋ ለቅንጦት የሚበላ ምግብ ነው። የአንድ ኪሎ ስጋ ዋጋ የአነስተኛ ደመወዝተኛ የወር ገቢ ሆኗል።ይሄ የህብረተሰቡን አቅም ያላገናዘበ ነው። በሬው የሀገራቸን ምርት ምን ሆኖ ነው በዚህ ደረጃ ዋጋው የተሰቀለው ›› ሲሉ ይጠይቃሉ።
የኑሮ ውድነቱ በሁሉም ምርቶች ላይ ንሯል። ዛሬ ይሄ የቀነሰ ዋጋ አለው ተብሎ የሚመረጥ ምን አይነት አትክልትም ሆነ ጥራጥሬ የለም ። ህብረተሰቡም በየዕለቱ እየጨመረ በሚመጣው የኑሮ ውድነት እየተበሳጨ ነው። ይባስ ብሎ የአንድ ኪሎ ስጋ ዋጋ የአንድ በግ መግዣ ያክል ሆኗል።
መንግስት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ አለበት።አንዱ ጉዳይ ደግሞ የኑሮ ውድነት እንዲረጋጋ ማድረግ ነው። ህገወጥ ነጋዴዎችን የተጋነነ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ይሄንን መንግሥት መስራት አለበት ሲሉ ያሳሰባሉ።
አቶ ባይር ገብረኪዳንን ያገኘኋቸው ካዛንቺስ አካባቢ ጨርጨር ሥጋ ቤት ነው። አንድ ኪሎ ስጋ የገዙት 700 ብር ነው ። ቀደም ባሉት ጊዜያት የስጋው ዋጋ ከሰባት መቶ ብር በላይ እንደነበረም አስታውሰዋል። የስጋ ዋጋ በዚሁ ከቀጠለ በቀጣይ ሁሉም ሰው ስጋ መብላት ያቆማል የሚል ስጋት አላቸው። እርሳቸውም ልጆቻቸው ቢያስቸግሯቸው እንጂ ሰባት መቶ ብር ለአንድ ኪሎ የማውጣት ፍላጎት እንዳልነበራቸው ይናገራሉ።
‹‹ሥጋ ይሄን ያህል እንዲወደድ ያደረገው ምንድነው››ሲሉ የጠየቁንና ሥጋ ቤት ደጃፍ ያገኘኋቸው ወይዘሮ ደሚቱ ቀልቤሳ ናቸው።ወይዘሮዋ እንደነገሩን ከዚሁ ሥጋ ቤት ለወጥ የሚሆን ሥጋ የገዙት በአራት መቶ ብር ነው።ሰሞኑን ግን በአካባቢው ባሉ ሌሎች ስጋ ቤቶች እስከ 800 ብር ተሸጧል። በዘንድሮ ዓመት ዋጋ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ባለመምጣቱ ከእንግዲህ ይጨምራል እንጂ አይቀንስም የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።
‹‹የሥጋ ዋጋ ለእኛም ግራ እስከሚገባን በጣም ጨምሯል››ያሉን የጨርጨር ሥጋ ቤት ባለቤት አቶ ዮናስ ግርማ ናቸው። እንደ አቶ ዮናስ የስጋ ዋጋ የጨመረው ከፋሲካ ማግስት ጀምሮ የከብት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ በማሳየቱ ነው።የከብት ዋጋ ጭማሪ በእጥፍ አድጓል።ከበዓሉ በፊት 30 ሺህ ይገዙት የነበረውን በሬ ከበዓል በኋላ ስድሳ ሺህ ብር ለመግዛት ተገድደዋል። ለስጋ መወደድ ዋናው ምክንያት ከበሬ የመግዣ ዋጋ ውድነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ይናገራሉ።
እንዲሁም ቀደም ሲል 300 ብር የነበረው የአንድ በሬ የቄራ እርድ አሁን ሁለት ሺህ ብር ገብቷል። 210 ብር የነበረው አንድ የእርድ ከብት ተገዝቶ የሚመጣበት የትራንስፖርት ዋጋም 1ሺህ 400 ብር ደርሷል። ከበሬ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የሌሎች አገልግሎቶች ዋጋ መጨመርም በስጋ በላተኛው ላይ የስጋ ዋጋ እንዲንር አድርጎታል ሲሉ ለስጋ ዋጋ መወደድ ምክንያት ያሉትን ነግረውናል።
አቶ ዮናስ እንዳሉት ሁሉም ስጋ ቤቶች የሚሸጡበት ዋጋ እኩል አይደለም። በኪሎ እስከ 300 ብር የሚሸጥ የወጥ ሥጋ አለ። ይሄም ቢሆን ለማህበረሰቡ አቅም ርካሽ የሚባል አይደለም። በመሆኑም ዋጋው እንዲቀንስ መፍትሄው የሥጋ አቅርቦቱን ማብዛት ፣ አርሶ አደሩ በቂ መኖ እንዲያገኝ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ፣ የከብት እርባታ በተገቢው መንገድ በብዛት የሚራባበትን መንገድ መፈለግ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
ከገበያ ግሽበት ጋር በተያያዘ በቅርቡ መግለጫ የሰጡት የብሄራዊ ባንኩ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ እንዳሉት ከምርጫ በኋላ ባለው ጊዜ የሀገሪቱ ሁኔታ በፀጥታውም ሆነ በዋጋ ንረቱ እየተሻሻለ ይሄዳል ፤ የተሻለ አፈፃፀም ይኖረዋል ብለዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2013