ወጣቶች ናቸው። የእጅ ጥበበኛው ተጨንቆ የሰራውን የሽመና ውጤትና ከአልባሱ ጋር የሚስማማውን ጌጣጌጥ ከራስ ፀጉራቸው ጀምሮ ተውበውበታል። በአለባበሳቸው ቀልብ በመሳባቸው ስለባህላዊ አልባሱና ጌጣጌጡ ብዙዎች ሲጠይቋቸውና አብረዋቸውም ፎቶግራፍ ለመነሳት ሲያስፈቅዷቸው ነበር። ወጣቶቹ የተዋቡባቸው አልባሳትና ጌጣጌጦች ከተለመዱና ከሚታወቁ ግብአቶች የተሰሩ ቢሆኑም የቀለም አገባባቸውና አሰራራቸው የእጅ ጥበበኛውን ድካም የሚያሳዩ ናቸው። ወጣቶቹ የለበሱት የባህል አልባስ ይዘቱን ባይለቅም በዘመናዊው ተተክቶ ለማመሳሰል ጥረት መደረጉንም ታዝቤያለሁ።ያም ሆኖ ግን የሲዳማ ባህላዊ አልባስና ጌጣጌጥ ያምራል።በአልባሱና በጌጣጌጡ የተዋቡት ወጣቶችም መቼና እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል አጫውተውኛል።ወጣቶቹ ለምለም ፀጋዬ እና ቤተል ዳንኤል ይባላሉ።በሐዋሳ ከተማ ነው የሚኖሩት።
ከፀጉራቸው ጀምሮ ያለውን አጋጌጥ እንዳጫወቱን።የፀጉር አሰራሩ ጎዳያ ይባላል። ያላገቡ ከ12 አመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ሴቶች የሚሰሩት የፀጉር አሰራር ሲሆን፣ሙሉ ለሙሉ ወደታች የወረደ ሹርባ ነው የምትሰራው። የሹርባው ጠርዝም በተለያየ ቀለም ክር ይሰፋል። በተጨማሪ ደግሞ በሹርባው ላይ የሚውል በግንባሯ ላይ በአካባቢው ኢልኮ ወይንም ኢልካ ተብሎ የሚጠራውን ጌጥ ታደርጋለች። በዚህ መልኩ መሰራቱ የተለያየ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። ዋናው ጥቅሙ ለማሳመሪያ ነው። ልጃገረድ በመሆኗም የወንዶች ቀልብን ለመሳብም ሌላው ዘዴ ነው። በተለይም እንደ ፊቼ ጫባላላ ያሉ በአካባቢው ልዩ በሆኑ የክበረበአላት ወቅት ልጃገረዶች በዚህ የፀጉር አሰራር ደምቀው ሲወጡ በወንዶች እይታ ውስጥ ይገባሉ። ወንዶቹም ያላገባች እንደሆነች በፀጉር አሰራራቸው ስለሚያወቁ ለማጨት መንገድ ያገኛሉ። ልጃገረዶቹም እንግዳ አይሆንባቸውም። የህፃናት ደግሞ ጉዱሮ ይባላል። ሙሉ ፀጉራቸው ተላጭቶ ከኋላ እንዲቀር ይደረጋል። ከዚህ ነው ወደ ጎዳያ የፀጉት አሰራር የሚሸጋገሩት። የሲዳማ ህፃናትና ልጃገረዶች እንዲህ የሚዋቡት በተፈጥሮ ፀጉራቸው ነው። የከተሜውና የገጠሩ የፀጉር አሰራርና አጋጌጥ ለየቅል መሆኑ እርግጥ ቢሆንም ቱባው ባህል እንዲታወቅ ባለመደረጉ እንጂ ውብ ሥራው ገጠር እንደሆነ ያየ ብቻ ነው የሚመሰክረው። አንዳንዶችም ፋሽን የሚል ስያሜ ይሰጣቸው እንጂ መሠረቱ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሆነም ሥራዎቹ ምስክር ናቸው። ፀጉራቸው ውብ ሆኖ የተፈጥሮ ይዘቱን እንዲጠብቅና እንዲያድግ እንደከተማው የፋብሪካ ውጤት የሆኑ ቅባቶችንና ፀጉር ለማሳደግ የሚጠቀሙባቸውን ግብአቶች ሳይሆን ቅቤ በመጠቀም ነው ፀጉራቸውን የሚንከባከቡት። በአጋጣሚ በተፈጥሮ ፀጉራቸው አጭር የሆነ ሴቶች ሹርባቸው ረዘም እንዲልላቸው ከፈለጉ ዘመን የፈጠረው አርተፊሻል ዊግ ፍለጋ አይሄዱም። በአካባቢውም ስለማይታወቅ ፀጉራቸውን ሲያበጥሩ የሚነቃቀለውን በማጠራቀም መልሰው በመጠቀም ያጌጡበታል። በዘመኑ ሂማን ሄር እየተባለ በውድ ዋጋ የሚሸጠው የሰው ፀጉር ውጭዎች የፈለሰፉት ነው ለማለት አያስደፍርም። ውስጣችንን ባለመፈተሻችን ዘመናዊነት ያመጣው እንደሆነ አድርገን የምናስብ ጥቂቶች እንደማንሆን እገምታለሁ።
ከጨሌ የተሰራው አንገት ላይ የሚደረገው ጌጥም እንዲሁ ልዩ ነው።ወጣቶቹ ስለዚህም እንዲህ ነገሩኝ ከጨሌ የሚሰራው ጌጥ በሶስት ወይንም በአራት ቀለማት ነው የሚሰራው።በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች በጌጡ ሊጠቀሙ ይችላሉ። ከጨሌ ጋር አብሮ በተለያየ ቀለም ከክር የተሰራ ማጌጫ ይኖረዋል። እንዲሁም በአካባቢው ጩአ ተብሎ የሚጠራው ቀለበትም በአስሩም ጣቶቻቸው ላይ በማድረግ ያጌጡበታል። ወደ ባህል አልባሱ ስናመራ ደግሞ ከላይ እንደ ካባ ደረብ የሚደረገው በአካባቢው ቆጥሎ ተብሎ የሚጠራው የባህል አልባስ ነው ያላገቡ ሴቶች ናቸው የሚለብሱት። ያገቡ ሴቶች የሚለብሱት ደግሞ ጎዳሬ ወይንም ጎርፋ ይባላል።የባህል አልባሱ ከከብት ቆዳ ነው የሚሰራው። ቆዳው በፋብሪካ ውስጥ ያላለፈ በመሆኑ ለአለባበስ ምቾት በሚሰጠው በዘመናዊ በመተካት ለማመሳሰል ነው ጥረት የተደረገው። ወጣቶቹ እንደሚሉት ከላይ ከሚለበሰው ከቆዳ ከሚሰራው አልባስ በስተቀር የተቀሩት አልባሳትና መዋቢያዎች ቱባ ባህሉን እንደጠበቁ ናቸው። የውስጠኛው ልብስ ወይንም ቀሚስም እንዲሁ በአካባቢው የሽመና ውጤት የተሰራ ሲሆን፣ የተለያዩ ቀለማት ያለው ደማቅ ነው። በተለይም ቢጫ፣ቀይ ቡናማ፣ጥቁር፣ቀይ ቀለማት የተለመዱ ናቸው። አልባሱ በአካባቢው ቆሎ ተብሎ ነው የሚጠራው። የሚለብሱትም ያላገቡ ሴቶች ናቸው። የሲዳማ ልጃገረዶች በአልባሳቶቻቸው፣ በአጋጌጣቸውና በፀጉር ሥራቸው ይለያሉ።
ታዲያ ወጣቶቹ እንዲህ ቀልብን በሚስብ የልጃገረዶች አለባበስ ተውበው እጮኛ አግኝተው ይሆን? ቀልዱን በቀልድ ነበር የመለሱልኝ። ‹‹ያው የአዲስ አበባ ከተማ ሰው አላጨነም›› አሉኝ እየሳቁ። የተገናኘነው አዲስ አበባ ከተማ ስለነበር። ወጣቶቹ እንዳሉት የተመረጠችው ልጃገረድ መፋቂያ ነው የሚበረከትላት። ልጃገረዷን የፈቀዳት ወንድ መፋቂያውን በህፃን ልጅ አሲይዞ ነው የሚልከው። ፈቃደኛ ከሆነች ከልጁ መፋቂያውን ጥቀበላለች። እጮኛ እንደሌላት ማረጋገጫው መፋቂያውን መቀበሏ በመሆኑ መልዕክቱን የላከው ተሳክቶለታል ማለት ነው። እዚህ ላይ ግን ሴቷ ከፈቀደችው ነው መፋቂያውን ከተላከው ልጅ የምትቀበለው። ከመቀበሏ በፊት የተላከው ልጅ ላኪውን እንዲያሳያት ጠይቃ በርቀት ታየዋለች። በዚህ መልኩ መተጫጨቱ የተለመደው በፍቼ ጫባላላ ወቅት ሲሆን፣ በዓሉ በተለያየ ስያሜ ከሳምንት በላይ ስለሚቆይ በፍቼ ጫባላላ ማግሥት ጉዱማሌ ላይ ሲወጣ ቄጠላ ተብሎ በሚጠራው በዓል ላይ ነው። በዚህ መንገድ መፈላለጉ ቢፈጠርም ወዲያው ወደ ፍቅር አይገቡም። ለአመት ዳግም ለመገናኘት ተስፋ አድርገው ቀጠሮ ይይዛሉ። ያኔ መሥመር ይይዛል። በዚህ መንገድ የሰመረው መተጫጨት የጋብቻ ውሳኔ ላይ ሲደርስ ከወንዱ የሚጠበቅ ጥሎሽ እንደሚኖር በመገመት ወጣቶቹን ጠየኳቸው። እነርሱም ሲመልሱ፤ ጥሎሹ በሀብት መጠን ይወሰናል። ያለው እስከ መቶ ሺህ ብር ወጪ ሊያወጣ ይችላል። ጥሎሽ እንደቀደመው መሆኑ ቀርቶ የሀገር ሽማግሌዎች ጥሎሽ ከሁለት ሺህ ብር በላይ ወጪ እንዳይኖረው ባካባቢው ሴራ ተብሎ በሚጠራው ባህል መሠረት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ወጣቶቹ አጫውተውኛል። ሴራውን አልፈው ከተባለው በላይ ጥሎሽ የሚፈጽሙ ካሉ በድብቅ ካልሆነ በስተቀር ሴራው ባህል በመሆኑ ይከበራል። ጨዋታን ጨዋታ ያነሰዋል ነውና በከተማው ያለው ወይንም ዘመን አመጣሹ ከዚህ ቀደምም ሲባል እንደሚሰማው ሎሚ መወርወር በተለይም በጥምቀት በዓል ወቅት በስፋት የሚነሳው፣ አሁን ደግሞ በሲዳማ የተለመደው የመፋቂያ መስጠት በተግባር ሊሆን ቀርቶ ሰምቶ የማያውቅም ሊኖር ይችላል። ዘመኑ ባፈራው በእጅ ላይ ተንቀሳቃሽ ሥልክ እጮኝነቱ ማለቅ ጀምሯል። ልጅህን ለልጄ የሚለውም ጊዜ ያለፈበት ሆኗል። ተቃራኒ ጾታዎች ጨርሰው ነው ለቤተሰብ የሚያሳውቁት። ቤተሰብ እንግዳ የሚሆንበትም አጋጣሚ እየተፈጠረና እየተለመደ ነው። ከመተዋወቅ እስከ የሰርግ ሥነሥርአት ያለው ሂደት የተጋቢዎች ጉዳይ ከሆነ ውሎ ሰንብቷል። የድሮና ዘንድሮ ከእጮኝነት እስከ ሰርግ ሥነ ሥርአት ያለውን እንዲህ በአጭሩ የምናወጋው ባለመሆኑ ወደ ተነሳንበት የሲዳማ የባህል አልባስና አጋጌጥ ልመልሳችሁ።
ወጣቶቹ የተዋቡበትን ጌጣጌጥ በዋጋ ለማወቅም ጠይቄያቸው እንደነገሩኝ በአንገታቸው ላይ ያደረጉት ከጨሌ የተሰራው ጌጥ አንዱ ብቻ አንድ ሺህ ብርና ከዚያ በላይ ዋጋ ያወጣል። ቀለበትና የእጅ ጌጥ የመሳሰሉት አነስተኛው 50 ብር ዋጋ ያለው ነው። እንደካባ ከላይ የሚለበሰው አነስተኛው ዋጋ ሶስት ሺ ብር ቢሆን እንጂ ከዚያም በላይ ነው ገበያ ላይ የሚሸጠው። ወጣቶቹ በአጠቃላይ ሊያውም 50 ከመቶ በላይ የሚሆነው ሳይሟላ የለበሱትና የተዋቡበት ጌጣጌጥ እስከ 10 ብር ዋጋ የሚያወጣ ነው። ለዋጋው መጨመር ምክንያቱ ግልጽ ነው። ግብአቱ የሰው ጉልበት ዋጋ ጨምሯል።
መቸም ሁሉም በዘመኑ የነበረበትን ይወደዋል። በዕድሜ ሲገፋ እንኳን የቀደመው ነው የሚያስደስተው። ግን ደግሞ ትውልድን እየተሻገ ቱባው ባህል የዛሬው ወጣት ላይ እየታየ ነው። ነገር ግን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እየተበረዘና የእተሸረሸረ ነው የሚቀርበው።በዚህ በኩል ወጣቶቹ ያላቸውን አስተያየትና ወጣቱ ቱባ ባህሉ ለማቆየት ያለውን ፍላጎት ላቀረብኩላቸው ጥያቄም በሰጡት ምላሽ፤ በእነርሱ አስተያየት ባህሉ መሠረቱን ሳይለቅ ቢዘምን ይመርጣሉ። በፀጉር ሥራውም ሆነ በሌሎቹ ዘመናዊነት ታክሎበት ከበዓል ውጭ በአዘቦቱም በመጠቀም መዋብ የሚቻልበት ዕድል ቢኖርም በበዓል ወቅት መሆኑ ግን ብዙዎች የሚጠቀሙ በመሆኑ በህብረት ይደምቃል። ደግሞም የአካባቢ ባህልና እሴት መገለጫ በመሆኑ የብዙዎችን ትኩረት ይስባል። ወጣቶች የሚተጫጩበት መንገድም ቢጠናከር መከባበርን የበለጠ ያጎለብተዋል ብለውም ያምናሉ።
ወጣት ለምለም ባህሉን ማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን በመሥራትም ትሳተፋለች። በተለይም ከጨሌ የሚሰራውን የአንገት ጌጣጌጦች ሰርታ ለገበያ ታቀርባለች። ለምለምና ቤተል እንዳጫወቱኝ በሞዴልና ፋሽን ተመርቀዋል። ሀዋሳ ላይ የሲዳማ አምባሳደሮች ሆነው፤ የሲዳማን የባህል አልባስ፣ ጌጣጌጥ፣ ምግብ፣ በአጠቃላይ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቱን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ። ከሌሎች ሁለት ጓደኞቻው ጋር ሆነው ሲዳማን ለማስተዋወቅ በሚደረግ ዝግጅት ላይ ሁሉ በመገኘት በአልባሱና በጌጣጌጡ ተውበው ያስተዋውቃሉ። ወጣቶቹ የአካባቢያቸውን ባህል እንዲህ በተጨማሪ ያስተዋውቁ እንጂ በተለያየ ሙያ ነው ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁት። ለምለም ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ሳይንስ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቃለች። የተቀሩትም ጓደኞችዋ በሂሳብ (አካውንቲግ) እና በፋርማሲ ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል።
ለምለም እንደነገረችኝ የተማረችው ኮምፒውተር ሳይንስ ቢሆንም ፍላጎትዋ ግን በፋሽን ኢንደስትሪው ውስጥ መሥራት ነው። በተለይም የሲዳማን ተዝቆ የማያልቀውን ባህልና የተፈጥሮ ሀብቶች ከሀገር አልፎ ሌላው ዓልም እንዲያውቀው፣ ከዘርፉም ገቢ እንዲገኝ ጥረት ለማድረግ ነው ፍላጎትዋ። ፍላጎትዋን ለማሳካትም በዘርፉ ያላትን ትንሽ ዕውቀት በትምህርት ለማሳደግ ከወዲሁ ጥረቷን ለማጠናከር በዝግጅት ላይ መሆኗን ነው የነገረችኝ። በራሳቸው የሚተማመኑ ጠንካራ ሴቶችን ማብቃትም ሌላው ፍላጎትዋ ነው። ስልጣኔ ባልነበረበት ዘመን የቀደመች። የሴትና የወንድ ሥራ የሚባል ነገር መኖር እንደሌለበት በማስታወቅ ሁሉም በእኩልነት እንዲሰሩ፣ ወንዱ እበት እንዲጠርግ፣ ቆጮ እንዲቆርጥ በማድረግ፣ የሴቶች ጭቆና እንዳይኖር፣ ሴት የሀገር መሪ መሆን እንደምትችል በተግባር ያሳየች፣ በዘመኗ የሰራችና ዛሬም የሲዳማ ንግሥት እየተባለች የምትጠራውን የንግሥት ኩራ መልካም የሆኑ ተግባሮች በውስጧ በመኖሩ ይሄንን ለማስቀጠል ጥረት እንደምታደርግ የገለጸችልኝ ለምለም መንፈሰጠንካራነቷን ነበር ከገጽታዋ ያነበብኩት። ‹‹ዘመናያዊ ንግሥት ኩራ ነኝ››ስትልም ገልፃለች።
ወጣቱ በምዕራባውያኑ ባህል ተጠልፎ ማንነቱን እየዘነጋ ነው እየተባለ በሚተችበት በዚህ ወቅት እንደነ ለምለም ያሉ ወጣቶች የባህል አምባሳደር ሆነው በፍላጎት ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ጥረት ሲያደርጉ ማየት ይበል የሚባል በጎ ተግባር ነው። ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2013