ትምህርት ቤቱ በመልከ ብዙ ገጽታዎች ሲደምቅ ይውላል። መምህራን የማስተማሪያ ነጭ ካፖርታቸውን ደርበው ከወዲያ ወዲህ ይላሉ። በቡድን ሰብሰብ ብለው የሚቀመጡ ተማሪዎች ጥናት አልያም ጨዋታ መያዛቸው የተለመደ ነው።
አንዳንዶቹ በሩጫና ልፊያ ግቢውን ያተራምሱታል ። ገሚሶቹ ሁለትና ሶስት ሆነው ጉዳዮቻቸውን ያወጋሉ። የተቀሩት በራሳቸው ሀሳብ ተይዘው ይተክዛሉ። ብዙ ጊዜ ይህ አይነቱ ዝብርቅርቅ ገጽታ በድንገቴ የደወል ድምጽ ይቀይራል። የትምህርት ቤቱ ደወል ጎልቶ በተሰማ ጊዜ ሜዳ ያለው ወደ ክፍል ፤ደጅ የቆየው ወደግቢ ለመዝለቅ ይጣደፋል።
ተማሪዎች ክፍል ገብተው ፣መምህራን ማስተማር ሲጀምሩ፣ የግቢው የቀድሞ ግርግር በዝምታ ይዋጣል። በየክፍሉ ማዕዘን የቀለም ፣ የዕውቀት በር ይከፈታል። ጥያቄዎች ይነሳሉ መልሶች ይወረወራሉ። በየቀኑ እንዲህ አይነቱ እውነት ተደጋግሞ ይቀጥላል። የትምህርት ቤቱ፣ የተማሪዎችና የመምህራን ቁርኝት እንደጠበቀ ዓመቱ ይጠናቀቃል።
መምህሩ…
መምህር ነው ። ለተሰማራበት ሙያ በሙሉ ልብ ያገለግላል። ለስራው የተለየ ፍቅር አለው። ከጠዋት እስከማታ ሲባትል፣ሲደክም መዋል ልማዱ ነው። ነገ አገር ለሚረከቡ፣ ትውልድ ለሚተኩ ተማሪዎቹ ያስባል፣በውስጡ ያደረውን ዕውቀት ለእነሱ ለማጋባት የአቅሙን ማድረግ መገለጫው ሆኖ ቆይቷል።
መምህር ታሪኩ ሁሌም ለጎበዝ ተማሪዎቹ የተለየ ትኩረት አለው። ተማሪዎቹ የሰጣቸውን ሲይዙለት የዘራውን ሲለቅሙለት ደስ ይለዋል። ሁሌም ብርቱዎቹን እያወደሰ፣ በዕውቀት ደከም ያሉትን ያግዛል። ፈለጉን የሚከተሉ ከውሰጠቱ ይስማማሉ። መንገዱን ለማይሞክሩ፣በትምህርት ለማይጠነከሩ ደግሞ ዘወትር አባታዊ ምክርን ይለግሳል ።
ተቀጥሮ በሚያስተምርበት የ2ኛ ደረጃ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ከአምስት አመታት በላይ ቆይቷል። የፊዚክስ መምህር ነው። ብቃትና ችሎታን በሚጠይቀው በዚህ ሙያ አመታትን ዘልቆበታል። እስከዛሬ እሱን የሚተኩና ልቀው የሚያልፉ ተማሪዎችን ለማፍራትና ዕውቀትና ችሎታውን ለማጋባት ሲታትር ቆይቷል።
ክስና እገዳ…
በትምህርት ቤቱ ግቢ ሰሞኑን አዲስ ወሬ ሽው ማለት ይዟል። መምህራን ሰብሰብ ብለው ስለጉዳዩ ያወራሉ። አንዳንዶችም እንደ ሚስጥር በሹክሹክታ ያወጋሉ። ርዕሱን አንስተው በአንድ የሚፈርጁና በተቃራኒ ሀሳብ የሚሟገቱም በርካታ ናቸው። ለጉዳዩ ወግነው የሚቆሙና የሚወስኑ ፣ የሚቃረኑና የሚስማሙ፣የሚፈርዱና የሚጨቃጨቁ አልታጡም። ሁኔታው በትምህርት ቤቱ ግቢ የተለያዩ መልኮች ይዞ እየተንሸራሸረ ነው።
በትምህርት ቤቱ የተከሰተው አዲስ ነገር ለመምህር ታሪኩ በእጁ የደረሰው የስራ እገዳና ስንብትን የሚገልጸው ደብዳቤ ጉዳይ ነበር። ደብዳቤው ከየካ ክፍለከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ቀንና ቁጥር ይዞ የተጻፈ ነው። የውስጡ ፍሬሀሳብ መምህር ታሪኩን ጨምሮ የሌሎች መምህራንን ማንነት የሚነካ ስለመሆኑም ብዙዎች ሲነጋገሩበት ቆይተዋል።
ደብዳቤው በትምህርት ቤቱ ያሉ መምህራንን በማስተባበር፤ የስራ ማቆም አድማ እንዲመታ፣የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲቆምና ተማሪዎች እንዲበተኑ አድርጓል ። ይላል። ለዚህ ህገወጥነትና ያልተገባ ድርጊት ዋንኛው ተጠያቂ መምህር ታሪኩ ስለመሆኑም በመረጃ አጣቅሶ አስቀምጧል።
መምህሩ በዚሁ ያልተገባ ድርጊቱ ፤ተማሪዎች ለጉዳት እንዲዳረጉና የትምህርት ቤቱ ሀብት እንዲባክን አድርጓል። እንደ ደብዳቤው ገለጻ ግለሰቡ ድርጊቱን እንደፈጸመ በታወቀ ጊዜ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ሆኗል። ይሁን እንጂ መምህሩ ከጥፋታቸው ሊታረሙ አልቻሉም። ይህ በመረጋገጡም ከስራ ገበታቸው እንዲሰናበቱ መወሰኑን ከክፍለ ከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት መጋቢት 19 ቀን 2004 ዓም የተጻፈው ደብዳቤ ያመለክታል።
መምህር ታሪኩ በበኩሉ ከትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ማስጠንቀቂያ እንዳልተሰጠውና ክስ እንዳልተመሰረተበት ያውቃል። ድርጊቱን ፈጽሟል ተብሎ ቢታሰብ እንኳን ደንቡ በሚፈቅደው አግባብ የዲሲፒሊን ክስ ሊመሰረትበትና በተከሰሰበትም ጉዳይ መልስ በመስጠት ሊከራከር እንደሚገባ ያምናል። ይሁን እንጂ ይህ አይነቱ መብት ሳይከበር በአንድ ግለሰብ ውሳኔ ብቻ ከስራ እንደተሰናበተ በሚገልጽ ደብዳቤ የተባለውን ጥፋት አምኖ እንዲቀበል ተገዷል።
መምህሩ በስሙ ተዘጋጅቶ በእጁ እንዲደርስ የተደረገውን የስንብት ደብዳቤ ይዞ በሀሳብ ሲብሰለሰል ቆየ። አሁን ከሚወደው ሙያና እንጀራ ከሚበላበት ስራው ሊሰናበት ግድ ብሏል ። ዛሬ እንደትናንቱ ከተማሪዎቹ መሀል ቆሞ ዕውቀትን አይዘራም። ነገ አገር ይረከባሉ ለሚላቸው ትውልዶች ቀለም አያደርስም። አሁን ከግቢው አጸድ እንዲያልፍ፣ ከሙያ አጋሮቹ እንዲገናኝ አልተፈቀደለትም ። ደሞዙን ተነጥቆ፣ ከሙያና ውሎው ርቆ እንዲሄድ ተወስኖበታል።
መምህር ታሪኩ በተለያዩ ጊዜያት ጉዳዩን በአካል ተገኝቶ ለማስረዳት ሞከረ ።እየሆነ ያለው እውነት ትክክል ያለመሆኑን በመግለጽም የሚመለከታቸውን ሁሉ ሞገተ። ሙከራዎቹ አልተሳኩም። ከአምስት ዓመታት በላይ ከቆየበት፣ ዕውቀት ዘርቶ ፍሬ ካፈሰበት፣ትምህርት ቤት መሰናበቱ የማይቀርለት ሆነ።
ክስና ክርክር …
መምህር ታሪኩ ደሞዙ ታግዶ ከስራውና ከሚወደው ሙያው ከተሰናበተ ቀናት ተቆጠሩ። እሱ ከትምህርት ቤቱ እግሩ ከራቀ ወዲህ ጉዳዩ ተቀዛቅዞ ህይወት እንደቀድሞው ቀጠለ። ተማሪዎች መምህራንና የትምህርት ቤቱ መላ ማህበረሰብ የመማር ማስተማር ሂደቱን አላቆመም።
መምህር ታሪኩ ከቀናት በአንዱ ዕለት በትምህርት ቤቱ አመራር አካላት ደርሶብኛል ያለውን በደል በመጥቀስ ማመልከቻውን አዘጋጀ። ከትምህርት ቤቱ በጽሁፍ የተሰጠውን የስንብት ደብዳቤ በማያያዝም ድርጊቱን ተቃውሞ ‹‹ይግባኝ››ሲል ጠየቀ ጥያቄውን ያቀረበው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ፍርድ ቤት ነበር።
መምህር ታሪኩ ለፍርድቤቱ በጽሁፍ ያስገባውን የቅሬታ ደብዳቤ ምላሽ እስከሚያገኝ ጊዜ ሰጥቶ ጠበቀ። ፍርድቤቱ ጉዳዩን በትኩረት አጢኖ ምላሽና መፍትሄ እንደሚሰጠው ገምቷል። ከሚያገኘው በጎ ምላሽ ተነስቶም ያለአግባብ ከስራ ገበታው የተሰናበተበት አጋጣሚ በመልካም እንደሚካስ እያሰበ ነው።
መምህሩ በፍርድ ቤቱ ቀነ ቀጠሮ በሰአቱ ተገኘ። ከፍርድቤቱ ሬጅስትራር የተሰጠውን ምላሽም በአካል ተገኝቶ አረጋገጠ ። የፍርድ ቤቱ ምላሽ እንዳሰበው አልሆነም። ፍርድቤቱ ቅሬታውን በቃል ለመቀበል እንዳልፈቀደ በመጥቀስ መምህሩን አሰናበተ። ታሪኩ ይህን እንዳወቀ ወደቀጣዩ የክስ ሂደት ማለፍ እንደሚኖርበት ተረዳ። ከትምህርት ቤቱ በእጁ የደረሰውንና ከስራ የተሰናበተበትን ደብዳቤ በማያያዝ የአቤቱታ ማመልከቻውን አዘጋጀ። ደብዳቤውን ለአዲስ አበባ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ዳይሬክተር ቢሮ በማስገባትም ምላሹን ጠበቀ። ከቀናት በኋላ ከቢሮው የተሰጠው ምላሽ ለችግሩ መፍትሄ የሚሰጥ አልሆነም። ቀደም ሲል ‹‹ አቤት››ካለበት ፍርድቤት ባልተለየ መልኩ ተስፋ የሚያስቆርጠው ሆነ።
መምህር ታሪኩ የተሰጠውን ምላሽ ተቀብሎ በይሁንታ አልተቀመጠም። አሁንም በጉዳዩ መፍትሄ ይሰጠኛል ወደሚለው አካል ለማለፍ ራሱን አዘጋጀ። ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤትም ማመልከቻውን አቅርቦ ‹‹ፍረዱኝ›› አለ። እንደተለመደው የስንብት ደብዳቤውን ከአቤቱታው ጋር አያይዞ በእሱ ላይ የሆነው ድርጊት ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስ ለመፍትሄው ተማጸነ።
ማመልከቻውን የተቀበለው የከንቲባ ጽህፈት ቤት ምላሽ ከሌሎቹ የተለየ አልሆነም። ቀደም ሲል የተላለፉ የውሳኔ ሀሳቦችን በሚያጠናክር መልኩ ለአመልካቹ ምላሽ ሰጠ። ይህኔ መምህር ታሪኩ ሀሳብ ገባው። ውስጡ አዘነ። ያም ሆኖ ተስፋ መቁረጥ አልፈለገም። መድረስ እሰከሚገባው ጫፍ መጓዝ እንዳለበት አስቦ ቀጣዩን ዕድል ለመሞከር የማመልከቻ ደብዳቤውን አዘጋጀ።
ማመልከቻውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቅም ግንባታ ቢሮ ካስገባም በኋላ እንደተለመደው ምላሹን መጠበቅ ያዘ። ከቀናት በኋላ ከቢሮው ሲጠብቀው የቆየውን የአቤቱታ ምላሽና ውጤት በአካል ተገኝቶ አረጋገጠ ። አሁንም ከምላሹ የተመለከተው እውነት ከቀድሞዎቹ የተለየ አልሆነም።
ያልተገታ ጉዞ …
መምህር ታሪኩ እስካሁን አቤቱታ ባቀረበባቸው ቢሮዎች የተሰጡት ምላሾች ለችግሩ መፍትሄ የሚሰጡት አልሆኑም። ያለስራና ያለምንም ደሞዝ በአቤቱታና ይግባኝ የሚመላለስባቸው ጉዳዮች በውሳኔያቸው ተመሳሳይ የመሆኑ አጋጣሚ አሳስቦታል። አሁንም ግን መምህሩ ቀጣዩን መንገድ ለመጀመር ተስፋ አልቆረጠም። በጉዳዩ መላና መፍትሄ ይሰጠኛል ወዳለው የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማመልከቻውን አስገብቶ ምላሹን በጉጉት ናፈቀ።
የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የአመልካቹን የአቤቱታ ደብዳቤ ተቀብሎ ጉዳዩን በጥልቀት ማጥናት ያዘ። መምህሩን በአካል አቅርቦም በተገቢው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ አገኘ። የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ይገባል ያለውን የማጣራት ሂደት እንዳበቃ በቁ231/ 48-81/482/4 በቀን 07/05/05 ለየካ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ‹‹ይድረስ››ሲል የውሳኔ ሀሳቡን የያዘውን ደብዳቤ ላከ።
ተቋሙ ለጽህፈት ቤቱ ያደረሰው ምላሽ አመልካች ያቀረበውን አቤቱታ መሰረት ያደረገና የመምህሩን መብት የሚያስጠብቅ ይዘት ያለው ነበር። የምላሹ ፍሬ ሀሳብ ሲመረመርም አመልካች የዲሲፒሊን ቅጣት ፈጽሟል ተብሎ የሚጠረጠር ከሆነ አዋጅና ደንቡ በሚፈቅደው አግባብ የዲሲፒሊን ክስ ሊመሰረትበት ይገባ እንደነበር ያስረዳል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ግለሰቡ በክሱ መልስ የመስጠትና የመከራከር መብታቸው ተጠብቆ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የሚቀጡ ሆኖ ሳለ በአንድ ደብዳቤ ብቻ ከስራ ገበታቸው መፈናቀላቸው አግባብ እንዳልሆነ ይገልጻል። ይህ በመሆኑም የትምህርት ጽህፈት ቤቱ ስነስርአቱን በጠበቀ መልኩ ጉዳዩን አይቶና መርምሮ ውጤቱን በሰላሳ ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቅ ግዴታ የተጣለበት ስለመሆኑ በደብዳቤው አክሎ ገለጸ።
መምህር ታሪኩ ከህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለየካ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት የተጻፈውን የውሳኔ ደብዳቤ ባወቀ ጊዜ ህጉ በአግባቡ ተፈጻሚ የሚሆንበትን ቀን ናፈቀ። አሁን የተቋሙ ደብዳቤ ለሚመለከታቸው አካላት ስለመድረሱ አረጋግጧል።
ለመምህሩ እስካሁን ፍትህ ለማግኘት ያለፈባቸው መንገዶች ቀና አልነበሩም። በበርካታ ውጣ ውረድና ልፋት የታጀበው ትግል ብዙ ሲፈትነው ቆይቷል። በመጨረሻ አቤት ያለበትና ጉዳዩን ያስረዳበት ተቋም የልፋቱን ዋጋ እንደማያሳጣው ተማምኗል። መምህር ታሪኩ ከደብዳቤው ምላሽ በኋላ ጊዜ ሰጥቶ ቀጣዩን ምላሽ ጠበቀ። አሁንም ሌላ ትዕግስትና ተስፋ ተላብሶ ከጽህፈት ቤቱ ለእርሱ የሚደርሰውን አዲስና የተሻለ ምላሽ እያሰበ ነው።
መምህሩ ዛሬ ላይ ቆሞ ወደስራ የሚመለስበትን ቀን ማሰብ ይዟል። እስካሁን ያለተግባር የባከኑት ቀናት ቆጩት፣ ያለደሞዝና ያለአንዳች ገቢ የታለፉት ጊዜያት ብዙ አስታወሱት። ታሪኩ በነዚህ ሁሉ ስሜቶች መሀል ጉዳዩን ከመከታተል አልቦዘነም። በየቀኑ ከጽህፈት ቤቱ ደጃፍ ያለእረፍት ተመላለሰ። ከትምህርት ፅህፈት ቤቱ ለእርሱና ለዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚደርሰውን የይሁንታ ምላሽ እያሰበ ቀናት ቆጠረ ።
አሁንም ጊዜውን እያሰላሰለ በጽህፈት ቤቱ ደጃፍ ተመላለሰ። ጉዳዩን እያነሳ ምክንያቱን እየጠቀሰ ምላሽ እንዲሰጠው ጠየቀ። በሌሎች ቀናትም ደጅ ጠና። ስለእሱ የደብዳቤ ምላሽና ወደስራ መመለስ ጉዳይ ደንታ የሰጠው አልተገኘም።
የመምህር ታሪኩ ሀሳብ ዳር አልደረሰም። አዲስ ነገር አልተፈጠረም። አሁንም ጉዳዮች በታሰበው መልኩ አልቀጠሉም።መምህሩ ወደስራው የመመለስ ተስፋው ቢጨልም አዲስ ነገር መናፈቁን ትቶ በሌላ ሀሳብ ተጠመደ። ከዚህ በኋላ መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለው ጉዳዩን ከፍ ወዳለ ደረጃ ሲያደርሰው ብቻ እንደሆነ ተረዳ።
መምህር ታሪኩ ላሰበው ሀሳብና ዕቅድ የሚበጅ የማመልከቻ ደብዳቤውን አዘጋጀ። በማመልከቻው ላይም ፍትህ የማግኘት ህገመንግስታዊ መብቴ ተጥሷል፣ያለአግባብም ከስራዬ ተባርሪያለሁ በማለት ትርጉም ይሰጠኝ ሲል የህገመንግስት ትርጉም ጥያቄን አቀረበ።
ሌላው ችሎት…
የጉዳዩን አመጣጥ ከስር መርምሮ ማጥናት የጀመረው የህገመንግስት አጣሪ ጉባኤ አመልካቹ በሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቱ በፊዚክስ መምህርነት ሲያገለግል መቆየቱን ተረድቷል። ግለሰቡ በቀረበበት ክስም ከስራና ደሞዙ ታግዶ ስለመቆየቱ ጉባኤው ለማወቅ ችሏል ።
አቶ ታሪኩ የተጠየቀበትንና ከስራ የታገደበትን ክስ በመቃወም እስከዛሬ የተለያዩ ተቋማትን ለመፍትሄ ተማጽኗል። ይሁን እንጂ ከህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በቀር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሄ ያመላከተው አልተገኘም ። ተቋሙ የአመልካቹን አቤቱታ መሰረት አድርጎ ለትምህርት ጽህፈት ቤቱ በጻፈው የሰላሳ ቀናት የምላሽ ገደብ የተገኘ መፍትሄ አለመኖሩን ጉባኤው መረዳት ችሏል።
ጉባኤው ይበልጥ ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ጥረት የየካ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ነሀሴ 4 ቀን 2004 ዓም ለተቋሙ ባደረሰው ደብዳቤ ከአመልካቹ ጋር ከስራ የተሰናበቱ መምህራን ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ ስለጠየቁ ወደስራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ይጠቅሳል።
መምህር ታሪኩም ከክፍለ ከተማው አስተዳደር ትምህርት ቢሮና በሙያ ማህበራት በኩል ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ ከጠየቁና ክፍት በጀት ካለ ብቻ ወደስራ ለመመለስ ትምህርት ቤቱ ፈቃደኛ እንደሆነ የገለጸበት ደብዳቤ መኖሩንም ጉባኤው በተጨማሪነት አረጋግጧል።
ጉባኤው ከደብዳቤው መረዳት እንደቻለው አመልካቹ የዲሲፒሊን ክስ ሳይመሰረትባቸውና ሳይከራከሩ በትምህርት ቤቱ ጽህፈትቤት ኃላፊ ደብዳቤ ብቻ ከስራ እንዲሰናበቱ መደረጉን ነው። አመልካች በጊዜው ለነበረው የሬጅስትራር ጽህፈት ቤት ይግባኝ ማስገባት ያለማስገባታቸውን ለማጣራት ጥረት ተደርጓል። በወቅቱም ግለሰቡ ከስንብቱ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይግባኝ ማስገባታቸው ተረጋግጧል።
ጉባኤው የሲቪል ሰርቪስ ፍርድቤት ለአመልካች ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ሲገባው ይህን አለማድረጉ ተገቢ እንዳልሆነ አምኖበታል። ጉዳዩ በህገመንግስቱ አንቀጽ 37 ላይ ከሰፈረው ድንጋጌ የሚቃረን መሆኑን ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ያመነበት በመሆኑ ይህ የመጨረሻ የውሳኔ ሀሳብ ለፌዴሬሽን ምክርቤት እንዲተላለፍ ተደርጓል።
በመጨረሻም…
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክርቤት የአጣሪ ጉባኤውን የውሳኔ ሀሳብ መሰረት በማድረግ በጉዳዩ ላይ የምክርቤቱን የህገመንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ውሳኔ መረመረ። ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድቤት አልያም ለሌላ በህግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብ መብት እንዳለው በመረዳትም ጥያቄ የቀረበበት ጉዳይ የህገመንግስት ትርጉም የሚያስፈልገው ስለመሆኑ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2013