የዛሬው የዘመን እንግዳችን ለረጅም ዓመታት አዲስ አበባን በአመራርነት ከአስተዳደሩ ግለሰቦች አንዱ ናቸው። ውልደታቸውና እድገታቸው በደቡብ ወሎ ደላንታ ወረዳ ላይ ነው ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ጥቅሽን በተባለ ትምህርት ቤት እስከ 4ኛ ክፍል ተምረዋል። እስከ 8ኛ ክፍል ደግሞ መርጦ በተባለ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በወልድያ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ እስከ 10ኛ ክፍል ተምረዋል። ይሁንና በወቅቱ በነበረው አገራዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው ትግሉን ተቀላቀሉ። ከደርግ ስርዓት ውድቀት በኋላ የኢትዮጵያ የትምህርት መገናኛ ዘዴዎች ድርጅት ይባል በነበረው ተቋም በርቀት ተከታትለው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
እንግዳችን በተወለዱባት ደላንታ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪነት፣ በዋና አስተዳዳሪነት እንዲሁም ላስታ መቄት ወረዳ የድርጅት ፀሐፊ ሆነው ሰርተዋል። ከ1992 ዓ.ም ደግሞ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በልማት አስተዳደር ጨረሱ። ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በቀጥታ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል ። የአራዳ እና የጉለሌ ክፍለ ከተማ የድርጅት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። 2002 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ አዲስ አበባ ላይ ኢህአዴግ ሲያሸንፍ የከተማዋ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ለሁለት ዓመታት ፤ ከ2004 ዓም እስከ 2010 ዓም ድረስ ደግሞ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል። በዚህ ሂደት ውስጥም የአሜሪካው ፓስፊክ ዩኒቨርሲቲ ከኢንተርናሽናል ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የሚሰጠውን ስልጠና በመውሰድ በተቋማዊ አመራር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ማግኘት ችለዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የጥረት ኮርፖሬት ምክትል ሥራአስፈፃሚ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶዎ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአመራርነት በነበሩበት ጊዜ በስኬት የሚያዩትና አሁን ድረስ ያኮራኛል የሚሉት አብይ ጉዳይ ካለ ቢገልፁልኝ? በተመሳሳይ ባይሆን ኖሮ ብለው የሚቆጩበትና እንደትልቅ ተግዳሮት የሆነቦትን ነገር ያንሱና ውይይታችንን ብንጀምር?
አቶ አባተ፡- እንግዲህ እንደምታስቢው የኢህአዴግ አጠቃላይ አሰራር የጋራ አመራር (collective leadership) የሚባል ነበር። ከዚህ አኳያ ነጥለሽ የአንድ ግለሰብ ስኬት ወይም ድክመት ብለሽ አትወስጂም። ያም ሆኖ ግን እኔ አዲስ አበባ በነበርኩበት ጊዜ መልካምና የሚያኮሩ ሥራዎች የተሰሩትን ያህል ጉድለቶችም ነበሩ። ጥሩ ነገር ብዬ የምወስደው በተለይም በቤት ልማት ዙሪያ ያስመዘግብናቸው ውጤቶች ናቸው። ባለፉት ዓመታት የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ሥራ ተሰርቷል ብዬ ነው የማምነው። በተለይም ያንን ዘርፍም እከታተል ስለነበር በርካታ ችግረኞች የቤት ባለቤት መሆናቸውና ሃብት ማፍራታቸው እንደጥሩ ነገር ነው የምወስደው። በዚሁ የቤት ልማት መርሐ ግብር አማካኝነት ኮንትራክተሮችና ተቋራጮች የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል። ከተማዋም ወደ ከፍተኛ መነቃቃት ውስጥ እንድትገባ አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም እንደ ስኬት የማየው የሥራ እድል ፈጠራዎችን ነው። ከቤት ልማቱ ባሻገር በተመቻቹ የሥራ እድል ፈጠራዎች ላይ በርካታ የከተማዋ ወጣት ተጠቃሚ ሆኗል። በመንገድ ልማት ዘርፍም ያስመዘግብናቸው ውጤቶች ጥሩ ነበሩ ብሎ መውሰድ ይቻላል። ያው ፍላጎቱ ብዙ ቢሆንም በመንገድ ልማት ዘርፉ የተመዘገቡት ስኬቶች ሊነሱ የሚችሉ ናቸው። ይህም በከተማዋ ላይ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የተደረጉት ሥራዎች እንደጥሩና መልካም ነገር ነው የሚወሰዱት።
በተግዳሮት ደረጃ የማያቸው ብዙ ነገሮች አሉ። በሥራ ሂደት ያጋጠሙን ትልልቅ ፈተናዎች አሉ። አንዱና ትልቁ ነገር ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ጋር ተያይዞ በከተማዋ በርካታ ምስቅልቅል ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ያ ሁኔታ ለሁላችንም ፈታኝ ነበር። በብዙ መንገድ ከፖለቲካው አለመረጋጋትና ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በከተማዋ ውስጥ ህገወጥነት የተስፋፋበት ጊዜ ነው የነበረው። ይህም ወደ መደበኛ ሁኔታ እስኪመለስ ድረስ ያሉት ጊዜያት እንደአመራር አስጨናቂ ነበሩ ማለት ይቻላል። ሁለተኛው አስቸጋሪና ፈታኝ ሥራ ነበር ብዬ የማስበው የከተማዋ መልሶ ማልማት ሥራ ነው። በተለይም ከተፈናቃዮች ጋር ተያይዞ የካሳ ክፍያ ስርዓቱም አስቸጋሪ ሆኖብን ነበር። የተነሺዎችን ፍላጎት በሚያሟላ መንገድ ምላሽ መስጠትና በእነሱ ደረጃ ተጠቃሚ ለማድረግ ከባድ ነበር። ይህ ሥራ በከተማዋ ሥራ ውስጥ ትልቁና የአስተዳደሩን አቅም የሚፈታተን ሥራ ነበር ማለት ይቻላል። በነገራችን ላይ አሮጌ ከተማን የማልማት ሥራ ለሚነሳው የህብረተሰብ ክፍል የተሟላ ምትክ ቤት ማዘጋጀት ይጠይቅሻል፣ ቦታ እና መሰረተ ልማት ማዘጋጀት ይጠበቅብሻል። ማህበረሰቡ ደግሞ ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር ያለው እንደመሆኑ በልማት ምክንያት የሚፈጠረው ማህበራዊ ቀውስም ቀላል አይደለም። በሌላ በኩል ያንን ሁሉ ህዝብ በአንድ ላይ የምታሰፍሪበት ቦታ ያለመኖሩ ሌላ ቅሬታ መፍጠሩ አይቀርም። በአጠቃላይ የመልሶ ማልማት ሥራ በጣም ፈታኝ ነበር፤ ወደፊትም ፈታኝ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል ብዬ አስባለሁ።
ከዚህ ባሻገር በከተማዋ በወሳኝነት ያጋጥም የነበረው ችግር ህገወጥነት ነው። በተለያዩ ጊዜያት ህገወጦች ግንባታ ይፈፀማሉ፤ አስተዳደሩ እርምጃ ይወስዳል፤ መልሶ ይስፋፋል። በተለይ የምርጫ ወቅትና መንግሥት ደከም ሲል ህገወጥነቱ እየጨመረ የሚመጣበት ሁኔታ አለ። በየጊዜው እየተከማቸ እዳ ሆኖ ቀጥሏል።
በአንድ በኩል ጥርግ አድርጎ እርምጃ ለመውሰድ ተጨማሪ ቀውስ ይፈጥራል። ምክንያቱም ዜጎች ናቸው፤ ሜዳ ላይ ይወድቃሉ፤ በመሆኑም እንደመንግሥት ኃላፊነት መውሰድ ይገባሻል። ሁለተኛ ደግሞ ዝም ካልሽ ከተማዋ ያለፕላን ህገወጥነት የምትቀጥልበትና ውስን የሆነው የህብረተሰቡ ሃብት ጥቂቶች የሚቀራመቱበት ሁኔታ ይፈጠራል። ሌላው ደግሞ አገልግሎትን የማሻሻል ፣ መልካም አስተዳደርና ቢሮክራሲው አካባቢ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከባድ ሥራ ነበር። ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ረገድም ብዙ ይቀረን ነበር። ያም ሆኖ ግን ከጊዜ ወደጊዜ ከተማችን እያደገች እድገቷ በጉልህ የሚታይበት ሁኔታ መፈጠሩ የሚካድ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡– እንደ አመራር ለመወሰንም ሆነ ለመፈፀም ፈተና ሆኖቦት የነበረ ችግር ካለ ለአብነት ቢጠቅሱልን ?
አቶ አባተ፡– እንግዲህ አሁን ላይ በግሌ ሳላከናውነው የቀረሁትና የሚቆጨኝ ይሄ ነው ብዬ የማነሳው ችግር የለም። እንዳልኩሽ በአሰራር ሂደት ድክመቶችና ጥንካሬዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በተለይም እኔ ከ15 ዓመት በላይ በቁልፍ የኃላፊነት ቦታ ላይ እንደመቆየቴ አቅሜ የቻለውን፤ ህሊናዬ የሚፈቅደውን ያህል ለከተማዋ እድገት እና ብልፅግና አስተዋፅኦ አበርክቻለሁ ብዬ አስባለሁ። እዚህ ላይ ተነስቼ ይሄን በግሌ ባደርገው ኖሮ ብዬ የምፀፀትበት ነገር የለም። በአጠቃላይ ግን አሁን ላይ ስታያቸው የሚሰሙሽ ነገሮች ይኖራሉ። ለምሳሌ እኔ አንዱ የሚሰማኝ ነገር ከልማት ተነሺዎች ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው ነገር ነው። በልማት ምክንያት ከይዞታቸው የሚነሱ አርሶ አደሮችና ነዋሪዎችን በሚገባው ልክ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመቻሉ ሁሌም የሚያሳዝነኝ ነገር ነው። እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ በመንግሥት የነበረው አሰራር ስለሚከለክለን ነዋሪውን ቅር የሚያሰኝበት ሁኔታ ነው። በተለይም የካሳ ክፍያ ስርዓቱ በህግ የሚመራና በመመሪያ የሚያዝ በመሆኑ ተነሺዎቹ የተጎዱ መሆናቸውን በግልፅ ትገነዘቢያለሽ። ያም እኔም ሆንክ ሌላው እየፈለገ ግን ምንም ሊያደርገው የማይችለው መሆኑ የሚያስጨንቅ ነበር። ግን በግሌ የፈጠርኩትም ሆነ ልፈታው የምችለው አልነበረም። ከዚያ ውጭ አሁን ላይ ይሄን ባደርገው ኖሮ ብዬ ምንም የምፀፀተው ነገር የለም። እንደነገርኩሽ ደግሞ ብዙ ጊዜ በአስተዳደሩ ውስጥ እንደማሳለፌ አቅሜ የፈቀደውን ያህል ለከተማዋ እድገት አስተዋፅኦ አበርክቻለሁ ብዬ ነው የማስበው።
አዲስ ዘመን፡– በወቅቱ ከመሬት ወረራ ጋር ተያይዞ የሚነሱ በርካታ ችግሮች ነበሩ፤ በተለይም ለችግሩ መባባስ አመራሩ በዋናነት ተጠያቂ እንደነበር ይነሳል። ከዚህ አኳያ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ያልተቻለበት ሁኔታ ምን ነበር ይላሉ?
አቶ አባተ፡– ልክ ነው፤ እንዳልኩሽ የመሬት ወረራ ለበርካታ ዓመታት እየተስፋፋ የመጣ ችግር ነው። ምርጫንም ሆነ ሌሎች አጋጣሚዎችን በመጠቀም ህገወጥ ግንባታዎች በከፍተኛ ደረጃ ይስፋፋሉ። ይሄ ህገወጥ ግንባታ ደግሞ ውስብስብ የሚያደርገው ነገር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከመዋቅሩ ጋር የተሳሳረ መሆኑ ነው። አንድ አንድ አመራሮች እጃቸውን የሚያስገቡበት ሁኔታ አለ። የመሬት አካባቢ ያሉ ባለሙያዎችም እንደዚሁ የሚሳተፉበት አጋጣሚ አለ። ይህም በህገወጦች ላይ እርምጃ ለመውሰድ በምንዘጋጅበት ጊዜ ከፍተኛ ፈተና ይሆንብናል።
አንድ ምሳሌ ላንሳልሽ፤ በኮልፌ ክፍለ ከተማ እያለሁ በህገወጦች ላይ እርምጃ ለመውሰድ በምንዘጋጅበት ጊዜ ወዲያውኑ ተከበብንና የተደበደብንበት አጋጣሚ አለ። በተለይም ምክትል ኃላፊ የነበረው ሰው በድንጋይ ግንባሩ ተፈንክቷል። እናም ያ ሂደት በጣም ፈታኝና ውስብስብ ነበር። ሁለተኛ ደግሞ ቁርጠኛ ሆኖ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት በሚደረግበት ጊዜ በአንድ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም ያለመኖር ነበር። በአንድ በኩል እርምጃው ሲገፋ እርምጃ ተወሰደብኝ የሚለውን ሰው አቤቱታ የሚያዳምጥ አካል አለ፤ ልክ ንፁሃን የህብረተሰብ ክፍሎች እንደተፈናቀሉና እንደተጎዱ በማድረግ በሚዲያውም ሆነ ባገኙት አጋጣሚ የማስጮህ ሁኔታ አለ። ይህ ሁኔታ ሲያጋጥም እንደገና ወደኋላ የማለት ነገር ይታያል።
በተለይም በ2009 ዓ.ም እና በ2010 ዓ.ም ላፍቶ ላይ ይሄ የመሬት ወረራ አልቆም አለ ተብሎ ቁጥጥር በማጠናከር እርምጃ መውሰድ ጀምረን ነበር። ያ ሁኔታ ችግሩ ምንያህል ስር የሰደደ እንደሆነ የምትረጅው እርምጃው የህይወት መስዕዋትነት የተከፈለበት መሆኑን ስትገነዘቢ ነው። በርካታ የፖሊስ አመራሮች፤ የወረዳ አመራሮች ህይወታቸውን የገበሩበት ሁኔታ አለ። ይሄ የሚያሳይሽ የተለያየ መዋቅር በህገወጥነቱ ላይ እጁ መኖሩን ነው።
በየደረጃው ያለው አመራር ፣ የድርጅት እና የፀጥታ አባላት በእጅ አዙር ህገወጥነት ላይ የሚሳተፉበት ሁኔታ ስላለ ለከተማዋ አሁንም ድረስ ተግዳሮትና ፈተና ሆኖ የቀጠለበት ሁኔታ ነው ያለው። በየጊዜው እርምጃ ይወሰዳል፤ መልሶ ደግሞ ይተካል። ከዚህ ጋር ተያይዞ 1997 ዓ.ም በፊት የሰሩ ግንባታዎች ህጋዊ የሆነበት ሁኔታ ስላለ አሁንም እንደምንም አድርገን ህጋዊ ይሆንልናል የሚል አስተሳሰብና ምኞት ነው በስፋት ይታይ የነበረው። በአጠቃላይ የህገወጥነቱ ጉዳይ ለከተማው ትልቅ ፈተና ሆኖ ያለፈበት ሁኔታ ነው ያለው። ከዚህ በኋላም ቢሆን ፈተና ሆኖ ይቀጥላል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– እርሶ በነበሩበት ጊዜ በጣም በስፋት እንደ ችግር ይነሳ የነበረው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳይ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ሁኔታ ሲያስቡ ምንድን ነው የሚሰማዎት?
አቶ አባተ፡– ይሄንን ጉዳይ አሁን ላይ ማንሳቱ ምን ያህል እንደሚጠቅም አላውቅም። ግን ዞሮ ዞሮ ማስተር ፕላኑ ችግር አልነበረበትም። እንደእኔ እምነት ያ ማስተር ፕላን አዲስ አበባንም ሆነ ዙሪያዋን ያለ ማህበረሰብ ሊጠቅም የሚችል ማስተር ፕላን ነበር። ሃሳቡ ቆንጆና የሚደገፍ ነበር። አዲስ አበባ ብቻዋን ከምታድግ በአካባቢዋ ካሉት ከተሞች ጋር አስተሳስረን፣ ተደጋግፈንና እጅ ለእጅ ተያይዘን ለማደግ የሚያስችለን ነበር። በተቀናጀ መንገድ ከተማዋንና አካባቢዎቹን እናሳድግ የሚል ሃሳብ ነበር የነበረው። ግን ደግሞ ችግር የሆነው የማስተር ፕላኑ አላማና ይዘት በትክክል የተሟላ ግንዛቤ አለመያዙ ነው። ከመልካም ጎኑ ይልቅ በአፍራሽ መንገድ ነው ቅስቀሳ የተደረገበት። እኔ እዛ እንደነበረ አንድ አመራር ክፍተት ነበር ብዬ የምወስደው ሥራው ሲጀመር ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ያለመቻሉ ነው። ለህብረተሰቡ የማስተር ፕላኑ አላማ ምን እንደሆነ ግንዛቤ ያለመፈጠሩና ነዋሪው ራሱ የዚህ ልማት ደጋፊና ተሳታፊ እንዲሆን ጥረት ያለመደረጉ እንደክፍተት የሚታይ ነው። ይህም የእኛም ሆነ የሌሎች የመንግሥት ኃላፊነት የነበረና ግን ደግሞ ያልፈፀምነው ተግባር ነው ።
እርግጥ ነው ሥራው እንደተጀመረና ገና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ሳንፈጥርበት በተቃራኒ መንገድ ወሬዎች ተሰራጩ። በተለይም የአካባቢውን ማህበረሰብ ሊጎዳ እንደሚችል፤ አዲስ አበባን የማስፋፋትና መሬት የመውሰድ ዓላማ ያለው ነው ተብሎ በስፋት ተሰራበት። ዞሮ ዞሮ አሁን ላለውም የለውጥ እንቅስቃሴ የራሱ አስተዋፅኦ ነበረው ብዬ አስባለሁ። ይህ ማስተር ፕላን በራሱ ለለውጡ ንቅናቄ ፈጥሯል። አላማው ጥሩ የነበረ ቢሆንም ሊያሳካ የፈለገውን ግብ ሳያሳካ እንዲቆም ተደርጓል። ለአዲስ አበባም ሆነ ለዙሪያውም አካባቢ ማህበረሰብ ያለውን ጥቅም የተሟላ ግንዛቤ ተይዞ እና መግባባት ተፈጥሮበት ወደ ሥራ ባለመገባቱ ትልቅ ተቃውሞ የእንቅስቃሴ ማዕከል ሆኗል። ይህንን ተከትሎ በርካታ ፈተናዎች አጋጥመዋል። ግን ደግሞ አስቀድሜ እንዳልኩሽ ወደዚህ ጉዳይ መመለስ ብዙም ጠቃሚ ነው ብዬ አላስብም። በአጠቃላይ ግን ትክክለኛ የማስተር ፕላኑን አላማ በተረዳ መልኩ ንቅናቄው ባይጀመርም ለውጡ ለመምጣቱ ግን አንዱ አብይ ምክንያት ነው ብዬ ነው የማስበው።
አዲስ ዘመን፡– እርሶዎ በአመራርነት በነበሩበት ጊዜ የአዲስ አበባ ወጣት ዋነኛ ችግር ምን ነበር? ያንንስ ለመፍታት ምን ያህል ጥረት አድርገናል ብለው ያምናሉ?
አቶ አባተ፡– አዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ኃላፊ ከመሆኔ በፊት የተጀመረ የለወጥ ፓኬጅ ተዘጋጅቶ እንደነበር አስታውሳለሁ። ይሄ የወጣቶች የለውጥና የእድገት ፓኬጅ በርካታ ጉዳዮችን ለይቷል። አንደኛው የወጣቶች የሥራ እድል ችግር ነው፡ ይህም መሰረታዊ ሆኖ ነው የተለየው። ሁለተኛ የወጣቱ የስፖርትና መዝናኛ ቦታዎች እጥረት ተብሎ ነው የተለየው። በሶስተኛ ደረጀ የስብዕና መገንቢያ እና የወጣት ማዕከላት እጥረት ባለመኖሩ ወጣቱ በተለያየ መንገድ ለአልባሌ ነገሮች የተጋለጠበት ሁኔታ ነበር። ይህ የለውጥና የእድገት ፓኬጁ ይህንን ችግር መነሻ ተደርጎ የተዘጋጀ ነበር። በእነዚህ ችግሮች ምክንያት ወጣቱ የልማቱ ባይተዋር ሆኖ ከመንግሥት የሚርቅበትን ሁኔታ ስለሚፈጥር እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በከፍተኛ አመራር ደረጃ አቅጣጫ ተቀምጦ የተገባበት ነበር።
ወጣቱን ካልያዝን የከተማችን እድገት እውን ሊሆን አይችልም። በተቃራኒው ወጣቱ ያለውን እውቀት እና ጉልበት በአግባቡ ከተጠቀምንበት ለልማት ትልቅ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል። ይህንን ኃይል ካመከነው ደግሞ ለጥፋት መሳሪያ የሚሆንበት አጋጣሚ ይፈጠራል በሚል ሰፊ ሥራዎች ተሰርተዋል። በዚህ ሥራ ሙሉ ለሙሉ የወጣቱ ችግር ተቀርፏል ባንልም በጣም ሰፊ የሆኑ የሥራ እድል ፈጠራ መርሐግብሮች ተከናውነዋል። ከቤት ልማት ጋር በተያያዘ ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ግብዓት በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል። ለምሳሌ ጠጠር ፣ ብሎኬት በማምረት፤ የህንፃውን የተወሰነ ክፍል በመያዝ የውበት ና የቀለም ቅብ ሥራዎች ላይ በስፋት ተሳትፈዋል።
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች እየተገነቡ ወጣቱ ሰፊ የሥራ እድል እንዲያገኝ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህም በመደረጉ አሁን በርካታ ወጣቶች ሃብት ፈጥረው የተሻለ ደረጃ የደረሱበት ሁኔታ አለ። ይህም ሆኖ ግን ከወጣቱ የሥራ ፍላጎትና ቁጥር አንፃር ሲታይ ብዙ መስራት ይጠይቃል። የተሰሩት ሥራዎች ግን ቀላል አልነበሩም።
በሌላ በኩል በእያንዳንዱ ወረዳ ቢያንስ አንድ የወጣት ማዕከል መገንባት አለብን ብለን ትኩረት ሰጥተን የሰራናቸው ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው። ማዕከላቱ ከተገነቡ በኋላ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል። የቤተ መፅሐፍት አገልግሎት፣ የተለያዩ የስፖርት ቤቶች ፣ የስነ-ተዋልዶ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል። ከሞላ ጎደል እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በእያንዳንዱ ወረዳ ቢያንስ ቢያንስ አንድ የወጣት ማዕከል እንዲገነባ ተደርጓል። የስፖርት ማዘውተሪያዎችን የማስፋፋት ሥራም በጎ ጅምሮች ነበሩ። አንደኛ በየአካባቢው አነስተኛ የእግር ኳስ የቅርጫት ኳስ፣ መረብ ኳስ ሜዳዎችን የመገንባት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር። መካከለኛ ስታድየሞች ፕሮጀክቶች ተቀርፀው በቅርቡ ተመርቋል። ለምሳሌ የራስ ሃይሉ የውሃ መዋኛ ገንዳ ግንባታ ያኔ ነው የተጀመረው። ጃንሜዳ ላይ የሚገነባው ጅምናዚየምንና የአበበ ቢቂላን ስታዲየም በተመሳሳይ ለማሻሻል ፕሮጀክት ነድፈን ወደ ሥራ ገብተን ነበር።
አዲስ ዘመን፡– ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ አስተዳደሩ ከከተማዋ ወጣት ይልቅ ከክልል ለመጡና ለፖለቲካ አባላት ቅድሚያ እንደሚሰጥ በስፋት ቅሬታ ይነሳበት ነበር። ይህ ምን ያህል ተጨባጭ ነው ይላሉ?
አቶ አባተ፡– እንግዲህ ምን መሰለሽ በሥራ ሂደት ጉድለት አልነበረም ልልሽ አልችልም። ግን ከዚህ አካባቢ የመጣ ወይም የፖለቲካ አባል መሆን አለበት የሚል ገደብ ነበር የሚለውን ነገር ለመቀበል እቸገራለሁ። ምክንያቱም እኛ እንዳውም ቅድሚያ ለአዲስ አበባ ወጣት ሰጥተን መስራት አለብን ብለን ነበር ስንሰራ የነበረው። አንደኛ ከዩኒቨርሲቲና ከቴክኒክና ሙያ ተመርቀው የወጡ ፣ አካል ጉዳተኛ የሆኑ ወጣቶች ፣ በተለያየ መንገድ ችግር ውስጥ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች እና ለሴቶች ቅድሚያ ሰጥተን ነበር ስንሰራ የነበረው። ግን በወቅቱ የነበረው ትልቁ ችግር ሥራ ማማረጥ ነው። ለምሳሌ ኮብልስቶን ላይ ሰፊ ፕሮግራም ነበር የቀረፅነው። ራሱን የቻለ የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት አቋቁመንም ነበር ስንሰራ የነበረው። አሁን ከተማችን ውስጥ በየቦታው የምታያቸው መንገዶች የዚያ ውጤት ናቸው። ደግሞም ብዙ ሺ ሰው ነው የሥራ እድል ያገኘበት። በአንድ በኩል ድንጋይ ፈላጭ አለ፤ ሁለተኛ የወጣውን ድንጋይ ወደ ኮብልስቶን የሚቀይር አለ፣ በሶስተኛ ደረጃ የተጠረበውን ድንጋይ የሚያነጥፉ አሉ። ያን ያህል የሥራ እድል ተመቻችቶ እያለ ቀላል የማይባለው የከተማዋ ወጣት እንደዚህ ጠንከር ያሉ ሥራዎችን ያለ መቀበልና ሥራ የመምረጥ ሁኔታ ነበር።
የከተማው ወጣት የናቀውን ይህንን የሥራ እድል ደግሞ ከክልል የሚመጡ ወጣቶች ቶሎ ብለው የመጠቀም ሁኔታ ተስተውሏል ። ከዚህ ውጭ ግን በብሄር ወይም በፖለቲካ ሰዎች እየተመረጡ የሚገቡበት ሁኔታ አልነበረም። ይሄ ማለት ግን በሂደቱ ክፍተት አልነበረም ማለት እንዳልሆነ እንድትገነዘቢልኝ እፈልጋለሁ። በጓደኛም፣ በቤተሰብም ተመራርጦ የመግባት ነገር ሊኖር ይችላል። አደረጃጀቱ ላይ ግን ምንም ሰው የፖለቲካ አባል መሆን አለብህ ተብሎ የሚገደድበት አሰራር ፈፅሞ አልነበረም። ግን ደግሞ እነዚህ አባላት ከአመራሩ ጋር ቅርበት ስለነበራቸው እድሉን ቶሎ የመጠቀም ነገር ሊኖር ይችላል። ይሁን እንጂ አባል የሆነና ያልሆነ ብለን የምንለይበት አሰራርም በምንም መንገድ አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡– ሌላው የቀድሞው አመራር ይነሳበት የነበረው ቅሬታ የኮንዶሚኒየም ቤት አሰጣጥ ግልፀኝነትና ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑ ነው። በተለይም የድርጅትና የአንድ ብሄር አባላት በህገወጥ መንገድ በርካታ ቤቶችን የያዙበት ሁኔታ እንደነበር ይነሳል። ከዚህ አኳያስ ምላሾት ምንድን ነው?
አቶ አባተ፡– ለእኔ የቤት ልማት መርሐ ግብሩ በአጠቃላይ እንደስኬት ከማያቸውና ከምኮራባቸው ሥራዎች አንዱ ነው። የአዲስ አበባን ገፅታዋንም የቀየረ ነው ብዬ ነው የማስበው። ብዙ ዜጎችን የቤት ባለቤት አድርጓል፤ በሺ የሚቆጠሩ ኮንትራክተሮችን ያፈራ፤ ከትንሽ ተነስተው ደረጃቸውን አሻሽለው ትልቅ ደረጃ የደረሱ ብዙ አማካሪ ድርጅቶችን ያወጣ፤ በርካታ የሥራ ዕድልን በከተማዋ ውስጥ የፈጠረ፤ የሃብት ክፍፍሉን ፍትሃዊ እንዲሆን ያደረገና የከተማዋን ገፅታ በመቀየር በኩል ትልቅ ሚና የተጫወተ ነው።
እንደእኔ ሊነሳ ይገባ የነበረው ቅሬታ የተመዝጋቢው ብዛትና የምንገነባው ቤት መጠን ተመጣጣኝ ያለመሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም የአፍሪካ መሪ መጥቶ የቤት ልማት ፕሮግራሙን ሳይጎበኝ የሚሄድ አልነበረም። ስርጭቱንም በተመለከተ ሶፍትዌሩ ተፈጥሮ 1997 ዓ.ም የተፈጠሩ የመረጃ መዛባቶችን በ2005 ዓ.ም ዳግም በመመዝገብ የማጥራት ሥራ ተሰርቷል። በዚሁ ሥራ ላይ ብቻችን ሳይሆን እንሰራ የነበረው የመረጃ ደህንነት ኤጀንሲ( ኢንሳ) ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤትም ጭምር ገብተው ነበር ሲሳተፉበት የነበሩት። እንደሚታወቀው ሶፍትዌሩን ያበለፀገው ኢንሳ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና በከተማ ልማት ሚኒስቴር የቅርብ ቁጥጥር ይደረግበት ነበር። ይሄ እንግዲህ እኛ ጋር ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ከመስጋት የመነጨ ነው። ከቁጠባ ጋር ተያይዞ ሙሉ መረጃውን የሚሰጠውም ባንክ ነው። ባንክ የሰጠውን መረጃ ወደኮምፒዩተር ሲስተም የሚያስገባው ኢንሳ ነው። እጣውም የሚወጣውም በቀጥታ ስርጭት በቴሌቪዥን እየተላለፈ ነው። ከዚህ ውጭ ግልፀኝነት ያለው አሰራርና አካሄድ ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቅም። ደግሞም ከዚህ የተለየ ጥንቃቄ ይኖራል ብዬ አላስብም። አንችም እንዳነሳሽው ግን ያልተመዘገቡ ሰዎች ቤት ተሰጥቷል ሲባል ሰምቻለሁ። ግን በእኛ በኩል ይህ ሊሆን የሚችልበት እድል አልነበረም። ምክንያቱም ኃላፊነቱን የወሰደው አካል ሌላ በመሆኑ ነው። አጠቃላይ አሰራሩን የሚቆጣጠረው ኢንሳ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ግን እኮ ያ ድርጅት በወቅቱ የነበረው አመራር ያለአግባብ ይጠቀምበት እንደነበር ይታወቃል?
አቶ አባተ፡– እንግዲህ ኢንሳ ከተመዘገበው ነዋሪ ውጭ ቤት እንዲሰጥ ስለማድረጉ ማወቅ የሚቻለው በባለሙያ ሲጣራ ብቻ ነው። እኔ አሁን ላይ ይሄ ነው ልልሽ አልችልም። አጠቃላይ የሄድንበትን ጥንቃቄ ነው ላስረዳሽ የምችለው። ግን ደግሞ በእርግጥ እዛ ያሉ ባለሙያዎች ሙያቸውን ተጠቅመው የፈለጉበትን የሚያስገቡበት ፤ ያልፈለጉትን የሚያስወጡበት ሁኔታ ካለ መጣራት ነው ያለበት። እኛ ግን ንክኪ እንዳይኖር ኃፊነቱ በእኛ ብቻ ስር እንዳይወድቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገናል ብዬ ነው የማስበው። በተለይም በ1997 ዓ.ም ምርጫውን ተከትሎ ችግሮች እንደነበሩ ስላየን ነው በ2005 ዓ.ም ላይ የማጣራት ሥራ የሰራነው። ስለዚህ እኛ የምንችለውን ያህል አድርገናል ብዬ ነው የማስበው። በአጠቃላይ ይህ ብልሹ አሰራር ነበር ከተባለ ዝም ብሎ በግምትና በሃሜት ሳይሆን በባለሙያ ተጣርቶ ችግር ከተገኘ የሚጠየቀው አካል ይጠየቃል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ እንዳነሱት አሁን ላይ እየተጠናቀቁና እየተመረቁ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ የማጠናቀቁ ነገር እምብዛም አይታይም ነበር። አሁን ላይ መጀመር ብቻ ሳይሆን ማጠናቀቅና ለጥቅም የማዋሉ ነገር እየተለመደ መምጣቱ የምን ውጤት ነው ይላሉ?
አቶ አባተ፡– እንግዲህ የፕሮጀክት መጓተቶች ምንም ጥያቄ የለውም በስፋት ነበር። ለዚህ ግን የተለያዩ ምክንያቶች አሉት። ለምሳሌ የቤቶች ግንባታን ብንወስድ ብዙ ጊዜ ይጓተታሉ። ይህ የሚሆነው ጨረታ የማውጣት ሂደቱና አቅም ላለው ኮንትራክተር ኃላፊነት የመስጠቱ ሥራ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ስለነበር ነው። ምክንያቱም የሥራ እድል መፍጠሪያ
በመሆኑ አነስተኛ አቅም ያላቸው ኮንትራክተሮች የሚገቡበት ነው። ግብዓት የሚያቀርበው መንግሥት ነው። ስለዚህ ይሄ የሚፈጥረው ችግር አለ። ሁለተኛ ፕሮጀክትን የማስተዳደር አቅም አልነበረንም። ይሄ አንግዲህ ካለን ፕሮጀክት የመምራት አቅም እና ልምድ ውስንነት የሚመነጭ ነው። ደግሞም አብዛኛው ለሀገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የሚሰጥ በመሆኑ ሰፊ የአቅም ውስንነት ነበር። በአጠቃላይ ፕሮጀክት አመራር ላይ ቶሎ ጨርሶ በተያዘለት ጊዜ የማጠናቀቁ ባህል ላይ ሰፊ ክፍተት እንደነበረብን እሙን ነው። ልንማርበትም የሚገባ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተሰሩ ፕሮጀክቶች በእኔ እምነት በጣም ጥሩና ሊበረታቱ የሚገባቸው ናቸው ብዬ ነው የማስበው። ማንም ዜጋ ባለፉት ሶስት ዓመታት በከተማዋም ሆነ እንደሀገር የተሰሩትን ሥራዎች ካለደነቀ ጤናማ ነው ብዬ ልወስድ አልችልም። በተለይም ሜጋ ፕሮጀክቶች ተብለው እንደእንጦጦ ፓርክ፤ አንድነት ፓርክ ፣ የወንዞች ዳርቻን ማልማት ሥራዎች እንዲሁም በመስቀል አደባባይ ላይ የተሰራው ሥራ በእኔ እይታ ለአዲስ አበባ ትልቅ ገፀበረከቶች ናቸው ብዬ ነው የማስበው። አንደኛ የከተማችንን ገፅታ በትልቁ የሚለውጡ ናቸው። ሁለተኛ የቱሪስት መስህብ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። በከተማችን የተሰሩት ሥራዎች አዲስ አበባን የበለጠ ተወዳዳሪና ተመራጭ እንድትሆን የሚያደርጉ ምርጥ ፕሮጀክቶች ናቸው። አፈፃፀማቸውም በአጭር ጊዜ ተጀምረው በአጭር ጊዜ የተጠናቀቁ ትልቅ ልምድ ሊወሰድባቸው የሚገቡ ፕሮጀክቶች ናቸው ብዬ ነው የማስበው።
የእነዚህን ፕሮጀክቶች ልምድ በደንብ ቀምሮ ወደ ሌሎቹ ማስፋት ይገባል። በአጠቃላይ የተሰራው ሥራ ሁላችንም የምንኮራበት ነው። አሁን ላይ የአዲስ አበባ ህዝብ ሌላ ቦታ ለመዝናናት መሄድ አይጠበቅበትም። ፕሮጀክቶቹ እያንዳንዱ ነዋሪ ከቤቱ ሳይርቅ የሚዝናናበትና እረፍት የሚያደርግበት እድል ፈጥረዋል። በአውሮፓና በሌሎች አገራት እያየን የምንቀናባቸው የመዝናኛ ሥፍራዎችን ሩቅ ሳንሄድ አግኝተናል። ይህ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ምርጥ ሥራ ነው ብዬ ነው የማስበው።
አዲስ ዘመን፡– አዲስ አበባ ከተማን እንደስሟ አበባ ለማስዋብ የከተማ አስተዳደሩና የመንግሥት አመራሩ የወሰደውን ቁርጠኝነት እንዴት አዩት? ከዚህ በኋላ በምን መልኩ ነው መቀጠል የሚገባው ይላሉ?
አቶ አባተ፡– የሸገር ፕሮጀክቶችን ለማስፈፀም በአመራሩ የተደረገው ጥረትና ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው። ከመጀመሪያው ጀምሮ በደንብ በተቀናጀ መንገድ ነው ሥራው የተጀመረው። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በአመራሩ ሲደረግ የነበረው የቅርብ ክትትል የሚያስገርም ነው። በመሰረቱ አጠቃላይ ሥራው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች ናቸው ብሎ ነው መውሰድ የሚቻለው። በየጊዜው እንደ አንድ የፕሮጀክት ማናጀር ነው ሥራው ከግብ እንዲደርስ ሲከታተሉ የነበረው። በአጠቃላይ የአመራሩ ቁርጠኝነት ፕሮጀክቶቹን ቶሎ ጀምሮ ቶሎ በመጨረስ በኩል የሚሰጠው ትልቅ ትምህርት አለ። አጠቃላይ ፕሮጀክት አመራራችን ላይ ልንማርባቸው የሚገቡ ሂደት ነው ያየነው፡ በተጨማሪም የፕሮጀክቶቹ ይዘት የሚያስደንቅና ለወደፊት እድገታችንም መሰረት የሚጥሉ ናቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ እኔ አንዳንድ ሰዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ሲያነሱ እሰማለሁ። እኔ ግን በዚህ አልስማማም። እነዚህ ፕሮጀክቶች አንደኛ የሀገሪቱንም ሆነ የከተማችንም ገፅታ የሚለውጡ ናቸው። ቱሪስት ፍሰቱም በከፍተኛ ደረጃ የሚጨምሩ ናቸው። ከዚህም ባሻገር ገቢ የሚያመነጩ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል።
ከዚህ ቀደም ቱሪስቱ እንዲቆይ የሚያደርግ ቦታ የለንም ። አሁን ግን አንድ ቱሪስት ሲመጣ እንጦጦ ላይ ብቻ ሁለት ቀን ቆይቶ የሚዝናናበት እና የሚጎበኝበት እድል ተፈጥሯል። ሌሎችንም የሸገር ፕሮጀክቶችን በማየትና በመጎብኘት ከሶስት እስከ አንድ ሳምንት ድረስ ቆይቶ የሚሄድበት እድል ተፈጥሯል። በመሆኑም የተሰራው ሥራ በሁሉም መመዘኛ ሲታይ በጣም ውጤታማና ለአዲስ አበባ ህዝብም ትልቅ ስጦታ ነው ብዬ ነው የማስበው። ይሄ ሥራ መበረታት ያለበት ነው።
የእነዚህ ፕሮጀክቶች በአግባቡ ተገምግሞ በሰነድ ተሰንዶ ተሞክሮው ለሌሎችም የሚተላለፍበት ሁኔታ መኖር አለበት ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ሌሎቹም ብዙ የሚጓተቱ ፕሮጀክቶች ስላሉ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች የምንማርበት ሁኔታ መኖር አለበት ብዬ አስባለሁ። በሁለተኛ ደረጃ እዚህ ጋር የተመዘገቡት ስኬቶች በሌሎችም መደገም መቻል አለባቸው። በተለይም ከተማችንን በሁሉም መልኩ ውብ ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ ማስቀጠልና ማስፋት ያስፈልጋል። አሁን ላይ በከተማችን ህዝብ በከፍተኛ የሆነ የኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው። ከዚህ አንፃር የሚሰራው ሥራ ነዋሪው ኪስ ውስጥ የሚገባ ነገር እንዲያመጣ በስፋት መታሰብ ይገባዋል። አጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያሳድግና የኑሮ ውድነቱን የሚያረጋጋ ሥራ መሰራት አለበት።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። አሁን ላይ በርካታ ወጣት ከየትምህርት ተቋሙ እየተመረቀ ነው። በዚያው ልክ ግን ሥራ እያገኘ አይደለም። ይህ ችግር ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ሳይሆን እንደሀገርም ያለ ነው። ስለዚህ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ሰፊ ሥራ መሰራት መቻል አለበት። ይህንን ለመስራት ይህ ፕሮጀክት መነሻ ሆኖ ያገለግላል። ሌላው የቤት ልማት ፕሮግራም ለአዲስ አበባ ህዝብ ቅንጦት ሳይሆን መሰረታዊ ጉዳይ ነው። በነገራችን ላይ የቤት ልማት የቤት ችግርን ብቻ አይደለም የሚፈታው፤ አስቀድሜ እንዳልኩሽ ከፍተኛ የሆነ የሥራ እድል የሚፈጥር ጭምር ነው። ኢኮኖሚ ያመነጫል፤ ያነቃቃል። ከተማዋንም ይለውጣል። ከዚህ አንፃር ባለፉት ሶስት ዓመታት አዲስ የቤት ግንባታዎች አልተከናወኑም። ሰሞኑንም ከውጭ ድርጅቶች ጋር አስተዳደሩ ቤት ለመገንባት መስማማቱን ሰምተናል። ይህ ጥሩና የሚበረታታ ነው። ምክንያቱም በመንግሥት ብቻ ሊፈታ የሚችል ባለመሆኑ ነው። ግን ዘርዘር አድርጎ ማየት ያስፈልጋል። እነዚህ የውጭ ድርጅቶች የሚገነቧቸው ቤቶች ዋጋ ምንያህል ነዋሪው የሚችሏቸው ናቸው ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ለየትኛውስ ማህበረሰብ ነው እነዚህ ቤቶች የሚተላለፉት? የሚለውን ነገር በዝርዝር ፈትሾ መስራት ያስፈልጋል።
በጥቅሉ አሁን አዲስ አበባ ላይ የተሰሩ ከውበትና ከመዝናኛ ጋር የተያያዙ ፕሮጀክቶች በሁለንተናዊ መመዘኛ ሲታዩ በጣም የሚደነቁ ናቸው። ግን ደግሞ ማስፋትና የህዝቡን ዘላቂ ኑሮ በሚቀይር መልኩ መረባረብ ያስፈልጋል።እርግጥ ነው መንግሥት ባለፉት ሶስት ዓመታት የነበረበት ሁኔታ ከዚህ በላይ ሊሰራ ይገባል ብለሽ በድፍረት የምትናገሪበት ነባራዊ ሁኔታ አልነበረም። ከነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ሰከን ብሎ ልማት ላይ ለመረባረብ የሚያስችል ሁኔታ አልነበረም። በብዙ መንገድ ተወጥሮ እንደነበር ይታወቃል። ከምርጫ በኋላ ግን ወደ ተረጋጋ ስርዓት የምንገባ ከሆነ በዚህ መልኩ ከተሰራ ከተማችንንም ሆነ ሀገራችንን በተሻለ መልኩ ወደፊት ማራመድ ይችላል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– የተሰሩት የልማት ሥራዎች ከአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ አኳያ ያላቸው ፋይዳ እንዴት ይታያል?
አቶ አባተ፡–እንግዲህ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው አያጠያይቅም። የሰለጠኑት አገራትም ከተሞቻቸውን እየገነቡ ያሉት በዚሁ መንገድ ነው። በህንፃ ብቻ ሳይሆን ለኑሮ የተመቸ አካባቢ ጥበቃ ላይ ጥንቃቄ የሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ያተኮረችው። በአጠቃላይ አረንጓዴነት የተላበሱ ከተማዎችን ነው እየገነቡ ያሉት። እኛም በዚህ መልኩ መጀመራችን ተገቢና ወቅቱን የሚያገናዝብ ነው። አሁን ለምሳሌ ዝም ብለን የሸገር ወንዞች ዳርቻ ልማትን ብናየው ከእንጦጦ ጀምሮ ፣ ጉለሌ የእፅዋት ማዕከልና የቀበና እና ሌሎች ወራጅ ወንዞችን ተከትሎ የሚሰሩት ሥራዎች ከተማዋን አረንጓዴ ከማድረግ ባለፈ ለህዝቡ የመዝናኛ ማዕከል እየተፈጠረ ነው ብዬ ነው የማስበው።
በነገራችን ላይ አንድ አንድ ሀገሮች ህንፃ ብቻ ገንብተው ከተሞቻቸው በከፍተኛ የአካባቢና የአየር ብክለት ሰለባ ሆነው ነዋሪው ለመኖር አዳጋች የሆነባቸው ከተሞች አሉ። በሁለተኛ ደረጃ አሁን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ‹‹ኢትዮጵያን እናልብሳት›› በሚል ከጀመሩት የአረንጓዴ ልማት ጋርም ተቀናጅቶ መታየት አለበት። እናም ሀገራችን አጠቃላይ የአረንጓዴ ልማት ሽፋኗ ከፍ ያደርገዋል። ሌሎች ከተሞች ላይ መስፋፋት አለበት።
ለምሳሌ ባህርዳርና ሃዋሳ የመሳሰሉ ከተሞች ላይ ተፈጥሯቸው በራሱ አመቺ በመሆኑ ትንሽ ብቻ ሥራ በመስራት ብዙ ልንለውጣቸው የምንችላቸው ናቸው። ከተሞቻችን በአረንጓዴ ልማት ቅኝት የምንገነባቸው ከሆነ አካባቢያቸውን በአጠቃላይ ምቹና ተስማሚ እናደርጋቸዋለን። አለበለዚያ ህንፃ ብቻ እየጠፈጠፍን የምንቀጥል ከሆነ ነገ ከነገወዲያ ነዋሪዎቿ የሚጠሏቸውን የማይመቹ ከተሞችን እንፈጥራለን።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼ እና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ አባተ፡– እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2013