ኦ! ዲሞክራሲ በስምህ ስንት ግፍ ተሰራ?
<<ለአብነት ያህል ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ “በሕገ መንግሥቱ ላይ በተጻፈው መሠረት የመጀመሪያውን ሴናውንና (የላይኛው ምክር ቤት፤ ዛሬ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚባለውን መሰል) እና ፓርላማውን (የታችኛው ምክር ቤት የሚባለውንና ዛሬ የሕዝብ ተወካዮች በመባል የሚታወቀውን የእንደራሴዎች ሸንጎ) በይፋ ባስጀመሩበት የዛሬ ሰማንያ ዘጠኝ ዓመት፤ ሐምሌ 14 ቀን 1924 ዓ.ም፤ በሁለቱ ምክር ቤቶች ፊት የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር>>
“እናንተ ከየሀገሩ ተመርጣችሁ የተወከላችሁትን ሁሉ ወደዚህ ወደ ከተማችን መጥራታችን በአጠገባችን ሆናችሁ ለኢትዮጵያ ላንድነቷ በሚሆነው ሐሳብ በምክር እንድትረዱ ነው። እንደዚህ ባንድነት ሁናችሁ በጉባኤ ስትመክሩ ርስ በርሳችሁ ትላመዳላችሁ፤ የየሀገራችሁን ትዳር (ተሞክሮ) ለመነጋገር ትችላላችሁ። የጋራ ጥቅማችሁ ወይም ጉዳታችሁ የሚሆነውን ታገኛላችሁ። የመንግሥቱንም ስራ በሙሉ ትለምዱታላችሁ። በመጨረሻውም ሁላችሁም አንድ ቤተሰብ፣ ያንዲት ኢትዮጵያ ልጆች መሆናችሁን ትገነዘባላችሁ። እናታችሁን መውደድ፣ እንደ ወንድማማቾች መፋቀር የሚያስፈልጋችሁ መሆኑን እንድታውቁ።”
በንጉሠ ነገሥቱ መልካም ፈቃድ ተመርጦ ስራውን “ሀ” ብሎ ከጀመረው ከዚህ ጉባዔ በኋላ “ሕዝቡ ተሳትፎበታል” የተባሉ በርካታ የፓርላማ ተወካዮች “ምርጫ” ተከናውኗል። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በልጅነቱ ከሚያስታውሳቸው “የፓርላማ ምርጫዎች” መካከል ባደገበት አካባቢ በእጩነት የቀረቡት እነ አቶ ዘውገ ቦጂያ ሲፋለሙ ትዝ ይለዋል። የቤተሰቡ የቅርብ ወዳጅ የሆኑት የግንደበረቱ ባላምባራስ ምናሴ ነገዎ በአሸናፊነት ተወጡ ተብሎ ጮቤ ሲረገጥ የዓይን እማኝ ነበርኩ። የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ግርማ ወ/ጊዮርጊስና የዚህ ጸሐፊ የቅርብ ጓደኞች አባት የሆኑት መምህር ዘውዴ የተፋለሙበትን ትንቅንቅ የሞላበት ምርጫ በጨቅላ አእምሮው መዝግቦት ስለነበር ዛሬም ድረስ ያስታውሰዋል። ይሁን እንጂ በዘመኑ ምርጫ ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ሳትሆን “የሞአ አንበሳ ዙፋን” መሆኑን ልብ ይሏል። ዴሞክራሲ ስሙ እንጂ ግብሩ የቀለለበት ዘመን መሆኑም አይዘነጋም።
ኮሚዩኒዝም የተቀነቀነበትና የሶሻሊዝም ስም ገኖ የወጣበት የዘመነ ደርጉ የኢሕዲሪ (የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ) የእንደራሴዎች ምርጫም ፌዝ ብቻ ተብሎ የሚታለፍ ሳይሆን “ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ” በሚል መርህ የተከናወነ ስለነበር ከሕጻናት ልጆች ጨዋታ ጋር በእጅጉ ተመሳሳይነት ነበረው። በዝሆን የምርጫ ምልክት ጫንቃ ላይ ተፈናጠው መቶ በመቶ ፓርላማውን የወረሩት የኢሠፓ አባላት “የሕዝብ ተወካዮች” እየተባሉ ራሷን ኢትዮጵያን አቂለው ሕዝቡንም በአደባባይ አሞኝተዋል። “ኦ! ዴሞክራሲ በስምህ ስንት ግፍ ተሠራ!”
“የባሰ አለና ሀገርህን አትልቀቅ” እንዲል ብሂላችን፤ በህወሓት መራሹ ዘመነ ኢህአዴግ የተከናወኑት አምስት የኮሚዲና የትራዤዲ ተውኔታዊ ምርጫዎች የትናንት ከትናንት ወዲያ ክስተቶች ስለሆኑ ለብዙ ዜጎች ትውስታቸው አልመሸበትም። የሥርዓቱ ዋነኛ ሰው (Master mind) የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን “የሁለት ምርጫዎች ወግ – ናዳን የገታ አገራዊ ሩጫ” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ ከጠቃቀሷቸው ጉዳዮች መካከል ጥቂት ሃሳቦችን ቆንጥረን እናስታውስ።
“ኢህአዴግ ለፈረንጆቹ በተናዳፊነት፤ ለኢትዮጵያዊያን ደግሞ በታታሪነት የምትታወቀውን ንብ ይዞ፤ ተቃዋሚዎች ደግሞ መልኳ ቢለያይም የተለመደችውን ጣት ይዘው ለፉክክር ቀርበዋል። በነውጡ ዘመን አቶ መለስ ‘ዋ! ይህቺ ጣት አላርፍ ያለች እንደሆነ’ (አባባሉን እንጨርሰውና እንቆርጣታለን) ብሎ የሰጠውን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ወደ መርሳቱ የተቃረቡት ተቃዋሚዎች በሙሉ … የሚራኮቱት በተዓምረኛዋ ጣት ላይ ሆኗል” (ገጽ 199)።
በስመ ዴሞክራሲ የተጠመቀው ይህን መሰሉ ግፍ የታጨቀበት ምርጫ ሥርዓቱ እንደምን በእብሪት አብጦ፣ በራሱ እጅ “የሲኦልን ደጃፍ ማንኳኳት” እንደጀመረ በጥሩ አብነት ሊጠቀስ ይችላል። ሥርዓቱ የመንኮታኮቻው ጊዜ እየተቃረበ መሄዱን እያወቁት እንኳን በንቀት ቸል ብለው ባካሄዱት የክህደት ምርጫ ውጤቱን የገለጹት እንዲህ በማለት ነበር። “ምርጫው ‘አንድም ሁሉን ታገኛለህ፤ አለያም ሁሉን ታጣለህ’… የሚለው አባባል በተግባር የተገለጠበት ነበር።… ኢህአዴግና አጋሮቹ ሁሉንም (ድምጾች) ሙጥጥ አድርገው ወሰዱት። ኢህአዴግ ሕዝቡ ድምጹን ይሰጠው ዘንድ የትኛውንም ሂደት ለእድል ወይ ለአጋጣሚ ከቶም ሳይተው፣ ለአምስት ዓመታት ጠንክሮ በመስራቱ ያገኘው ውጤት ሁሉን (ድምጽ) ሙጥጥ አድርጎ ለመውሰድ አስችሎታል” (ገጽ 195)።
አለቦታው ስሙ ብቻ የተረፈንና ስያሜውን ከግሪኮች የተዋስነው “አያ ዴሞክራሲ” ባእድነቱን አረጋግጦ የኢህአዴግ አምስት ምርጫዎች ኮሮጆ እየተገለበጠባቸውና የተመራጮችና የመራጮች ጀርባ በአኮርባጅ እየተገረፈ እንደምን ሀገሪቱን በስቃይ መከራ ውስጥ እንደዘፈቋት በጭራሽ የሚዘነጋ አይደለም።
ባለፉት ሥርዓተ መንግሥታት የተደረጉ ኢዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተብዬዎች በሙሉ የሚያስታውሱን ትርጉሙ ላቅ ያለን አንድ ሀገራዊ ብሂል ነው። እንዲህ ይላል፤ “ዐውድማ የቆረጠችውን ቆርጣለች፤ ፌጦ በከንቱ ትረጫለች።” ግሩም አባባል መሆኑ ብቻም ሳይሆን የትርጉሙ ፍቺ እጅግም ባእዳችን አይደለም። በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች አርሶ አደሮች የሚያበራዩት አዝመራ “ይበረክትልናል” በሚል የየዋህነት እምነት በዐውድማቸው ዙሪያ ፌጦ መነስነሳቸውን ለማመልከት የተፈጠረ ብሂል ነው። ዐውድማው የሰጡትን እንጂ እንደምን በተዓምር ምርቱን ሊያበራክት ይችላል?
በንጉሠ ነገሥቱ ሥርዓት፣ በዘመነ ደርግና ከዚያም በኋላ ለሃያ ሰባት ዓመታት የሀገሪቱን በትረ ሥልጣን ጨብጦ ሕዝቡን በብረት በትሩ ሲቀጠቅጥ በኖረው ህወሓት መራሹ ሥርዓት ሲደረጉ የነበሩት ምርጫዎች በሙሉ ስለ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ጥቅም ሳይሆን ለራሳቸው ለሥርዓቱ ምሰሶዎች፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጆቻቸው፣ ለአጎንባሽ አፋዳሽ ጀሌዎቻቸው ጥቅም ሲባል እንደነበር አይዘነጋም። ለዚህም ነው “ዐውድማው የቆረጠው” የመቶ በመቶ ውጤት ሲታወጅልን የኖረው።
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት ከነገ ወዲያ እየተባለ ነው። በዚህ ታሪካዊ የምርጫ ግብግብ ጎልታ እንድትወጣ የምትጠበቀው ደግሞ ኢትዮጵያ ራሷ እንጂ ራስ ተኮር የሆኑ ፓርቲዎች እንዳልሆኑ ሲቀሰቅስ ከርሟል፤ እኛም ሳንታክት ብእራችንን ከወረቀት እያዋደድን “ይድረስ” እያልን መወትወታችን አይዘነጋም።
መራጩ ሕዝብ ወሳኝ ካርዱን ይዟል። ተወዳዳሪ ፖለቲከኞች እንዲያውቁት የሚያስፈልገው ትናንት ዛሬን መሆን ያለመቻሉን ነው። ጠላቶቻችንም ቢሆኑ የመከራ ዳፋቸውን እንደ ሲሳይ ቆጥረን በጫንቃችን ላይ እንደማንሸከምላቸውና በደም ግብር እንደማንወራረድ ሊረዱት ይገባል። ይኼኛው ምርጫ ከቀዳሚዎቹ “ምርጫ ተብዬዎች” ይለያል የሚባለው ለፖለቲካ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ተደርጎ የሚታሰብ ከሆነ ጅልነት ይሆናል። አሸናፊዋ ኢትዮጵያ ራሷ እንጂ እከሌ የተባለ ፓርቲ ሊሆን እንደማይገባ አዝለነው እሹሩሩ ስንለው የኖርነው የመከራ ተሞክሮ በሚገባ አስተምሮናል።
የስንዴ ዘር ከጎታችን ተሟጦ ርሃብ እያቀራራብን “ሕዝቡን በጥጋብ እናንበሸብሸዋለን” የሚሉ ስላቅ የገነነባቸው የፖለቲከኞች ቅስቀሳና ማላገጥ ሰልችቶናል፤ መሮናል፤ አጥወልውሎናልም። የምርጫ ውጤትን ተከትለው የሚፈነዱ ግጭቶች፣ ሞትና የንብረት ውድሞቶችም እንኳን ሊደገሙ ቀርቶ በፖለቲከኞች የአፍ እላፊ ንግግሮች ውስጥ አንዳንድ ቃላት አፈትልከው ሲወጡ ጠረናቸው እየቀፈፈን ተጠይፈናቸዋል።
“እኛ ካላሸነፍን ሀገሪቱን የሀዘን ማቅ እናለብሳታለን ፉከራና መፈክር” እንዴት አዘቅት ውስጥ ጥሎን ከሰብእና በታች አዋርዶ እንዳስጨነቀን ስለምናስታውስ እንኳን ተግባሩ ንግግሩን ራሱን የምንቆጥረው እንደ ክፉ “በላ” ነው። ተናጋሪውንና አሳቢውንም እንዲሁ እንደ “ዲያቢሎስ ታናሽ ወንድምና እህት።”
ጆሮ ላለው ሁሉ ይህ የሕዝባችን የጋራ መልእክት እንዳለ ይድረስልን። የምንመርጠው ኢትዮጵያን እንጂ ከምራጭ ላይ ወድቀን ሌላ የመከራ አሳር ስናጭድ አንኖርም። የፍዳ ፍም በአናታችን ላይ ተሸክመን ለመንገታገት አቅቶናል ብቻም ሳይሆን አንገፍግፎናል። የምንመርጠው ኢትዮጵያን ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ራሷ በአሸናፊነት ተወጥታ እልል ማለቷን ለመስማት ጓጉተናል። ይህቺን ኢትዮጵያን ያረገዘው ፓርቲ ብቻ እንዲመረጥ የምርጫ ካርዳችንን አዋላጅ አድርግን እንሾመዋለን። ኢትዮጵያችን ከምርጫም፣ ከተመራጮችም ሆነ ከመራጮች በላይ ስለሆነች እርሷው በክብር ከፍ ትበልልን። ሰኔ 14 ለሀገራችን የምጥ ቀን ሳይሆን ምርጥ ቀን ተስፋ አድርገናል። ይሄው ነው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2013