በቁጥር ስድስተኛው፣ በዓይነቱ ግን የመጀመሪያው የሆነው የ2013 የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ከነገ በስቲያ ይካሄዳል:: ይህ ምርጫ ምንም እንኳን በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ተራዝሞ የቆየ ቢሆንም፤ መራዘሙ ለመራጩም ለተመራጩም የተሻለ የትውውቅ ጊዜ የፈጠረ መሆኑ እሙን ነው:: ላለፉት ዓመታት በተከናወኑ ምርጫ ተኮር ተግባራት ከምርጫ አስፈጻሚው ጀምሮ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርጫ ታዛቢዎችና ሌሎችም ባለድርሻዎች ለምርጫው ስኬታማነት ሰርተዋል::
በዚህ መልኩ ጊዜ ወስዶና ተናብቦ መስራት መቻል ደግሞ በምርጫ ሂደት (ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ) ለሚከናወኑ ተግባራትም ሆነ ለሚፈጠሩ ችግሮች የጋራ መፍትሄና ቀና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ይሆናል:: ይሄም በቅድመ ምርጫ ሂደት ወቅት በጉልህ የታየ ሲሆን፤ ከዕጩ ማስመዝገብ፣ ከመራጮች ምዝገባ፣ የቅስቀሳና መሰል መርሐ ግብሮች ጋር ያሉ አካሄዶች ሁሉም በተሳተፈበትና በተስማማበት በሚያስብል ደረጃ ተከናውነዋል::
ከ37 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የምርጫ ካርድ በወሰደበት ምርጫ ከምርጫ ቁሳቁሶች አቅርቦትና የህትመት ችግር፣ ከዕጩዎች ምዝገባ ብሎም እገዳ እና መሰል ጉዳዮች ጋር በሂደቱ ሲያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችም በቦርዱም፣ በፍርድ ቤትም እልባት እያገኙ መሄዳቸው ደግሞ ቀጣይ ለሚፈጠሩ ችግሮች የተሻለ መፍትሄና መልስ ማግኘት እንደሚቻል ከወዲሁ ያሳዩ እርምጃዎች ናቸው::
ፓርቲዎችም ቢሆኑ ከሌሎች የተሻሉ መሆናቸውን ለማሳየት አሉኝ ያሏቸውን ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እንዲሁም አማራጭ ሀሳቦች የሚያቀርቡባቸው ነጻ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ተደልድሎላቸው ከሁለት ወር ለዘለለ ጊዜ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ቆይተዋል:: መኪናና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀምም በከተሞች እየተዘዋወሩ ራሳቸውን፤ እጩዎቻቸውም፣ ፕሮግራሞቻቸውን፣ ወዘተ ገልጸዋል፤ ህዝብ እንዲመርጣቸውም ቀስቅሰዋል::
በዚህ ሁሉ ሂደት የታጀበው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ደግሞ ኢትዮጵያውያን የሚመርጡበት እና ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት እንዲሆን ይጠበቃል:: ለዚህ ደግሞ ምርጫው ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ግልጽ፣ ዴሞክራሲያዊና ሁሉንም ያሳተፈ ሆኖ እንዲከናወን የግድ ይላል:: ይሄም እንዲሆን በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑም በተደጋጋሚ ተገልጿል:: ሌሎች የምርጫው ተዋናዮችም በዚሁ ልክ እንዲሰሩ፤ ምርጫውም ስኬታማና ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እንዲወጣ ተደጋጋሚ ጥሪ ቀርቧል::
ይህ ሁሉ ልፋት እና ጥረት ፍሬ የሚያፈራውና ኢትዮጵያ የምታሸንፈው ግን ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ከማለዳ 12 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት ባለው የምርጫ ተግባር ላይ በሚታይ የህዝብ ተሳትፎ መሆኑ እሙን ነው:: ምክንያቱም ምርጫው ህዝብ የሚመርጥበት እና ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት ስለሆነ ነው:: ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ኢትዮጵያውያን መምረጥ አለባቸው ማለት ነው::
በዚህ ረገድ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ከ37ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚልቅ ህዝብ ተመዝግቦ ካርዱን መውሰዱ፤ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ምርጫ ብዙ እንደጠበቁ፤ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል፣ ምርጫ ደግሞ ቀጣይ የአገሬን እጣ ፈንታ የምወስንበት እንደመሆኑ የምርጫው ሂደትም ያገባኛል በሚል የምርጫው ባለቤት የመሆን ስነልቡና መገንባታቸውን እና በምርጫው ላይ ያላቸውን መተማመን የሚያመላክት ነው::
በዚህ መልኩ ህዝቡ ካርድ መውሰዱም ሆነ ለምርጫው መዘጋጀቱ ደግሞ የሚደነቅ ተግባር ነው:: ይሁን እንጂ ካርድ መውሰድ ብቻውን የሚፈለገውን ግብ ለመምታት፤ ውጤትም ለማምጣት አያስችልም:: ይልቁንም ካርድ በወሰዱበት አግባብ በካርዱ የሚፈልጉትንና በቅስቀሳ ሂደቱ የተሻለ ሀሳብና አማራጭ አቅርቦልኛል ያሉትን፤ ለቀጣይ አምስት ዓመት እየመራ ወደተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ያሻግረኛል ያሉትን ፓርቲ በድምጽ መምረጥ ይጠበቅባቸዋል::
ምክንያቱም ካርድ መውሰድ ብቻውን የሚፈልጉትን ዕጩ ወይም ፓርቲ መምረጥ አይደለምና፤ ይህ የሚሆነው ድምጽን በምርጫ ሳጥን ውስጥ ሲያኖሩ ብቻ ነው:: ይህን ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ እርሶ ካርድ ቢወስዱም እስካልመረጡ ድረስ ሌሎች ካርድ ወስደው የሚመርጡ ሰዎች ካርድ ወስደው ያልመረጡ ሰዎችንም የቀጣይ አምስት ዓመት ጉዞ ይወስናሉ ማለት ነው::
ሆኖም ኢትዮጵያ የሁሉም እንደመሆኗ የሁሉንም ውሳኔ ትፈልጋለች:: እናም ካርድ የወሰደ ሁሉ ድምጹን በመስጠት ለውጡንም፤ ኢትዮጵያንም ማሻገር ይጠበቅበታል:: ይህም ሲሆን ህዝብ በነጻነት መርጦ ማንም ያሸንፍ ማን ኢትዮጵያም አሸናፊ ትሆናለች!
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2013