የአፍሪካ መዲና፤ የሚሊዮኖች ማዕከል፤ የኢትዮጵያዊያን አንድነት ማሳያ፤ የህብረ ቀለማት ጥምር ጌጥ አዲስ አበባ። ውብ ሆኖ የመታየት ፍኖትዋ ተገለጠ። አንገትዋን አስግጋ ቁልቁል ታሪካዊ የሆነውን የቸርችል ጎዳና ላይ ባየችው ብርሀን ፈካች። ንጋትዋን በደማቅ ብርሀን ጀመረች። ያረጀ ገጽታዋ ተቀይሮ፣ ስምዋን የሚመጥን አዲስነት፤ የሚገባትን አበባነት በተላበሰች ጊዜ መዲናችን ተደሰተች። መነሻውን ማዘጋጃ ቤት መድረሻው መስቀል አደባባይ ያደረገው የውበት ስጋጃ ተነጥፎላት ሸገር ተዋበች።
ትላንት ባለ ራዕይ ልጆችዋ ለውጥዋን አጥብቀው ተመኙ። ይህች የብዙኃን ማደሪያ የእልፎች መዲና አብባ ማየት፤ ፈክታ መመልከትን ናፈቁ። ለዚህም የተዋበ ምስል ነድፈው ወደ ተግባር ለመለወጥ ጥረት ጀመሩ። በጥረታቸው የድካማቸው ፍሬ ማየት፤ የውጥናቸው ስኬት ማጣጣም ዛሬ ጀመሩ። ትላንት ለውጥዋን ሽተው የተጉ፤ መዲናዬ ብለው ቀን ከሌት የሰሩ ልጆችዋ ዛሬ ፍካትዋን ደስ ተሰኙ።
የውበት ስጋጃው ከመስቀል አደባባይ እስከ ማዘጋጃ ቤት ዘልቋል። ውብ ገፅታዋ ከአገሪቱ ታላቁ አደባባይ ይጀምራል። ታሪካዊው መስቀል አደባባይ የውበት አክሊል ደፍቷል። ሙሉ ገፅታውን ቀይሮ ለከተማዋ ድምቀትና ውበት ለነዋሪዋ ምቾት እንዲፈጥር ታንፆል። በፊት ከነበረው በብዙ ተለይቶ ለእይታ ማራኪ ለሁነቶች ምቹ ተደርጓል።
ከላይ ባማረ
ዲዛይን
ተገንብቶ
ዙሪያውን
በሚማርክ
ረድፍ
በተሰሩ
መቀመጫዎች
ተበጅቶ
በረድፍ
ከታች
ወደ
ላይ
በተደረደሩና
የአካባቢውን
ልዩ
ውበት
በሚያላብሱ
መብራቶች
ደምቋል።
የአደባባዩ
የታችኛው
ክፍል
በጥልቀት
ተቆፍሮ
እጅግ
በዘመነ
ቴክኖሎጂ
የተሰናዳው
ከአንድ
ሺ
አራት
መቶ
መኪኖች
በላይ
ማቆም
የሚያስችለው
“ፓርኪንግ”
የግንባታው
ጥበብ
ያስደምማል።
እዚያ ቦታ ላይ ለሚታደሙ እልፎች ሙቀት ጉዳያቸው እንዳይሆን በቴክኖሎጂ ማቀዝቀዣ ተበጅቶለታል። መቀመጫዎች ጀርባ ባለው ግንብ አጥር ላይ የተሰቀሉ ትልልቅ ምስል ማሳያ ስክሪኖች ለአካባቢው ልዩ ውበት አላብሰውታል። ወደ አካባቢው አገልግሎት ፈልጎ ለሚመጣ የሱቆች፣ የካፌና የሻይ ቡና አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ማዕከላት ተገንብተዋል። ይህ እስከ አንድ ሚሊዮን ሰዎች በአንድ ጊዜ እንዲያስተናግድ ሆኖ የተሰራው አደባባይ ዙሪያው በተዋቡ አበቦች ተጊጦ ሲታይ ልዩ ውበቱ ይጎላል።
አደባባዩን አልፎ የሚገኘው የተንጣለለው የእስታዲያም ዋናው ጎዳና ሻገር ብሎ የሚገኘው ለገሀር የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በርቀት ማየት የሚያስችለውና በዚሁ ፕሮጀክት የተዋበው ቸርቸል ጎዳና መጀመሪያ ነው። በግራ በኩል የወደፊትዋ ለገሀር የሚያመላክት ገፅታ በምስል ለተመለከተ ልዩና ብሩህ የነገን ተስፋ በውስጥ ያጭራል፤ ነገን ያስናፍቃል።
ፊት ለፊት ስመለከት በርቀት የቸርቸር ጎዳና አዲስ ገፅታና ውበት ፈክቶ ይታያል። ለአመታት መኪናና እግረኛ ሲጋፋበት ውበት ርቆት የቆየው ጎዳና መኪኖችን በምቾት የሚያመላልስ፤ እግረኞች በነፃነት ሽር እንዲሉበት ተደርጎ ተውቧል። ዳርና ዳሩ በአበባ አጊጦ ሰፋ ተደርጎ የተሰራው መንገድ ከወትሮው በተለየ ምቹ ሆነዋል።
ለከተማዋ ውበት ለመሪዎችዋ ምቾት እንዲፈጥር ታስቦ የተገነባውና ልዩ ውበትን የተላበሰ ጎዳና እስከ ማዘጋጃ ቤት ይደርሳል። በዋናው መንገድ ላይ በተለያየ ውብ ዲዛይን የተሰሩት ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎችም የቸርቸር ጎዳናን ልዩ ግርማ አላብሰውታል።
ከማዘጋጃ እስከ መስቀል አደባባይ የሚደርሰው ይህ ከተማዋን የማስዋብ ፕሮጀክት አጠቃላይ ወጪው በ2.5 ቢሊዮን ብር መሆኑን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ይግልፃሉ። ፕሮጀክቱ አዲስ አበባን እንደ ስምዋ ውብ የማድረግ ስራ አንዱ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህ አፈፃፀሙ ስኬታማ ያሉት ፕሮጀክት አዲስ አበባ ውብ ምቹና ሳቢ የማድረግ ራዕይ ማሳያ መሆኑን ያስረዳሉ።
በተለይም ለተጠቃሚዎች ምቹ ሆኖ የተገነባው መስቀል አደባባይ ትልቅ ፕሮጀክት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንና በፊት የነበረውን ገፅታ ሙሉ በሙሉ በመለወጥ የአገሪቱ ርዕሰ መዲና የሚመጥንና የተዋበ ተደርጎ መሰራቱን ጠቁመዋል። ፕሮጀክቱ የማደግ አቅምን ያሳየ፤ በትክክል አስቦና አቅዶ በትጋት መስራት የሚያስገኘው ስኬት ያመላከተ መሆኑም ይጠቁማሉ።
ምክትል ከንቲባዋ ስለፕሮጀክቱ ሲያብራሩ ቀድሞ ከነበረው በእጥፍ የሰዎች ቁጥር ማለትም ከ 1 ሚሊዮን የማያንስ ታዳሚን እንደሚያስተናግድ አስረድተዋል። የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነው ከማዘጋጃ ቤት እስከ መስቀል አደባባይ የሚደርሰው 3.5 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ጎዳና ወይም ቸርችል የከተማዋ ታሪካዊ ቅርሶች መገኛ እንደመሆኑ በልዩ ሁኔታ ለእግረኛና ለመኪኖች ፅዱና ውብ ሆኖ መሰራቱን ገልፀዋል። ፕሮጀክቱ ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር የትራፊክ መጨናነቅን የሚቀንስና የከተማውን ገፅታ የሚቀይር መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህ ውብ ጎዳና ሽር የሚሉበት በርከተዋል። ወጣት ዮሀንስ በላይ የቸርቸል ጎዳናን ይዞ ቁልቁል ሲወርድ አናገርኩት። እንደ ከተማዋ ብሩህ ተስፋን ሰንቆ በስራ ትጋት ላይ መሆኑን የገለፀልኝ ዮሀንስ የከተማው ነዋሪ መሆኑንና በተለይ በቸርችል ጎዳና የተደረገው ለውጥ እንዳስደነቅው ይናገራል።
ለእግረኞች ምቹና ሰፊ ተደርጎ በተገነባው መንገድ አይንን መሳብ በሚችሉ አረንጓዴ እፅዋትና አበቦች መድመቁ ለመንገዱ ውበት እንደሰጠው ይናገራል። ከተማዋ ላይ እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች ለከተማዋ ለውጥ ትልቅ መሆናቸውንና ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የጠቆመው ወጣት ዮሀንስ፣ ማህበረሰቡም የተሰሩ ፕሮጀክቶች በመጠበቅና ለሚሰሩትም እገዛ በማድረግ ተሳታፊ ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል።
መምህር የቆየሰው አረጋ ሰሞኑን በልዩ ድምቀት የተመረቀው መስቀል አደባባይ ቆመው ሲመለከቱ አይቼ ድምፅ መቅረጫዬን አውጥቼ ተጠጋኋቸው። የአዲስ አበባ ነዋሪ መሆናቸውና ከዚህ በፊት የተለያዩ ዝግጅቶችን ለመታደም መስቀል አደባባይ ይገኙ እንደነበር አሁን ግን ባዩት የአደባባዩ ገፅታ ማማር እንደተገረሙ ይናገራሉ። በዚህ ፍጥነት እደዚህ በሚያምር መልኩ ተሰርቶ ይጠናቀቃል ብዬ አልገመትኩም ያሉት መምህር፣ የቆየሰው አደባባዩ አዲስ አበባ እንድትደምቅ ያደርጋታል ብለዋል።
በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ መሰል ፕሮጀክቶችና ፓርኮች ከተማዋን ለኑሮ ምቹና ተመራጭ እንደሚያደርጋት ጠቁመው በአስተዳዳሩ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመዋል። ማህበረሰቡ የፕሮጀክቶቹ ባለቤት በመሆን ሊንከባከባቸውና ለታሪክ ሊያቆያቸው እንደሚገባ የገለፁት መምህር የቆየሰው፣ ከተማዋ በእነዚህ መሰል ፕሮጀክቶች እንደ አዲስ መሰራትዋ ከቀጠለ በቅርብ ጊዜ ከአለም ታላላቅና ውብ ከተሞች ተርታ መሰለፍ የምትችልበት እድል እንዳለ አስረድተዋል።
የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን የሚገልፁ ቅርሶች እንዲታዩና፣ እንዲሸጡበት የተዘጋጁ ሱቆች፣ የቢሮ መገልገያ ክፍሎች፣ 6 ዘመናዊ ሊፍቶችና ለ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ የደህንነት፣ ካሜራዎች ተገጥመውለታል። እንዲሁም የዋይፋይ ኢንተርኔት አገልግሎትና ሳምንቱን ሙሉ ለ24 ሰዓት ክፍት የሚሆኑ የቴሌኮም፣ የባንክ አግልግሎት ይሰጥበታል። በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ለ10 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ከአዲስ አበባ መስተዳድር የተገኘው መረጃም ያመላክታል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2013