በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)
አሸባሪው ህወሓትን ይቺ ሀገር ምን ብትበድለው …! ይህ ሩህሩህና ደግ ሕዝብስ በምን እዳው ነው …! ? እንዲህ አምርሮ የሚጠላቸው !? ለልጆቹ እንደሚሳሳ መልካም አባት ዊንጌት ቢሉ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ራሳቸውን እያሻሹ ሚበሉት ፣ ሚጠጡትና ሚለብሱት ሳይጎድል ከቀዬአቸው አምጥተው ላስተማሯቸው ንጉስ ሀገርና ሕዝብ እንጥፍጣፌ ርህራሄና በጎነት እንዴት ያጣሉ። ውለታን ከማይረሳ ትግራዋይና ኢትዮጵያዊ አብራክ የተገኘ ስብስብ/ጉጅሌ /በዚህ ደረጃ ለምን አሪዎስ ሆነ !? ነው ከሌላ ፕላኔት የተገኘ ጉድ ነው !? አሸባሪውን ህወሓት አይደለም በርዕዮተ ዓለምና በስልጣኔ/civilization/በየአዘቦት ሰውነት እንኳን ለመገምገም ያስቸግራል። መቼም ነገርን ነገር ያነሳዋልና ለ40 ዓመታት የዘለቀው ርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሠረተው ቀዝቃዛው ጦርነት በአሜሪካና በአጋሮቿ አሸናፊነት ከተደመደመ በኋላ አዲሱ ጎጆ ስልጣኔንና ባህልን ዋልታ አድርጎ እንደገና የተቀለሰ ነው ። ሀገራት በስልጣኔ ፣ በባህል፣ በእምነትና በቋንቋ ከሚመሳሰላቸው ሀገራት ጋር የሚፈጥሩት ግንኙነት ነው እንግዲህ ስልጣኔያዊ ትስስር የሚባለው። ከዚህ አኳያ አሜሪካና ምዕራባውያን በአንድ ረድፍ የሚሰለፉ ሲሆን ፤ ቻይናና እስያ በኮንፊሽየስና በቡድሀ ጥላ ሲሰባሰቡ ፤ ራሽያ ደግሞ የኦርቶዶክስ አማኝ ሀገራትን አስከትላ በሌላ ረድፍ የምትሰለፍ ሲሆን ፤ ሱኒዎች ሳውዲ አረብያን ከፊት አድርገው ሲከተሉ ፤ ሽያዎች ደግም ኢራንን አስቀድመው ይሰደራሉ። የሚገርመው ሀገራችን ኢትዮጵያ አልተጠቀመችበትም እንጂ በድህረ ቀዝቃው ጦርነት ከምዕራባውያን ፣ ከራሽያና ከአረብ ሀገራትና ከኢራን ጋር ጠንካራ የስልጣኔ ግንኙነት መፍጠር ትችላለች ። ምክንያቱም የሶስቱ አብርሀማዊ እምነቶች ማለትም የክርስትና ፣ የአይሁድና የእስልምና ቀደምት መገኛ ታምረኛና ልዩ ሀገር ከመሆኗ ባሻገር ጥንታዊውን ስልጣኔንም ስለምትጋራ ።
አሸባሪውና ፖለቲካዊ ድውዩ ህወሓት ከስልጣኔ አኳያ በስነ ልቡና ፣ በእምነትና በቋንቋ ከተሳሰረው የኤርትራና የአማራ ሕዝብ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ሊኖረው ሲገባ የለየለት ጠላቱ አርጓቸው አረፈ። ይህ የፖለቲካዊ ድድብናው ጥሩ መገለጫ ነው ። በታሪኩ መርህ ሚባል ነገር ያልፈጠረበት አሸባሪው ህወሓት ከአማራና ከኢትዮጵያ ሕዝበ ይልቅ ሱዳንና ግብፅ ይቀርቡኛል እስከማለት የደረሰ ጥልቀ ወመቀመቅ ወረደ ። ጉጅሌው በድምሰሳው ከሰብዓዊነት ይልቅ ለጭራቅ ወይም ለዙምቢ ይቀርባል። በዚህ አውድ ሆኖ አሸባሪው ህወሓትን ይቺ ሀገር ምን ብትበድለው …! ይህ እሩህሩህና ደግ ሕዝብስ በምን እዳው ነው …! ? እንዲህ አምርሮ የሚጠላቸው በሚል የሚነሳው ጥያቄ የእኔም ፣ የትውልዴም፣ የትውልዶችም፣ የታሪክም ጥያቄ ሆኖ ይኖራል። ከባዕድ ወራሪ፣ ከደመኛ ፣ ከአባት ገዳይ በላይ አምርሮ የሚጠላቸው ፤ ከጀርባ እንዲህ ደጋግሞ የሚወጋቸው ፣ ጥፋታቸውን ውድቀታቸውን የሚመኘው ፤ በቁማቸው መቃብር የሚምሰው፤ ጥላቻን ፣ ግጭትን 24 ሰዓት የሚቀፈቅፈው፤ በሴራና በደባ ፖለቲካ ጠለፎ ለመጣል ሌት ተቀን የሚታትረው፤ ትንሳያቸውን ለማብሰር ሳይሆን ቀውሳቸውን ለማርዳት በጥፍሩ የቆመው፤ ይቺ ሀገር፣ ይህ ሕዝብ ምን ቢያጠፉ ነው እንደ ወገቡ ቅ** ጠምዶ የያዛቸው!? ይቺ ሀገርስ በየትኛው እዳዋ ነው እንድትፈርስ ያለ እረፍት መሰረቷን የሚነቀንቀው!? የሚያናገው!? እነዚህን ጥያቄዎች የማዥጎደጉደው በታሪክ ሀገርና ሕዝብ ማንንም በድለው ፣ አስከፍተው እንደማያውቁ በተቃራኒው አገዛዝና ገዥዎች ሕዝብንም ሀገርንም እንደሚበድሉና እንደሚያጎሳቁሉ ዘንግቸው አይደለም። አሸባሪው ትህነግ ለሀገርና ለሕዝብ እንዲህ የመረረ ጥላቻ ያደረበት ምክንያት ግራ ቢያጋባኝና አልገለጥ ቢለኝ እንጂ።
አሸባሪው ህወሓት ያለፉት 30 ዓመታት ግፍና በደል አልበቃ ብሎት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሀገሪቱን ወደ ለየለት የእርስ በርስ ግጭት ለመክተት፣ ለማተራመስ ያልወጣው አቀበት፣ ያልወረደው ቁልቁለት የለም። ይህ እንዳሰበው ሳይሳካለት ሲቀር ደግሞ ትውልድም ታሪክም ይቅር የማይለውን ክህደት በሀገርና በሕዝብ ላይ ፈጸመ። ቀድሞ በታቀደ ፣ በተጠና ፣ ዝግጅት በተደረገበት በተመሳሳይ ሰዓት በተለያዩ በሰሜን ዕዝ መዋቅሮች ላይ ከ40 በላይ ጥቃቶችን ከፈተ። ወደ 20 ለሚጠጉ ዓመታት የቀን ጽሐይ የሌሊት ቁር ሳይበግረው፤ የእድሜውን ሲሶ በቀበሮ ጉድጓድ በምሽግ ሰውቶ ፤ ከገበሬው ጋር እያረሰ ፣ እየዘራ፣ እያረመ ፣ እያጨደ ፣ እያበራየ፤ አንበጣ ሲከሰት እየተከላከለ ፤ በሌለ አቅሙ ከቤተሰቦቹ ጉሮሮ ቀምቶ ትምህርት ቤት ፣ ጤና ጣቢያ የገነባ ፤ አረጋውያንን የሚጦር ወላጅ አልባ ወይም ችግረኛ ህጻናትን የሚያሳድግ ፤ ከትግራዋይ ጋር የተጋባ የተዋለደ ፤ አበልጅ የተናሳ ሰራዊት ፤ በአንድ ኮዳና ጋቤጣ በጠጡ በአንድ ማዕድ በቆረሱ ከሀዲ የአሸባሪው ህወሓት ጀሌዎች ለመስማት የሚሰቀጥጥ ለማየት የሚዘገንን አረመኔአዊ ግፍ ተፈጸመበት ።
ዕዙ የታጠቀው ከነፍስ ወከፍ እስከ ከባድ መሳሪያ ተዘረፈ። ከሀገሪቱ መከላከያ ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው ኃይሉ ተጠቃ ። የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሽያ ፤ የኤርትራ ሕዝብና መንግሥት ደርሰው ሰራዊቱ መልሶ እንዲደራጅና ከከበባና ከጥቃት ሰብሮ እንዲወጣ ወሳኝ ሚና ባይጫወቱ ኑሮ፤ የአሸባሪው ህወሓት ቅዠት ቢቻል በቀናት አዲስ አበባን መቆጣጠር ካልሆነ ጎንደርና ጎጃምን ተቆጣጥሮ የለውጥ ኃይሉን እጅ ጠምዝዞ ወደቀደመ የበላይነቱ መመለስ ፤ በኤርትራም የመንግሥት ለውጥ ከማምጣት ባሻገር እጩ ፕሬዚዳንት እስከማዘጋጀት ደርሶ ነበር። ደግነቱ መብረቃዊ ጥቃት ፈጽሜ ደምስሸዋለሁ ያለው ሰራዊት በአጭር ጊዜ በጀግንነት፣ በእልህና በቁጭት መልሶ ተደራጅቶ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ብትንትኑ ወጣ። በአሸዋ ላይ እንደተቀለሰ ሰቀላ በቁሙ ፈረሰ። ይሄን ተአምር በአሰብሁ ቁጥር የመታበይና የእብሪት መጨረሻ ምን ሊሆን እንደሚችል ያስታውሰኛል።
ከሴራዎቹ ሁሉ አረመኔያዊና ዘግናኝ የሆነው ይህ ክህደቱ ሲከሽፍበትና ሲባርቅበት ነጮች ፕላን ቢ ወደሚሉት አይነት ቀጣይ ሴራውና ዘመቻው ፊቱን አዞረ ። ከድሀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተዘርፎ በየሀገራቱ የሸሸውን ዶላር ፤ በየዓለምአቀፍ ተቋማቱና ሚዲያው የተሰገሰጉ ጭፍራዎቹን ፤ አራጋቢዎችን/lobbyist/ በመቅጠር ፣ ዲጅታል ወያኔንና እንደ ትግራይ ሚዲያ ሀውስ ያሉ ብዙኅን መገናኛዎችን ፤ እንደ ሱዛን ራይስ ያሉ የመለስ ዜናዊ ታማኝ ወዳጆችንና ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖምን አናቦ በማቀናጀት በጦር ሜዳ የተከናነበውን የውርደት ማቅ በዲፕሎማሲውና በሕዝብ ግንኙነቱ ጊዜያዊ ድል ነጠላ ለመቀየር ሌት ተቀን ማሰነ። የእኛ ተቋማዊና መዋቅራዊ ዳተኝነትና እንዝህላልነት ተጨምሮበት ጊዜያዊ ቢሆንም በሀሰተኛና በተዛባ መረጃ የሕዝብ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ግዳይ ጣለ። በአሜሪካ ማዕቀብ እስከማስጣል፤ በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ከሰው እስከ ማቆም ፤ በአውሮፓ ሕብረት በጥርጣሬ እንድትታይ ፤ በአሜሪካ ሰኔት ባልዋለችበት እንድትከሰስ ፤ ገጽታው እንዲጠለሽ በማድረግ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲሉ ለታሪካዊ ጠላታችን ግብጽ ጥቃት፤ ለሱዳን ወረራ አመቻቾት። ዛሬ ሀገራችን የምዕራባውያን ሚዲያ ማሟሻ እስከመሆን ደርሳለች። እውነትንና ፍትሕን ታቅፈን ቀርተናል። ምንም እንኳ የማታ ማታ እውነት ማሸነፉ ባይቀርም።
እንደ መውጫ
ሀሰተኛ መረጃን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሞ ሀገራችንን በማጠልሸቱ ረገድ ቢቀናውም የለውጥ ኃይሉ ከሙት መንፈስና ከአሸባሪው ህወሓት ጋር አልደራደርም በሚለው አቋሙ መጽናቱና ዓለምአቀፉ ማህበረሰቡ የሰላም ማስከበር ጦር እንዲያስገባ ከተቻለም ጣልቃ እንዲገባ ያደረገው ውትወታና ተማጽኖ እንደማይሰምር ቁርጡን ሲያውቅ ደግሞ ሌላ ሀገርን ብሎም ቀጣናውን ለማተራመስ ያዘጋጀውን የሽብር እቅድ ዙም በተሰኘ ኮቪድ አመጣሽ የበይነ መረብ መገናኛ ዘዴ ከጀሌዎቹ ጋር የመከረበትና የዘከረበት ሰነድ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ደርሶት ይፋ በመሆኑ ሰሞኑን መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። ሽብር ጠማቂ በሆነው በዚህ ስብሰባ ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት በማስነሳት ትግራይን እንደ ሀገር ለመመስረት ያስችላሉ ብሎ ያስተላለፋቸውን 19 ዓለም አቀፋዊ፣ ቀጠናዊና ሀገራዊ ስትራቴጅያዊ ውሳኔዎችን ፤ እኔ የቀን ቅጀት ያልኋቸውን ተመለከትኋቸው። እውነት ለመናገር አሸባሪው ህወሓት ለዚች ሀገርና ሕዝብ ያለው የመረረ ጥላቸው እስከመጨረሻዋ ህቅታ እንደሚቀጥል ከማረጋገጡ ባሻገር ዛሬም መጨረሻዋ ጣዕረ ሞት ላይ ሆኖ ከሽብር፣ ከደባ ፣ ከጭካኔና ከአውሬነቱ እንደማይላቀቅ ፤ ለዚች ሀገርና ሕዝብ አንድ አሙስ ቀርቶትም እንደማይተኛ ያረጋገጠበት ሰነድ ነው። የዚህ ጉጅሌ የሽብርና የጥላቻ ጥግ የት ድረስ እንደሆነ፤ ከተጨባጭ ሁኔታው አፈንግጦ ራሱ በፈጠረው የቅዠት ዓለም እየባተለ መሆኑን፤ ያጣውን የበላይነት አገዛዝ ለማስመለስ አይደለም ኢትዮጵያና ቀጣናው ዓለም ብትጠፋ ወደ ምድራዊ ሲዎልነት ብትቀየር ጉዳዩ እንዳልሆነ ዳግም አረጋግጧል።
ሆኖም ያልጨረስነው ወዝፈን የተውነው የቤት ሥራ እንዳለብን ያሳያል። የዚህን አሸባሪ ጉጅሌ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ ፣ ዲፕሎማሲያዊና ተግባቦታዊ የመጨረሻ ምሽግ መደምሰስ ላይ መረባረብ ይጠይቃል ። ከዚህ ጎን እንደ ዝንጀሮ ገደል ለገደል እየዘለለ ፤ እንደ ቀበሮ በጉድጓድ ጎድቦ እየዋለ አደጋ የሚጥለውን የአሸባሪውን ርዝራዥ የመልቀምና የማጽዳት ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እና በዚሁ ጋዜጣ አበክሬና ደጋግሜ ለማሳሰብ እንደሞከርሁት የትግራዋይን ልብና ህሊና ማሸነፍ ላይ የበለጠ መስራት ይጠይቃል። በጦር ግንባር ድል ማድረግ በራሱ ሙሉኡ አለመሆኑን አረጋግጠናልና።
የሆነው ሆነና ፣ አሸባሪው ህወሓት ይቺ ሀገር ምን ብትበድለው …! ይህ ሩህሩህና ደግ ሕዝብስ በምን እዳው ነው …! ? እንዲህ ሊያጠፋቸው ቀን ከሌት የሚታትረው !? የሚለው ጥያቄ ፣ ትውልዶች መልስ ያጡለት ጥያቄ እንደሆነ ይዘልቃል።
አሸባሪው ህወሓት ይውደም !
ኢትዮጵያ ትቅደም !
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2013