የቡድን ሃያ ሀገራት በኢኮኖሚ ያደጉ 19 ሀገራትንና የአውሮፓ ህብረትን ያቅፋል። አስራ ዘጠኙ ሀገራትም አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ብራዚል፣ ካናዳ፣ ቻይና፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ህንድ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ጣልያን፣ ጃፓን፣ ሜክሲኮ፣ ሩሲያ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቱርክ፣ እንግሊዝና አሜሪካን ናቸው። እነዚህ አባል ሀገራት ከ80 ከመቶ በላይ የሚሆነውን የዓለም አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት፣ 75 ከመቶ ያህሉን ዓለም አቀፍ ንግድና 60 ከመቶ የሚሆን የዓለም ህዝብ ይሸፍናሉ።
ከእነዚህ አባላት ውጪ አውሮፓዊቷ ስፔን እንግዳ ሆኗ በቋሚነት በቡድኑ ውስጥ ትሳተፋለች። በየዓመቱ ቡድኑ በሚያከናውናቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሌሎች እንግዳ ሀገራት እንዲሳተፉም ይጋብዛሉ። በተመሳሳይ የተለያዩ ዓለም አቀፍና ቀጠናዊ ተቋማትም ቡድኑ በሚያካሂዳቸው ፎረሞች ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ።
በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ ያላቸው እነዚህ የቡድን ሃያ ሀገራት፤ የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በሌሎች ሀገራት ላይ እንዳደረሰው ሁለንተናዊ ተፅእኖ ሁሉ እነርሱንም ገርፏቸዋል። በተለይ ደግሞ ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ እ.ኤ.አ በ2020 አራተኛው ሩብ ዓመት አጠቃላይ ሀገራዊ ምርታቸው ተንሸራቶ ቆይቷል። ይሁንና በ2021 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በቅድመ ወረርሽኝ ወቅት ወደነበረበት ደረጃ መመለሱን የሲ ኤን ቢ ሲ ዘገባ ከሰሞኑ አመልክቷል።
ዘገባው የቡድን ሃያ ሀገራት ኢኮኖሚ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት በ2021 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በቅድመ ወረርሽኝ ወቅት ወደነበረበት እድገት መመለሱን ነገር ግን በቡድኑ ሀገራት መካከል ልዩነት መኖሩን አስታውቋል። ባለፈው ሳምንት በኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት በተለቀቀው የመጨረሻ ሪፖርት መሰረት የቡድን ሃያ ሀገራት አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ከ2020 አራተኛ ሩብ ዓመት ጋር ሲወዳደር በ 0 ነጥብ 8 ከመቶ ማደጉም በዘገባው ተጠቅሷል።
በቀድሞው ሩብ ዓመት የ 0 ነጥብ 7 ከመቶ መኮማተር አሳይቶ የነበረው የቡድን ሃያ ሀገራት
አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት በ2021 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የ 3 ነጥብ 4 ከመቶ እድገት ማሳየቱም ተገልጿል። የኮሮና ቫይረስ አስቀድሞ የታየባት የቡድኑ አባል ሀገር የሆነችው ቻይና በ18 ነጥብ 3 ከመቶ ከፍተኛውን ዓመታዊ እድገት በማሳየት ለቡድኑ ጥቅል ሀገራዊ ምርት ትልቁን ድርሻ መውሰዷን ዘገባው አመልክቷል። ከዚህ በተቃራኒ ሌላኛዋ የቡድን አባል ሀገር የሆነችው እንግሊዝ በ6 ነጥብ 1 ከመቶ ዝቅተኛውን እድገት እንዳስመዘገበች በዘገባው ተጠቁሟል።
የአውሮፓ ቀጠና በሦስተኛው የኮቪድ ወረርሽኝ ክፉኛ በመመታቱ በዚህ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ የቡድኑ አባል ሀገራት ከሌሎቹ ሀገራት ጋር ሲነፃፀሩ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቱ ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ አስተዋፅአዋቸው ዝቅተኛ መሆኑም ተጠቁሟል። ቀደም ባሉት ሩብ ዓመታት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርታቸው ከቅድመ ወረርሽኝ መጠን በላይ የነበረባቸው ህንድ ፣ ቱርክ እና ቻይና በ 2021 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እያንዳንዳቸው በ 2 ነጥብ 1 ፣ በ 1 ነጥብ 7 እና በ 0 ነጥብ 6 ከመቶ ማገገም ማሳየቱም ተገልጿል። በተጨማሪም አውስትራሊያ ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ብራዚል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ወደ ቅድመ ወረርሽኝ እድገት ደረጃዎች መመለሳቸውን ጠቅሷል።
ነገር ግን ለቀሪዎቹ የቡድን ሃያ አባል ሀገራት ምጣኔ ሀብቶች የሀገር ውስጥ ምርት አሁንም ከቅድመ ወረርሽኝ ደረጃዎች ወደ ኋላ የቀረ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል። በ 2021 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ውስጥ ሀገራቱ አስገራሚ ልዩነቶችን እንደሚያስመዘግቡ አብራርቷል። አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት በአሜሪካን በ2020 በአራተኛው ሩብ ዓመት ከነበረበት የ 1 ነጥብ 1 ከመቶ ወደ 1 ነጥብ 6 ከፍ ማለቱንና በተመሳሳይ በጣልያንም እያደገ መሆኑንም ዘገባው ጠቅሶ፤ ሆኖም እድገቱ በኢንዶኔዢያ፣ ካናዳ፣ ደቡብ አፍሪካና ሜክሲኮ አዝጋሚ መሆኑን ጠቁሟል።
በጀርመንም አጠቃላይ ሀገራዊ የምርት እድገት በአራተኛው ሩብ ዓመት ከነበረው 0 ነጥብ 5 ከመቶ ከዜሮ በታች ወደ 1 ነጥብ 8 ከመቶ መውረዱንና በተመሳሳይ በእንግሊዝም ከ 1 ነጥብ 3 ከመቶ ከዜሮ በታች ወደ 1 ነጥብ 5 ከመቶ መንሸራተቱን በዘገባው አስነብቧል። በጃፓን፣ ሳኡዲ አረቢያና ፈረንሳይ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርቱ ምንም እንኳን አነስተኛ ፍጥነት ያለው ቢሆንም ለሁለት ተከታታይ ሩብ ዓመት መኮማተር መቀጠሉን ጠቅሷል።
በአጠቃላይ እንግሊዝና ጣልያን ለቅድመ ወረርሽኝ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን በቅደም ተከተል ከዜሮ በታች 8 ነጥብ 7 ከመቶና ከዜሮ በታች 6 ነጥብ 4 ከመቶ ትልቁን ክፍተት ማስመዝገባቸውንና ጀርመን ፣ ፈረንሳይ ፣ የአውሮፓ አካባቢ እና የአውሮፓ ህብረት አሁንም ከአራት ከመቶ በላይ ክፍተቶችን ማስመዝገባቸውን ዘገባው በመቋጫው አስቀምጧል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2013